Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

ኢትዮጵያ የጉምሩክ ታሪፏን በአራት ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ልታነሳ እንደምትችል ኮሜሳ አስታወቀ

$
0
0

-የቀጣናውን የንግድ ስምምነት ቀስ በቀስ ለመቀላቀል መወሰኗን እንደማይቃወም ገልጿል

በብርሃኑ ፈቃደ፣ ማሔ ደሴት ሲሼልስ

የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) በመጪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የጉምሩክ ታሪፏን ሙሉ በሙሉ ልታነሳ እንደምትችል አስታወቀ፡፡

በሲሼልስ አስተናጋጅነት በተካሔደው የኮሜሳ ንግድና ልማት ባንክ 33 ጠቅላላ ጉባዔ የተገኙት የኮሜሳ ዋና ጸሐፊ ሲዲሶ ንዴማ ንግዌና፣ በመጪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ የጉምሩክ ታሪፍ አሁን ከሚገኝበት የ40 በመቶ ምጣኔ ወደ ዜሮ እንደሚወርድ ተናግረዋል፡፡ አገሪቱ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ውስጥ ቀስ በቀስ ለመታቀፍ ካላት ፍላጎት አኳያ የታሪፍ ለውጡን እንደምታደርግ ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ 

በኮሜሳ አባል አገሮች መካከል የንግድና የኢኮኖሚ ትስስርን ለመፍጠር አንዱ መሠረታዊ መስፈርት የጉምሩክ ቀረጥ ማስከፈያ ታሪፍን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት አሊያም ዝቅተኛ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ በአባል አገሮች መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት፣ አባል ካልሆኑ አገሮች ይልቅ ተጠቃሚ እንዲያደርጋቸው በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ የታሪፍ ምጣኔው ብቻም ሳይሆን ሌሎችም ታሳቢ የሚደረጉ የንግድ ልውውጦችን ለማቀላጠፍ ይታሰባል፡፡

ከኮሜሳ ባሻገር በአፍሪካ አገሮች መካከል ለሚጠበቀው ነፃ የንግድ ስምምነት በኮሜሳ፣ በደቡባዊ የአፍሪካ አገሮች የልማት ማኅበረሰብ እንዲሁም የምዕራብ አፍሪካ አገሮች አኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ የተሰኙት ሦስት ተቋማት፣ ከወራት በፊት በግብፅ ባደረጉት ስምምት መሠረት የሦስትዮሽ ነፃ የንግድ ስምምነት ማዕቀፍ ለመመሥረት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

ይሁንና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ባላቸው ዝቅተኛ የአምራች ኢንዱስትሪ አቅም፣ ባላቸው የሥራ አጥ ቁጥር ወይም በጠቅላላው ባላቸው የተወዳዳሪነት አቅም ሳቢያ የኮሜሳን ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት አለያም የአኅጉራዊው የንግድ ቀጣና ስምምነትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቀላቀል ከባድ እንደሚያደርግባቸው ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ የቀጣናው ነፃ የንግድ ስምምነት ለመቀላቀል ማሰቧ ምክንያታዊ እንደሆነም ይገለጻል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱ ከምትሰበስበው የገቢ መጠን ውስጥ ከጉምሩክ የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑም ጭምር ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጉምሩክ የምትሰበስበውን ቀረጥ በማስቀረት የነፃ ገበያውን ትቀላቀላለች ተብሎ አይጠበቅም፡፡ 

በአንፃሩ በኢትዮጵያ እየተገነቡ የሚገኙ የመሠረተ ልማት አውታሮች የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችሉ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ ለአብነት ኢትዮጵያ ከኬንያ፣ ከጂቡቲ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከታንዛንያና ከመሳሰሉት አገሮች ጋር በመንገድ፣ በባቡርና በአየር ትራንስፖርት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አማካይነት የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ቀስ በቀስ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስርን ለማስፈን መነሻዎች ይደረጋሉ፡፡

የኮሜሳ ዋና ጸሐፊው እንደሚያምኑት ኢትዮጵያ በቆዳና በቆዳ ውጤቶች ዘርፍ፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራችነት የምታደርገው እንቅስቃሴ ወደ አጎራባች አገሮች ብሎም ወደ ሌሎች የአኅጉሪቱ መዳረሻዎች ምርቶቿን የማስፋፋት ዕድል አላት፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚመረቱ ቆዳ ነክ ምርቶች የአውሮፓ ምርቶችን የመወዳደር አቅም እንዳላቸው ሲጠቅሱም የቆዳ ጃኬቶችን ምሳሌ አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአማካይ 25 ዶላር የሚያወጣ ቆዳ ጃኬት፣ በአውሮፓ 200 ዶላር ከሚያወጣው ጋር ያለው ተወዳዳሪነት እኩል እየሆነ በመምጣቱ ምክንያት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ባሻገር በምዕራቡ ዓለም ተፈላጊነት ያላቸው ምርቶችን የማምረት አቅም እየገነባች መሆኗ፣ ለቀጣናው ትስስር ያላትን አቅም እንደሚያመላክት ጠቅሰዋል፡፡

በአገሪቱ ከተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞንን ጨምሮ የቦሌ ለሚን፣ የሐዋሳና የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን መጎብኘታቸውን የገለጹት ንግዌና፣ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአፍሪካ የነፃ ንግድ ስምምነትን ለመቀላቀል የሚያበቋት ምልክቶች እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

በአንፃሩ በተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባዔ (UNCTAD) ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ከሆኑት መካከል ታፈረ ተስፋቸው (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካን የነፃ የንግድ ስምምነት ለመቀላቀል የሚያስችላት አቅም ላይ እንደምትገኝ ያምናሉ፡፡ የቀጣውን የንግድ ስምምነት ለመቀላቀል መዘግየቷም ተቀባይነት እንደሌለው ሲገልጹ ይታወቃሉ፡፡ አገሪቱ ካላት የሕዝብ ብዛትና እያመረተች ከምትገኘው ሸቀጥ አኳያ በሌሎች አገሮች የበላይነት ተወስዶባት፣ የሌሎች አገሮች ሸቀጥ ማራጋፊያ ትሆናለች፣ የሥራ አጥ ቁጥር ይባባሰል የሚለው ሥጋት አያሳምናቸውም፡፡ ይልቁንም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ አቅም ያለው በመሆኑ በሌሎች አገሮች ሰፊ የገበያ ዕድል የማግኘት ብቃት እንዳለው የሚያጣቅሱት፣ የሲሚንቶ፣ የመጠጥ እንዲሁም የቆዳ ኢንዱስትሪውን እንቅስቃሴ በማጣቀስ ነው፡፡

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles