በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ የሥራ ላይ አደጋዎች እያጋጠሙ እንደሆነ ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና የማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ፍቅሩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በ2009 ዓ.ም. ብቻ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሥራ ላይ አደጋ የ11 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡
‹‹ይህ አኃዝ ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሪፖርት የተደረገ ብቻ ነው፡፡ በድርድር የሚያልቁ ጉዳዮችን ደግሞ ቤቱ ይቁጠረው፤›› በማለት አቶ ደረጀ የሥራ ላይ አደጋዎች ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ደረጀ ጨምረው እንደገለጹት፣ ቢሮው መረጃ የሚያጠናቅረው ፖሊስ አጣሩልን ብሎ ሲጠይቅ በሚገኝ ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ በየሳይቱ በሚደረግ ድርድር ተጎጂዎች ትክክለኛ ጥቅማቸውን ሳያገኙ እየቀሩ፣ ለማኅበራዊ ቀውስ እየተደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ለአብነት በቅርቡ ያጋጠማቸውን ክስተት አቶ ደረጀ ያብራራሉ፡፡ ስሙን መናገር ያልፈለጉት አንድ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ ውስጥ የሚሠራ ባለሙያ በማሽን እጁ ተቆረጠ፡፡ የድርጅቱ ባለቤት አደጋ የደረሰበትን ተጎጂ ካሳከመ በኋላ አምስት ሺሕ ብር ብቻ ሰጥቶ ጉዳዩ እንዲያበቃ አደረገ፡፡ አቶ ደረጀ ጉዳዩን ጨምረው ሲገልጹ፣ በሕጉ መሠረት ቢኬድ ግን ተጎጂው ሕክምና ከተደረገለት በኋላ የሐኪሞች ቦርድ የጉዳቱን ደረጃ ያሳውቃል፡፡ ሠራተኛው በጉዳቱ መጠን መሠረት ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘው ደመወዝ ለአምስት ዓመት ተባዝቶ ይከፈለዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ተግባዊ እንዳልሆነ አቶ ደረጀ ይናገራሉ፡፡
በግንባታዎች ወቅት ደረጃውን የጠበቀ መወጣጫ (ስካፎልዲንግ) የማይጠቀሙ፣ ይልቁንም ለአደጋ የተጋለጠ የእንጨት መወጣጫ የሚገለገሉ፣ ለአሳንሳር የተተው ቦታዎች መከላከያ እንዳይኖራቸው በሚያደርጉ ኮንትራክተሮች ምክንያት የሰው ልጆች ሕይወት እየተቀጠፈ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 377/1996 አንቀጽ 92 በሥራ ቦታዎች ላይ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች በግልጽ ቢደነገግም፣ አዋጁ ተግባራዊ አለመደረጉን አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ኮንስትራክሽን ቢሮ አዘጋጅነት በተጀመረው የኮንስትራክሽን ሳምንት የውይይት መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተቋማት ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አበበ ድንቁ እንደገለጹት፣ የሙያ ሥነ ምግባር በሌላቸው ወገኖች የሚካሄዱ ግንባታዎች ጥራት የጎደላቸው፣ ተጠያቂነት የሌለባቸውና እንደተገነቡ የሚፈርሱ ናቸው፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት ግንባታዎች በሰው ልጆች ሕይወትና አካል ላይ፣ እንዲሁም በሕዝብ ሀብት ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት የሚያደርሱ ሆነዋል፤›› በማለት ፕሮፌሰር አበበ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የግንባታ ፈቃድ የመስጠት፣ በሰጠው ፈቃድ መሠረት ግንባታ መካሄዱን መቆጣጠር፣ ግንባታው ተካሂዶ ሲጠናቀቅም የመጠቀሚያ ፈቃድ የመስጠት ሥልጣንና ኃላፊነት አለው፡፡
ነገር ግን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ ባለሥልጣኑ የተሰጠውን ሥልጣን ተጠቅሞ ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም፡፡
ለዚህም እንደ ማስረጃ እየቀረበ የሚገኘው በከተማው ውስጥ በግንባታ ላይ ያሉ ሕንፃዎች በተለይ የመጀመሪያው ወለል ላይ ለባንኮች ተከራይተው አገልግሎት ሲሰጡ መመልከት የተለመደ መሆኑ ነው፡፡
