በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ የሚስተዋለው የውልና የዋስትና አፈጻጸም ውስንነት የሚታየው በአብዛኛው በሥራ ተቋራጩ አማካይነት በሚከሰት ክፍተት ሳቢያ መሆኑ ተገለጸ፡፡ በኢትዮጵያ ከኮንስትራክሽን ሕግና ደንብ ባሻገር፣ በሁለት ሥራ ተቋራጮች መካከል የሚደረግ ስምምነት በዘርፉ ለሚከናወኑ የውልና የዋስትና ጉዳዮች የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ነሐሴ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል በተዘጋጀው ‹‹ወሰኑ ያለየለት የኮንስትራክሽን ዋስትና ምንነትና ተግባር ላይ የሚስተዋሉ የሕግ ክፍተቶች›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ነበር፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፉ የሕግ ማዕቀፍ አተገባበር ሲቃኝም በሥራ ተቋራጮች መካከል የሚከናወነው ስምምነት ግልጽነት የጎደለው ነው ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ መንግሥት ከሚመድበው ጠቅላላ በጀት 60 በመቶውን የሚወስደው ይኸው ዘርፍ ነው፡፡ በተቋራጮች፣ በአማካሪዎችና በአስገንቢዎች እንዲሁም በፋይናንስ ተቋማት መካከል ያለው ግንኙነት የተያያዘ በመሆኑ፣ አንዱ ከሌላው በግልጽ የተለያየ የሥራ ድርሻ እንዳላቸውና ይኼንንም የሚገዛ አሠራር ባለመዘውተሩ ምክንያት በዋስትና ላይ ችግሮች እንዲፈጠሩ መንስዔ መሆኑንም ተገልጿል፡፡
ዋስትናው በውል አፈጻጸም ወቅት እንደተጨማሪ ግዴታ የሚቆጠርና በሕግ ፊት የፀና እንደሆነ፣ የኮንስትራክሽን አደጋዎችን ከመቀነስ አንፃር በተለይም ከሕንፃ አዋጅ መውጣት በኋላ ማንኛውም ሥራ ተቋራጭ በሚሠራው ሥራ ምክንያት ለሚደርስ ጉዳት ከታወቀ የመድን ድርጅት ዋስትና ማቅረብ እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡
‹‹በሁለት ሥራ ተቋራጮች መካከል የሚከናወን የውል ስምምነት በኢትዮጵያ ከተቀመጠው የኮንስትራክሽን ሕግ በተጨማሪ፣ በግላቸው የካሳ ውል ማሠር ይኖርባቸዋል፤›› ያሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አማካሪና የአየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር ሙሉጌታ መንግሥቴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በውል አፈጻጸም ወቅት የተለያዩ ዋስትናዎች የሚተገበሩ ሲሆን፣ ዋስትና አብዛኛውን ጊዜ በገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ማለትም እንደ ባንክና ማይክሮ ፋይናንስ ባሉት አካላት ሽፋን ይሰጠዋል ተብሏል፡፡ በዚህም መሠረት የሰው ዋስትና፣ የንብረት፣ የፋይናንስ ዋስትናና የኮንስትራክሽን ዋስትናን ያካተተ ነው፡፡
በመድረኩ የተለያዩ የስምምነት ክፍተቶች የተነሱ ሲሆን፣ በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የመንግሥት ግንባታዎች ቁጥር ላቅ ያለ መሆኑ ተጠቅሶ፣ በተለምዶ የመንግሥት ኪስ እርጥብ (Solvent) ነው ቢባልም በወጭ አስተዳዳር ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች የክፍያ መዘግየት እንደሚያጋጥም ተጠቅሷል፡፡
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ የታወቁ የዋስትና ዓይነቶችም ቀርበዋል፡፡ በዋነኛነት የውል ማስከበሪያ፣ የጨረታ ማስከበሪያና ቅድሚያ ክፍያ፣ የዋናው ገንዘብ መያዣና የጥገና ብልሽት ዋስትናዎች ክፍተቶች የሚታዩባቸው መስኮች ናቸው፡፡
የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ውል ከመጠንሰሱ ቀደም ብሎና ሥራ ከጀመረ በኋላ እስከመጠናቀቂያው ድረስ ባለው ሒደት ላይ ዋስትናዎቹን ዓለም አቀፍ የማድረግ ጉዳይ ሌላኛው በፕሮጀክቶች ላይ የሚታይ የችግር መነሻ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
በ52 ፕሮጀክቶች ማለትም አሥሩ በሕንፃ፣ አሥሩ በውኃ ሥራና 32 በመንገድ ግንባታ ሥራዎች ላይ ጥናት ተደርጎ እንደተገኘው ከሆነ፣ የፕሮጀክቱ ቀረፃ ላይ የሚታየው ክፍተት ዋነኛ ችግር እንደሆነ አረጋግጠናል ያሉት አቶ አረጋ ዋሻ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡
‹‹በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ወጥነት ያለው የአሠራር ሥርዓት ባለመኖሩ፣ ዘርፉ ለሙስና የተጋለጠ ነው፤›› በማለት አቶ አረጋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ያለው የዋስትና ገበያ ላይ የመንግሥት ክትትል አናሳ በመሆኑ፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሥራ ተቋራጭ በርካታ ሠራተኞችን በሥሩ ቀጥሮ ሊያሠራ ቢችልም፣ በሠራተኞች ማጭበርበር ለሚደርስበት ጉዳት ማካካሻ የሚሆን የመተማመኛ ዋስትና (Fidelity Bond) አለመኖሩም በጥናቱ ቀርቧል፡፡
በኮንስትራክሽን ዋስትና አፈጻጸም ወቅት በተግባር ከሚስተዋሉ ተግዳሮቶች አንዱ በመንግሥት የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የዋናው ገንዘብ መያዣ (Retention) የፕሮጀክቱ ግንባታ ተጠናቆ የጊዜያዊና የመጨረሻ ርክክብ ከተፈጸመ በኋላ ሳይከፈል የሚቀየረው አምስት በመቶ ገንዘብ አብዛኛውን ጊዜ ተመላሽ ስለማይደረግ፣ ተቋራጮች ለሌላ ወጪ እየተዳረጉ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በፍርድ ቤቶች ዘንድ የሚታዩ የአተረጓጎም ክፍተቶችም ተነስተዋል፡፡ በኮንስትራክሽን ፕሮጀክት የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትናን በተመለከተ በንግድ ሕግ ይታይ ወይስ በፍትሐ ብሔር ሕግ ይገዛ? የሚለው ነጥብም በጥናቱ ተካቷል፡፡
የመንግሥት የጨረታ ሰነድን በተመለከተ የሰብዓዊ መብት ድርድር በውስጡ ማካተት እንዳለበትና በኢትዮጵያ በሥራ ወቅት ሠራተኞች ላይ የሚደርሰውን አደጋ አሠሪው ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን መውሰድ እንዳለበት በሕግ ከማስቀመጥ ባሻገር አፈጻጸሙ ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል፡፡
የዋስትና ሕግ ውስብስብነትን ተከትሎ የሥራ ተቋራጮች ከአገር ውስጥ ሕግ በተጨማሪ በውጭ ሕግ በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት ሲሞከሩ መስተዋሉም ተገልጿል፡፡
በፌዴራል የመንግሥት የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 47 በተቀመጠው መሠረት፣ የመንግሥት ግንባታ ውሎች ላይ አቅራቢ (ውል ተቀባይ) ሆኖ የሚቀርብ ወገን፣ ግዴታውን ባለመፈጸሙ ምክንያት በመንግሥት መሥሪያ ቤት ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ማካካሻ የሚውል የውል ማስከበሪያ ማቅረብ እንደሚጠበቅበት ይጠቀሳል፡፡ ይሁንና ይኼ ሕግ እንደሚጠበቀው መጠን ዋስትና እያረጋገጠ ባለመሆኑ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገውና የሥራ ተቋራጮችም ሕጉ ላይ ከተቀመጠው ባሻገር ተጨማሪ የውል ስምምነቶችን ማካተት እንደሚገባቸው በስብሰባው ወቅት ተነስቷል፡፡
