ከኢትዮጵያ ውጭ በመጓዝ ከፍተኛ ሕክምና የሚከታተሉ ዜጎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል፡፡ በአገር ውስጥ ተፈላጊውን ሕክምና ማግኘት ያልቻሉና አቅም ያላቸው ዜጎች ወደ ውጭ በሟገዝ ለሕክምና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያወጡም ይገለጻል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ለውጭ ሕክምና የሚወጣው ወጪ በየዓመቱ በአራት በመቶ እያደገ መጥቷል፡፡
በዚህ ምክንያት የውጭ አገር ሕክምናዎችን በአገር ውስጥ ለመስጠት የሚያስችል ሆስፒታል ለመገንባት በማሰብ፣ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ኢስተርን ስታር ቴርሸሪ ሆስፒታል የተሰኘ አክሲዮን ማኅበር ተመሥርቶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ የቦርድ ሰብሳቢው ዶ/ር መብራቱ ጀምበር እንደሚገልጹት፣ በሰነድ ከተረጋገጡ የውጭ ሕክምና መረጃዎች በመነሳት ዓመታዊው የሕክምና ወጪ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ይልቃል፡፡ ከሰነድ ውጭ የሚወጣው ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚሆን ይገምታሉ፡፡
የቴርሸሪ ሆስፒታል ለመመሥረት አንዱ ምክንያትም ለውጭ ሕክምና የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ በየጊዜው እያደገ መምጣቱና ዜጎች በውጭ ሆስፒታሎች የአገልግሎት ደረጃ እዚህ መታከም እንዲችሉ በመታሰቡ እንደሆነ ዶ/ር መብራቱ ይገልጻሉ፡፡
በፕሮጀክቱ ኢንቨስት ማድረግ ሊያስገኝ የሚችለውን ጠቀሜታ የሚገልጹት የአክሲዮን ኩባንያው መሥራቾች፣ በአገሪቱና በጎረቤት አገሮች መካከል የሚታየውን የሕክምና ክፍተት ለመቀነስ ልዩ የሕክምና መሣሪያዎችን የሚጠይቁ ሕክምናዎችን ሥራ ላይ በማዋል ሆስፒታል ማቋቋሙ ከአገልግሎቱ ባሻገር ለአትራፊነቱም መልካም ውጤት እንደሚሰጥ ይገልጻሉ፡፡ ከኢትዮጵያ በየዓመቱ ለውጭ ሕክምና የሚከፈለውን ወጪ በማስቀረት፣ ከምሥራቅ አፍሪካና ከሌሎች አገሮች በሜዲካል ቱሪዝም ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ ፕሮጀክት በመሆኑ፣ አክሲዮኖቹን በቶሎ ሸጦ ፕሮጀክቱን እውን የማድረግ እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡
እንደ ዶ/ር መብራቱ ገለጻ፣ ጊዜ ተወስዶ በተደረገ ጥናት፣ ኢትዮጵያን የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን የሚያስችላት ትልቅ ሆስፒታል መገንባት እንደሚቻል በመረጋገጡ፣ የአክሲዮን ኩባንያ ለመመሥረት የሚያስችል እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በሕክምና ዘርፍ በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ሆስፒታል የመገንባት አቅም መኖሩም እንደተረጋገጠ ተገልጿል፡፡ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ይጠይቃል የተባለው ሆስፒታል በአጭር ጊዜ ወደ ግንባታ እንደሚገባም ይጠበቃል፡፡
ኢስተርን ስታር ቴርሸሪ ሆስፒታል አክሲዮን ማኅበር በ41 ግለሰቦች መሥራችነት የተቋቋመ ነው፡፡ የአክሲዮን ኩባንያው አማካሪ ሥራና የአክሲዮን ሽያጩን ለማከናወን ኃላፊነት የወሰደው ኮም ሊንክ ቢዝነስ አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሲሆን፣ የድርጀቱ የማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ ታዲዮስ አበበ እንደሚገልጹት፣ ኩባንያው አመኔታ እንዲኖረው ከዚህ ቀደም በአክሲዮን ኩባንያዎች ውስጥ የሚታየውን ክፍተት በመገንዘብ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ኩባንያ ለመፍጠር እንደመሥራች የተሰባሰቡት 41 ግለሰቦች በኅብረተሰቡ ዘንድ ዕውቅና ያላቸውና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች መልካም የሥራ ምግባር የተላበሱ ናቸው፡፡
ከ41 መሥራቾች ውስጥ 15 የሕክምና ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡ አብዛኛዎቹም ታዋቂ ኩባንያዎችን በመምራት የሚታወቁ ሲሆን፣ አምባሳደሮች፣ መሐንዲሶች፣ ታዋቂ ጠበቆች፣ የኢንሹራንስና የባንክ ባለሙያዎች፣ ነጋዴዎች፣ የተቋራጭ ድርጅትቶች ኃላፊዎችና በሌሎች መስክ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንን አሰባስቧል፡፡
አክሲዮን ኩባንያው ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት ትልቅ ጠቀሜታ የሚሰጠው ሲሆን፣ ለአክሲዮን ኩባንያው መነሻ ካፒታል ይሆን ዘንድም 41ዱ መሥራቾች እያንዳንዳቸው የ20,000 ብር ዋጋ ያላቸው፣ አክሲዮኖች በመግዛት በ820 ሺሕ ብር ኩባንያውን መሥርተዋል፡፡
ይህ የሕክምና ቱሪዝም ጠቀሜታና አትራፊ ዘርፍ ስለመሆኑ በደንብ አይታወቅም ያሉት አቶ ታዲዮስ፣ ሆኖም በአክሲዮን ደረጃ ተቋቁመው ውጤታማ ከሆኑት መካከል የቢራ ፋብሪካዎች፣ የፋይናንስ ኢንዱስትሪዎች ከሚያተርፉት የበለጠ እንደሚያስገኝ ይናገራሉ፡፡
‹‹እንዲያውም ዛሬ አሥር ባንኮች በዓመት ከሚያተርፉት የበለጠ ከሕክምና ቱሪዝም ብዙ ይገኛል፤›› ያሉት አቶ ታዲዮስ፣ ይህም እንዲሁ በማጋነን እንዳልሆነ ለማስረዳት ምሳሌዎችን ጠቅሰዋል፡፡ የአንድ አክሲዮን አነስተኛ የትርፍ መጠን ከ40 በመቶ በላይ እንደሚሆን አቶ ታዲዮስ ገልጸው፣ ዛሬ የሕክምና ቱሪዝምን ያራመዱ አገሮች እያገኙ ያሉት ዓመታዊ ገቢና ኢትዮጵያም በየዓመቱ ለውጭ ሕክምና የምታወጣው ወጪም ጥሩ ማሳያ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
በሕክምና ቱሪዝም ኬንያ በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደምታገኝ ጠቅሰው፣ ‹‹ኢትዮጵውያን ለሕክምና የሚሄዱባቸውን አገሮች ደረጃ ያሟላ ሆስፒታል ቢኖረን ከኬንያ የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርገን ዕድል ሊፈጠር ይችል ነበር፤›› ብለዋል፡፡
የሜዲካል ቱሪዝም ገበያ ሰፊ ስለመሆኑም ከኢትዮጵያ ወደተለያዩ አገሮች የሚሄዱ ታካሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨምሩን የጠቀሱት አቶ ታዲዮስ፣ ከስድስት ዓመታት በፊት ወደ ኬንያ፣ ወደ ደቡብ አፍሪካና ወደ ህንድ ታካሚዎችን ከኢትዮጵያ የሚልኩ የውጭ ሆስፒታሎች ወኪሎች ሁለት ብቻ እንደነበሩ፣ አሁን ግን ወደ 12 ማሻቀባቸውን አስታውቀዋል፡፡ ወኪሎቹ በየዓመቱ በነፍስ ወከፍ ከ2,500 በላይ ታካሚዎችን ወደ ውጭ ስለሚልኩ፣ የውጭ ታካሚዎችን ቁጥር ዕድገት አመላካች አኃዝ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ሌላው ማሳያ የህንድ የሕክምና ተቋማት ከምሥራቅ አፍሪካ ብቻ ከ100 ሺሕ በላይ ታካሚዎችን ተቀብለው ማስተናገዳቸው ነው፡፡ ይህም ከምሥራቅ አፍሪካ የሚጓዙ ታካሚዎች ለህንድ በዓመት 2.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኙላታል፡፡ በመሆኑም እንዲህ ያሉ ተጨባጭ መረጃዎች በዘርፉ ሰፊ ገበያ ለመኖሩ ያመለክታሉ ተብሏል፡፡
እንደ ቦትስዋና ባሉ አገሮች ከ50 በመቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ዶክተሮች ተገኝተው አገልግሎት የሚሰጡባቸው ትላልቅ ሆስፒታሎች ከሕክምና ቱሪዝም ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በኢትዮጵያ ይቋቋማል የተባለው ሆስፒታልም በሌሎች አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎችን ወዲህ ለመሳብ ጭምር እንደሚያግዝ ታምኖበታል፡፡
ሆስፒታሉ ወጪን ማዳን ብቻም ሳይሆን የውጭ ምንዛሪን ምንጭ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡ ሥራ በሚጀምርበት የመጀመርያው ዓመት የሕክምና ቱሪዝም የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ ዘርፎች አንዱ ሆኖ እንደሚጠቀስ የሚያምኑት አቶ ታዲዮስ፣ መንግሥት ቸል ብሎ መቆየቱንም ይጠቅሳሉ፡፡ የውጭ ሕክምና ወጪ ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር፣ ለኩላሊት ንቅለ ተከላ በህንድ 17 ሺሕ ዶላር፣ በኬንያ ደግሞ 20 ሺሕ ዶላር እንደሚከፈል፣ ሌሎች ሕክምናዎችም ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቁ አኃዞችን አጣቅሰዋል፡፡
በመሆኑም እንዲህ ያሉ ለውጦችን የሚያመጣው ይህ ሆስፒታል እውን እንዲሆን የአክሲዮን ሽያጭ ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለውጭ ዜጎች ክፍት ይደረጋል ተብሏል፡፡ ተቋማትና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም ባለአክሲዮን እንዲሆኑ እንፈልጋለን ያሉት ዶ/ር መብራቱ፣ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉት ተቋማት የዚህ ፕሮጀክት አካል እንዲሆኑ መታሰቡንም ጠቅሰዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሕክምና ቱሪዝም ሲታሰብ ያለ አየር መንገድ ስለማይሆን ነው ይላሉ፡፡
የሆስፒታሉ ፕሮጀክት እውን እንደሚሆን ቢታሰብም፣ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መንገድ የተቋቋሙ ኩባንያዎች ዳር አለመድረሳቸው የሆስፒታሉን የወደፊት አካሔድ ጥያቄ እንዲቀርበበት ያስገድዳልና እናንተስ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር መብራቱ፣ ከዚህ ቀደም በመሰል ቢዝነስ ላይ ለመሰማራት አክሲዮን ወደ መሸጥ የገቡ ኩባንያዎች ዓላማቸውን ዳር ሳያደርሱ መቅረታቸውን ጠንቅቀው እንደሚያውቁ ገልጸው፣ የአክሲዮን ኩባንያው የቀደመው ታሪክ እንደማይደገም በልበ ሙሉነት ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለውን ሆስፒታል በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ ለመገንባት የተነሱ ኩባንያዎች ለምን ሳይሳካላቸው ቀረ? የሚለውን እንዳጠኑም ጠቅሰዋል፡፡ ከዳሰሳ ጥናቱም አክሲዮን ኩባንያዎቹ ሊሳካላቸው ያልቻለው ‹‹አክሲዮኑን ሲሸጡ ቢዝነሱን ከዕርዳታ ጋር አያይዘው አክሲዮን ለመሸጥ በመሞከራቸው ነው፡፡ የቢዝነሱን አዋጭነት በትክክል ካለማስረዳት የተነሳም ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡
ከውጭ የሚመጡ ታካሚዎችን በዓለም አቀፍ የሕክምና አገልግሎት ደረጃ መሠረት የክፍያ ዋጋ በመጠየቅ፣ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ትርፋማ መሆን እንደሚቻል በጥናት መረጋገጡን የሚገልጹት ዶ/ር መብራቱ፣ አክሲዮን ማኅበሩ ከሕክምና አገልግሎት ጎን ለጎን የሕክምና ሥልጠና የሚሰጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ስለሚኖሩት ይህም ሌላ የገቢ ምንጭ ከመሆኑ ባሻገር ባለሙያዎችን ለማፍራትም እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል፡፡ የሆስፒታሉ የግንባታ ዲዛይንም ይህንኑ ታሳቢ አድርጎ የተሠራ ሲሆን፣ የተለያዩ የሕክምና መሣሪያዎችና መድኃኒቶችንም የማስመጣትና የማከፋፈል ሥራዎችን የማከናወን ዓላማ እንዳለው የአክሲዮን ኩባንያው መመሥረቻ ጽሑፍ ውስጥ ሰፍሯል፡፡
ቴርሸሪ ሆስፒታሉ ሥራ ሲጀምር ለባለአክሲዮኖች ዓመታዊ ነፃ የሕክምና ምርመራና የዱቤ ሕክምና በመስጠት ጭምር፣ የአክሲዮን ሽያጭ በተጀመረ በስድስት ወራት ውስጥ አክሲዮን ለሚገዙም የመሥራችነት መብትና ጥቅም ይሰጣል ተብሏል፡፡ በገንዘብ አቅም ማነስ ምክንያት ወደ ውጭ አገር ሄደው መታከም ለማይችሉ ለኅብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙም እገዛ ያድርጋል ተብሏል፡፡
በ55,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አቅራቢያ የሚገነባው ቴርሸሪ ሆስፒታሉ፣ የተለያዩ የሕክምና አገልግሎቶች መስጫ ክፍሎች፣ የሄሊኮፕተር ማረፊያና የዩኒቨርሲቲ ቦታ ይኖረዋል፡፡ ከመሥራቾቹ መገንዘብ እንደተቻለው ግን እስካሁን የግንባታ ቦታ አላገኙም፡፡ ለግንባታው ቦታ መንግሥት እንደሚሰጣቸው ይተማመናሉ፡፡
የካንሰርና የፓቶሎጂ (ፎረንሲክ ሜዲስን) ምርመራ፣ የልብ ቀዶ ሕክምና፣ የኩላሊት ንቅለ ተከላና ሕክምና፣ የነርቭ ቀዶ ሕክምና፣ የመውለድ ችግርን በዘመናዊ ሕክምና መፍትሔ የመስጠትና ሌሎችም ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎቶች ይሰጥበታል የተባለው ይህ ሆስፒታል፣ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ግንባታው እንደሚጠናቀቅም በዕቅድ መያዙን ከዶ/ር መብራቱ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ግንባታው በምዕራፍ ተከፋፍሎ የሚካሄድ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ እንዳለቀ የሕክምና አገልግሎቱን እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡
