ኒውኢራ ማይኒንግ ኩባንያ ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች በጥሬ ዕቃነት የሚያገለግለውን የሲልከን አሸዋ በሰፊው ለማምረት የሚያስቸለውን ስምምት ከማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ጋር ተፈራረመ፡፡ ስምምነቱ ለ20 ዓመታት የሚቆይ የማምረት መብትን ለኩባንያው ያስገኛል፡፡
የኒውኢራ ማይኒንግ ምክትል ሥራ አስኪጅና የአክሲዮን ባለድርሻ አቶ ዳዊት ሽብሩ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በኢትዮጵያ የሲልከን አሸዋን በሰፊው ለማምረት የሚያስለቸው ፈቃድና ስምምነት በመፈጸም ኩባንያው የመጀመሪያው ሲሆን፣ በጉራጌ ዞን፣ ቡይ ወረዳ ውስጥ በሚገኘውና ኬላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ1.4 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ውስጥ እንደሚገኝ የሚገመተውን 91.91 ሚሊዮን ቶን ሲልከን አሸዋ ለማምረት ስምምነት ፈጽሟል፡፡
የምርት ሥራው በ18 ወራት ውስጥ እንደሚጀመር የገለጹት አቶ ዳዊት፣ ኩባንያው ለዚህ ሥራ የመደበው የኢንቨስትመንት ወጪ አሥር ሚሊዮን ዶላር እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ የሲልከን አሸዋ ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ ሲገባም ለ120 ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚያስገኝ ጠቅሰዋል፡፡
የሲልከን አሸዋ ለግንባታ ዘርፍ፣ ለሴራሚክ ማምረቻነት፣ ለዓይን መነፅር ሥራ የሚውለን የፋይበር መስታዋት ለማምረት፣ የሞባይል ስልኮች ስክሪን መሥሪያነት፣ ለቀለም ማምረቻነትና ሌሎችንም ምርቶች በግብዓትነት የሚፈለገው ይህ ምርት እስካሁን በብዛት ከውጭ እየገባ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡ በአገር ውስጥ በሰፊው ማምረት በሚጀመርበት ወቅትም ከውጭ የሚገባውን መጠን ለመቀነስ እንደሚያስችል አቶ ዳዊት ገልጸዋል፡፡
ኒውኢራ ማይኒንግ አስፈላጊውን የፍለጋ ሥራና የአዋጭነት ጥናት አጠናቆ ያቀረበው ባለፈው ዓመት እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ዳዊት፣ በዚህም መሠረት ለመጠነ ሰፊ የማዕድን አምራችነት ፈቃድን የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚደነግግ በመሆኑ፣ የኩባንያው ዝርዝር ሰነዶች ለምክር ቤቱ ቀርበው በመጽደቃቸው፣ ሐምሌ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ፈቃድ ማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡
ይህንን ተከትሎም በሚኒስቴሩና በኩባንያው መካከል የሲልከን አሸዋ ለማምረት የሚያስችል ስምምነት ሐሙስ፣ ነሐሴ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲፈረም ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳና የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅና የአክሲዮን ባለድርሻ የሆኑት ወ/ሮ ሊዲያ ሞሲሳ ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡
እንደ አቶ ዳዊት ገለጻ፣ የ20 ሚሊዮን ዶላር መጠን ያለው ምርት ለውጭ ኩባንያ ለማቅረብ ስምምነት መደረጉን እንዲሁም ከሌላ የአገር ውስጥ መስታወት አምራች ኩባንያም የምርት አቅርቦት ስምምነት በመግባቱ ምርቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጀመር ኩባንያው መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡
ከሲልከን አሸዋ በተጓዳኝ በወርቅ ፍለጋና በድንጋይ ከሰል ምርት ዙሪያ ፈቃድ ለመውሰድ ኩባንያው ጥናት መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡
