የህንዱ አርቲ ስቲል ኩባንያ በ75 ሚሊዮን ዶላር ወይም በ1.1 ቢሊዮን ብር ወጪ የብረት ማቅለጫ ፋብሪካው ላይ የማስፋፊያ ግንባታ ሊያከናውን እንደሆነ ተገለጸ፡፡
ጠቅላላ ሀብቱ ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ ይገመታል፡፡ ኩባንያው በገላን ከተማ የተለያዩ ዓይነት የቤት ክዳን ቆርቆሮዎች፣ የላሜራ ብረቶች፣ አልቲዜድና ቱቦላሬዎችን እንደሚያመርት ሐምሌ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በሸራተን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡
በ2003 ዓ.ም. በ700 ሚሊዮን ብር ካፒታል በኢትዮጵያ የብረታ ብረት ማምረቻ በመገንባት ሥራ የጀመረው አርት ስቲል፣ በማስፋፊያው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን ለማምረት እንዳቀደም ተገልጿል፡፡
ታኅሳስ ወር ላይ የማስፋፊያ ግንባታውን የሚያካሂደው ኩባንያውን በዓመት 100,000 ሜትሪክ ቶን ምርት ለገበያ ለማቅረብ ያስችለዋል ተብሏል፡፡ በመሆኑም 47 ሚሊዮን ዶላር ለግንባታ ሥራና ለማሽነሪ ግዥ እንደሚውል ሲገለጽ ጋልቫናይዝድ የቆርቆሮ ምርቶችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የብረት ውጤቶችን የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡
ማስፋፊያው ሦስት ዓይነት ሒደት ሲኖረው፣ በመጀመርያው የማስፋፊያ ወቅት የግብዓት ምርቶች ላይ እንደሚያተኩር የአርት ስቲል ሥራ አስኪያጅ ራጄሽ ቨርማ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ጠቅሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 40 በመቶ የገበያ ድርሻውን ለመያዝ ብሎም በርካታ ምርቶችን የማምረትና ለገበያ የማቅረብ አቅም የማስፋፊያ ግንባታው እንደሚፈጥርለት አስታውቋል፡፡
አርቲ ስቲል የብረታ ብረት ማምረቻ ፋብሪካ በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ገላን ከተማ የሚገኝ ሲሆን፣ የተቋቋመበት ካፒታል ሰባት መቶ ሚሊዮን ብር ነው፡፡ 29 የውጭ አገር ሠራተኞችና 171 ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች በድምሩ 200 ሠራተኞችን በሥሩ እያስተዳደረ የሚንቀሳቀስ ድርጀት ነው፡፡
ኩባንያው ሥራ ከጀመረበት ወቅት ጀምሮ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተደጋጋሚ እያጋጠመውና በሥራው ላይ እንቅፋት ሆኖበት መቆየቱን ሥራ አስኪያጁ ራጄቭ አስታውሰዋል፡፡
