ከተቋቋመ አምስት ዓመታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር፣ ለቀጣይ ሦስት ዓመታት ማኅበሩን የሚመሩ የቦርድ አባላት ምርጫ መጋቢት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊያካሂድ መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለቦርድ አባልነት ለመወዳደር በራሳቸው ፍላጎት፣ በአባላት ጥቆማና የዳያስፖራውን ፕሮፋይል በማየት 100 ያህል ዕጩዎች ቀርበው የነበረ ሲሆን፣ አስመራጭ ኮሚቴው ባደረገው ማጣራት 12 ዕጩዎች ለመጨረሻው ዙር አልፈዋል፡፡
አምስት ሴትና ሰባት ወንድ ዕጩዎች ከተካተቱበት ስብስብ ውስጥ በጊዮን ሆቴል በሚደረገው ምርጫ ወቅት የማኅበሩ አባላት ሰባት የቦርድ አባላት ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የቦርድ አባላት ምርጫው በነሐሴ 2008 ዓ.ም. ላይ ሊደረግ ታስቦ በተለያዩ ምክንያቶች አለመሳካቱን ያስታወሱት ዳሬክተሩ፣ ቅዳሜ ከሚደረገው የቦርድ አባላት ምርጫ በተጨማሪ በተሻሻለው የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብና በአባላት መዋጮ ላይ ውይይት ተደርጎ ውሳኔ ይተላለፋል ብለዋል፡፡ አባላት ሊያውቁት በሚገባቸው ተጨማሪ ጉዳዮች ላይም ውይይት ይደረጋል፡፡
ስድስት ሺሕ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር፣ ዳያስፖራው በአገሩ ልማት ተሳታፊ እንዲሆን መረጃ ለመስጠት፣ የልምድ ልውውጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግበትን ሁኔታ ለማመቻቸትና በዳያስፖራውና በመንግሥት መካከል ድልድይ ሆኖ ለማገልገል መቋቋሙ ተጠቅሷል፡፡
