Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በሐሰተኛ ሰነድ አጭበርብረዋል ያላቸውን 177 መካከለኛና አነስተኛ ተቋራጮች አስጠነቀቀ

$
0
0

- በምሕረት ከታለፉት ውስጥ 36 አድርሻቸው ያልታወቀ ተቋራጮች እየተፈለጉ ነው

- ከ90 በመቶ በላይ በሐሰተኛ ሊብሬ እንዳጭበረበሩ ተደርሶባቸዋል

በብርሃኑ ፈቃደ

ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በሐሰተኛ ሰነድ ያለደረጃቸው ደረጃ ለማግኘት ሲሉ ሠራተኞች ጋር በመመሳጠር አጭበርብረዋል የተባሉ ከደረጃ አራት እስከ ደረጃ አሥር ባለው እርከን የተመዘገቡ 177 ተቋራጮች ከእንግዲህ ተመሳሳይ ድርጊት ቢገኝባቸው ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው በማስጠንቀቅ በምሕረት እንዲታለፉ ማድረጉን የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ይፋ አደረገ፡፡

እንደ አዲስ የተዋቀረው የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ ቀደም ሲል የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ቤቶች ሚኒስቴር ይባል በነበረበት ወቅት ሲሰጥ በቆየው የብቃት ማረጋገጫና የሙያ ፈቃድ ምስክር ወረቀት አሰጣጥ ሥርዓት የተፈጠሩ ማጭበርበሮቹ እንደተፈጠሩ አስታውቆ፣ በዚህ መሠረት ከፌዴራል ፖሊስና ከሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በመሆን ባደረገው ማጣራት ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አሥር ባለው ርከን ውስጥ በርካታ ተቋራጭች በተጭበረበረ ሰነድ ፈቃድ ሲያወጡ፣ የብቃት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት ሲያገኙ እንደቆዩ፣ ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደ ስብሰባ ወቅት፣ የኮንስትራክሽን ሚኒስትር  አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) ይፋ አድርገዋል፡፡

ሚኒስትሯ ባስታወቁት መሠረት፣ የፌዴራል ፖሊስ ከፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በመሆን ባደረጉት ክትትል መሠረት ‹‹ፈቃድ ሳያድሱ፣ የብቃት ማረጋገጫ ሳይኖራቸው በተጭበረበሩ ሰነዶች በዜጎቻችን ላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ የሀብት ብክነት የደቀኑ ከደረጃ አንድ እስከ አሥር ያሉ ተቋራጮች ተለይተዋል፤›› ያሉት ወ/ሮ አይሻ በእነዚህ ተቋራጮች የወንጀል ክስ ከመመሥረት ይልቅ አስተዳደራዊ ዕርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል፡፡

‹‹መንግሥት ጥናት አድርጓል፡፡ ተገቢ ውሳኔም አሳልፏል፡፡ በዋናነትም ከደረጃ አራት እስከ ደረጃ አሥር ያሉና በተሳሳቱ ተግባራት ውስጥ የነበሩ ሥራ ተቋራጮች መንግሥትንና ሕዝብን ለመጨረሻ ጊዜ ይቅርታ ጠይቀው፣ ተገቢው ሥልጠና ተሰጧቸውና ወቅታዊ ብቃታቸውን የሚያረጋግጥ ፈቃዳቸውን አሳድሰው ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ውሳኔ አሳልፏል፤›› ብለዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንደ አዲስ የተዋቀረው አምና ሲሆን፣ በሕግ ከተሰጡት የሥራ ድርሻና ኃላፊነቶች መካከል በግንባታው ዘርፍ ለሚሰማሩ ተቋራጮችና አማካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት መስጠት አንዱ ነው፡፡ ይሁንና ይህንን ጨምሮ በተለያዩ በተሰጡት ሥልጣኖቹ አማካይነት ተመሳጥረው ሙስና ሲሠሩ የኖሩ አካላትን በውስጡ ይዞ የቆየ ተቋም መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገርለት የቆየ መሆኑም ይጠቀሳል፡፡ በአገሪቱ ሙሰኞች እንዲንሰራፉ ካመቻቹ ዘርፎች አንዱ በሆነው በኮንስትራክሽን መስክ በተለይ ከብቃት ማረጋገጥ፣ ከግንባታ ግብዓትና ጥራት፣ ከምዝገባ ሥርዓትና ከመሳሰሉት ችግሮች ጋር በተያያዘ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በቀደመው አሠራሩ ችግሮች እንደነበሩበት አምኗል፡፡

የኮንስትራክሽን ብቃት ማረጋገጥና ምዝገባ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ተገኘ እንዳብራሩት ከሆነ፣ ከትራንስፖርት ባለሥልጣን የተሰጣቸው በማስመሰል ሐሰተኛ ሊብሬ በማዘጋጀት ሲጠቀሙና ማረጋገጫ ደብዳቤ እንደተጻፈላቸው በማስመሰል ሲጠቀሙ የነበሩ፣ ሐሰተኛ የባንክ ብድር መያዣ ደብዳቤ የሚያጽፉ፣ ያልታደሰ የሙያ ብቃትና ፈቃድ በመያዝ የፈቃድ ሰጭ ኃላፊዎችን ፊርማና ማኅተም በማስመል አዘጋጅተው ሲጠቀሙ የነበሩ ተቋራጮች ተደርሶባቸዋል፡፡ ‹‹ለደረጃ ስምንት ፈቃድ የተሰጠው ተቋራጭ በተለያየ ዘዴ ሰነዶችን በማጭበርበር ደረጃውን ቀይሮ ደረጃ አራት ሆኖ ሲቀርብ ተገኝቷል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

በእነዚህና በመሳሰሉት ችግሮች ምክንያት የአገሪቱ የሙስና መመዘኛ ጠቋሚ ደረጃ ቀስ በቀስ እየረወደ እንደሚገኝ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ ሚኒስቴሩ በየጊዜው ፈቃድ ያደሱና የወሰዱ እንዲሁም የብቃት ማረጋገጫ ያገኙ ተቋራጮችንና አማካሪዎችን ስም ዝርዝር በድረገጹ ይፋ ቢያደርግም ክልሎችም ሆኑ ሌሎችም አካላት አይጠቀሙበትም ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ እንዲህ ያሉ በሰነድ የታዘጉ ማጭበርበሮችን ለማስቀረት የማያዳግም የዕርምት ዕርምጃ መወሰድ አለበት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና መከላከል ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዳነ መለሰ በበኩላቸው ከአገሪቱ 60 በመቶውን የመንግሥት በጀት የሚይዘው የግንባታው ዘርፍ ሐሰተኛ የማጭበርበሪያ ሰነዶች በብዛት የሚታይበት የኢኮኖሚ ክፍል እየሆነ እንደመጣ ጠቅሰዋል፡፡ በሐሰተኛ ሰነድ ከማጭበርበር ባሻገር ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከተመደበው ጊዜና በጀት ይልቅ ያለአግባብ የሚጓተቱ ፕሮጀክቶችም በብዛት በግንባታ ዘርፍ እንደሚታዩ ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በተደረገ ጥናት መሠረትም በ52 የመንግሥት ፕሮጀክቶች ተለይተሱ ሲጠኑ፣ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች ከተመደበላቸው በጀት በላይ 16.43 በመቶ ተጨማሪ ገንዘብ ሲጠይቁ፣ ፕሮጀክቶቻቸውን ለማጠናቀቅም 160 በመቶ ተጨማሪ ጊዜ አስፈልጓቸዋል ብለዋል፡፡ መንገዶች 42 በመቶ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲሁም 90 በመቶ ተጨማሪ ጊዜ ጠይቀዋል፡፡ የውኃ ሥራዎች ግንባታዎችም እንዲሁ የ175 በመቶ ተጨማሪ በጀትና የ144 ተጨማሪ ጊዜ በመጠየቅ ያልተገባ ወጪና ጊዜ መፍጀታቸው ይህም የሀብት ብክነትን ያስከተለ አካሄድ መሆኑን አቶ አዳነ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

እንዲህ ሀብትና ንብረት ባክኖባቸው ተጓተውም የሰዎችን ሕወይት የሚቀጥፉ፣ ለጉዳት የሚዳርጉ ግንባታዎችም እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ በየጊዜው የሚደረመሱ ሕንጻዎች፣ የመሠረት ማውጣት ቁፋሮዎች፣ የጉድጋድ ሥራዎች፣ የግድ ሥራዎች፣ የኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ወዘተ. ለዚህ ዓበይት ምክንያቶች ናቸው፡፡ አቶ አዳነ በዚህ መስክ የሚደርሱ ጉዳቶች ሲጠቅሱ ዋቢ ካደረጓቸው መካከል የርብና መገጭ የመስኖ ፕሮጀክትን ግንባታ ሒደት ላይ የደረሰው አደጋ ይገኝበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተለመደ እየሆነ የመጣው የግንባታ አደጋ ቀስ በቀስ እያሻቀበ ይመስላል፡፡ ክሬኖች ይወድቃሉ፤ በእንጨት መወጣጫ እንደ ድሪቶ የተቧተቱ የግንባታ ስፍራዎች ከተማዋን ወረዋት ይታያሉ፡፡ እነዚህም ለአደጋ መንስዔ ከሚሆኑባቸው ምክንያቶች መካከል በሕጉ መሠረት፣ በተሰጣቸው ትክክለኛ ፈቃድ እንዲሁም በሙያ ብቃታቸው መሠረት የማይሠሩ በመሆናቸው ምክንያት ጭምር እየደረሱ የሚታዩ አደጋዎች እንደሆኑ እየታየ ነው፡፡

እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቀነስ መነሳቱንና የሌሎች እንደ ፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ያሉ መሥሪያ ቤቶችን ትብብር የጠየቀው ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ እስካሁን በታዩት የሰነድ ማጭበርበር ድርጊቶች ውስጥ ከ90 በመቶ ያላነሱት ሐሰተኛ ሊብሬ ያቀረቡ መሆናቸውን አቶ ቴዎድሮስ ይፋ አድርገዋል፡፡ እነዚህ ማጭበርበሮች በተለይ በፒክ አፕ እንዲሁም በገልባጭ መኪኖች ላይ የታዩ ማጭርበሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በአንፃሩ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በተገኘ መረጃ መሠረት 19,137 የግንባታ መሣሪዎችን የተመለከቱ መረጃዎች በማግኘቱ በዚህ መስክ ችግር እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡  

እስካሁን በሐሰተኛ ሰነድ ያጭበረበሩ ተብለው ከተለዩት 177 ተቋራጮች ውስጥ በአድራሻቸው ሊገኙ ያልቻሉ 36 ተቋራጮች በፖሊስ እየተፈለጉ እንደሚገኙ አቶ ቴዎድሮስ አስታውቀው፣ ምሕረት ተደርጎላቸዋል የተባሉት 141 ተቋራጮችም ቢሆኑ ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጽሙ ቢገኙ ከባድ ቅጣት እንደሚጣልባቸው፣ ለአሁኑ ግን የቃለ መሐላ ሰነድ ፈርመው የተጣለባቸው ዕግድ እንደሚነሳላቸው ጠቅሰዋል፡፡ ከሚኒስቴሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት ተቋራጮቹ እንደገለጹት ከሆነ፣ እስከ አራት ዓመታት የቆየ ዕግድ ተጥሎባቸው ቆይተዋል፡፡ አንዳንዶቹም በማያውቁት ምክንያት ተጭበርብሮ በተገኘ ሰነድ መጠየቃቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡

ሚኒስትሯ ወ/ሮ አይሻ ምንም እንኳ በወንጀል የሚያስጠይቁ ጉዳዮች ቢገኙባቸውም ተቋራጮቹ ግን ብቻቸውን እንዳልነበሩ፣ የአስፈጻሚው እጅ ስለነበረበት፣ ከዚህም ባሻገር በሥራቸው በርካታ ሰዎችን የሚያስተዳድሩ ሰፊ መሠረት ያላቸው ተቋራጮች ሆነው በመገኘታቸው ምሕረት እንዲደረግላቸው መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥሩ የሚታመንባቸው፣ ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ ሦስት ያሉ በሰነድ ማጭበርበር ተግባር የተጠረጠሩ ተቋራጮች ላይ ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ 

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles