- የቦብ ማርሌ ኪነ ቅርጽ የሚገኝበት አደባባይ የሚፈርስ በመሆኑ ምትክ ቦታው እየተጠበቀ ነው
ለአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ መጨናነቅ በማስከተላቸው እንዲፈርሱ ከተባሉና ተላላላፊ መንገድ ከሚገነባቸው መካከል አንዱ የሆነው የቦሌ ሚካኤል አደባባይ የተላላፊ መንገድ ዲዛይን መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡ የቦብ ማርሌ ኪነ ቅርፅ ከሚገኝበት ቦታ ተነስቶ ይዛወርበታል የተባለው ምትክ ቦታ የት እንደሚሆን ውሳኔ እስኪሰጥበት እየተጠበቀ ነው፡፡
ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የቦሌ ሚካኤል ተላላፊ መንገድ ዲዛይን ርክክብ ከተፈጸመ በኋላ ተላላፊ መንገዱን ለሚገነቡ ተቋራጮች ጨረታ ይወጣል፡፡ ስለመንገዱ ሥራ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እንደቦሌ ሚካኤል አደባባይ ሁሉ ተሽከርካሪዎችን ከበላይ የሚያሻግሩ ተላላፊ መንዶች ዲዛይን እየተሠራላቸው የሚገኙ ሌሎችም አደባባዮች አሉ፡፡
የቦሌ ሚካኤል ተላላፊ መንገድን ዲዛይን የሠራው ሔክ የተባለ አገር በቀል አማካሪ ድርጅት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ለከተማዋ የትራፊክ ፍሰት እንቅፋት መሆናቸው ታውቆ እንዲፈርሱ ከተባሉት አደባባዮች ውስጥ ቦሌ ሚካኤል አደባባይ፣ 18 ማዞሪያና መካኒሳ አደባባዮች ፈርሰዋል፡፡ ሊገነቡ የታቀዱላቸው ተላላፊ መንገዶች እስኪሠሩ ድረስ የትራፊክ ፍሰቶችን አሁን ባሉበት ጊዜያዊ ሁኔታ እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡ ከቦሌ ሚካኤልና ከመካኒሳ አደባባዮች ባሻገር በቅርቡ እንደሚፈርሱ የሚጠበቁት የለቡ (መብራት ኃይል)፣ የቃሊቲ፣ የኢምፔሪያል፣ የሳሪስ አቦ፣ የጃክሮስ አደባባዮች እንደሆኑ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡
ከቃሊቲ አደባባይ ባሻገር ያሉት ቀሪዎቹ አደባባዮች ከፈረሱ በኋላ የሚገነቡላቸው ተላላፊ መንገዶች እስኪገነቡ ድረስ አደባባዮቹን የሚያገናኙ መንገዶች የትራፊክ መብራት ይተከልላቸዋል ተብሏል፡፡
የቃሊቲ አደባባይ ተላላፊ መንገድ ከሌሎች በተለየ ሁኔታ እንደሚገነባ ታውቋል፡፡ የዚህ አደባባይ ግንባታ የሚካሄደው በቅርቡ ከቃሊቲ አደባባይ በሁለት አቅጣጫ ወደ ቂሊንጦ የሚወስደው ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክት አካል ሆኖ ነው፡፡ ይህንን ፕሮጀክት ቻይና ኮሚዩኒኬሽንስ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሆን፣ መንገዱን በ4.7 ቢሊዮን ብር ለመገንባት በመስማማት ወደ ግንባታ መግባቱ ይታወሳል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀድሞው ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ የሚገኘውና የቦብ ማርሌ አደባባይ እየተባለ የሚጠራው መንገድ አንዱ ፈራሽ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከሚታየው የትራፊክ መጨናነቅ አንፃር በቅድሚያ መፍረስ አለባቸው ተብልው ከተለዩት ውስጥ አንዱ ይኸው የቦብ ማርሌ አደባባይ ቢሆንም፣ በአደባባዩ የተተከለውን የቦብ ማርሌ ኪነ ቅርፅ አንስቶ ወደ ሌላ ቦታ ለማዛወር የሚጠይቀው ሒደት ጊዜ በመፍጀቱ አደባባዩን የማፍረሱ ሥራ ሊዘገይ እንደቻለ ተነግሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሐውልቱን ወደ ሌላ ቦታ በማዛወር አደባባዩን ለማፍረስ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ተብሏል፡፡ ባለሥልጣኑ የዚህን አደባባይ ጉዳይ ለመፍታት የቦብ ማርሌን ቅርጽ የያዘውን ምስል ከማንሳቱ በፊት ኪነ ቅርጹን ካሠሩት አካላትና ከቦብ ቤተሰቦች ጋር እንደተመካከረ አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኪነ ቅርፁ ሊዛወርበት የሚችልበት አማራጭ ቦታዎች በመመረጣቸው ሐውልቱን የማዛወር ሥራ በቅርቡ ይጀመራል ተብሏል፡፡ የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ የቦብ ኪነ ቅርጽ አሠሪዎች የተለያዩ አማራጭ ቦታዎችን አቅርበው ከቀረቡት ውስጥ አንደኛው በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሏል፡፡ ኪነ ቅርጹ ይዘወርበታል ተብሎ የተለየውን ቦታ የአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ይጠበቃል፡፡
ኪነ ቅርፁን በማዛወሩ ተግባር ላይ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም ሌሎች የአስተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች ከኪነ ቅርጹ ገንቢዎች ጋር በጋራ እንዲሠሩ የተደረገ ሲሆን፣ የማዛወር ሥራውም በልዩ ዝግጅት በክብር እንዲከናወን መታቀዱን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
ኪነ ቅርጹን በዋናነት አርቲስት ዘለቀ ገሠሠ ከተባባሪዎቹ ጋር በመሆን ማስገንባቱ የሚታወስ ሲሆን፣ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የፈጀ የኪነ ቅርጽ ሥራ እንደሆነ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
