Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

አዲስ የዲቪዲና የሲዲ ማምረቻ ፋብሪካ በአዲሱ የቴዲ አፍሮ አልበም ሥራውን እንደሚጀምር ይፋ አደረገ

$
0
0

ከ50 ሚሊዮን ብር ብላይ ወጪ የተደረገበት ዘመናዊ የሲዲና የቪሲዲ ማምረቻ ፋብሪካ ማሟሻውን የቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) አዲስ አልበም በማድረግ ለማተም ትዕዛዝ መቀበሉ ተገለጸ፡፡

ቆልያ ማኑፋክቸሪንግ አክሲዮን ማኅበር ተብሎ የተሰየመው የሲዲና የዲቪዲ ማምረቻው ባለፈው ሳምንት ሥራ መጀመሩ ይፋ ሲደረግ እንደተገለጸው፣ በዓመት ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሲዲዎችንና ዲቪዲዎችን የማምረት አቅም አለው፡፡ የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ አደመ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት ፋብሪካው በዓመት ይህንን ያህል ሲዲና ዲቪዲ ለማምረት የሚችልባቸውን መሠረተ ልማቶች አሟልቶ ሥራ ጀምሯል፡፡ ከአዲስ አበባ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በዱከም ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የተገነባው ይህ ማምረቻ፣ ደረጃቸው የተረጋገጠላቸውን ዲቪዲዎችንና ቪሲዲዎችን ለማምረት የሚያስችል ሲሆን፣ በዚሁ መሠረትም ሥራዎቹን በፋሲካ በዓል ዋዜማ ለአድማጮች ለማድረስ የተሰናዳውን የቴዲ አፍሮን አልበም በማተም እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡

የአዲሱን የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ አልበም አትሞ ለፋሲካ በዓል ለማድረስ ውል መዋዋላቸውና በታዘዘው ኮፒ ብዛት መሠረት አትመው እንደሚያስረክቡም ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ያሬድ ከሆነ፣ ወደዚህ ቢዝነስ የገቡት ጥራት ያለው ዲቪዲና ቪሲዲ አቅርቦት ላይ የሚታየውን ችግር በመገንዘባቸው ነው፡፡ ይህንን ማምረቻ ከማቋቋማቸው ቀደም ብሎ እሳቸውና አንዳንድ የአክሲዮን ኩባንያው አባላት ከሲዲና ዲቪዲ ሽያጭ ጋር የተገናኙ ሥራዎች ውስጥ ይሳተፉ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ይህ ሥራ ግን ጥራት የጎደላቸው የዲቪዲና የቪሲዲ ምርቶች ገበያውን በማጥለቅለቃቸው ሳቢያ ደንበኞቻቸውም ሆኑ አርቲስቶች ሲቸገሩ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በቀላሉ የሚበላሹ ሲዲዎች ይቀርቡ ስለነበር ይህንን ለማስተካከል የሚያስችል ዘመናዊ ማሽን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ሥራ መጀመር እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡ ማሽኑ በአሁኑ ወቅት ህትመት በኢንዱስትሪው የመጨረሻው ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑ የተነገረለትን የጀርመን ሥሪት ቴክኖሎጂ በማስመጣት እንደተከሉ የሚገልጹት አቶ ያሬድ፣ የእያንዳንዱ ምርት ጥራት የሚቆጣጠር ሶፍትዌር ያለው መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ በቪሲዲና በዲቪዲዎቹ ላይ የሚታተመውን ማስተር ብቻ በመቀበል ሙሉ የዲቪዲና የቪሲዲ ኅትመትና የማሸግ ሥራዎችን አከናውኖ ለማስረከብ የሚያስችል ነው፡፡ እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ አዲሱ ማሽን ፖሊ ካርቦኔት ከሚባለው የቴርሞፕላስት ኬሚካል ጥሬ ዕቃ ሲዲውን ከማምረት ጀምሮ ምስልና ድምፅ፣ ፊልሙንና የሙዚቃ ወይም ፊልሙን የሚገልጹ ምስሎችን በማተም አሽጎ የሚያወጣ ሲሆን፣ ባዶ ዲቪዲና ቪሲዲ ከሚመረትበት ቴክኖሎጂ በተለየ መልኩ እንደሚሠራም ተጠቅሷል፡፡  

በአሁኑ ወቅት በቪሲዲና በዲቪዲ ታትመው ለገበያ ከሚቀርቡ የተለያዩ ሃይማኖታዊ መዝሙሮች፣ መንዙማዎች፣ ሙዚቃና ፊልሞች ፍላጎት አንፃር አሁንም ኢንዱስትሪው ሰፊ ገበያ እንዳለው ተጠቅሷል፡፡ በየዓመቱ በአሥር ሚሊዮኖች የሚገመቱ በዲቪዲና በቪሲዲ የሚታተሙ ፊልሞችና ሙዚቃዎች፣ ሃይማኖታዊ መዝሙራትና መንዙማዎች ለተጠቃሚው እንደሚሰራጩ የጠቀሱት አቶ ያሬድ፣ ይህንን ፍላጎት ለመሙላት እስካሁን በነበረው አሠራር መሠረት በአነስተኛ ማሽኖች ታትመው ለገበያ ሲውሉ መቆየታቸውን አብራርተዋል፡፡

በፋብሪካ ደረጃ ከቆልያ ማኑፋክቸሪንግ ባሻገር በህንድ ባለሀብቶች የተያዘ አንድ የዲቪዲና የቪሲዲ ማምረቻ መኖሩን የገለጹት አቶ ያሬድ፣ አብዛኛው የዲቪዲና የቪሲዲ ኅትመቶች የሚካሄዱት ግን በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ አነስተኛ ማተሚያዎች ውስጥ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በአርቲስቶች የተመሠረተ የሲዲ ማምረቻም የሚጠቀስ ነው፡፡

ቁልያ በዓመት ስምንት ሚሊዮን ኮፒዎችን በማምረት ወደ ኢንዱስትሪው የገባ ትልቁ አምራች መሆኑ ቢገለጽም፣ ካለው ፍላጎት አንፃር የገበያ ድርሻው ከ10 እስከ 15 በመቶ ያህል ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ ከዚህም በላይ ሕገወጥ በሆነ መንገድ  በፍላሽና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች አማካይነት ኮፒ የማድረግ ሥራዎችም ታክለውበት የሲዲና የዲቪዲ ፍላጎት አለ የሚሉት አቶ ያሬድ፣ እንዲህ በፋብሪካ ደረጃ የዲቪዲና የቪሲዲ ማምረቻ እየተበራከቱ በመምጣታቸውም ከኤሌክትሮኒክስ ኅትመት ኢንዱስትሪ የሚገኘው ጥቅም እያደገ እንዲሄድ ያደርገዋል ይላሉ፡፡

የኪነ ጥበብ ባለቤቶችም ሆኑ መንግሥት በሕጋዊ መንገድ በሚመረትና በሚሰራጨው የቪሲዲ ኅትመት ውጤቶች አማካይነት የገበያ ልውውጡ የሚያስገኘው ከፍተኛ ገቢ እንደሆነ የገለጹት አቶ ያሬድ፣ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ የገንዘብ የሚሽከረከርበት በመሆኑም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም በዚያው ልክ ከፍተኛ እንደሆነ ያምናሉ፡፡

በርካታ አገሮች ከዚህ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ገቢ እንደሚያገኙ ያስታወሱት አቶ ያሬድ፣ ፋብሪካው በቀላሉ የማይበላሹ ሲዲዎችንና ቪሲዲዎችን ከማምረት ባሻገር በሕጋዊ መንገድ እየተባዛ ለገበያ በሚቀርበው የኅትመት ውጤት አማካይነት የሚካሄደው ግብይት የኪነ ጥበብ ማኅበረቡን፣ ሸማቹንና መንግሥትን በብዙ መንገድ ተጠቃሚ ያደርጋል ይላሉ፡፡

ኩባንያው ለሲዲና ዲቪዲ ማምረቻ ኢንቨስትመንቱ ለማዋል ከአዋሽ ባንክ አንድ ሚሊዮን ዩሮ ብድር ፈቅዶለት ማሽኑን እንዳስመጣ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles