Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

ትራንስፖርት አቅራቢዎች ወደ ካርቱም የሚደረገው ጉዞ ከታቀደው በላይ አራት ቀናት እየወሰደባቸው እንደሚገኝ ገለጹ

$
0
0

-የፍተሻ ኬላዎች መብዛት ጉዞውን ካራዘሙ ችግሮች ዋናዎቹ ናቸው

- ወደ ሱዳን የሚገቡ መኪኖች ሦስት ሺሕ ብር ይጠየቃሉ

 ከአዲስ አበባ ካርቱም፣ ከካርቱም አዲስ አበባ በደርሶ መልስ ሕዝብ የማመላለስ አገልግሎትን በቅርቡ የጀመሩ ተሸከርካሪዎች እስካሁን ከ400 በላይ መንገደኞችን ቢያጓጉዙም ሁለት ቀናት ይፈጃል የተባለው ጉዞ እስከ አራት ቀናት ድረስ እየወሰደባቸው መሆኑን ገለጹ፡፡ የሁለቱ አገሮች ባለሥልጣናት በጉዳዩ ለመምከር ቀጠሮ ይዘዋል፡፡

በኢትዮጵያ ወገን አገልግሎቱን እየሰጡ ከሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት ድርጅቶች ተወካዮች ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ ከአዲስ አበባ ካርቱም ድረስ ያለውን 1500 ኪሎ ሜትር ርቀት በሁለት ቀናት ውስጥ በመሸፈን አግልግሎቱ እንዲቀርብ የተቀመጠውን መርሐ ግብር ለማሳካት አልተቻለም፡፡

የኢትዮ ሱዳን የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ጥምር ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሁም የጎልደን ባስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወጋየሁ አራጋው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እስካሁን የሁለቱ አገሮች ትራንስፖርት ድርጅቶች ወደ አዲስ አበባና ወደ ካርቱም በየፊናቸው ስምንት ያህል የደርሶ መልስ ጉዞዎችን አከናውነዋል፡፡ ሆኖም ሁሉም ጉዞዎች በታቀደላቸው መሠረት በሁለት ቀናት ውስጥ መጠናቀቅ አልቻሉም፡፡ በተለይ ከሱዳን ወገን ያሉ አሽከርካሪዎች ጉዞዎቻቸው አራት ቀናት ድረስ እየፈጁባቸው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያለው ችግር የተፈጠረበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ በሱዳን ክልል ውስጥ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶቹ ከ20 ባላነሱ ጣቢያዎች እንዲቆሙ እየተገደዱ ፍተሻ ስለሚካሄድባቸው ነው ተብሏል፡፡  

የቀናቱ መራዘም ደግሞ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ችግር እያስከለተ በመሆኑ ሌሎችንም መሰል ችግሮች በማካተት መፍትሔ ይሰጣል የተባለ ውይይት ለማድረግ የትራንስፖርት ተቋማቱና የሁለቱ አገሮች ባለሥልጣኖች ለስብሰባ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ በካርቱም ሊደረግ የታሰበው ስብሰባ በእስካሁኑ እንቅስቃሴ የታዩ ክፍተቶች ላይ ለመምከር በስብሰባው የሚሳተፉ የኢትዮጵያ ልዑካን ትናንት፣ መጋቢት 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ካርቱም አቅንተዋል፡፡ መፍትሔ ያሻቸዋል ከተባሉ ጉዳዮች አንዱ በመሆን መፍትሔ ይሰጥበታል የተባለው ይኸው የጉዞ ቀናቶችን ያራዝማሉ የተባሉት የፍተሻ ጣቢያዎች መብዛት እንደሆነ ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ፈተሻው መተማ ላይ ብቻ እንደሚደረግ የገለጹት አቶ ወጋየሁ፣  በሱዳን ክልል ውስጥ ያለው በርካታ ፍተሻ እንዲሁም በየመንገዱ መኪኖች እንዲቆሙ የሚስገድዱትን ጣቢያዎች ብዛት መቀነስ የሱዳን መንግሥት ድርሻ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ 

እንደ አቶ ወጋየሁ ገለጻ፣ ከኢትዮጵያ ወገን ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ተብለው ከሚነሱት ጉዳዮች መካከል አገልግሎቱን ለመጀመር በሁለቱ አገሮች ባለሥልጣናት መካከል ከተደረሰው ስምምነት ውጭ ወደ ሱዳን ድንበር ሲገባ እየተጠየቀ ያለው ክፍያ ሌላው የሚመከርበት ጉዳይ ነው፡፡   

‹‹በስምምነታችን መሠረት የኮሜሳ አባል አገሮች ተሽከርካሪዎች ከአንዱ አገር ወደ ሌላው ሲገቡ፣ ኮሜሳ የሚሰጠውን መለያ ካርድ አሳይቶ መንቀሳቀስ ይችላል፡፡ በዚህ የይለፍ ካርድ አማካይነት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ክፍያ የሚከፈልበት ሲሆን፣ ይህንን ካርድ የያዘ ተሽከርካሪ ያለ ተጨማሪ የኮቴ ክፍያ ድንበር ሊሻገር ይችላል፡፡ አሁን ግን እየተጠየቀ ያለው ከስምምነቱ ውጪ በመሆኑ ሊፈታ ይገባዋል፤›› ብለዋል፡፡

በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችለው ስምምነትም ይህንኑ የኮሜሳ አባል አገሮች የሚገዙበትን አሠራር ተከትሎ እንዲካሄድ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ይህ ጉዳይ መፍትሔ የሚያሻው መሆኑን አቶ ወጋየሁ ገልጸዋል፡፡ አሁን ግን የኢትዮጵያ የሕዝብ ማመላለሻዎች ወደ ሱዳን ሲገቡ በአንድ መኪና እስከ ሦስት ሺሕ ብር ክፈሉ መባላቸው ችግር እየፈጠረ ነው፡፡

የበካርቱም የሚካሄደው ውይይት እንዲህ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ተስፋ እንደተጣለበት የገለጹት አቶ ወጋየሁ፣ እየተጠየቀ ያለው ተጨማሪ ክፍያ ከስምምነቱ ውጪ በመሆኑ ይህ እንዲቀር የሚያደርግ ውሳኔ ይተላለፋል ብለው እንደሚጠብቁ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡  

ከአዲስ አበባ ካርቱም የሚካሄደው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በይፋ ሥራ የጀመረው መጋቢት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡ ለአንድ ጉዞ 60 ዶላር የሚከፈልበት ይህ አገልግሎት፣ በሙከራ ጊዜው እንደታየው በርካታ ተሳፋሪዎችን እያገኙ ያሉት ከካርቱም ወገን ወደ አዲስ አበባ የሚጓጓዙ መኪኖች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡ እስካሁን ወደ አዲስ አበባ ከተደረጉ ስምምነት ጉዞዎች ውስጥ በአማካይ 40 መንገደኞች በአንድ መኪና ተጓጉዘዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ካርቱም የተደረጉት ስምንት ጉዞዎች ደግሞ በአማካይ 15 መንገዶችን አጓጉዘዋል፡፡

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles