Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚያዊ ድርሻ እያደገ መምጣቱ ተገለጸ

$
0
0

 

  • 170 የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የተሳተፉበት ዓውደ ርዕይ ነገ ይጠናቀቃል

 የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በአማካይ 28.7 በመቶ ዕድገት እየተመዘገበበት እንደመጣና የኢኮኖሚ ድርሻውም 8.5 በመቶ መድረሱን የኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ወ/ሮ አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) ገለጹ፡፡

  ሚኒስትሯ ይህንን የገለጹት አምስተኛውን ‹‹ኮንስትራክሽን ለኢትዮጵያ ህዳሴ›› የተሰኘውን ዓውደ ርዕይ ሐሙስ፣ መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን በከፈቱበት ወቅት ነበር፡፡  

ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ አገሪቱ በምትከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉ እያንሰራራ መምጣቱን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ በአሁኑ ወቅት በጠቅላላው ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ትልቁን ሚና ከሚጫወትበት ደረጃ ላይ መድረሱንም አውስተዋል፡፡

ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ ባሻገር፣ ከ1994 ዓ.ም. ወዲህ በመኖሪያ ቤቶች፣ በመንገድ፣ በኃይል፣ በባቡር መሠረተ ልማት፣ እንዲሁም በሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውስጥ የዘርፉን ተሳትፎ ያሳደጉና አገሪቱን ተጠቃሚነት ያጎሉ ውጤቶች መታየታቸውንም ወ/ሮ አይሻ አመልክተዋል፡፡

በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የሚከናወኑ ሰፋፊ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች በሥራ ዕድል መስክ ያላቸው ሚና እያደገ በመምጣቱ፣ በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪው የሚያሳትፈው የሰው ኃይል ብዛት 1.2 ሚሊዮን መድረሱን ገልጸዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲወጣ ያስችላሉ የተባሉ እንቅስቃሴዎችን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው እየሠራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በዋናነት እየተሠሩ ናቸው ካሉዋቸው መካከል የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የማስፈጸም አቅም ግንባታ ፕሮግራም አንዱ ነው፡፡

ሚኒስቴሩ ለአቅራቢዎች፣ ለተቋራጮች፣ ለአማካሪ ድርጅቶችና በአጠቃላይ በኢንዱስትሪው ውስጥ ለሚገኙ ተዋንያን የአቅም ግንባታ የሚሰጥበት ፕሮግራም መቅረጹን ወ/ሮ አይሻ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ጠቅሰዋል፡፡ የግንባታ ዘርፉን ለማሳደግ ሚኒስቴሩ እንደሚተገብራቸው ከሚጠበቁት መካከል እንደ ሕንፃ አዋጅ ያሉትን ሕግጋት፣ የተሻሻሉና አዲስ የወጡ መመርያዎችና ደረጃዎች ተዘጋጅተው ወደ ተግባር መቀየር እንደጀመሩም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ያዘጋጀውና ለአምስት ቀናት የሚቆየው ዓውደ ርዕይ 170 የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የተሳተፉበት ነው፡፡  የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ እንደገለጹት፣ ዓውደ ርዕዩ ላይ ኢንዱስትሪውን የሚመሩና የሚያስተባብሩ እንዲሁም የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎች፣ አከፋፋዮች፣ አምራቾችና የመሳሰሉት ታደመውበታል፡፡ እነዚህን በአንድ ላይ በማሰባሰብ ኢንዱስትሪው የደረሰበትን ደረጃ ከማመላከት በተጓዳኝ አማራጭ የገበያ መረጃዎችንም ለመለዋጥ እንደሚረዳ አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደረጃ አንድ ተቋራጮች ማኅበር በአሁኑ ወቅት የደረጃ አንድ ግንባታ ፈቃድ ያላቸው ከ45 በላይ አባላትን አቅፎ የሚንቀሳቀስ የሙያ ማኅበር ነው፡፡ 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles