አቶ ዋና ዋኬ፣ የውኃ ሀብት ልማት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር
አቶ ዋና ዋኬ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ለዓመታት አግልግለዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የውኃ ሀብት ልማት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከመሾማቸው ቀድሞ ለስምንት ዓመታት ያህል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነበሩ፡፡ አባል ብቻም ሳይሆኑ በበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነት ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከፈረንሣይና ከጣልያን መንግሥታት የተገኘውን የ75 ሚሊዮን ዩሮ ብድር (በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በኩል የተገኘ) መነሻ በማድረግ ለዓመታት ተስተጓጉሎ የቆየውንና የ15ቱ ከተሞች የውኃ ፕሮጀክት በመባል የሚታወቀውን ፕሮጀክት በስምንት ከተሞች አማካይነት ዳር ለማድረስ የሚመሩት የውኃ ልማት ፈንድ የብድር ስምምነት አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከ15 ከተሞች ስምንት ብቻ የሆኑት ከ75 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ የቀሪዎቹ ሰባት ከተሞች በአማራ ክልል በጀት የፕሮጀክት ወጪያቸው ተሸፍኗል፡፡ ለስምንት ከተሞች ተቋሙ የ189 ሚሊዮን ብር ብድር እንዲያገኙ በማድረግ፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የመጠጥ ውኃ ለሕዝብ ማድረስ እንዲጀምሩ ስምምነት ተደርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር መንግሥት ከዓለም ባንክ የሚያገኘው የ450 ሚሊዮን ዶላር ብድር በአብዛኛው ለከተሞች የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ እንደሚውል አቶ ዋና ከሪፖርተር ጋር ከጥቂት ሳምንታት በፊት ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡ ተቋሙ ለከተሞች ከሚያቀርበው ብድር ምን ያህል ወለድ እንደሚያገኝ፣ የብድር መክፊያ ጊዜ፣ ፕሮጀክቶች በምን መመዘኛ ተቀባይነት እንደሚያገኙና በሌሎችም ነጥቦች ላይ ብርሃኑ ፈቃደ ከውኃ ልማት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዋና ዋኬ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሪፖርተር፡- የውኃ ልማት ፈንድ ለከተሞች የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችን የሚደግፍ ነው፡፡ ዋና ዋና ሥራዎቹ ምንድን ናቸው?
አቶ ዋና፡- የውኃ ልማት ፈንድ ከ15 ዓመታት በፊት የውኃ ዘርፍ አስተዳደር ፖሊሲ ወጥቶለት ነበር፡፡ የሚገነቡት መሠረተ ልማቶች የወጣባቸውን ዋጋ በማስመለስ መርህ ላይ ተመሥርቶ እንዲሠራ የሚል እሳቤ ተይዞ የውኃ ልማት ፈንዱ ተመሥርቷል፡፡ ይኼ ለምን ይጠቅማል? ካልን አንደኛው ለከተማውም ሆነ ለገጠሩም እንዲህ ያለው ሰፊ ፍላጎት ያለበትን ኢንቨስትመንት በነፃ ማቅረቡ ይሻላል ወይስ ከአንዱ የከተማ ፕሮጀክት በኋላ ሌሎች ባዷቸውን የሰነበቱ፣ የውኃ አቅርቦት ችግር ያልተቀረፈላቸው በተራቸው እንዲጠቀሙ ለማድረግ ዋጋ በማስመለስ መሥራት ይሻላል የሚለውን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ ጎን ከውጭ በሚመጡ ብድርና ዕርዳታዎች ላይም ከምናማትር በራስ ወጪ ፕሮጀክቶችን እየገነባን ለመቀጠል በማሰብ ነው ፈንዱ የተቋቋመው፡፡ ከውጭ የሚመጡ ብድሮች ወይም ዕርዳታዎች እንደየሰጪዎቻቸው ከበስተኋላቸው የሚመጡ የተለያዩ ፍላጎቶችን ይዘው የሚመጡ ናቸው፡፡ የከተሞች መስፋፋት በጣም እየጨመረ መጥቷል፡፡ ገጠር የነበሩ አካባቢዎች ከተማ እየሆኑ በመምጣታቸው የውኃ አቅርቦት ፍላጎት እየጨመረ ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ለውጦችን ለማዳረስ በውጭ ብድር ብቻ የሚዘለቅ ስላልሆነ የራሳችን ፈንድ ብናቋቁም ግን ለእነዚህ ጥያቄዎች በተሻለ ፍጥነት መድረስ የምንችልበትን አቅም ይሰጠናል፡፡
ሪፖርተር፡- ፈንዱ ለከተሞች የሚሰጠው ብድር በምን መልኩ ነው ተመላሽ የሚደረገው?
አቶ ዋና፡-የፈንዱ የወጪ ማስመለስ አሠራር ሙሉ በሙሉ ተመላሽ ማድረግ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ለመሠረተ ልማቶች ዝርግታ የሚወጣው ወጪ ሙሉ በሙሉ ተመላሽ ማድረግ ቢባልም እስካሁን ገና አልጀመርንም፡፡ በከፊል ነው እያስመለስን የምንገኘው፡፡ ሌላው ከተጠቃሚ ከተሞች፣ ከክልሎቻቸው ወይም ከከተማ አስተዳደሮች ወይም ከውኃ አገልግሎቶች የሚዋጣ ገንዘብ እያጋጨን በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡ ስለዚህ የሚመለሰው ከእኛ በብድር የሚሄደው መጠን ነው ማለት ነው፡፡ የሚሄደው ገንዘብ ግን የዕርዳታ ክፍልም አለው፡፡ እኛ እንዲመለስልን የምጠይቀው ግን የብድሩን ክፍል ብቻ ነው፡፡ የከተሞች ውኃ አገልግልቶች በምንፈልገው ብቃት ደረጃ ላይ አለመገኘታቸው አንዱ ትልቅ ችግር ነው፡፡ በሙሉ ኃይላቸው ተጠቅመው አገልግሎቱን ለሚፈልገው ሕዝብ የማዳረስ ሥራና አቅም በታሰበው ጊዜ ውስጥ የማቅረብ ሒደት ችግር ይታይበታል፡፡ ይኽም የሰው ኃይሉ ላይ የሚታይ ነው፡፡ አሁን ያለውን ዘመናዊ ማኅበረሰብና ፈጣን የውኃ አቅርቦት ጥያቄን የሚያስተናግዱ፣ በቂ ዕውቀትና ክህሎት ኖሯቸው የውኃ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች የማይገኙበት አጋጣሚ ይበዛል፡፡ ስለዚህ ይኼ አንዱ የጉዳት አካባቢ ነው፡፡ ከክልሎች ጋርም የምንነጋገርበት ርዕስ ነው፡፡ የውኃ መሐንዲሶች ያስፈልጋሉ፡፡ የውኃ ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ሶሺዮ ኢኮኖሚስቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ ሥርዓትን የሚተገብሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የደገፈ አሠራሮች ያስፈልጋሉ፡፡ የተሟላ መዋቅር ሊኖር ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ጉድለት አለ፡፡ የተሻለ የአሠራር ሥርዓት ያልተዘጋላቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ በአብዛኛው ከውኃ መዋቅሩ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የሌላቸው ናቸው፡፡ ከከተማ መዋቅሩም ጋር ቢሆን የአሠራር አለመጣጣም የሚታይባቸው፣ ለእያንዳንዱ የሚሠሯቸው ሥራዎች የሕጎችን መጣጣም ለማስፈን ዕውቀት ያላቸውን ሰዎች የመጠቀም ችግር ይታይባቸዋል፡፡ የሰው ኃይል ፍልሰትም ችግር እየሆነ ቆይቷል፡፡ ፕሮጀክቶች ሲጠኑ ጀምሮ የነበሩ ሰዎች ወደ ተግባር ሊገባ ሲል ይለቃሉ፡፡ በአሁኑ አሠራር ግን መላ አስቀምጠናል፡፡ እነዚህ ክፍቶች ባሉበት ወደ ሥራ እየተገባ ችግሮች ይታያሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ዋጋ ወደ ማስመለሱ ሥራ እየገባን ያለነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ ወደዚህ አስተሳሰብ መሻገር መቻል ትልቅ ዕመርታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በሰው ውስጥ ያለው አስተሳሰብ ዕርዳታ ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ፣ ብድርና ብድርን በመመለስ ሥራ ላይ ሲተኮር ፈንዱን ለሌሎች አካባቢዎችም እንዲውል ለማድረግ ያስችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ብድር የሚሰጥበት የወለድ ምጣኔ ምን ይመስላል? የሚመለስበት አሠራርስ እንዴት ነው የሚተገበረው?
አቶ ዋና፡- ብድር ሲባል ውኃ ልማት ፈንድ በዓመት ከሦስት በመቶ ያልበለጠ ወለድ በማስከፈል የሚሰጠው ነው፡፡ ይህ ግን የራሱን አስተዳደራዊ ወጪ እንኳ የማይተካ ነው፡፡ በዋጋ ንረት ገንዘቡ የሚያጣውን የመሸመት አቅም እንኳ አይተካም፡፡ የሚሰጠው ብድርም ከ25 እስከ 40 ዓመታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ የሚከፈል ነው፡፡ ስለዚህ ብድር ሊባል የሚችል ገንዘብ አይደለም የምንሰጠው፡፡ ይልቁንም ከተሞች ከውኃው አቅርቦት የሚገኘውን ጥቅም አጣጥመው ሲሄዱ ትልቅ የኢኮኖሚ ለውጥ ስለሚኖር የምንሰጣቸውን ገንዘብ ለመተካት ምንም አይቸግራቸውም፡፡ ከዚህ ቀደም ያጋጥመን የነበረው ችግር ብድር ስንሰጥ አመላለሱን ለማረጋገጥ የሚያስቸለን አሠራር አልነበረም፡፡ ይህ ተቋም እንደ ንግድ ባንኮች የሚታይ ቢሆንም የብድር ማስያዣ አይጠይቅም፡፡ ከዚህ ቀደም በእምነት ላይ ተመሥርቶ የሚሰጠው ብድር አሁን ግን በክልሎች ዋስትና እየተገባበት መሰጠት ተጀምሯል፡፡ ክልሎች ተጠያቂነት እንዳለባቸው አውቀው፣ ሕዝቦቻቸውን ውኃ የማጠጣት ኃላፊነት እንዳለባቸው አውቀው ክትትል እንዲያደርጉ የሚያግዝ ነው፡፡ ከተሞቹ የወሰዱትን ብድር መመለስ በሚያቅታቸው ወቅትም ክልሎች እንዲያግዟቸው ከበጀታቸው የመተካት አሠራር እንዲኖር ለማድረግ የሚረዳ አሠራር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ክልሎች ለከተሞች ዋስትና መግባታቸው ብድር እንዲመለስ የሚረዳ ነው ከተባለ ዋስትናው እንዴት ያለ ነው?
አቶ ዋና፡-ክልሎች የሚገቡት ዋስትና የሰነድ ዋስትና ነው፡፡ የሰነድ ግዴታ ነው፡፡ ብድሩ እንዲመለስ የሚያስችል ትኩረት እንዲሰጡ፣ እንዲከታተሉ ለማድረግ በማሰብ እንጂ የማቴሪያል ወይም የገንዘብ ዋስትና አይደለም የሚጠየቁት፡፡ ቢያንስ በሥነ ልቦና ደረጃ ይህ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል ኃላፊነትን ለመጫር እንጂ እንደ ባንኮች የብድር አከፋፈል በሚዛነፍበት ጊዜ ማስያዣ የተደረገውን ንብረት ወደ ገንዘብ የመለወጥ አሠራር የለንም፡፡
ሪፖርተር፡- እንግዲህ የውኃ አቅርቦት ሥራዎች በምትሰጡት ብድር የሚከናወኑ ከሆኑ የታሪፍ ለውጥም ይኖራል ማለት ነው፡፡ ይህ አንዴት ነው የሚስተናገደው?
አቶ ዋና፡-ውኃ እንዲሁ በተፈጥሮ የሚገኝ በመሆኑ ሊከፈልበት አይገባም፤ ማኅበራዊ የወል ሀብት ነው የሚል አስተሳሰብ የሚያራምዱ አሉ፡፡ ውኃ የተፈጥሮ ፀጋ መሆኑ ትክክል ነው፡፡ ማልማቱ ግን ውድ ነው፡፡ የልማት ወጪው ከፍተኛ ነው፡፡ ውኃውን በተሻለ አገልግሎት ሰዎች በሚፈልጉት ልክ ለማቅረብ የተሻለ መክፈል ይኖርብናል፡፡ የተሻሻለ አገልግሎት የሚሰጥ መዋቅር መኖር አለበት፡፡ ችግር ሲፈጠር ወዲያኑ መፍታት የሚችል መዋቅር ካለ፣ አመልክተህ ወዲያው ምላሽ የምታገኝበት አሠራር መኖሩ ግድ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ የተሻለ አገልግሎት ሲኖር የተሻለ ክፍያ መኖሩ ግድ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ግን ታሪፍ መከለስ ይኖርብናል፡፡ በአብዛኛው በየሁለት ዓመቱ ታሪፍ መከለስ አለበት ይባላል፡፡ የዕቃ ዋጋ ይጨምራል፡፡ የሰው ኃይል፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ መሠረተ ልማት መስፋፋት ሲኖር ይህንን ሁሉ የሚመጥን የውኃ መስመሮች ዝርጋታ መስፋፋት ሲኖር ተጨማሪ ወጪ ስለሚመጣ ተጨማሪ መክፈል ይጠበቃል፡፡ ለውኃ የሚከፈል ወጪ ለሕይወት የሚከፈል በመሆኑ ዋጋ ያንሰዋል የሚል አመለካከት አለ፡፡ በሕዝቡም ዘንድ ይህ አስተሳሰብ አለ፡፡ ጭማሪ መኖሩ መደበኛ እንጂ እንደ ችግር የሚታይ አይደለም፡፡ የተሻለ አገልግሎት ሳይሰጥ ታሪፍ ብትጨምር ግን ትክክል አይሆንም፡፡ ይህ የመልካም አስተዳደር ጥያቄን ያመጣል፡፡ የውኃ ታሪፍ ለመጨመር የተሻለ አገልግሎት መስጠት የግድ ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- በብድር አመላለስ ወቅት የማፈግፈግ ችግር አያጋጥማችሁም? ብድር ስትሰጡ አንደኛው መመዘኛችሁ አዋጭ ፕሮጀክት መሆኑን ማጣራት ነው፡፡ ይህንን ስታደርጉ በሌላ በኩል ይዛችሁ የተነሳችሁት ዓላማ ንፁህ የመጠጥ ውኃን ለሁሉም ማዳረስ የሚል በመሆኑ እንዴት ነው እነዚህን የምታስማሙት?
አቶ ዋና፡-የማፈግፈግ ሁኔታ የምርጫ ጉዳይ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ከተሞች በራሳቸው በቂ አቅም ኖሯቸው እነዚህን ሥራዎች መሥራት ከቻሉ እሰየው ነው፡፡ በከተሞች የሚዘረጉ መዋቅሮችን መዘርጋት ቀርቶ የተበላሹ መስመሮችን መጠገን ፈተና እየሆነባቸው ፈስሶ የሚባክነው ውኃ ብዙ እኮ ነው፡፡ ከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ዕውቅና የሰጣቸው 1,000 ያህል ከተሞች አሉ፡፡ በተለያየ የከተማ ደረጃ የሚመደቡ ናቸው፡፡ በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲም የተለዩ ከ900 በላይ ከተሞች አሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ከሁለት ወይም ሦስት ዓመት በፊት የነበረ መረጃ ነው፡፡ ከተሞች በተለያየ ብቃትና ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው፣ ብቃትና አቅሙ የሌላቸው ከተሞች ከውኃ አቅርቦት ችግራቸው እንዲወጡ የሚያስላቸውን የፋይናንስ ድጋፍ እናቀርባለን፡፡ ነገር ግን ከውኃ ችግራቸው ከወጡ በኋላ ከሌሎች ችግሮቻቸው የመውጣት ዕድላቸው ሰፊ ይሆናል፡፡ የውኃ አቅርቦት ንግድ እንዲስፋፋ ይረዳል፡፡ አገልግሎቶች እንዲበራከቱ ፋብሪካዎች እንዲበዙ ይረዳል፡፡ ከሻይ ቤት ጀምሮ ትልልቅ የንግድ እንቅስቃሴዎች እንዲፈጠሩ ያግዛል፡፡ እዚህ የተስፋፋ እንቅስቃሴ የተፈጠረላቸው ከተሞች የተሻለ ገቢ ማግኘታቸው ስለማይቀር፣ ከዚህ ገቢያቸው ላይ ብድር መክፈል ብዙም ከባድ አይሆንም፡፡ ለመበደር ፕሮጀክት አጥንተው የማይጠይቁ ከተሞችን ተበደሩ ብለን አናስገድድም፡፡ ፕሮጀክት አጥንተው፣ የከተማውን ሁኔታና የውኃ ምንጭ መገኛ መኖሩ፣ ዋጋውስ ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል? ከየትኛው የገንዘብ ምንጭ ብድሩ መከፈል ይችላል? ታሪፍስ መቼ ነው የሚከለሰው? በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ምን ያህል ደንበኞች ይኖራሉ? ምን ያህል የውኃ ቆጣሪዎች ይኖራሉ? ምን ያህል የጋራ የቦኖ ውኃ አቅርቦቶች ይኖራሉ? የሚሉት ሁሉ በፕሮጀክት ጥናት ሰነድ ውስጥ ከቢዝነስ ፕላን ጋር አብሮ ተካቶ ለብድር ጥያቄው ይቀርባል፡፡ በዚህ መሠረት ፈቃደኛ ሆነው ገንዘቡን ለመመለስ የሚችሉበት አስተማማኝ ምንጭ እንዳላቸው፣ የሚያቀርቡት ውኃም በጥራቱና ለሰው ልጅ ጤና አስተማማኝ መሆኑ የመሳሰሉትን የሚያካትት ትልቅ የጥናት ሰነድ አካተው ሲያቀርቡና የብድር ማመልከቻ ሲያስገቡ እኛም ጥያቄውን መመልከት እንጀምራለን፡፡ አንዱ ከተማ ውኃ አግኝቶ ሌላውም እንዲደርሰው ለማድረግ በማሰብ ነው በብድር የሚሠራው፡፡ ለልማት ሲባል ችለን የምናልፋቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ የማይመለስ የተበላሸ ብድር ይኖራል፡፡ ለምሳሌ መንግሥት ለልማት ሲል ከ70 እስከ 80 በመቶ ብድር በማቅረብ ቀሪዋን እንዲያወጡ በማድረግ ባለሀብቶችን ወደ ልማት ያስገባል፡፡ ይሁንና አደጋዎች አሉበት፡፡ ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ እንደማይታደረው ሁሉ አደጋውን ለመቀነስ ስልት ታበጃለህ እንጂ ብድር ላይመለስ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ፡፡ ወደፊት ሥራው እየተስፋፋ ሲመጣም አደጋውም ሊጨምር ይችላል፡፡ ይሁንና የሕግ ማሻሻያ እንዲደረግልን ለመጠየቅ አስበናል፡፡ የምንሰጠው ብድር አነስተኛና ተዘዋዋሪ ነው፡፡ ለሁሉም ለማዳረስ እንዲቻል፣ ላልደረሳቸው እንዲደርስ ለማድረግ ግን ተጠቃሚዎች ማገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በራሳቸው ብቃት ማነስና ድክመት ገንዘቡን አጥፍተው ቁጭ የሚሉ ከሆነም ከክልሉ በጀት ተቀንሶ ለውኃ ልማት ፈንድ እንዲውል ለማድረግ የሚያስችል የሕግ አሠራር እንዲኖር ለማድረግ አስበናል፡፡ ይህ ሲሆን ለሁሉም ክልሎች እያዳረስን እንድንሄድ ሊረዳን ይችላል፡፡ ፍላጎት በጣም እየጨመረ ነው፡፡ ለ20 ዓመታት ታስቦ የተሠራው ሳይታሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያልቅና ተጨማሪ መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማሟላት ፈንድ መኖር አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የከፍተኛ ብድር ዕዳ ጫና ካለባቸው አገሮች ተርታ ወጥታለች፡፡ ይህ በመሆኑም በአብዛኛው የብድር ምንጫችን ኮሜሪሺያል አበዳሪዎች እየሆኑ ነው፡፡ ከወለድ፣ ከዕፎይታና ብድር ከመመለሻ ጊዜ አኳያ ይህ ለእኛ ከባድ ስለሚሆን መበደር አንችልም፡፡ በአገር ውስጥ የራሳችን ገንዘብ ካለን ግን የውስጥ ችግሮቻችንን የምንፈታበት አቅም ይኖረናል፡፡ ዛሬ የምንሰጣት ጥቂት ፈንድ የምትጠፋ ከሆነ፣ የዕርዳታ አመለካከት ካለ እንደ ውድ ነገር መቁጠር እንደሚበላሽና ጉዳት እንደሚያደርስ ነገር መቁጠር ስለማይኖር ተመላሽ በሚደረግ ገንዘብ እንዲሠሩ ማደረጉ ጥቅም አለው፡፡ የእኔነት ስሜትም ያሳድራል፡፡ የምከፍልበት ነው፣ የራሴ ንብረት ነው የሚል አመለካከት ሲኖረው በአግባቡ የመጠቀም ልማድ ይመጣል፡፡
ሪፖርተር፡- የግንባታ ወጪ እየናረ መጥቷል፡፡ አንድ ጉድጓድ ለመቆፈር የሚጠየቀው ወጪ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የሚሰጠው ብድርና የሚሠራው ሥራ እንዴት ይገመገማሉ?
አቶ ዋና፡-የእኛ ቡድን ፕሮጀክቶቹ በሚሠራበት ቦታ ሄዶ ክትትል ያደርጋል፡፡ ያረጋግጣል፡፡ በፕሮጀክት ሰነዱ ላይ ያቀረቡት ምንጭ እውነትም አለ ወይ? የሚለውን እናያለን፡፡ አንዳንዱ የውኃ መሠረተ ልማት ከተሠራለት በኋላ አልከፍልም እንዳይል የሚያስገድደው በየጊዜው የሚጨምር የተጠቃሚው ሕዝብ ፍላጎት አለ ወይ? የሚለውን እናያለን፡፡ አንዳንዱ የምንጭ ውኃ ስላለው እኛ ፕሮጀክቱን ከሠራንለት በኋላ ብድር ላለመክፈል እንዳያንገራግር ክትትል እንደርጋለን፡፡ የተለያዩ መለኪያዎችና መጠይቆች ተሠርተው ነው ብድሩ የሚለቀቀው፡፡ የተሠራው ሥራና ወጪው መመጣጠናቸው ይታያል፡፡ ፕሮጀክቱ መክፈል የሚችልባቸው መለኪያዎችን የሚሠሩ ቀመሮች አሉን፡፡ ቀመሩ በሚሰጡት መለኪያዎች አማካይነት እስከምን ያህል መጠን ድረስ ተበዳሪው መሸከም እንደሚችል ያመላክታሉ፡፡ መሸከም ከሚችለው በላይ የሆነበትን የፕሮጀክት ወጪ ጥያቄ እኛ በብድር በማቅረብ ፕሮጀክቱን እናግዛለን፡፡ እኛ የምናቀርበው አስተማማኝ የሆነው መጠን ላይ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ወጪ ምን ያህል እንደሚሆን ከዚህ ወጪ ውስጥ እኛ በብድር ማቅረብ የምንችለው መጠን ምን ያህል እንደሆነ፣ የተቀረውን አዋጥተው እንዲሸፍኑ ይደረጋል፡፡ መመለስ የማይቻለውን የወጪ ክፍል ተበዳሪ ከተሞች እንዲሸፍኑ በማድረግ ለሁለት አጋጭተን ለሕዝቡ ንፁህ ውኃ እንዲቀርብ ለማድረግ እንሞከራለን፡፡ ይሁንና የዋጋ ውድነት ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ነው፡፡ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች በተለይ ከዓለም አቀፍ ገበያ ተገዝተው የሚመጡ በመሆናቸው ዋጋቸው ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ነው፡፡ ወደፊት በአገር ውስጥ ምርቶች የመጠቀም አዝማሚያም አለን፡፡
ሪፖርተር፡- 1,000 ያህል ከተሞች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለ15 ከተሞች የተመደበ ፕሮጀክት ነበር፡፡ ይሁንና በውኃ ልማት ፈንድ በኩል ለስምንት ከተሞች የሚውል ብድር ከውጭ አበዳሪዎች የተገኘ ገንዘብ በቅርቡ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ ይሁንና የታሰበውን ያህል ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ይህ የሆነበትን ምክንያት ቢያብራሩልን?
አቶ ዋና፡-ለ15ቱ ከተሞች የሚለው የቀድሞው ስምምነት በውኃ ልማት ፈንድ የተፈጸመ አልነበረም፡፡ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክና ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘ ገንዘብ ከአሥር ዓመት በፊት ከመንግሥት ጋር የተደረሰውን ስምምነት መሠረት በማድረግ ነበር 15ቱ ከተሞች የተመረጡት፡፡ በወቅቱ ግን በብድር አቅራቢያዎች በኩል በነበረ ግፊት ይመስለኛል አንድ ዓለም አቀፍ ተቋራጭ የ15ቱንም ከተሞች የውኃ መስመሮች እንዲዘረጋ የሚል አሠራር ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይሁንና ወደ ሥራው ሒደት ሲገባ 15ቱ ከተሞች በአራት ክልሎች የሚገኙ ትልልቅ ከተሞችን የሚያካትት በመሆኑ፣ በወቅቱ በሚፈለገው ሒደትና ፍጥነት ሊሄድ አልቻለም ነበር፡፡ ከብዙ ጉትጎታም በኋላ ከአውሮፓው ተቋራጭ ጋር ሥራውን መቀጠል እንዳልተቻለ የኢትዮጵያ መንግሥት በመገንዘቡ ስምምነቱን አቋርጦታል፡፡ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትም ደርሶ ክርክር ተደርጎበት ነበር፡፡ በመጨረሻው ለኢትዮጵያ መንግሥት ተፈርዶ አሁን ነገሮች መልክ የያዙበት መንገድ ተፈጥሯል፡፡ በወቅቱ በተገባው ስምምነት መሠረት ሊሠራ ባለመቻሉ ግንባታዎች ተቋርጠው ቆይተዋል፡፡ በአገር ውስጥ ተቋራጮች አማካይነት ሥራዎች ተከፋፈለው ሥራው ተሰጥቶ ነበር፡፡ ከ15ቱ ከተሞች ፕሮግራም ውስጥ ውኃ የማምረትና ዋና ዋናዎቹን መስመሮች የመዘርጋት ሥራ እንጂ ወደ ተጠቃሚው የማዳረስ ሥራ የፕሮጀክቱ አካል አልነበረም፡፡ በቅርቡ በተደረገው ስምምነት መሠረት የተመረተው ውኃ ለተጠቃሚው የሚደርስበትን የመጨረሻውን ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ሥራ የሚሠራበት ወቅት ነው፡፡ ከመነሻው በገንዘብ ዕጥረት ምክንያት ከመጀመርያው ፕሮጀክት ተቀንሶ የነበረውን ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ ከፈረንሣይና ከጣልያን መንግሥታት ጋር ባደረግነው ስምምነት መሠረት ለመጨረሻው ተጠቃሚ የሚውል ውኃ ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ቀድሞ ከስምንት ከተሞች ጋር ተፈራርመናል፡፡ ከ15ቱ ከተሞች ውስጥ ሰባቱ በአማራ ክልል፣ አራቱ በኦሮሚያ ክልል፣ ሁለቱ በደቡብ እንዲሁም ሌሎች ሁለት በትግራይ ክልል የሚገኙ ከተሞች ነበሩ፡፡ የቀድሞው ፕሮጀክት መስተጓጎል ባስከተለው መጓተት ምክንያት አማራ ክልል በራሱ ፋይናንስ ሥራዎችን ዳር አድርሷል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ በሦስቱ ክልሎች የሚገኙት ስምንቱ ከተሞች ውስጥ ግን ፕሮጀክቶቹ ስላልተጠናቀቁ ፋይናንስ አፈላልገን ሥራውን ዳር ለማድረስ መንቀሳቀስ ጀምረናል፡፡
ሪፖርተር፡- ለውኃ ፕሮጀክቶች የሚውለው ብድር ከሦስት የውጭ አበዳሪዎች መገኘቱ ይታወቃል፡፡ የተገኘው የ75 ሚሊዮን ዩሮ ገንዘብ በምን መልኩ ነው ለከተሞቹ የሚከፋፈለው?
አቶ ዋና፡-የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ 40 ሚሊዮን ዩሮ አበድሮናል፡፡ የፈረንሣይ መንግሥት 20 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ እንዲሁም የጣልያን መንግሥት 15 ሚሊዮን ዩሮ አበድረዋል፡፡ ይህ ገንዘብ አሁን ባለው ምንዛሪ ወደ 1.8 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚገመት ነው፡፡ ብድሩ በአንድ ቋት የሚተዳደር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 189 ሚሊዮን ብር ነው ለስምንቱ ከተሞች የሚሰጠው፡፡ ከተሞቹ የራሳቸውን መዋጮ ያክሉበታል፡፡ እኛ የምንሰጣቸው ገንዘብ እንዲሁም እነሱ የሚዋጡት ገንዘብ ተዳምሮ ጠቅላላ የፕሮጀክቱ ወጪ 335 ሚሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ በብድር የሚተላለፈው ግን 189 ሚሊዮን ብሩ ነው ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቀደመው የ15 ከተሞች ፕሮጀክት ተመድቦ የነበረው የገንዘብ መጠን ምን ያህል ነበር?
አቶ ዋና፡-በእርግጥ እኔ የምመራው ተቋም አልሠራውም፡፡ ሆኖም ገንዘቡ ምን ያህል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለአብነት ለስምንቱ ከተሞች ተመድቦ የነበረውን የገንዘብ መጠን መጥቀስ ካስፈለገ 1.2 ቢሊዮን ብር አካባቢ ነበር፡፡ ይህ የመጀመርያው ብድር ሲሆን፣ በዚሁ ፕሮጀክት ወቅት አብዛኞቹ የግንባታ ሥራዎች ተጠናቀዋል፡፡ አሁን የምንሠራው የቀደመውን ፕሮጀክት ወደ መጨረሻው ምዕራፍ የማድረስ ሥራ ነው፡፡ የአሁኑ ወጪያቸው ጠቅላላ ወጪ 335 ሚሊዮን ብር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የብድር መጠይቆችን የማያሟሉ ከተሞች ከተጠቃሚነት ውጭ ይደረጋሉ ማለት ነው?
አቶ ዋና፡-የብድር መስፈርቶችን የማያሟሉ ካሉ ለብድር አሰጣጡ ብቁ ስለማይሆኑ እንዲቀሩ ይደረጋሉ፡፡ ይሁንና ግን ከታች ጀምሮ እንዲያሟሉ ድጋፍ አድርገን ስለምናመጣ የሚያልፉ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ እናደርጋለን፡፡ ዋናው ዓላማ ሕዝቡ ውኃ በአግባቡ እንዲያገኝ፣ ሥራውም የማይስተጓጎልበትን ምቹ መንገድ መፍጠር ነው፡፡ ተቋማችን የልማት ዓላማ ያለው በመሆኑም የሚሰጠው ብድር ተግባር ላይ ውሎ ጥቅም እንዲሰጥ የማድረግ እንጂ፣ ለሚሰጠው ብድር የሚያስከፍለው ወለድና የእፎይታ ጊዜ እንዲሁም የማስከፊያ ጊዜ ሲታይ ብድሩ በተበዳሪ ከተሞች ላይ ጫና የሚፈጥር አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ተቋሙ በብድር የሚያገኛቸውን ገንዘቦች በምን መልኩ ነው የሚያመጣው? መንግሥት ዋስትና ገብቶለት ነው ወይስ በመንግሥት በኩል ነው የሚያገኘው?
አቶ ዋና፡-ከውጭ ምንጮች የመበደር ሥልጣኑ በጠቅላላ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ነው፡፡ ሚኒስቴሩ ከተበደረ በኋላ ለእኛ ማስተላለፍ የሚችልበት የስምምነት አሠራር ስላለ በዚያ መሠረት ነው የብድር ገንዘቡ የሚደርሰን፡፡ ተቋሙ መጀመርያ በአዋጅ የተቋቋመ ሲሆን፣ የመነሻ ገንዘብ ተሰጥቶት በሒደት ግን ከሚያገኛቸው ብድሮችና ዕርዳታዎች እያጠረቃቀመ እንዲጠቀም በሚል እሳቤ ነው የተመሠረተው፡፡
ሪፖርተር፡- በተባለው ሒደት መሠረት የማይፈጸሙ ፕሮጀክቶችን እንዴት ነው የምትከታተሉት?
አቶ ዋና፡- የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ሒደት በተለያዩ አካላት ነው የሚታየው፡፡ የእኛ ሥራ ፋይናንሱን ማቅረብ ነው፡፡ እርግጥ የፕሮጀክት አተገባበር ላይ የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ አንደኛው የኮንትራት አስተዳደር ብቃታችን እንደ አገር ገና ነው፡፡ ሁለተኛ ጥናቶች ሲሠሩ ከመጀመርያውም በጥልቅ እስከሚፈለገው ደረጃ ድረስ ያለመሄድ ችግርም አለ፡፡ ጥናት የሚሠሩ አማካሪዎች የተሟላና ተፈጻሚነት ያለው ሰነድ የማቅረብ አቅምና ችሎታ ገና አልዳበረም፡፡ ወደ ፕሮጀክት ትግበራ ከተገባ በኋላ ብቅ እያሉ የሚያስቸግሩ ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ የኮንትራት ሰነዶችን ካዘጋጀን በኋላ ለማስተዳደርም በአገር ደረጃ ትልቅ ችግር አለበት፡፡ አሁን ግን እየተሻሻለ ይገኛል፡፡ የፕሮጀክት ባለቤቶችም ወጥረው ይዘው በመከታተል ውጤታማ እንዲሆኑ የማድረግ እንቅስቃሴ ላይም ደካማ ሆነው ይታያሉ፡፡ በአጠቃላይ ሲደመር የማስፈጸም አቅም ድርሻ አለው፡፡ በተቀመጡ ሕጎች መሠረት መሥራት፣ ፋይናንስ አቅራቢዎችም የየራሳቸው መጠይቆች ስላሏቸው እንዲህ ያሉትና ሌሎችም ጉዳዮች ፕሮጀክቶችን ሊያጓትቱ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡
