- ኢትዮጵያ ለ5.6 ሚሊዮን ሰዎች ዕርዳታ የሚሰጠኝ አላገኘሁም ብላለች
በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኬንያ፣ በኢትዮጵያ እንዲሁም በየመን የተንሰራፋው ችግር ወደ ችጋርና ረሀብ በመሻገር የሰውና የእንስሳት ነፍስን እያጠፋ ይገኛል፡፡ የየመን ጉዳይ በጦርነት ሳቢያ የተቀሰቀሰ የሰብዓዊ ቀውስ ሲሆን፣ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የተከሰተው የምግብ ዕጥረት እየተባባሰ በመምጣት ወደ ረሀብነት መሸጋገር የጀመረው ግን በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለአስቸኳይ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ፈላጊ ለመሆን ተገደዋል፡፡
ሶማሊያ በረሀብ ቸነፈር መመታቷን ባወጀች ማግሥት በሁለት ቀናት ውስጥ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች አልቀዋል፡፡ አሁንም በርካቶች ሰዎች ሕይወታቸውን እያጡ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በሕፃናትና በሴቶች ላይ ስቃዩ በርትቶ በሚታየው ድርቅ፣ ደቡብ ሱዳናውያንም ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡ በእርስ በርስ ጦርነት በርካቶች በሚማገዱባት ጨቅላዋ አገር፣ ረሀብ የሚፈጃቸው ሰዎች ከቀን ወደ ቀን በመጨመር ላይ ይገኛል፡፡
በተመድ ትርጓሜ መሠረት ሕዝቦች በአንድ አገር ውስጥ የረሀብ ቸነፈር የሚታወጀው ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆናቸው ሕፃናት ውስጥ 30 በመቶው ለከፋ የምግብ ዕጥረት (ለተመጣጠነ) ሲዳረጉ፣ ከአሥር ሺሕ ሰዎች መካከል በየቀኑ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች የሚበሉት በማጣት ለሞት የሚዳረጉ ከሆነና ሌሎችም መሠረታዊ መመዘኛዎች ከተሟላ በአንድ አገር ውስጥ ረሀብ ወይም ችጋር ተከስቷል ብሎ ለማወጅ የሚያበቁ ምክንያቶች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
በኬንያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለአስከፊው የድርቅ አደጋ መዳረጋቸውን ብቻም ሳይሆን፣ ወደ ረሀብ አፋፍ እየተንደረደሩ እንደሚገኙ በመገንዘብ የአስቸኳይ ጊዜ እንዲያውጅ መንግሥቱን ግድ ብሎታል፡፡ ናይጄሪያም በድርቅ ከተመቱ አገሮች ተርታ ለመሰለፍ መገደዷን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ይሁንና እስካሁን በአኅጉሪቱ ከታየው የድርቅ ክስተት በቁጥር ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የዘንድሮው ድርቅና ያስከተለው ረሀብ ከሌላው ጊዜ ይልቅ የብዙዎችን ትኩረት ያጣ፣ ጉዳት እየደረሰባቸው ለሚገኙ ወገኖች የሚሰጠው ድጋፍም እንደሌላው ጊዜ ቸል የተባለ ሆኗል፡፡ በርካታ አገሮችም እንደቀድሟቸው ለዕርዳታ የሚሰጡት ምላሽ ተቀዛቅዞ በመታየቱ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ሥጋቱን በማስተጋባት የጉዳቱን መጠን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊው ስቴፈን ኦብራየን በቅርቡ ይፋ እንዳደረጉት በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በየመንና በናይጄሪያ የተከሰተውን ረሀብና ቸነፈር እስከመጪው ሐምሌ ብቻ ለመቋቋም በጥቂቱ 4.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ በመግለጽ አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡
ኦብራየን በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ወቅት ተገኝተው ለዓለም ይፋ እንዳደረጉት፣ ዓለም አይታ የማታውቀው የሰብዓዊ ቀውስ ተጋርጦባታል፡፡ በእነዚህ ጥቂት አገሮች ውስጥ ለአደጋ የተዳረጉት ሕዝቦች ተመድ ከተመሠረተ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን በማጉላት አስከፊውን አደጋ ለማሳየትና ሳይረፍድ መነሳት እንደሚገባ ለማስጠንቀቅ ሞክረዋል፡፡ ‹‹ዓለም ተባብሮ ካልተረባረበ በቀር በርካቶች በረሀብ ጦስ ያልቃሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሰዎችም ለበሽታ ስቃይና ለሞት ይዳረጋሉ፤›› በማለት ለፀጥታው ምክር ቤት ስለአስለፊው አደጋ አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዓምና ለዕለት ደራሽ ዕርዳታ ከተዳረጉት 10.2 ሚሊዮን ሰዎች መካከል ዘንድሮም በዕርዳታ ለመኖር የተገደዱ በርካቶች ናቸው፡፡ በአገሪቱ የዝናብ ዕጥረት ያስከተለው ድርቅ ዘንድሮም ከ5.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሚገኙበት የበልግ አብቃይ የአርብቶ አደር አካባቢዎችን ለድርቅ አደጋ አጋልጧል፡፡
ሐሙስ መጋቢት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመንግሥታቸውን የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይህንኑ ገልጸዋል፡፡ በዝናብ ዕጥረት ምክንያት በአገሪቱ የደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ 5.6 ሚሊዮን ሰዎች ለዕለት ደራሽ ምግብ ዕርዳታ ከመዳረጋቸውም ባሻገር፣ እነዚህን ሰዎች ለመታግ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከ948 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነም ለፓርላማው አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጠቀሱት ገንዘብ ውስጥ 600 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ለምግብ አቅርቦት የሚለው ሲሆን፣ ቀሪው 350 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ምግብ ነክ ላልሆኑ አቅርቦቶች ማሟያ ይውላል፡፡
በብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ የሎጂስቲክስና አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ ኢድሪስ ሐሰን ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳብራሩት፣ 948 ሚሊዮን ዶላሩ ለ920 ሜትሪክ ቶን የምግብ እህሎች ግዥ ይውላል፡፡ ከዚህ ውስጥ 745 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ፣ 74,400 ሜትሪክ ቶን ጥራጥሬ፣ 22,320 ሜትሪክ ቶን የምግብ ዘይት እንዲሁም 78,150 ሜትሪክ ቶን አልሚ ምግቦች ተገዝተው ለድርቅ ተጎጂዎች መቅረብ አለባቸው ያሉት አቶ ኢድሪስ፣ ይህም ሆኖ መንግሥት ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ያቀረበው የዕርዳታ ድጋፍ ጥሪ ያገኘው ምላሽ ቀዝቃዛ ሆኗል ብለዋል፡፡ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም እንዲሁም በጣት ከሚቆጠሩ ሌሎች ተራድዖ ድርጅቶች በቀር ለአገሪቱ ተጎጂዎች የዕርዳታ እጃቸውን የዘረጉ አገሮች አልተገኙም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት፣ የዓለም ትኩረት በመካከለኛው ምሥራቅ፣ ወደ ምዕራብ አፍሪካ እንዲሁም ወደ ጎረቤት አገሮች ያነጣጠረ በመሆኑ የኢትዮጵያ ጥሪ ችላ መባሉን ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ የመን፣ ደቡብ ሱዳን ያሉ የጦርነት አውድማ የሚንጣቸው አገሮች የዓለም አትኩሮት በመሳባቸው ዓለም ወደ እነዚህ አገሮች ፊቱን በማዞሩ የሚፈለገውን ድጋፍ ማግኘት እንዳልተቻለ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ አቶ ኢድሪስ ከሰጡት ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በመሆኑም የፌደራል መንግሥት አንድ ቢሊዮን ዶላር በመመደብ በድርቅ የተጎዱ ሰዎችንና እንስሳትን ለመታደግ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም አቶ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡
አምናም ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዓለም አቀፍ ለጋሾች የተገኘው ዕርዳታ የሚፈለገውን ያህል እንዳልነበር መንግሥት ደጋግሞ አስታውቋል፡፡ ድርቁ ባስከተለው ጫና ምክንያት የግብርና ዘርፉ ዕድገት አሽቆልቁሎ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ከስምንት በመቶ በላይ እንደሚያድግ ሲጠበቅ የነበረው የግብርናው ኢኮኖሚ ወደ ሁለት በመቶ ዝቅ ብሎ እንደነበር በሪፖርታቸው አውስተዋል፡፡ ይህ በመሆኑም በጠቅላላ ኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ያስከተለውን ተፅዕኖም ጠቅሰዋል፡፡ የድርቁ ተፅዕኖ ግን ይህን ያህል አሳሳቢ አይደለም የሚል መግለጫ በተለያዩ የመንግሥት ሹማምንት ሲሰጥ እንደነበር የሚታወስ ቢሆንም፣ የአገሪቱ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) በ11 ከመቶ ያድጋል ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ስምንት በመቶ ዝቅ እንዲል ማስገደዱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምነዋል፡፡
እንደ ኦብራየን ማብራሪያ፣ በየመን ጦርነት ሳቢያ ለዕለት ደራሽ የምግብ ዕርዳታ ከተዳረጉ 18.8 ሚሊዮኖች ውስጥ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ለረሀብ አለንጋ ተዳርገዋል፡፡ በየመን ጦርነት መባባስ እጃቸውን እንዳለበት የሚነገርላቸው እነ ሳዑዲ ዓረቢያና ሌሎች አገሮች ለሰብዓዊ ቀውሱ መባባስ ጣት ቢቀሰርባቸውም፣ የየመን ሕፃናት ግን በረሀብ ከመርገፍ የሚታዳጋቸውን ድጋፍ ለማግኘት ይጠባበቃሉ፡፡ ይሁንና 12 ሚሊዮን የመናውያንን ከረሀብ እልቂት ለመታደግ በትንሹ 2.1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ኦብራየን ጠቅሰዋል፡፡
በደቡብ ሱዳንም 7.5 ሚሊዮን ሕዝቦቿ ለዕርዳታ የተዳረጉባት ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት በ1.4 ሚሊዮን የተረጂዎች ቁጥር የጨመረባት፣ ከ3.4 ሚሊዮን በላይ ከቀዬያቸው የተፈላቀሉባት ደቡብ ሱዳን፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕፃናቶቿ ለአስከፊ የምግብ ዕጥረት ተዳርገውባታል፡፡
ሶማሊያ የ6.2 ሚሊዮን ተረጂዎች ብዛትን ከማስመዝገቧም በላይ 2.9 ሚሊዮን የረሀብ ተጎጂዎችን ከሞት ለመታደግ ድረሱልኝ በማለት ላይ ትገኛለች፡፡ በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ የተከተሰው ረሀብም በዓለም አራተኛዋን ነዳጅ አምራች አገር ከተረጂዎች ተርታ አሰልፏታል፡፡ በጽንፈኛው አሸባሪ ቦኮ ሃራም አበሳዋን የምታየው ናይጄሪያ፣ ከተገደሉባት 200 ሺሕዎችና ከተሰደዱባት 2.6 ሚሊዮን ዜጎቿ ባሻገር ሚሊዮኖቿ ለረሀብ አደጋ ተጋልጠውባታል፡፡
እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ተመድ ከተመሠረተ ወዲህ ታይቶ አይታወቅም ያሉት ኦብራየን፣ የምሥራቅ አፍሪካ ሕዝቦች በተለይ የድርቅና የረሀብ አለንጋ እየሸነቆጣቸው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳ አደጋው የቱንም ያህል አስከፊ ቢሆን ለዕርዳታ ሥራ ዝግጁ ነን በማለት ለዓለም ልዕለ ኃያላን አገሮች የገለጹት የተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ፣ የነፍስ አድን ጥሪያቸው ግን ተገቢውን ምላሽ ያገኘ አይመስልም፡፡ እንደውም በተቃራኒው ምላሹ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑ የሚነገረው አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለተመድ የሚደረገው ድጋፍ ይቀነሳል በማለታቸው ጭምር ነው፡፡
አነጋጋሪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶላንድ ትራምፕ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤኣይዲ)ን ጨምሮ ሌሎችም በልማት ትብብር መስክ የሚንቀሳቀሱ የአሜሪካ መንግሥታዊ ተቋማት በጀት ይቀነሳል በማለታቸው፣ ከተመድ ኤጀንሲዎች አብዛኞቹ ሥጋት ውስጥ ወድቀዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ብቻውን የሁለት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ከአሜሪካ ያገኝ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ዕርዳታዎች ከምንጊዜውም ይልቅ ዘንድሮ በሚያስፈልጉበት ወቅት አሜሪካ እጇን ለመሰብሰብ ማሰቧ ቀውሶችን እንደሚያባብስ ሥጋታቸውን የገለጹት በአፍሪካ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ ካሊስ ማክዶናሁ ናቸው፡፡ በደቡብ ሱዳን በአሁኑ ወቅት ከአውሮፕላኖች የሚጣል የዕለት ደራሽ የምግብ ዕርዳታ እየተሰራጨ ይገኛል ያሉት ቃል አቀባዩ፣ በረሀብተኞችና በሞት መካከል ያለው ብቸኛው መድን ይኸው ዕርዳታ ነው በማለት ዕርዳታው ቢቋረጥ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት እንደሚዳረጉ አበክረው በመግለጽ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የያዙትን አቋም ተችተዋል፡፡
ዓለም በድርቅና በረሀብ ጦስ ለሚረግፉ ሚሊዮኖች እያሳየ የመጣው ቸልተኝነት እየተባባሰ መምጣቱን የሚያመላክቱን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ብቻም ሳይሆኑ አኅጉራዊ ተቋማትም ጭምር ናቸው፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት በምሥራቅ አፍሪካ በርካቶች ለረገፉበት የረሀብ አደጋና ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የተሰናዳው የዕርዳታ ጥሪ በአሁኑ ወቅት አይታይም፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያና ታንዛንያን ያካለለው ድርቅ ከ14 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የዳረገ እንደነበር ሲታወስ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ለሕልፈት ሕይወት መዳረጉም አይዘነጋም፡፡
የዘንድሮው ድርቅ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ሕልውና ለአደጋ አጋልጦ እየተሰጠው ያለው ትኩረት ግን ዝቅተኛ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሊከሰት የሚችለው ዕልቂት ከወዲሁ እየተስተጋባም ቢሆን፣ እንደ አፍሪካ ኅብረት ያሉት አኅጉራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይቀሩ ዝምታን መርጠዋል፡፡ 14 ሚሊዮኖች ለአስቸኳይ ዕርዳታ በተጋለጡበት ወቅት የአፍሪካ ኅብረት የዕርዳታ ማሰባሰቢያ ጉባዔ በመጥራት አንድ ቢሊዮን ዶላር ለተረጂዎቹ አገሮች አሰባስቦ ለማከፋፈል ሲንቀሳቀስ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁንና ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ያልበለጠ ገንዘብ ማሰባሰቡና የዕርዳታ ቴሌቶኑም ሳይሳካለት መቅረቱ አይዘነጋም፡፡ ዘንድሮ ካለፈው የተሻለ ለማገዝ የሚችልበትን እንቅስቃሴ ማድረግ ሲጠበቅበት፣ ኅብረቱ ዝምታን መምረጡ አስገርሟል፡፡
