የአገሪቱን ባንኮች በአባልነት ያቀፈው የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር፣ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውንም ሆነ ማኅበሩን በዕውቀታቸውና በጉልበታቸው በማገልገል አስተዋጽኦ ላበረከቱ የባንክ ፕሬዚዳንቶች ከኃላፊነታቸው በሚለቁበት ጊዜ ዕውቅና እንዲሰጣቸው ለማድረግ ወሰነ፡፡
ማኅበሩ ይኼንን ውሳኔ ያሳለፈው የማኀበሩን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም በገመገመበትና በልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመከረበት ስብሰባ ወቅት እንደሆነ የባንኮች ማኅበርና የደቡብ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ፣ ከዚህ ቀደም ለባንክ ባለሙያዎች ዕውቅና የመስጠት ልማድ ያልነበረ ቢሆንም አስፈላጊነቱ ስለታመነበት በየትኛውም መንገድ ከባንክ ፕሬዚዳንትነታቸው የሚለቁ ሰዎች ስላበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅና እንዲሰጣቸው ተወስኗል፡፡ ይህ የዕውቅና አሰጣጥም በቋሚነት እንደሚካሄድና እ.ኤ.አ. በ2016 ከፕሬዚዳንትነት ከለቀቁ ባለሙያዎች እንዲጀመር ገልጸዋል፡፡
በዚሁ ውሳኔ መሠረት ይመሩት የነበረውን ባንክ ወክለው በማኅበሩ ውስጥ ሲያገለግሉ ቆይተው በተለያዩ ምክንያቶች ከሥራ ለለቀቁ ሦስት የባንክ ፕሬዚዳንቶች ዕውቅና በመስጠት ቋሚ መርሐ ግብሩን ጀምሯል ተብሏል፡፡
በመሆኑም ሐሙስ፣ የካቲት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በተሰናዳው ፕሮግራም ወቅት የጀመሪያዎቹ ዕውቅና የተሰጣቸው የቀድሞ የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባሕረ፣ የቀድሞ የቡና ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ እሸቱ ፋንታዬና የቀድሞ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለኢየሱስ በቀለ ናቸው፡፡
ሦስቱም ፕሬዚዳንቶች በአዲሱ የማኅበሩ ውሳኔ መሠረት ላበረከቱት አስተዋጽኦ መግለጫ የምስክር ወረቀትና ለእያንዳንዳቸው የወርቅ የጣት ቀለበት ተበርክቶላቸዋል፡፡
የምስክር ወረቀቱንና የጣት ቀለበቱን በፕሮግራሙ ወቅት በመገኘት ያበረከቱላቸው ታዋቂው የባንክ ባለሙያ አቶ ለይኩን ብርሃኑ እንዲሁም በቅርቡ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሆነው የተሾሙት አቶ ጥሩነህ ሚጣፋ ናቸው፡፡
በዕለቱ በማኅበሩ ዕውቅና ከተሰጣቸው የቀድሞ የባንክ ፕሬዚዳንቶች ውስጥ አቶ ኢሳያስ ባሕረ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡ ያልተገኙበት ምክንያት ባይገለጽም ለክብራቸው የተዘጋጀው የምስክር ወረቀትና የጣት ቀለበት በማኅበሩ ጽሕፈት ቤት በኩል እንዲደርሳቸው ይደረጋል ተብሏል፡፡ አቶ ኃይለ ኢየሱስ፣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡
ማኅበሩ ለባንክ መሪዎች በቋሚነት መስጠት የጀመረውን ዕውቅና በተመለከተ ንግግር ያደረጉት አቶ ለይኩን፣ እንዲህ ያለው ተግባር የባንክ ባለሙያዎችን ያበረታታል ብለዋል፡፡ መለመድና መቀጠል ያለበት በጎ ተግባር መሆኑን በመግለጽ፣ በሌሎች ዘርፎችም እንዲህ ያለው ሥራ መለመድ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
