Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

የቆዳ ነጋዴዎች ማኅበር ዋጋ እያዛቡ ነው በማለት ፋብሪካዎችን ኮነነ

$
0
0

- መንግሥት በቆዳ ፋብሪካዎች ላይ ቁጥጥር እንዲያደርግ ጥሪ አቀረበ

በአገሪቱ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ገበያ ልቅ በመሆኑ ምክንያት ዘርፉን የሚመራ ሕግ ያስፈልጋል ያለው የኢትዮጵያ ጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ማኅበር፣ ቆዳ ፋብሪካዎች ይህንን ክፍተት በመጠቀም ዋጋ በማዛባት ገበያውን እየበጠበጡ እንደሚገኙ አስታወቀ፡፡

የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ አባተ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአገሪቱ ከ30 በላይ ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ቢኖሩም፣ ጥሬ ቆዳ የሚገበያዩበት መንገድ ልቅ በመሆኑ ለዋጋ መውደቅም ሆነ መናር ተጠያቂ ናቸው፡፡

ከአዲስ ዓመት ማግሥት ጀምሮ ባልተመለደ ሁኔታ የበግ ቆዳ ከ15 ብር ጀምሮ እስከ 30 ብር ሲሸጥ ታይቷል፡፡ እንዲህ በወረደ ዋጋ ሊሸጥ ከቻለባቸው ምክንያቶች መካከል የዓለም ዋጋ መውረድ እንደሆነ የቆዳ ፋብሪካዎችም ሆኑ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሲገልጽ መቆየቱን ይታወሳል፡፡ ይሁንና ቆዳ አቅራቢዎቹ ግን ይህ ሆን ተብሎ እየተፈጸመ የሚገኝ፣ ቆዳ ፋብሪካዎች መግዛት ሲፈልጉ አንዱ ከሌላው ዋጋ እየጨመሩና የገበያ ዋጋ እያዛቡ ሲሻሙ እንደሚታዩ የሚናገሩት አቶ ብርሃኑ፣ አልሆን ሲላቸው ደግሞ ጥሬ ቆዳ ነጋዴው በሕጋዊ መንገድ ከሕዝቡ በውድ ዋጋ ያጠራቀመውን ቆዳ ዋጋ አራክሰው አንገዛም እያሉ እንደሚገኙ በመግለጽ መንግሥት ተገቢውን የገበያ ሥርዓት እንዲያበጅለት ጠይቀዋል፡፡

ከ40 በላይ አባላትን በማሰባሰብ በሕጋዊ መንገድ ቆዳ አሳበስበው ለቆዳ ፋብሪካዎች ለማቅረብ የተቋቋመው ማኅበር፣ የበኩሉን እየጣረም ቢሆን ስምምነት የተደረሰባቸውን ነጥቦች ሳይቀር ፋብሪካዎች እየጣሱ ዋጋ በማዛባትና ገበያውን በማመሳቀል ነጋዴዎችን ለኪሳራ እየዳረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

እርስ በርሳቸው በሚሻሙበት ወቅት ሕጋዊ ያልሆኑ ሰብሳቢዎችንና ነጋዴዎችን በማሰማራት መንግሥት ለፋብሪካዎች እንዲቀርብላቸው የሠራውን ዋጋ በማጣረስ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ ፋብሪካዎች ለዋጋው መዘበራረቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በተለይ በአገር ውስጥና በውጭ ባለሀብቶች መካከል የሚታየው የጥሬ ቆዳ ሽሚያ ለዋጋው መውጣትና መውደቅ አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱን የጠቀሱት አቶ ብርሃኑ፣ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በቅርቡ ለሪፖርተር የሰጠው መግለጫ ማኅበሩን ቅር እንዳሰኘውም አልሸሸጉም፡፡

ፋብሪካዎች የሚረከቡበት ዋጋ እስከ 50 ብር እንዲደርስ መወሰኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ለገሠ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይሁንና ከዚህ ዋጋ በታች ገበያው ላይ ከ15 ብር ጀምሮ ሲሸጡ የነበሩ ሰዎች ማኅበሩ የማያውቃቸው፣ ሕገወጦች ከመሆናቸውም ባሻገር ከኅብረተሰቡ እንዲህ ባነሰ ዋጋ ገዝተው ለፋብሪካዎቹ እንዲያቀርቡ የሚያደርጉት ፋብሪካዎቹ እንደሆኑ በመግለጽ መንግሥት በአግባቡ እንዲያጣራው ማኅበሩ ጠይቋል፡፡

በተለይ ከመቶ ብር በላይ ሲሸጥ የሚታወሰው የበግ ቆዳ፣ በአሁኑ ወቅት በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች አምራቾች በብዛት እየታዩ ባሉበት ወቅት እንዲህ ታች የወረደበት ምክንያት ሆን ተብሎ ነው የሚሉት አቶ ብርሃኑ፣ የጥሬ ቆዳ ግብይትን የሚመራ ሕግ መንግሥት እንዲያወጣ አሳስበዋል፡፡ የዓለም ዋጋ ስለወረደ፣ የህንድ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ገበያ ስለተቀዛቀዘ ነው አለያም የቻይና ገበያ ስለተዳከመ ነው የሚሉ ምክንያቶች እንደማያዋጡ የሚገልጹት አቶ ብርሃኑ፣ በአገር ውስጥ ያለው ገበያና ዋጋው በመዛባቱ ምክንያት ከ20 ሺሕ እስከ 30 ሺሕ ጥሬ ቆዳ ገዝተው ለፋብሪካዎች ለማቅረብ ሲጠባበቁ የነበሩ ነጋዴዎች የሚገዛቸው በማጣት ለኪሳራ መዳረጋቸውንና ቆዳውም በመበላሸቱ ምክንያት ለመጣል መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ቆዳ እንዲህ ዋጋ እያጣ እንዲጣል የሚደረግ ከሆነ ወደፊት ከፍተኛ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ሥጋታቸውን በመግለጽም፣ በአሁኑ ወቅትም የበሬ ቆዳ ፈላጊ እያጣ ጥራቱም ችግር እየገጠመው እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ ዋጋው እጅግ በመውረዱ ሳቢያ ገበሬውም ሆነ ሌላው ተጠቃሚ አካል ለቆዳ የሚያደርገውን ጥንቃቄ እየተወ በመሆኑ ችግር እየተፈጠረ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው የበግ ቆዳም ባልተገባ ሁኔታ ዋጋው የሚበላሽ ከሆነ፣ ኅብረተሰቡ ጥቅም ለማያገኝበት ቆዳ ጥንቃቄ ማድረግ ትርጉም የለውም የሚል አዝማሚያ ሊፈጠር እንደሚችልም ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በቆዳ ነጋዴዎች ቅሬታ የቀረበባቸው ፋብሪካዎች ምላሽ እንዲሰጡበት ለማድረግ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበርን ለማነጋገር በተደጋጋሚ የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ይሁንና የጥሬ ቆዳ ዋጋ እየተሻሻለ መምጣቱ ቆዳ ነጋዴዎች የሚደግፉትን ያህል ፋብሪካዎቹ የማይቀበሉት መሆኑ እየታየ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ይመስላል መንግሥት ፋብሪካዎች የሚረከቡበትን ዋጋ በስምምነት እንዲወሰን ሁለቱንም ወገን ለማግባባት ሲጣጣር የከረመው፡፡

በአንፃሩ ነጋዴዎች በአቅርቦትና በፍላጎት ላይ መሠረት ያደረገ የዋጋ ትመና እንዲኖር፣ በተለይም ነጋዴውን ከሕዝቡ የሚገዛበት፣ ለቆዳ ጥራት ማስጠበቂያ በተለይ በጨው ለማልፋት የሚያወጣው ወጪ፣ የትራንስፖርት ወዘተ ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ማኅበሩ ይፈልጋል፡፡ መንግሥትም ነጋዴዎች ከኅብረተሰቡ ጥሬ ቆዳ እስከ 40 ብር ድረስ በመክፈል እንዲገዙ፣ ለፋብሪካዎችም በ50 ብር እንዲያቀርቡ የሚያስማማ ሐሳብ አቅርቦ በዚሁ መሠረት እየተሠራ ቢሆንም፣ የዋጋ መጨመር በመታየቱና የቆዳ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ዋጋ ጨምረዋል በማለት ኢንስቲትዩቱ ነጋዴዎችን መውቀሱ አይዘነጋም፡፡

ይህ አግባብ አይደለም የሚሉት አቶ ብርሃኑ፣ ዋጋው ሲጨምር ብቻም ሳይሆን ሲወድቅም ትኩረት ተሰጥቶት ለምን እንደተፈጠረ መከታተል ይገባል ብለዋል፡፡ መንግሥት ፋብሪካዎችን መቆጣጠር አለበት ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ 60 በመቶ የጥሬ ዕቃ አቅርቦታቸው ቆዳ የሆነው ፋብሪካዎች በዱቤ የሚገዙበት አሠራርም ሊታይ ይገባዋል ብለዋል፡፡ አብዛኞቹ በቂ የሥራ ማስኬጃ የሌላቸው፣ ከአቅማቸው በታች የሚያመርቱ  ሆነው በመገኘታቸው፣ በመንግሥት እንደ አዲስ የተቋቋመው የኢንዱስትሪ ዕቃዎች አቅራቢ ድርጅት ባደረገላቸው ዕገዛ ሳቢያ ጥሬ ቆዳ ለመግዛት መብቃታቸውም ታውቋል።

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ባለው ሁኔታ በያመቱ ለፋብሪካዎች መቅረብ ከሚገባው 40 ሺሕ ቶን ቆዳ ውስጥ ግማሹ ብቻ እየቀረበላቸው እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ ይህም ሆኖ እየቀረበ ያለውም ቆዳ በዋጋና በጥራት ችግር በተገቢው መንገድ በፋብሪካዎች ዘንድ ተቀባይነት እንደማያገኝ ነጋዴዎች ይገልጻሉ፡፡

መንግሥት እሴት ያልተጨመረበት ወይም በከፊል ያለቀለት ቆዳ ወደ ውጭ እንዳይላክ ለመግታት የ150 በመቶ የወጪ ንግድ ታክስ መጣሉ ይታወሳል፡፡ ይህ በመሆኑ ምክንያትም በከፊል ያለቀለት ቆዳ ወደ ውጭ መውጣት ካቆመ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ መንግሥት ያሰበውን ያህል ያለቀለት ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ለውጭ ገበያ ማቅረብ አልቻለም፡፡ በዚህ ዓመት ስድስት ወራት እንኳ ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ለማግኘት ከታቀደው 113 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ከግማሽ ያነሰው ገቢ መገኘቱ ይታወቃል፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles