የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማቋቋሚያ አዋጅ ሰሞኑን ለሁለተኛ ጊዜ እንዲሻሻል መደረጉ ይታወቃል፡፡ የማቋቋሚያ አዋጁ እንደገና እንዲሻሻል የተፈገለው የአገሪቱን የቡና ዘርፍ ብቻም ሳይሆን ወጪ ንግዱን ችግሮች ለማሻሻል ከተጀመረው እንቅስቃሴ ጋር በማያያዝ ለውጥ እንዲመጣ በማሰብ ነው፡፡
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማቋቋሚያ አዋጅ የወጣው በ2000 ዓ.ም. ነበር፡፡ የመጀመሪያው የማሻሻያ አዋጅ ደግሞ በ2007 ዓ.ም. ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን፣ ይህ ማሻሻያ ዋናው ዓላማ አንድ ተጨማሪ አንቀጽ ለማከል ተፈልጎ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የፀደቀው አዋጅ ግን በርካታ መሠረታዊ ማሻሻያዎች ተካትተውበታል፡፡
በምርት ገበያው ለተደረገው ማሻሻያ የተሰጠው ምክንያት፣ ተቋሙ የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካትና ተደራሽነቱን የበለጠ በማስፋት የግብይት ተዋናዮችን ፍላጎት ብሎም አነስተኛ አምራቾችም በምርት ገበያው ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡
በቀደመው አዋጅ ውስጥ ከተካተቱ አንቀጾች አሥራ ሁለት ያህል ለውጦች መደረጋቸውን ያመላክታል፡፡ በቀድሞው አዋጅ ውስጥ የነበሩ ከስምንት በላይ ንዑስ አንቀጾች ሙሉ በሙሉ ተሰርዘው በአዲስ ተተክተዋል፡፡ አዳዲስ ንዑሳን አንቀጾችም ተካተዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ለውጦችን በመያዝ በፀደቀው አዋጅ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ የምርት ገበያ ባለሥልጣንና የቡና እና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በተሻሻለው አዋጅ ውስጥ ከተጨመሩት አንቀጾች ውስጥ ቡና በመኪና ላይ ሳለ ሽያጭ ማካሔድ እንደሚፈቀድ የተጠቀሰው ንዑስ አንቀጽ ይገኝበታል፡፡ ይህም የግብይት ምርት የጫኑ ተሽከርካሪዎች፣ ጭነቱ በተሽከርካሪው ላይ እንዳለ ተሸጦ ወደ ገዥ እስከሚተላለፍበት ወይም በምርት ማከማቻ መጋዘን እስከሚራገፍበት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚቆሙበት የተከለለና ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ እንዲፈጠር ማድረጉ ነው፡፡ በተሻሻለው አዋጅ ‹‹ጥብቅ ማቆያ ሥፍራ›› በማለት የተገለጸ ሲሆን፣ በመኪና ላይ የሚደረገውን ግብይት ለመደገፍ የተካተተ ንዑስ አንቀጽ ነው፡፡
የማሻሻያ አዋጁ ከሰረዛቸው አንቀጾች መካከል አንዱ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የነበረውን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣንን የሚመለከተው ይገኝበታል፡፡ የዚህ መሥሪያ ቤት ሚና አዲሱ አዋጅ ለንግድ ሚኒስቴር በመሰጠቱ፣ የምርት ገበያው አዲሱ ተቆጣጣሪ ሆኗል፡፡
ስትራቴጂያዊ በሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፉ የምርት ማከማቻ መጋዘኖችና ጥብቅ የማቆያ ሥፍራዎችን መገንባትና ማስተዳደር ለምርት የተሰጠ ኃላፊነት ሆኗል፡፡ በምርት ገበያው ግብይት የሚደረግባቸው ምርቶች የሚጓጓዙበትን ሁኔታ በተመለከተ እንደ አስፈላጊነቱ አግባብነት ካለው የመንግሥት አካል በሚሰጠው ውክልና መሠረት አስገዳጅ መስፈርት ማውጣት፤ ተፈጻሚነቱን የማረጋገጥና ተገቢውን ዕርምጃ የመውሰድ ሥልጣን የሰጠ አንቀጽ በማሻሻያ አዋጁ ተጨምሯል፡፡
በማሻሻያ አዋጁ እንደ መሠረታዊ ለውጥ የሚታየው ሌላው ነጥብ ደግሞ የምርት ገበያውን ካፒታል መጠን የቀየረ መሆኑ ነው፡፡ በቀድሞ አዋጅ የምርት ገበያው የተፈቀደ ካፒታል 250 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 90 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ስለመከፈሉ የሚደነግግ ነበር፡፡ በማሻሻያ አዋጁ ግን ይህንን የካፒታል መጠን ሙሉ በሙሉ በመሰረዝ የምርት ገበያው የተፈቀደ ካፒታል 1.25 ቢሊዮን ብር መሆኑን ይገልጻል፡፡ ከዚህ ውስጥ 725 ሚሊዮን ብር በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ እንደተከፈለ በማሳወቅ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡
የምርት ገበያው የአባልነት መቀመጫን በተመለከተ ተደንግጎ የነበረውን በማስቀረት “በምርት ገበያው የአባልነት መቀመጫ ሳይኖራቸው ያለአገናኝ በምርት ገበያው የግብይት መድረክ በራሳቸው መገበያየት የሚችሉ ምርት ሻጮች ወይም ገዥዎች የሚስተናገዱበት ዝርዝር ሁኔታ በምርት ገበያው ደንብ ይወሰናል፤” የሚል አንቀጽ እንዲካተትበት ተደርጓል፡፡ ይህም ማሻሻያ መቀመጫ ባላቸው አገበያዮች አስገዳጅ የነበረውን የማገበያየት ሥራ የሚያስቀር ነው፡፡ በቀድሞው አዋጅ ውስጥ የዳይሬክተሮች ቦርድ አሥራ አንድ አባላት የሚኖሩት ሲሆን፣ ሰብሳቢውን ጨምሮ ስድስቱ በሚኒስትሩ፣ እንዲሁም አምስቱ በአባላት እንደሚሾሙ ይገልጻል፡፡ የማሻሻያው አዋጅ ግን ይህ ሙሉ ለሙሉ ተሰርዞ የዳይሬክተሮች ቦርድ አሥራ አንድ አባላት የሚኖሩት ሲሆን፣ ሰብሳቢውን ጨምሮ ስድስቱ በሚኒስቴሩ (በንግድ ሚኒስቴር) ይሰየማሉ፤ አምስቱ በምርት ገበያው ደንብ መሠረት ከአባላት ወይም ከአባል ማኅበራት ይመረጣሉ በሚል ተሻሽሏል፡፡
ስለምርቱ ጥራት ወይም ደረጃ ከምርት ገበያው የምርት የምስክር ወረቀት ሳያገኝ እንዲሁም ስለምርቱ መጠን፣ መነሻ ቦታ ሁኔታና የማከማቻ መጋዘኑ ወይም ጥብቅ ማቆያው የሚገኝበትን ቦታ የሚገልጽ የመጋዘን ማከማቻ ደረሰኝ ሳይኖረው ምርቱን በምርት ገበያው ለግብይት ማቅረብ የተከለከለ ስለመሆኑ የሚገልጽ አዲስ አንቀጽ አለው፡፡ ይህም ምርት ገበያው ጥራትን ከመመዘን አኳያው አዲስ ኃላፊነት የሰጠው እንደሆነ አመላክቷል፡፡
በምርት ገበያው ግብይት የሚደግባቸው ርክክባቸው ወደፊት የሚፈጸምና ወደፊት የሚፈጸሙ ውሎችን በተመለከተ ዝርዝሩ ባለሥልጣኑ በሚወጣው መመርያና በምርት ገበያው የውስጥ ደንብ እንደሚወሰን ተገልጿል፡፡ ማሻሻያ አዋጁ ይህም በሚኒስቴሩ ወይም አግባብነት ባለው የመንግሥት አካል መጽደቁ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የምርት ገበያው ከግብርና ምርቶች ውጭ ያሉ ውሎችን በማጥናት ሊያገበያይ የሚችልበትን ሥልጣን የሚሰጥ አዲስ ንዑስ አቀንጽ ገብቷል፡፡
ከአዲሱ የቡና ግብይት ማሻሻያ ጋር በተያያዘ፣ የምርት ገበያውን የማቋቋሚያ አዋጅ ለማሻሻል እንደምትክ ከሚቀርቡት ውስጥ ቡናን በአካባቢ መጠሪያ ወይም ዱካ መሸጥ መፈቀዱም የሚጠቀስለት ነው፡፡
በዚህም መሠረት የምርት ገበያው የምርቱን ባለቤት ማንነትና የምርቱን ዱካ ያረጋገጠ የግብይት ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚችል በማሻሻያ አዋጁ ተመልክቷል፡፡ ባለቤትነትንና የምርት ዱካን ባስጠበቀ ሁኔታ በሚደረግ ግብይት መካተት ያለባቸውን ምርቶች ዝርዝር ንግድ ሚኒስቴር በየጊዜው እየከለሰ ሊወስን እንደሚችል ሥልጣን የሚሰጥ አንቀጽ ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት ግብይት የሚፈጸምባቸው ምርቶች የመጋዘን ውስጥ የምርት አቀማመጥ፤ አስተዳደርና ርክክብም የምርቱንና የባለቤቱን ወይም አቅራቢውን ማንነት የሚያረጋግጡ መሆን እንደሚኖርበት ተደንግጓል፡፡ በዚህ ሥርዓት ግብይት የሚደረግበትን ምርት እንደጫኑ በምርት ገበያው ጥብቅ ማቆያ ሥፍራ ግብይት የሚካሄድባቸውን ተሽከርካሪዎችና ጭነቶች አቀባበል፣ ናሙና አወሳሰድ፣ ደረጃ አወሳሰን፣ የክብደት ምዘና፣ ግብይት፣ ርክክብና የአደጋ ቁጥጥር አሠራሮችን የተመለከቱ ዝርዝር የአሠራር ሥርዓት በምርት ገበያው ደንብ እንደሚወሰንም የማሻሻያ አዋጁ ያመለክታል፡፡
ከዚህ አዋጅ ጋር ተያይዞ ምርት ገበያው ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቡናን የግብይት ሥርዓት ውጤታማና ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ የማሻሻያ ሥራዎች በመሠራታቸው በዚሁ መሠረት አገልግሎት ጀምሯል፡፡ ለቡና ግብይቱ የምርት ባለቤትነትንና መገኛን ገላጭ የሆነ የመኪና ላይ አዲስ የግብይት ሥርዓት አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤርሚያስ እሸቱ ተናግረዋል፡፡
ለእነዚህ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ልዩ ሥልጠና እየተሰጣቸው ነው፡፡ የግብይት ሥርዓቱ የሚካሄደው የምርቱንና የምርቱን ባለቤት ማንነት ባስጠበቀ (ገላጭ) መልኩ ሲሆን፣ ምርቱ ወደ መጋዘን ውስጥ ሳይገባ በተከለለ ጥብቅ ማቆያ (Bonded Yard) ውስጥ በመኪና ላይ እንዳለ መሸጥ የሚያስችል ጭምር ነው፡፡ ከመኪና ሽያጭ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ በቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር እንዲህ ላለው አገልግሎቶች የሚሆኑ መመርያዎች ተሰናድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ያለአገናኝ አባል በቀጥታ መገበያየት ለሚፈልጉ ግለሰቦች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ የንግድ ድርጅቶችና ሌሎችም አስፈላጊውን መመዘኛዎች እንዲያሟሉ በማድረግ በቀጥታ እንዲሳተፉ የሚያስችል ተደራሽነትን ያረጋገጠ የግብይት መድረክ እንደተዘጋጀም ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት ያለአገናኝ መገበያየት ለሚፈልጉ ሥልጠና እየተሰጠና ብቃታቸው በፈተና እየተረጋገጠ ወደ ግብይት መድረኩ የሚገቡበት ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ አቶ ኤርሚያስ ተናግረዋል፡፡
ሥርዓቱንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ መጠነ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ ባለቤትነትን ገላጭ የሆነ የመኪና ላይ ግብይት ለማካሄድ እንዲረዳ ስለ አዲሱ የቡና ግብይት አፈጻጸም ለሚመለከታቸው የግብይት ተዋንያን በአሠራር ሥርዓቱ ላይ ግልጽነትን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ስለመሆኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተነግሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቡና ምርት ቅበላ በሚካሄድባቸው በሁሉም ቅርንጫፍ መጋዘኖች ለሚሠሩ ሠራተኞች፣ የአዲሱን የቡና ግብይት ሥርዓት አስመልክቶ ሥልጠና እየተሰጠ ነው ተብሏል፡፡
የቡና ግብይት አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ለማከናወን እንዲቻል ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተለይቶ ራሱን ችሎ ተቋቁሞ የነበረው የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች የመጋዘን አገልግሎት ድርጅት ተመልሶ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር እንዲዋሃድ የአደረጃጀት ማሻሻያዎች ስለመደረጋቸውም አቶ ኤርሚያስ ሳያስታውሱ አላለፉም፡፡
አዲሱ የግብይት ሥርዓት የቡናን ግብይት ውጤታማነት ከማስጠበቅ አልፎ በቡና ልማትና ግብይት ዘርፍ የሚታየውን የተንዛዛ እሴት የማይጨምር የግብይት ሰንሰለትን በማሳጠርና ሥር የሰደዱ ችግሮችን በመቅረፍ የቡና የወጪ ንግድን ለማሳደግ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የሥራ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡
አዲሱ አሠራር ሕገወጥ ተግባራትን ለመገደብ የሚያስችል መሆኑን የለገጹት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አሌሮ ኦፒው፣ አዲሱን አሠራር በሚፃረር መልኩ የሚሳተፉ ላይ የሚወሰደውን ዕርምጃ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ አዲሱ አዋጅ አሠራራችንን እንድናቀላጥፍ ያደርጋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለኢትዮጵያ ወጪ ንግድ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል ብለዋል፡፡
የቡናው ዘርፍ ለአገራችን የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑ የሚታወቅ ስለመሆኑ የገለጹት አቶ ኤርሚያስ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የወጪ ንግድ ግኝቱ እየቀነሰ የግብይት ሥርዓቱም ችግር እያጋጠመው በመጣው ባለፉት ጥቂት ወራት ወደውጭ የተላከው የቡና መጠን ከፍተኛ ሊሆን መቻሉን በመጥቀስ አዲሱ አሠራር ከወዲሁ ውጤት የታየበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የተራዘመ የግብይት ሥርዓት ደረጃዎች መኖራቸው፤ እሴት የማይጨምር ረዥም የቡና ግብይት ሰንሰለት መኖር፤ ቡናችን በዓለም ገበያ ላይ ሊኖረው የሚገባው ተወዳዳሪነት እንዲያሽቆለቁል አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
አሁን ግን ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል አቅም የሚፈጥር አሠራር ስለመዘርጋቱ የተናገሩት አቶ ሻፊ፣ አገሪቱ በቡና ግብይት የተንዛዛ ሰንሰለት ታወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ይቀንሳል፣ የውጭ ምንዛሪዋም ይጨምራል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የቡና ግብይት ሰንሰለት መራዘም የቡና የወጪ ንግዱ ወጪ 40 በመቶ አድርሶታል ያሉት አቶ ሻፊ፣ አሁን ሰንሰለቱ ስለሚያጥር ወጪው ይቀንሳል ብለዋል፡፡ ይህም ተወዳዳሪ ዋጋ ያለው ቡና ለማቅረብ ያስችላል ተብሏል፡፡
አዲሱ የቡና ግብይት ሥርዓት በየጊዜው እየዳበረ የሚሄድና ጊዜው የሚፈቅደውን የአሠራር ሥርዓት ተከትሎ የሚቀጥል ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት መንፈስ ማሻሻያውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አሳስቧል፡፡