Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all 720 articles
Browse latest View live

የ1.2 ቢሊዮን ብር የግንባታ ወጪ የሚጠይቀው የንግድ ማዕከል መንግሥትና የግሉ ዘርፍን በባለቤትነት አሳትፏል

$
0
0

አዲስ አበባ የአፍሪካ የፖለቲካ ማዕከል ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ ኢኮኖሚ እቅስቃሴ እንብርት እንድትሆን ለማድረግ እንደሚያግዝ ታምኖበት ከአንድ ሳምንት በፊት የመሠረት ድንጋዩ ተቀምጦ ግንባታው የተጀመረው የአዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንፌዴሬሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል የተጠነሰሰው ከ13 ዓመታት በፊት ነበር፡፡

የኋላ ታሪኩ ሲፈተሽ ለማወቅ እንደሚቻለው፣ የማዕከሉ ግንባታ ጠንሳሾች የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት (አሁን የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት) የወቅቱ አመራሮች ነበሩ፡፡

ለዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ማካሄጃ እንዲሁም ለተዛማጅ አገልግሎቶች ማስተናገጃ የሚለው እዚህ ግባ የሚባል ማዕከል የሌላት አዲስ አበባ፣ ከአሁን በኋላ ከራሷ አልፎ በአፍሪካ ደረጃ የሚዘጋጁ ትርዒቶችን የምታስተናግድበት የንግድ ማዕከል ባለቤት ያደርጋታል የተባለውን ይህንን ማዕከል የመገንባት ሐሳብ ከውጥኑ ጀምሮ የበርካቶችን ቀልብ ገዝቶ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የወቅቱ ከንቲባ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ በነበሩበት ወቅት፣ ለማዕከሉ መገንቢያ የሚውል 110 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ንግድ ምክር ቤቱ ተርክቧል፡፡

በወቅቱ ለንግድ ምክር ቤቱ ትልቅ እመርታ ሆኖ የተቆጠረው የቦታ ርክክቡ በተከናወነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከንቲባ አርከበ፣ በዚያን ወቅት የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ከነበሩት ከአቶ ብርሃነ መዋ ጋር በመሆን ለዘመናዊው የንግድ ትርዒት ማዕከል ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠው ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በራሱ የሚያስተዳድረው ትልቅ ማዕከል ለመገንባት መነሳቱ ብሎም ቦታ መረከቡ ለተቋሙ ዳግመኛ መነቃቃትን የፈጠረ ክስተት ስለነበር በርካቶች እንደየ ምርጫቸው አጋጣሚውን ለመግለጽ ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡ የመጀመርያው የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሥርዓት ሲከናወን፣ አቶ ብርሃነ መዋ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችን በሚወክል ባህላዊ ልብስ ተሸልመው እንደነበርም ይታወሳል፡፡

ይኸው ሥነ ሥርዓት ሲካሄድ ንግድ ምክር ቤቱና የንግዱ ኅብረተሰብ ተቀናጅተው በወቅቱ ዋጋ ከ350 እስከ 400 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ የተገመተውን  የንግድ ማዕከል በጋራ እንደሚገነቡ ተነግሮ ነበር፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ ባለቤትነት ተይዞ በአባላቱ ርብርብ ግንባታው ይካሄዳል ተባለ፡፡ በዚሁ ተስፋና ወኔ አዲስ አበባ ዘመናዊና ግዙፍ የንግድ ማዕከላት እንዲኖራት ለማድረግ ደፋ ቀና ማለት ተጀመረ፡፡ በጋለ ስሜት የተጀመረው የማዕከሉ ግንባታ፣ ከመሠረት ድንጋዩ በኋላ ወደ ተግባር ለመግባት ግን የአነሳሱን ያህል ግን ሊራመድ አልቻለም፡፡ ከሦስት እስከ አራት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል የተባለው የንግድ ማዕከሉ ግንባታ ዕውን ሊሆን አልቻለም፡፡ መደበኛው የማዕከሉ ግንባታ በቁሙ መቅረቱ ብቻም ሳይሆን፣ ለግንባታ የተፈቀደው ቦታ የረባ አጥር ሳይኖው ዓመታት መቆጠር ጀመሩ፡፡ ምንም ግንባታ ሳይካሄድባቸው ታጥረው ከተቀመጡ ቦታዎች አንዱ በመሆንም የንግድ ምክር ቤቱ ቦታ በከተማው አስተዳደር ይጠቀስ ጀመረ፡፡ የማዕከሉ ግንባታ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ በቆመበት ወቅት ንግድ ምክር ቤቱ አራት ፕሬዚዳንቶችን አፈራረቀ፡፡ በልዩ ሁኔታ የግንባታ ቦታውን ለምክር ቤቱ በሊዝ የሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም አቶ አርከበን ጨምሮ አራተኛ ከንቲባውን አፈራረቀ፡፡

የፕሮጀክቱ አዝጋሚ ጉዞ

ብዙ የተባለለትና ተስፋ የተጣለበት ይህ ፕሮጀክት፣ እንደታሰበው ሳይራመድ ለመቆየቱ የተለያዩ ምክንያቶች ሲጠቀሱለት ቆይቷል፡፡ ይሁንና በተጓተተው የግንባታው ፕሮጀክት ሒደት ውስጥ ዳግመኛ እንደ አዲስ የሚታይበት መንገድ ተከፈተ፡፡ ይኸውም ንግድ ምክር ቤቱ ግዙፉን ግንባታ ለብቻው ለመወጣት አቅም የሌለው መሆኑ አንዱ አጋጣሚ ነበር፡፡

የንግድ ማዕከሉ በንግድ ምክር ቤቱ ብቸኛ ባለቤትነት መያዙ ቀርቶ ሌሎችም እንዲሳተፉበት ለማድረግ ከሌሎች ተቋማት ጋር አብሮ መሥራት የሚቻልበትን ሐሳብ በማንሳት ለዚሁ የሚያግዝ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ጊዜ መውሰዱ አልቀረም፡፡ ቀድሞ የታሰበው ቀርቶ በአዲስ አደረጃጀት እንዲመራ ሲታሰብ፣ የንግድ ምክር ቤቱ አዲሱ አካሄድ ማዕከሉ የሚገነባበት ሥርዓት ቢዝነስ ቀመስ እንዲሆን፣ በአክሲዮን ኩባንያነት ተደራጅቶ የአክሲዮን ድርሻዎች መሸጥ ጀመሩ፡፡ በዚሁ አነሳሽነትም መጠነኛ እንቅስቃሴ ይደረጉ ጀመር፡፡

      ጥቂት ቆይቶ ግን የፕሮጀክቱን አካሄድ የቀየረ ሌላ አመለካከት ተፈጠረ፡፡ ግንባታው በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ጥምረት ይካሄድ የሚል አዲስ አካሄድ ይንፀባረቅ ጀመረ፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ ስምምነት ከማድረጋቸው በፊት ንግድ ምክር ቤቱና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለብዙ ጊዜ እንደመከሩበት ይገለጻል፡፡ በመጨረሻውም የአዲስ አበባ የባላደራ ቦርድ ከንቲባ የነበሩት አቶ ብርሃኑ ደሬሳና የወቅቱ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ የንግድ ማዕከሉ ግንባታ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ጥምረት እንዲካሄድ የሚያስረግጥ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡፡ ስምምነቱ የተፈረመበት ብዕርም ‹‹ወርቃማ›› ነች ተባለ፡፡ በዚህም ሳይገታ የፕሮጀክቱን ዓላማ የሚተነትነው ሰነድም ተለወጠ፡፡ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በመጣመር መሥራት እንደሚችሉ ማሳያ ፕሮጀክት ስለመሆኑ ተጠቅሶም፣ በ20 መሥራች አባላት የአዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከል አክሲዮን ማኅበር እንደ አዲስ ተቋቋመ፡፡ የአክሲዮን ማኅበሩ መመሥረትና የማዕከሉ ግንባታ አስፈላጊነትን ከተመለከቱ አምስት ዋነኛ ዓላማዎች ውስጥ ሁለቱ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ በጥምረት የመሥራታቸውን ፋይዳ የሚያትቱ ነበሩ፡፡ አንደኛው ሐሳብ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ልማት ተሳታፊነቱ እንዲጨምር ያግዛል የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነትን ለማጠናከር ይጠቅማል በሚል የተቃኘ ነበር፡፡  

ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ባለቤትነት እንዲተዳደር ታልሞ በዚህ አኳኋን የተጓዘው የአክሲዮን ኩባንያው ታሪክ፣ ሁለቱንም ወገኖች ሚዛናዊ የባለቤትነት ድርሻ ኖሯቸው ፕሮጀክቱን በጋራ የማስተዳደር መብት እንዲኖራቸው ጭምር ያስቻለ ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡

ከአክሲዮን ኩባንያው ምሥረታ በኋላ ዋናዎቹ ባለአክሲዮኖች የሆኑት እነዚሁ የአዲስ አበባ አስተዳደርና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ናቸው፡፡ የተቀሩት ባለአክሲዮኖች 18ቱ የግል ኩባንያዎችና ሌሎች የግል ኩባንያ ኃላፊዎች ነበሩ፡፡ ወደ አክሲዮን ሽያጩ በተገባ በመጀመርያው ዙር፣ 300 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለገበያ ቀረበው ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ 150 ሚሊዮን የሚያወጡ አክሲዮኖችን የከተማ አስተዳደሩ ገዛ፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በበኩሉ አሥር ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖችን ወሰደ፡፡ ቀሪዎቹ ባለአክሲዮኖችም ከ25 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖችን ገዙ፡፡ ለሕዝብ የቀረቡ አክሲዮኖች ግን እንደተፈለገው መጠን ሊሸጡ አልቻሉም፡፡ ይህም ለፕሮጀክቱ መጓተት አንዱ ምክንያት ሆኖ ቀረበ፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደ የአክሲዮን ሽያጭም፣ ከቀረቡት የአንድ ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ውስጥ አስተዳደሩ የግማሽ ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን ገዛ፡፡ ከዚህ ውስጥ 415 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች የገዛው የከተማ አስተዳደሩ በሥሩ በሚተዳደሩ አምስት ተቋማት በኩል ነበር፡፡ በከተማው አስተዳደር አክሲዮን የተገዛላቸው ተቋማትም ሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ኩባንያ፣ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት፣ አዲስ ብድርና ቁጠባ እንዲሁም አዲስ ኢንተርፕራይዝ ናቸው፡፡ 85 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን ደግሞ በአንበሳ አውቶብስ ስም ተገዝተዋል፡፡ ይህ በመሆኑም አስተዳደሩ ትልቁን የአክሲዮን ድርሻ ይዞ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡ በሁለት ዙር ከተሸጡት አክሲዮኖች ውስጥ 97 በመቶውን አስተዳደሩ ይዞ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ግን በያዘው አክሲዮን ብቻ ተወስኖ የ1.68 በመቶ ድርሻ ይዞ ይገኛል፡፡ ቀሪዎቹ 18 መሥራች ባለአክሲዮኖች ድርሻ ሁለት በመቶ ያልሞላ ድርሻ ይዘው የአክሲዮን ሽያጩ በድጋሚ ቀጠለ፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ አሁንም ድረስ ይዞ የቆየው አሥር ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለውን አክሲዮን ብቻ ነው፡፡

ለፕሮጀክቱ እንደ አዲስ ምዕራፍ የሚቆጠረው ሌላው ታሪክ የሚጀምረው ባለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄዱ እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ በተለይ አስተዳደሩ በሁለቱ የአክሲዮን ሽያጮች ወቅት የአንበሳውን ድርሻ የያዘባቸውን አክሲዮኖች ከገዛ በኋላ ወደ ግንባታ ሊያሸጋግር የሚችል ሥራ ተሠርቷል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ ከተፈቀደ 1.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ውስጥ የመጨረሻዎቹን 669.255 አክሲዮኖች በዚህ ዓመት አጋማሽ ለሽያጭ አቅርቧል፡፡ በዚህን ወቅት ግን ከ20ዎቹ መሥራቾች በተጨማሪ አዳዲስ የገቡትን ጨምሮ በአጠቃላይ 747.255 ሚሊዮን ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖችን ለመሰብሰብ ችሏል፡፡

አዲሱ ምዕራፍ

የፕሮጀክቱ አዲሱ ምዕራፍ የሚጀምረው የማዕከሉን ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችለው አዲስ የመሠረት ድንጋይ ከመቀመጡ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በተገኙበት፣ ለሁለተኛ ጊዜ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት አዲስ ምዕራፍ የሆነው የግንባታውን የመጀመርያ ምዕራፍ ለማካሄድ የግንባታ ስምምነት መፈረሙና ወደ ተግባር ሥራ መገባቱም ጭምር ነው፡፡  

የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ለማካሄድ ከፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ጋር ስምምነት የፈረመው ሲጂሲኦሲ ግሩፕ የተባለው የቻይና ኩባንያ ነው፡፡ ነገር ግን በሁለት ዙሮች ከተደረገው የአክሲዮን ሽያጭ መገንዘብ የተቻለው፣ ከ13 ዓመታት ቆይታ በኋላ የዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት የባለቤትነት ድርሻ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ተመጣጣኝ ድርሻ ገና እንዳልተያዘበት ነው፡፡

የ595.9 ሚሊዮን ብር ዋጋ ካላቸው አክሲዮኖች ውስጥ የከተማ አስተዳደሩ 583.3 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች በመግዛት የ97.9 በመቶ ድርሻ መያዙ ያልተመጣጠነ የባለቤትነት ድርሻ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ከዚህ በኋላ 658 ሺሕ ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለሽያጭ ቢቀርቡም፣ እነዚህ አክሲዮች ተሽጠውም እንኳ ዋናው የኩባንያው ባለቤት የከተማው አስተዳደር ሆኖ መቅረቱን የሚያረጋግጥ አካሄድ እየታየ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ ግን እስካሁን በነበረው የአክሲዮን ሽያጭ ከፍተኛውን አክሲዮን የገዛው አስተዳደሩ ቢሆንም፣ ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት አስተዳደሩ ፕሮጀክቱን በፍጥነት ለማስጀመር ካለው ፍላጎት አኳያ ነው ብለዋል፡፡

ለሥራው ማስጀመሪያ የሚሆን ገንዘብ በማዋጣት ግንባታ እንዲጀመር በማድረግ፣ በቀሪዎቹ አክሲዮኖች ግዥ ላይ ግን የንግድ ኅብረተሰቡ እንዲሳተፍ ለማድረግ ብቻም ሳይሆን፣ አስተዳደሩ የግል ዘርፉን ለመደገፍ ብሎም ፕሮጀክቱ እንዳይቋረጥ በማሰብ የወሰደው ዕርምጃ እንደሆነ በመጥቀስ አቶ ጌታቸው ይሞግታሉ፡፡ ይህ የአስተዳደሩ ዕርምጃ ከዚህ በኋላ ለሚካሄደው የአክሲዮን ሽያጭ ትልቅ ድጋፍ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ጌታቸው፣ በአሁኑ ወቅት ወደ አስተዳደሩ ሚዛኑ ያጋደለው  ኢንቨስትመንትም፣ ወደፊት በሚሸጡት አክሲዮኖች እየተመጣጠነ እንደሚሄድ ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ፍላጎት ይህ ብቻ እንዳልሆነ ተናግረው፣ ቀሪዎቹን አክሲዮኖች ለመግዛት መነሳሳት መታየቱ ፕሮጀክቱን በፍጥነት ዕውን ለማድረግ እንደሚያግዝም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ዋናው ነገር ግንባታውን መጀመራችን ነው፡፡ አዋጭ በመሆኑ ሁሉም ይረባረብበታል፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ እንዲህ ያለው ቢዝነስ ውስጥ የንግድ ኅብረተሰቡ የሚሳተፍ በመሆኑ፣ መንግሥት ከገዛቸው አክሲዮኖች ውስጥ ወደ ወደፊት ወደ ግሉ ዘርፍ የሚያዛውር በመሆኑ የባለቤትነት ድርሻውን እየተመጣጠነ ይሄዳል ብለው ያምናሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በርካታ የግሉ ዘርፍ አባላት አክሲዮን እየገዙ በመሆኑ፣ ሥጋቱ እንደሚፈታ ያስረዳሉ፡፡  

የፕሮጀክቱ አዋጭነት መረጋገጡ ብቻም ሳይሆን የግንባታ ሥራውም በመጀመሩ በርካቶች አክሲዮን ለመግዛት እንደሚቀርቡ ይታሰባል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ በጋራ የመሥራት ዓላማውን ለማሳካት ያስችላል በማለት አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱም አባላቱ በዚህ ፕሮጀክት ባለቤት ለመሆን እንዲችሉ ቅስቀሳዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረው፣ ቀሪዎቹን አክሲዮኖች ለመግዛት የታየው መነሳሳት ፕሮጀክቱ በታሰበው ጊዜ ለማጠናቀቅ ያስችላል ብለዋል፡፡ ‹‹ዋናው ነገር ግን ግንባታውን መጀመራችን ነው፡፡ አዋጭም በመሆኑ ሁሉም ይረባረብበታል፤›› ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ይፈጃል የተባለው ይህ ፕሮጀክት፣ በጥንስሱ ወቅት ዲዛይኑ ሲሠራ 1.8 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ ታስቦ ነበር፡፡ ይህ ልዩነት የተከሰተው ግን የግንባታ ሒደቱ በመዘግየቱና ወጪውም በመጨመሩ ነው፡፡ ሆኖም ማዕከሉ ሥራ ሲጀምር፣ በመጀመርያው ዓመት ብቻ 220 ሚሊዮን የተጣራ ትርፍ እንደሚያስገኝ ይገመታል፡፡ በየዓመቱ የሚያስመዘግበው ትርፍም ከ16 እስከ 46 በመቶ የሚገመት ዕድገት ይኖረዋል ተብሏል፡፡

የማዕከሉ ዋና ዋና ክፍሎች

ይህ ማዕከል አንድ ባለአራት ኮከብ ሆቴል፣ በአዳራሽ ውስጥ 20,600 ካሬ ሜትር እንዲሁም ከአዳራሽ ውጭ 6,700 ካሬ ሜትር፣ በጠቅላላው 27,300 ካሬ ሜትር የቦታ ስፋት ያለው የኤግዚቢሽን ማሳያ ሥፍራ፣ በአንድ ጊዜ 5000 ሰዎችን የሚያስተናግድ አዳራሽ፣ 3000 መቀመጫዎች ያሉት ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች የሚስተናገዱበት አዳራሽ፣ እያንዳንዳቸው 500 ሰዎችን የሚይዙ ሁለት የቴአትርና የፊልም አዳራሾች፣ ከ50 እስከ 100 ሰዎችን የሚያስተናግዱ ስድስት አነስተኛ የመሰብሰቢያ ክፍሎች፣ ባለአራት ኮከብ ሆቴል፣ ዘመናዊ የገበያ ሥፍራ፣ ሬስቶራንት፣ ካፍቴሪያዎች፣ የሕፃናትና የአዋቂዎች መዝናኛ ሥፍራዎች ወዘተ. እንደሚገነበቡበት ከማዕከሉ መመሥረቻ ጽሑፍ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ለቻይናው ሲጂሲኦሲ የሚከፈለው ገንዘብ 1.2 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ሲታወቅ፣ እስካሁን ከ830 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው አክሲዮኖች መሸጣቸውም ተረጋግጧል፡፡ 

Standard (Image)

ዘመናዊ የጤፍ ዱቄት ማዘጋጃና የእንጀራ መጋገሪያ ፋብሪካ ሥራ ሊጀምር ነው

$
0
0

 

ሐጂ ቱሬ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ከ60 ዓመታት በላይ የሚታወቅ ስም ነው፡፡ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በአስመጪና ላኪነት ቀዳሚ የሆኑት ስመጥሩ ነጋዴ፣ ለአገሪቱ አዳዲስ ምርቶችን ከውጭ በማስገባትና በማከፋፈልም ይታወቃሉ፡፡ በተለይ ከቻይና ጋር የነበራቸው የንግድ ግንኙነትም በጉልህ የሚጠቀስ ነው፡፡ የዱቄት መፍጫ ማሽኖችንና ሌሎችንም በማስመጣት ዘርፉ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ስለእሳቸው ከሚነገሩት ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡

ሐጂ ቱሬ ለዓመታት ሲመሩት የነበረውን ቢዝነስ ወደ ልጆቻቸውና ወደ ልጅ ልጆቻቸው በማስተላለፍ ዛሬም ድረስ ሥር የሰደደ ኩባንያ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል፡፡ ወ/ሮ ሙና መሐመድ ሦስተኛ ትውልድ ላይ የሚገኙ የሐጂ ቱሬ የልጅ ልጅ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ሙና የአያትና የወላጆቻቸውን ቢዝነስ ብቻም ሳይሆን፣ ልክ እንደነሱ እኛም የራሳችንን አሻራ ማኖር አለብን በማለት አዳዲስ ቢዝነሶችን በማስተዋወቅ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

‹‹አያቴ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹን የዱቄት ማሽኖች አስመጥቶ ከ300 በላይ ማሽኖች እንዲተከሉ አድርገዋል፡፡ ሌሎች በወቅቱ አዳዲስ የሚባሉ ቢዝነሶች አስተዋውቀዋል›› በማለት ያብራሩት ወ/ሮ ሙና፣ ‹‹እኛም ከአያታችን መነሻውን በመያዝ አዲስ ነገር ለማበርከት የምንችለውን ነገር እያደረግን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ሙና አዲስ እንደሆነ የገለጹትና አሁን ላይ ወደ ተግባር ያሸጋገሩት ቢዝነስ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ እንደሆነ የሚጠቅሱት ዘመናዊ የጤፍ ዱቄትና የእንጀራ ማምረቻ ፋብሪካቸውን ነው፡፡

ቃሊቲ አካባቢ የኢትዮጵያ ቆርኪ ፋብሪካ ፊት ለፊት በሚገኘው ይዞታቸው ላይ የተተከለው የጤፍ ዱቄት ማምረቻ ማሽን፣ ዛሬ ላይ ለአገልግሎት ይብቃ እንጂ የዚህ ቢዝነስ ውጥን የተጠነሰሰው ከአሥር ዓመት በፊት እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በተለምዶ ለዘመናት ያገለገለውን የድንጋይ ወፍጮ እንደሚተካ የሚጠበቀው አዲሱ መፍጫ ዕውን ለማድረግ፣ ላለፉት አሥር ዓመታት ጤፍ ብቻ ሊፈጩ የሚችሉ ዘመናዊ የጤፍ ማሽኖችን ለማሠራት ወደ ቻይና በተደጋጋሚ መመላለስ ነበረባቸው፡፡

ማሽኑን ለመፈብረክ የሚያስችላቸውን ዲዛይን በመንደፍ ደፋ ቀና ሲሉ የከረሙ የቻይና ባለሙያዎች፣ በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ዲዛይን ንድፍ ከመሥራት ጀምሮ ማሽኑን ከሚያመርተው የቻይና ኩባንያ ጋር በመዋዋል በርካታ ሙከራዎች ከተደረጉ በኋላ ቢግባል የተባለ የቻይና ኩባንያ መሐንዲሶች የኢትዮጵያ ጤፍ በሚፈለገው ደረጃ ፈጭቶ ማውጣት የሚችል ማሽን ሠርተው በማስረከባቸው የሙከራ ሥራ ተካሂዶ ውጤታማነቱ መረጋገጡን ወ/ሮ ሙና አብራርተዋል፡፡

ከወ/ሮ ሙና ጋር በሽርክና የሚሠሩት ወንድማቸው አቶ ኤልያስ ወይብም ይህንን ሥራ ወደ ተግባር ለመለወጥ በርካታ ውጣ ውረዶች ታልፈው ወደ ተግባር ለማሸጋገር እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡ ጤፍን ከወፍጮ ቤት ባሻገር በዘመናዊ ማሽን አማካይነት ማስፈጨት የቻለበት ማሽን፣ በቀን 600 ኩንታል ጤፍ የመፍጨት አቅም አለው፡፡

የጤፍ ዱቄት ማምረቻ ፋብሪካ ንፁህ የጤፍ ዱቄት ገበያ ላይ እንደ ልብ እንዲገኝ ከማስቻሉም በተጨማሪ፣ በተለያዩ መጠኖች ታሽጎ በሱፐር ማርኬቶች ጭምር በቀላሉ ለገበያ ለማቅረብ የሚቻልበትን አሠራር አምጥቷል፡፡ ዱቄት ዋጋውን ተመጣጣኝ ለማድረግም ጤፍ በቀጥታ ከአምራቾች በመግዛት ያመርቃል፡፡ ጤፍ ወይም ደላላ ሳይገባበት በቀጥታ ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር በመደራደር የመረከብ ዕቅድ በመያዝ፣ የአቅርቦት ችግር እንዳይኖር፣ ዋጋውም እንዳይንር ለማድረግ እንደሚጥሩ አስታውቀዋል፡፡ የተፈጨ የጤፍ ዱቄት ዋጋ በዚህ አግባብ ተመጣጣኝ ይሆናል ብለዋል፡፡

ማሽኑ ጤፉን ከማበጠርና ከማንፈስ ጀምሮ የተለያዩ መጠን ባላቸው ወንፊቶች ውስጥ እየተንዘረዘረ በማለፍ የጥራት ደረጃዎችን በማለፍ ለመጨረሻው ደረጃ ሲበቃ የሚፈጭ ሲሆን፣ በተለያየ መጠን ዱቄቱን አሽጎ የሚያመጣ ማሽንም ከመፍጫው ጋር አብሮ የሚሠራ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ተያያዥ በሆነው ሒደት የሚወጣው ንጹህ ጤፍ፣ በቀላሉ በሱፐር ማርኬት መደርደያ እንደልብ የሚገኝበትን ሒደት የሚያቀላጥፍ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ከሁሉም በላይ በቤት ውስጥ በተለይ በሴቶች ላይ የሚታየውን አድካሚ የማዕድ ቤት ሥራ በማቃለል ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የሚታመንበት ይህ የአመራረት ሥርዓት፣ ደንበኞች የፈለጉትን ዓይነት የጤፍ ዱቄት እንደምርጫቸው ለማግኘት እንደሚያስችልም ወ/ሮ ሙና አስረድተዋል፡፡

የእነ ወ/ሮ ሙና ውጥን ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከጤፍ መፍጫው ማሽን ጎን ለጎን ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ ማሽን በመትከል ላይ ናቸው፡፡ ይህኛውም ማሽን በተመሳሳይ መንገድ ዲዛይኑ ተዘጋጅቶ ለቻይናውያን በመስጠት የተሠራ ነው፡፡ ማሽኑ እንጀራ ለመጋገር የሚያስችሉትን ግብዓቶችና ቅድመ ዝግጅቶች አጠቃለው የያዙ መሣሪያዎች ያሉት እንደሆነ ከእነ ወ/ሮ ሙና ገለጻ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሰዓት 500 እንጀራ የሚጋግረው ማሽን፣ በትኩሱ የወጣውን እንጀራ በማቀዝቀዝ ለአያያዝ በሚያመች አስተሻሸግ ጠቅልሎ ያወጣል፡፡ በዚህ ማሽን የሚጋገረው ግን የጤፍ እንጀራ ብቻ አይደለም፡፡ ከሌሎች ሰብሎች የሚዘጋጅ የእንጀራ ዓይነትም ይጋገርበታል ተብሏል፡፡ ለምሳሌ የዘንጋዳ እንጀራ ከሚጋገሩት ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ ጤፍን ከስንዴና ከሌሎች ሰብሎች ጋር በመቀላቀል በተፈጨ ዱቄት የሚዘጋጅ እንጀራም ይኖራል፡፡

ይህ ሲደረግ እያንዳንዱ እንጀራ ከምን እንደተዘጋጀ የሚገልጽ ዝርዝር የምርት መረጃና መግለጫ በማሸጊያው ላይ ስሚኖር፣ ተጠቃሚው የሚመርጠውን የእንጀራ ዓይነት በመግዛት የመጠቀም ዕድል ይኖረዋል ተብሏል፡፡ የእንጀራ ማምረቻው ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡ በሁለቱም ማምረቻዎች ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ዱቄትና እንጀራም ይመረትበታል፡፡

እነዚህን ዘመናዊ ማሽኖች በማስፈብረክ ሥራ ለማስጀመር ረጅም ጊዜ ከመውሰዱ አንፃር ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ለዚህ ሥራ ተብሎ የወጣው ወጪ ምን ያህል ነው ለሚለው ጥያቄ በተጨባጭ ለመናገር የሚያስችል አሐዝ ይህ ነው ተብሎ በተጨባጭ ባይጠቀስም በግምት ግን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሥራ እንደሆነ ባለቤቶቹ ገልጸዋል፡፡

 

Standard (Image)

የጃፓን ኩባንያ 30 የሚደርሱ ኩባንያዎች የሚገቡበትን ልዩ የማምረቻ ዞን ለመገንባት ስምምነት ፈረመ

$
0
0

 

ቶሞኒየስ የተባለው የጃፓን ኩባንያ በቦሌ ለሚ ምዕራፍ ሁለት እየተገነባ በሚገኘው የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በ31 ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍና ከ20 እስከ 30 ለሚገመቱ የጃፓን አምራቾች የሚውል ልዩ የማምረቻ ዞን ለመገንባት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ኩንባያው ሰኔ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት በ186 ሔክታር መሬት ላይ እየተገነባ በሚገኘው የቦሌ ለሚ ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገቡ የጃፓን ኩባንያዎችን የሚጠቀሙባቸውን የማምረቻ ሼዶች በራሱ ዲዛይንና በራሱ ወጪ እንደሚገነባ ይፋ አድርጓል፡፡

የቶሞኒየስ ኩባንያ ዳይሬክተር ሒሮሺ ኦትሱቦ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው እስከ 30 የሚደርሱ በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳና በተዛማጅ ምርቶች የሚሰማሩ ኩባንያዎች እንደሚመጡ በማሰብ የመግባቢያ ስምምነቱን በመፈረም ግንባታ ለማካሔድ ታቅዷል፡፡ የቶሞኒየስ እህት ኩባንያ የሆነው የካምቦዲያው ፕኖም ፔን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚና የቦሌ ለሚ ሁለት የጃፓን ልዩ ዞን ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሒሮሺ ኡይማትሱ እንደተናገሩት፣ ኩባንያው የመሬት ሊዝ ስምምነቶችን ከመንግሥት ጋር ከተፈራረመና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ካጠናቀቀ በኋላ በመጪው ዓመት ወደ ግንባታ የመግባት ዕቅድ ይዟል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የምትገኝበትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ሒደት እንዲሁም እየተስፋፋ የመጣውን የጨርቃጨርቅ ዘርፍ ከካምቦዲያና ከታይላንድ ጋር በማነፃፀር ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሁኔታ ከዛሬ አሥር ዓመታት በፊት ካምቦዲያ ውስጥ ይታይ የነበረው ዓይነት ነው ያሉት ኡይማትሱ፣ ከ30 ዓመታት በፊትም ታይላድ በተመሳሳይ የለውጥ ሒደት ውስጥ ለማለፍ ዛሬ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ዓይነት እንቅስቃሴ ስታደርግ መቆየቷን አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ምቹ ካሏቸው ነገሮች መካከል የሕዝብ ብዛቱ አንደኛው ጥሩ አጋጣሚ ሲሆን ይህም ሰፊ የአገር ውስጥ ገበያን በመፍጠር አገሪቱን ለአምራቾች ተመራጭ እንድትሆን ያደርጋታል ማለታቸው አንዱ ሲሆን፣ በቀላሉ መሠልጠን የሚችሉና ለፋብሪካ ሥራ ቀልጣፋ የሆኑ በርካታ ወጣቶች የሚገኙባት አገር መሆኗ፣ ለሠራተኞች የሚከፈለው ዝቅተኛ የክፍያ መጠን፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠየቀው ዝቅተኛ የአገልግሎት ታሪፍ ከተጠቀሱት አገሮችም ይልቅ ኢትዮጵያን ተመራጭ እንደሚያደርጋት ይናገራሉ፡፡

ይሁንና በኢትዮጵያ የሚታየው የሕግ አተገባበር፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የአገልግሎት መቆራረጥ በተለይም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ እንደ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መሥሪያ ቤት፣ ወዘተ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በውጭ ኢንቨስተሮች ሲነሱ ከሚደመጡ የቢሮክራሲ ችግሮች መደብ ውስጥ ይካተታሉ፡፡ ቪዛና የሥራ ፈቃድ በቀላሉ የማግኘት ጉዳይ በርካቶችን ሲያሳስባቸው እንደመቆየቱ መጠን መንግሥት እልባት ማበጀቱን ደጋግሞ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመዘርጋት ሁሉም መሥሪያ ቤቶች አገልግሎቶቻቸውን ለአምራቾች እንዲያቀርቡ በመደረጉ የተንዛዛ አሠራር ችግር እንደማይፈጠር የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ አስታውቀዋል፡፡

የጃፓን ኩባንያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት በርካታ ድርድሮች ሲካሔዱ መቆየታቸውን የጠቀሱት አቶ ፍፁም፣ በአሁኑ ወቅት የቶሞኒየስ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ትልቅ እመርታ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አፍሪካ እንደ ጃፓን ያሉ በአደጉ አገሮችን ለማስተናገድ ገና ብዙ ይቀረዋል ብለው ያምናሉ ያሉት አቶ ፍፁም ይህ አመለካከታቸው እየተቀየረ በመምጣቱ ቁጥራቸው እየተበራከቱ የሚመጡ ኢንቨስተሮች እንደሚጠበቁም ጠቅሰዋል፡፡

በአቶ ፍፁም አነጋገር የሚስማሙት ኡይማትሱ፣ አሁንም ድረስ ጃፓናውያን ለአፍሪካ ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ መሆኑን አልሸሸጉም፡፡ በርካቶች አፍሪካን የሚያዩበት ዓይን በዱር እንስሳት የተሞላ፣ መሠረተ ልማቶች ያልተሟሉት ሥፍራ እንደሆነና በድርቅና በረሃብ ቸነፈሮች ዘወትር የሚጠቃ አኅጉር እንደሆነ ማሰባቸው ዛሬም ድረስ ያልተቀረፈ እንደሆነ በመጥቀስ እንዲህ ያለው አመለካከት ቀስ በቀስ እየተለወጠ ሲመጣ የጃፓን ኩባንያዎች በብዛት ሊመጡ እንደሚችሉ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

በሌላ በኩል በጃፓን መንግሥት በሚደረግ የቴክኒክ ድጋፍ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ምክክር መድረክ ሲካሔድ ቆይቷል፡፡ በዚህ መድረክ የሚነሱ የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች፣ የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎች አወጣጥና አተገባበር፣ በተግባር ሒደት የታዩ ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳቦችም እየተነሱ ለመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ምክረ ሐሳቦች ሲቀርቡበት የቆየ መድረክ ነው፡፡

በዚህ መድረክ የሚሳተፉ የጃፓን ምሁራን አሁንም በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ያብራራሉ፡፡ መንግሥት በቅርቡ ኢንተርኔት መዝጋቱ፣ ሕጎችን በየጊዜው መለዋወጡ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁና ማራዘሙ፣ የፖለቲካ ቀውስ መከሰቱ ለአገሪቱ የውጭ ኢንቨስትመንት በተለይም እንደ ጃፓን ካሉ አገሮች ለሚመጣ ኢንቨስትመንት ጥቁር ጥላ እንደሚያጠላበት ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምሁራን ገልጸዋል፡፡ 

ይህም ሆኖ ከስምምነቱ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የንግድ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቁትን እነ ሚትሱቢሺ፣ ቶሺባ ኮርፖሬሽን፣ ማሩቤኒ የተባሉትን ጨምሮ 20 የጃፓን ኩባንያዎችን የወከሉ የንግድ ልዑካን በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትን መጎብኘታቸው ታውቋል፡፡

በአንፃሩ ሰሞኑን በተከታታይ ይፋ የተደረጉ የዓለም ባንክ፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባዔ ሪፖርቶች አገሪቱን በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት መሰላል ላይ ተንጠላጥለው ከሚገኙ አገሮች ተርታ በቁንጮነት ከማስቀመጥ በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ካስመዘገቡ አምስት ዋና ዋና አገሮች አንዷ መሆኗን፣ ከቬትናም በመቀጠልም በዓለም ሁለተኛዋ የጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች የሚገኙባት አገር ለመሆን እንደበቃችም በሪፖርቶቻቸው አመላክተዋል፡፡

 

 

Standard (Image)

ምርት ገበያና መጋዘን አገልግሎት በሰኔ ወር መጨረሻ ዳግም ይዋሀዳሉ

$
0
0

 

  • የቡና ግብይት ሥርዓት ማሻሻያ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገለጸ

ቡና ነጋዴዎች በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ በነበረው ቅሬታ መሠረት እንዲሁም በተለያዩ የአሠራር ችግሮች ሳቢያ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለሁለት እንዲከፈል መደረጉ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች መጋዘን አገልግሎት ድርጅት የተባለ መንግሥታዊ ተቋም ተመሥርቶ አገልግሎት ሲሰጥ ቆቷል፡፡ ይሁንና ተቋማት ለሁለት የከፈለው አሠራር ለሁለት ዓመታት ያህል ከተጓዘ በኋላ ከምርት ገበያው ጋር መልሶ እንዲዋሀድ፤ የሁለቱ ተቋማት ውህደትም በዚህ ወር መጨረሻ ዕውን እንዲሆን መወሰኑን ምርት ገበያው ይፋ አድርጓል፡፡

በአጭር በተቀጨው አሠራር ማዕቀፍ ውስጥ በአገሪቱ የግብርና ምርቶችን የወጪ ንግድ በማቀላጠፍ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዲገኝ ለማስቻል ተስፋ ተጥሎበት የተመሠረተው የግብርና ምርቶች መጋዘን አገልግሎት ድርጅት፣ በአንድ ቢሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታልና በሩብ ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል መመሥረቱ ይታወሳል፡፡ በዚሁ መሠረትም አብዛኛውን የምርት ገበያውን የሰው ኃይል በመጠቅለል ጭምር ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ምርት ገበያው ከነበሩት 750 ሠራተኞች ውስጥ 600 ለአዲሱ ድርጅት መመደባቸው ይታወሳል፡፡

የግብርና ምርቶች መጋዘን አገልግሎት ድርጅት ምርቶችን በማዕከል የማከማቸት አገልግሎት ለምርት ገበያውና ለላኪዎች ከመስጠት ባሻገር፣ የጥራት ደረጃ የማውጣት አገልግሎትም በዚሁ መጋዘን አገልግሎት ድርጅት እንዲሰጥ ተደርጎ ቆይቷል፡፡

የመጋዘን አገልግሎቱ ከምርት ገበያው መለየት እንዳለበት በጥናት ከጠቆሙት መካከል ለምርት ገበያው የአሥር ዓመት የፍኖተ ካርታ ጥናት በማጥናት አስተዳደራዊም ሆነ የኦፕሬሽን እንቅስቃሴው ምን መምሰል እንዳለበት እንዲሁም ላለፉት ዓመታት የተጓዘባቸውን ሒደቶች የገመገሙ አጥኚዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡

የመጋዘን አገልግሎቱ የተጠበቀውን ውጤት ሊያስገኝ ባለመቻሉ ግን በሚኒስሮች ምክር ቤት የተቋቋመበት ደንብ ተሽሮ በምትኩ የዳግም ውህደታቸው ሕግ መርቀቁንና ይህም ፀድቆ ወደ ተግባር መገባቱን ምርት ገበያው አስታውቋል፡፡

ይህ ዕርምጃ ከተወሰደባቸው ምክንያቶች አንዱ የቡና ግብይት አሠራርን ለማሻሻል ሲባል እንደሆነም ታውቋል፡፡ ምርት ገበያው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የቡና ልማትና ግብይት ላይ የሚታዩን ለዘመናት ሥር የሰደዱ ማነቆዎችን ለማስወገድ እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል ዘመናዊ የቡና ግብይት ተደራሽነትን ማስፋፋት አንዱ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግም የምርት ባለቤትነትንና የቡና መገኛ ሥፍራን ገላጭ የሆነ የመኪና ላይ የቡና ግብይት ማካሔድ፣ አቅራቢዎች፣ ሻጮችና ገዥዎች ያለአገናኝ መገበያየት የሚችሉት መንገድን ለመፍጠር እንዲረዳም ምርት ገበያው ገልጿል፡፡

እነዚህን ለውጦች በተግባር ለማዋል ዝግጅት መጠናቀቁን የገለጸው ምርት ገበያ፣ አዳዲስ የግብይት ሞዴሎች መዘጋጀታቸውንና እነዚህን ሞዴሎች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አስደግፎ ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችል የአጠቃቀም ማሻሻያዎች መደረጋቸው ተጠቅሷል፡፡

በቡና ጀምሮ ሰሊጥ፣ ቦሎቄ፣ ስንዴ፣ ማሾና ሌሎችም የቅባትና የሰብል ምርቶችን የሚገበያየው ምርት ገበያ ድርጅት ከዘጠኝ ዓመት በፊት ሲመሠረት የግብይቱ ዘይቤ በጩኸት የሚከናወን ነበር፡፡ ገዥና ሻጭ ፊት ለፊት ቀርበው፣ ሻጭ የሚሸጥበትን ዋጋ ገዢም የሚገዛበትን መጠን ከፍ ባለ ድምጽ በማስተጋባት፣ በዋጋ ከተስማሙ በመጨባበጥ ግብይቱን ያፀኑ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህንን የሚቀይር፣ በኮምፒዩተር የታገዘ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ዘዴ መተግበር ጀምሯል፡፡፡ በዚህም ከአዲስ አበባ ባሻገር በክልል ከተሞች የተስፋፋው የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሥርዓቱ በጩኸት ሲደረግ የነበረውን ግብይት ሙሉ ለሙሉ ሊተካው ጫፍ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

Standard (Image)

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 30 ሚሊዮን ዶላር የሚጠይቅ የፍሳሽ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊደረግ ነው

$
0
0

 

አርቪንድ ኤንቪሶል የተባለውና የአርቪንድ ጨርቃ ጨርቅ አምራች ሥር የሚተዳደረው የህንድ ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ በሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ከፓርኮቹ ውጪ ለሚገኙ ፋብሪካዎች የውኃ ማጣሪያና የመልሶ መጠቀም ቴክኖሎጂዎችን መሠረተ ልማት አውታሮች ለመዘርጋት ከመንግሥት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ፈረመ፡፡

የአርቪንድ ሊሚትድ ኩባንያ አካል ኦርቪንድ ኤንቪሶል፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተፈራረመው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት፣ የፋብሪካዎችን ፍሳሾች ከመልቀቃቸው በፊት በማጣራት መልሶ መጠቀም የሚያስችል ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር አካባቢ እንዳይበከል የሚያስችል አሠራር እንደሚተገብር ይጠበቃል፡፡ ስምምነቱ ማክሰኞ፣ ሰኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ምርት በይፋ በተጀመረበት በሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ተፈርሟል፡፡ ስምምነቱን የኢትዮጵያ መንግሥት በመወከል በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ፣ የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ ገመቹና የአርቪንድ ሊሚትድ ቦርድ ሊቀመንበር እንዲሁም ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሳንጄይ ላልብሃል ናቸው፡፡

አርቪንድ ኤንቪሶል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተፈራረመውን ስምምነት በማስመልከት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ በካይ ፍሳሾችን አጣርቶ መልሶ የመጠቀምና አካባቢ እንዳይበከል የሚጠቀምበት ምንም ዓይነት በካይ ፈሳሽ በማምረቻ ቦታ እንዳይለቀቅ የሚከላከል፣ ‹‹Zero Liquid Discharge Solution›› የሚል መጠሪያ ያለው ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ይህ ቴክሎጂ በቀን 11 ሚሊዮን ሊትር የፋብሪካ ፍሳሽ የማጣራት  አቅም እንዳለው ተጠቅሷል፡፡

ኩባንያው ከዚህ ስምምነት በፊትም በኢትዮጵያ ለጨርቃጨርቅና አልባሳት ማምረቻነት በተከለለው ግዙፉ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ይህንን ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ በማዋል የገነባው ማምረቻ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ ታውቋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ማምረቻዎች የሚያመነጯቸውን በካይ ፍሳሾች በመቀበል፣ በዘመናዊ አሠራር በማጣራት እንዲሁም ከተጣራው ውኃ ውስጥ 90 በመቶውን መልሶ ለማምረቻዎቹ ጥቅም እንደሚውል ተገልጿል፡፡

ፍሳሽ ለማጣራት በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ የተተከለው ማጣሪያና ከዚሁ አገልግሎት ጋር ለተያያዙ መሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ በጠቅላላው ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኩባንያው በሌሎች ግንባታቸው እየተካሔደ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚተገብር ሲሆን፣ ይህም ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚያከናውኗቸው የምርት ሥራዎች ከብክለት ነፃ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

የህንዱ ኩባንያ ከዋናው የጨርቃጨርቅ ማምረት ሥራው በተጓዳኝ፣ በፓርኮቹ ውስጥ የሚካሔዱ የምርት ተግባራት በኅብረተሰቡና በአካባቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይፈጥሩ የውኃ ማከምና የንፁህ ውኃ አጠቃቀም ቴክኖሎጂዎችን ይተገብራል፡፡ በመሆኑም ወደ አካባቢ የሚለቀቁ ፍሳሾች ጤንነታቸውና ንፅህናቸው ተረጋግጦ እንደሚሆን መንግሥት ከኩባንያው ጋር ባደረገው ስምምነት ቃል ገብቷል፡፡

አርቪንድ ኤንቪሶል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ይህንን የውኃ ማጣራትና መልሶ መጠቀም ቴክኖሎጂን ለሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ከፓርኩ ውጪ ለሚገኙ ፋብሪካዎች በሚመች መልኩ መጠቀም እንዲቻል ነው፡፡

አርቪንድ ኤንቪሶል፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ይህንን የፍሳሽ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ ሌሎችም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ብሎም ከፓርኩ ውጪ የሚገኙ ፋብሪካዎች እንዲጠቀሙበት በማሰብ መግባቢያ ስምምነት ለመፈረም መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ ኩባንያው ከመንግሥት ጋር በመተባበር በአካባቢ ጥበቃና በመሰል ጉዳዮች ላይ ጥናት በማካሄድና ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር በማቀናጀት፣ አካባቢ ተኮር ትምህርቶችን ለመሥጠት እንዲቻል የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ በኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ለማካተት እንደሚሠራ በስምምነት ሰነዱ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ ይህንን ውጥን በተግባር መለወጥ ከቻለም በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ለሚያከናውናቸው ተመሳሳይ ሥራዎች ዋቢ እንደሚሆነው ኩባንያው ይጠቀሳል፡፡

አርቪንድ ኤንቪሶል በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚተገብረው የZero Liquid Discharge ቴክኖሎጂን በመጠቀም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉ አገሮች ደረጃ ሊያሠልፋት እንደሚችል ተገልጿል፡፡ ኢንዱስትሪ ፓርኩም ከአካባቢ ጥበቃና ከአረንጓዴ ልማት ተግባራት ጎን ለጎን፣ ይህንን የፍሳሽ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ ሥርዓት መተግበሩ ብቸኛው ተቋም እንደሚያደርገው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ 13 ትላልቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፡ የቻይኖቹን ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ጨምሮ የቦሌ ለሚና አሁን የመጣው የሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስምና ዝና ያተረፉ ኩባንያዎችን ትኩረት ከመሳብ ባሻገር ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ እንዲሠሩ መደላድሉን እንደፈጠሩ ይታመናል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ በማምረቻ መሣሪያዎች፣ በመድኃኒት ምርት እንዲሁም በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ የተሰማሩት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

አርቪንድ ኤንቪሶል በዓለም አቀፍ ደረጃ በውኃ ማኔጅመንት መስክ የውኃ ማከም፣ የማጣራትና የኢንዱስትሪ ፍሳሽን መልሶ ለመጠቀም በሚያስችሉ አማራጭ መፍትሔዎች ላይ በመሥራት የአካባቢ ብክለት እንዳይፈጠር የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን የሚተገብር ኩባንያ ነው፡፡ አርቪንድ ኤንቪሶል ከዓለም አቀፍ ታላላቅ ኢንዱስትሪዎች ጋር በመሥራት ልምድና ተቀባይነት እንዳለው የኩባንያው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አርቨንድ ሊሚትድ በህንድ ከሚገኙ የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን፣ ይኼው ኩባንያ በሐዋሳ ፓርክ ውስጥ በጨርቃጨርቅ አምራችነት ገብቷል፡፡ አርቪንድ በህንድና በኢትዮጵያ ሰባት ደረጃቸውን የጠበቁ ፋብሪካዎች ሲኖሩት፣ እነዚህም ወቅቱን የጠበቁ ዘመናዊ አልባሳትና የፋሽን ውጤቶችን በማምረት ለዓለም ገበያ ያቀርባሉ፡፡ አርቪንድ ሊሚትድ በዓለም ደረጃ የሚታወቅባቸውን ምርቶች ከሚገዙ ደንበኞች መካከል ማርክስና ስፔንሰር፣ ሌቪስ፣ ጄሲ ፔኒ፣ ኤች ኤንድ ኤም፣ ጋፕ፣ ዛራ፣ ባናና ሪፐብሊክ ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡

አርቪንድ ከፍሳሽ ማጣራት ሥራ ባሻገር በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የ13.5 ሔክታር ስፋት ያለው ቦታ በመያዝ፣ ሰባት የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን ለማምረቻነት እያዘጋጀ ይገኛል፡፡ የሐዋሳ ማምረቻዎቹ በምርት ቅድመ ዝግጅት ላይ ሲሆኑ፣ አዲስ አበባ በሚገኘው የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ባሉት ሁለት የማምረቻ ፋብሪካዎችም እስካሁን 8.3 ሚሊዮን የሚደርሱ የአልባሳት ውጤቶችን፣ ማለትም ጂንስ፣ ሸሚዝ፣ እንዲሁም የሙሉ ልብስ ምርቶችን ወደ አውሮፓና አሜሪካ በመላክ ለገበያ አቅርቧል፡፡

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙት የአርቪንድ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ሥራ ሲጀምሩ ለ10,000 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሏል፡፡ ከእነዚህ ፋብሪካዎች 14 ሚሊዮን የአልባሳት ምርቶችን ለገበያ ለማቅረብ የታቀደ ሲሆን፣ ጠቅላላ የምርት ውጤቶቹም ሙሉ በሙሉ ለውጭ ገበያ እንደሚውሉ ይጠበቃል፡፡  ከአርቪንድ ሊሚትድ ባሻገር በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እስካሁን 16 የውጭ ፋብሪካዎች ሙሉ ለሙሉ ሥራ መጀመራቸው ሲታወቅ፣ እስካሁን ከስድስት በላይ ኩባንያዎች ልዩ ልዩ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ውጤቶችን ለውጭ ገበያ እንዳቀረቡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

 

Standard (Image)

ሐኮማል ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ያወጣባቸውን 80 አፓርታማዎች ግንባታ አጠናቀቀ

$
0
0

 

በሪል ስቴት ዘርፍ ስድስት ዓመታት ያስቆጠረው ሐበሻ ኮንስትራክሽን ማቴሪያልስ ልማት አክሲዮን ማኅበር (ሐኮማል)፣ በአዲስ አበባ ከተማ በአሥር ቦታዎች ከ1,500 በላይ የሚሆኑ የመኖሪያ ቤቶችና የንግድ ሱቆች ግንባታ እያካሄደ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል በካራ አሎ የሚገኘውንና ከሰንሴት ሆምስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር የገነባቸውን 80 የመኖሪያ ቤቶችን የያዙ ስምንት ባለአራት ፎቅ አፓርትመንቶችን አጠናቅቆ አስመርቋል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ የሚያከናውናቸውን ግንባታዎች በጊዜ አጠናቆ ማስረከብ ቢቸግረውም፣ ከያዛቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ ለኩባንያው የመጀመርያ የሆኑትን የ80 ቤቶች ግንባታ ከስድስት ዓመታት በኋላ በማጠናቀቅ ቅዳሜ፣ ሰኔ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሔደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ወቅት እንደተጠቀሰው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለማስረከብ የሚችልበት አቅም ፈጥሯል፡፡

የሐኮማል ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ኃይሉ እንደገለጹት፣ የሰንሴት ሆምስ የቤቶች ግንባታ ከአሥሩ የኩባንያው ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ቤቶች አጠቃላይ ወጪያቸው ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን የሰንሴት ሆምስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አበባው አበዛ ከስምንት ባለአራት ፎቅ አፓርትመንቶች ውስጥ ከሚገኙት 80ዎቹ የመኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ በሰንሴት ፕሮጀክት ሥር ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ 15 መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ አበባው ገለጻ፣ የእነዚህ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በአምስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለቤት ገዥዎቹ እንደሚተላለፉ ይጠበቃል፡፡

በመሆኑም በሐኮማልና በሰንሴት ኩባንያዎች አማካይነት ተገንብተው የተጠናቀቁት 80ዎቹ መኖሪያ ቤቶችና ቀሪዎቹን 15 መኖሪያ ቤቶችን በማጠቃለል ለግንባታ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሊጠይቅ እንደሚችል ከኃላፊዎቹ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የሐኮማል ሥራ አስኪያጅ እንደገለጹትም፣ በዕለቱ ከተመረቁት 80 መኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ 500 መኖሪያ ቤቶችን በቅርቡ ለማስረከብ ዕቅድ ይዟል፡፡

ሐኮማል እየገነባቸው ያሉትን የመኖሪያ ቤቶችና መደብሮችን በፈለገው ፍጥነት አጠናቅቆ ለማስረከብ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመውት እንደነበር አቶ ጌትነት ባደረጉት ንግግር ጠቅሰዋል፡፡ ለግንባታዎቹ መዘግየት የተለያዩ ምክንያቶችንም አቅርበዋል፡፡

ሐኮማል በሪል ስቴት ዘርፍ ተሳታፊ እንደመሆኑ መጠን የመሬት አቅርቦት ዋነኛው ግብዓት ነው ያሉት አቶ ጌትነት፣ ሆኖም አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የመሬት ፖሊሲ ከኩባንያቸው አቅምና ፍላጎት ጋር የሚጣጣም ሆኖ አለመገኘት አንዱ ችግር ነው፡፡ ይህ በመሆኑም፣ በመካከለኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ኩባንያው ይዞት የተነሳውን ዕቅድ እየተፈታተነው እንደመጣ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ለሪል ስቴት ልማቱ ማነቆ እንደሆነ የተገለጸው ሌላው ጉዳይ የፋይናንስ አቅም ውሱንነት ነው፡፡ የትኛውም የንግዱ እንቅስቃሴ ያለ ፋይናንስ አቅርቦት ግቡን ሊመታ እንደማይችል የጠቀሱት አቶ ጌትነት፣ የሪል ስቴት ዘርፉ በተለይ ግዙፍ የካፒታል አቅም የሚጠይቅ ቢሆንም በዘርፉ ለሚደረግ የሥራ እንቅስቃሴ ብድር ማግኘት እንዳልተቻለ አስታውቀዋል፡፡

ከመንግሥትም ሆነ ከግል የፋይናንስ ተቋማት ብድር ማግኘት ባለመቻሉ ሐኮማል የቤቶቹን ግንባታ ባቀደው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለማጠናቀቅ ችግር እንደፈጠረበት አቶ ጌትነት ተናግረዋል፡፡ በግንባታው ውስጥ ሌላው ተፅዕኖ እንደፈጠረ የተገለጸው ጉዳይ፣ በቤቶቹ ግንባታ መጀመርያ ወቅት የተከሰቱ የግብዓት ዕቃዎች እጥረትና የዋጋ ንረት ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህም የግንባታ ሥራዎችን ለማዘግየትና የግንባታ ማጠናቀቂያ ዋጋ ለማናር መንስዔ እንደሆኑ የአቶ ጌትነት ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

መሬት በሊዝ ገዝቶ ለመገንባት የሊዝ ዋጋ መወደድ፣ የግንባታ ሥራዎች ፋይናንስ ለማድረግም ከባንክ ብድር የማግኘት ችግር ግንባታዎቹን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የነበረው ውጥን እንዲይሳካ እንቅፋት እንደፈጠረበት ኩባንያው ከዚህ ቀደም መግለጹ አይዘነጋም፡፡ መሬት በሊዝ ገዝቶ የመገንባት ውጥኑ ባለመሳካቱ የግንባታ አካሄዱን እንዲቀይር አስገድዶታል፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁን ወቅት የሚያካሂዳቸው ግንባታዎች የሚከናወኑበት በጋራ ልማት መሠረት ሲሆን፣ ቦታ ካላቸው ግለሰቦችና ተቋማት ጋር በመሆን በጋራ የመገንባት ሥራ ውስጥ እንዲገባ አስገድዶታል፡፡ የሰንሴት ፕሮጀክትም በዚህ መንገድ የተገነባ ነው፡፡

በሰንሴት የቤቶች ምረቃ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታሁን ጫላ፣ ሐኮማል አጋጥመውኛል ላላቸው የመሬት አቅርቦትና ሌሎችም ችግሮች በቀጥታ ምላሽ ባይሰጡም፣ አስተዳደሩ እንዲህ ላሉ አልሚዎች ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡ የቤት ልማት ፈታኝ ቢሆንም፣ ሐኮማል ፈተናዎቹን አልፎ ለቤት ገንቢዎች ቤታቸውን ለማስተላለፍ መብቃቱን ግን አድንቀዋል፡፡

      

Standard (Image)

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 60 በመቶ ቡና አብቃይ አካባቢዎች ከአምራችነት ውጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመራማሪዎች ይፋ አደረጉ

$
0
0

 

  • ሐረር ከነጭራሹ ቡና ማብቀል ልታቆም እንድምትችል ተንብየዋል

የእንግሊዝ ተመራማሪዎች ከኢትዮጵያውያን አቻዎቻቸው ጋር ሆነው ባጠኑት መሠረት፣ እስከ 60 በመቶ የሚገመተው የኢትዮጵያ ቡና አብቃይ አካባቢ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለቡና አብቃይነት ያለውን ተስማሚነት ሊያጣ እንደሚችል ይፋ ከማድረጋቸውም በላይ በቡና ላይ ሊመጣ የሚችለው አስከፊ የጣዕም ለውጥም አገሪቱን እንደሚጎዳት በጥናታቸው ይፋ አደረጉ፡፡

ኢትዮጵያውያን ምሁራን የተሳተፉበትና የእንግሊዙ ሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ፣ ኪው የተባለው ተቋም ለንባብ ያበቁትና ‹‹ሬዚሊየንስ ፖቴንሺያል ኦፍ ዚ ኢትዮጵያን ኮፊ ሴክተር አንደር ክላይሜት ቼንጅ፤›› በሚል ርዕስ ይፋ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳው፣ በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የሙቀት መጠን ለቡና ማሳዎች ህልውና ሥጋት እየሆነ በመምጣቱ የአራት በመቶ ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት ጭማሪ ታሳቢ በማድረግ ዋና ዋና የቡና አብቃይ የሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የቡና አብቃይነታቸው በአስጊ ደረጃ እየቀነሰ እንደሚሔድ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት ከ39 እስከ 59 በመቶ ድረስ የሚገመቱ 16ቱ ዋና ዋና የኢትዮጵያ ቡና አምራች አካባቢዎች ቡና አብቃይነታቸው ሊቀንስ ብሎም ሊጠፋ እንደሚችል በጥናት አሳይተዋል፡፡ በመሆኑም ቡና አብቃይ በሆኑ ወይናደጋና ጫካ ገብ አካባቢዎች ላይ ተገቢው የሙቀት መጨመርን ሊከላከሉ የሚችሉ ዕርምጃዎች ካልተወሰዱ የቡና ምርት ወደፊት፣ ምናልባትም የተያዘው ክፍለ ዘመን ከመገባደዱ ቀድሞ የኢትዮጵያ ታላቅ የአራቢካ ቡና ዝርያ አምራችነት ሊያከትም እንደሚችል አጥኚዎቹ አስጠንቅቀዋል፡፡

ይሁንና በተገላቢጦሹ የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ላይ እያሳደረ የሚገኘውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከልና የቡና ምርትን ለመጨመር፣ ከዚህ ቀደም ቡና አምራች ወዳልነበሩ ሥፍራዎች ቡናን ማስፋፋት እስከ አራት እጅ የሚገመቱ ለቡና ምርት ተስማሚ አካባቢዎች እንዲፈጠሩ ለማድረግ እንደሚያግዝ ተጠቁሟል፡፡ ይህ የቡና አብቃይ አካባቢዎችን ከመሠረቱ የሚቀይር አካሔድ እንደሆነ የሚገልፁት አጥኚዎቹ፣ ለቡና በአብዛኛው ተስማሚ የሚባሉት ከፍተኛ ሥፍራዎች ሲሆኑ በእነዚህ አካባቢዎች የሚታየው የሙቀት መጠንም ዝቅተኛ እንደሚሆን ስለሚታመን ለቡና ምርት ተስማሚ እንደሚሆኑ ይታመናል ብለዋል፡፡ ቡና በባህሪው ቀዝቃዛ አካባቢ የሚፈልግ በመሆኑ እንዲህ ያሉ አካባቢዎች ተመራጭ ስለሆኑ የቡና እርሻዎችም ወደእነዚህ አካባቢዎች እንዲስፋፉ ይመከራል ብለዋል፡፡

ምንም እንኳ በሙቀት መጨመር ምክንያት የቡና ምርትና የአምራች አካባቢዎች ምርታማነት በየጊዜው እየቀነሰ እንደመጣ ከገበሬዎች የተገኙ ግብረ መልሶች እንዲሁም በመስክ ወደ እርሻ ማሳያዎች በመሔድ የተደረጉ ጥናቶች ማረጋገጣቸውን ጥናቱን በጋራ የመሩት፣ በሮያል ቦታኒክ ካርደንስ ተመራማሪ የሆኑት አሮን ዳቪስ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

ይሁንና የአየር ንብረት ለውጦች በቡና ላይ ያመጡት ለውጥ አዝጋሚ በሆነ ሒደት፣ በበርካታ አሥርታት ውስጥ የተከሰተ እንደሆነም ሚስተር ዳቪስ ያብራራሉ፡፡ ‹‹ይህ ጥናት ለበርካታ ዓመታት የተደረገ የምርምር ሥራ ውጤት ነው፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ ቡና ምርት ሒደት ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ በዝርዝር ለመረዳት ሞክረናል፡፡ እንዳረጋገጥነው ከሆነም እስካሁን ሲሠራበት በነበረው አኳኋን መቀጠል፣ በኢትዮጵያ የቡና ዘርፍ ላይ ለወደፊቱ ከባድ አደጋ እንደሚያስከትል ነው፡፡ በመሆኑም በመጪዎቹ ዓመታት ውስጥ ወቅታዊ፣ ተገቢና ሳይንስ ተኮር ውሳኔዎችን በማስተላለፍ የቡናውን ቀጣይነትና ለአየር ንብረት ለውጦች አይበገሬነት ማረጋገጥ የግድ ይላል፡፡››

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ዕፅዋት ሳይንቲስት የሆኑትና በጥናቱ ከተሳፉ ኢትዮጵያውያን አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው እንደገለጹት፣ ‹‹የአራቢካ ቡና በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች የሚበቅልና ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ስጦታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአራቢካ ቡና የጂን ብዝኃነት ተፈጥሯዊ መገኛ እንደመሆኗ መጠን፣ በኢትዮጵያ የሚከሰተው ማንኛውም ነገር ሁሉ ወደፊት በዓለም የቡና አምራቾች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለዋል፡፡

በዚህ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን በቡና ዘርፍ ላይ ያሳዩት ምሁራኑ፣ በሙቀት አማጪ ጋዞች አማካይነት በየጊዜው እየጨመረ በመጣው የዓለም የሙቀት መጨመር ሳቢያ ወደፊት ቡና አምራች የሆኑ አካባቢዎች እየተመናመኑ እንደሚመጡ ሥጋታቸው ሲገልጹ፣ ዋቢ ካደረጓቸው መካከል ሐረር ተጠቅሳለች፡፡ በዓለም የንግድ ምልክትና ስያሜቸው ከተረጋገጠላቸው ሦስቱ ዋና ዋና የልዩ ጣዕም ቡናዎች ማለትም የይርጋጨፌና የሲዳማ ቡናዎች ተርታ የሚመደበው የሐረር ቡና፣ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ በዚሁ መሠረት ለዓለም ገበያ ቀርቦ እየተሸጠ የሚገኝ ቡና ነው፡፡ 

ሐረር የኢትዮጵያ ምርጥ የቡና ዝርያ አብቃይ የመሆኗን ያህል፣ ተገቢው የመከላከል ዕርምጃ እንኳ ተወስዶ ቡና አብቃይነቱ በዚህ ክፍለ ዘመን ውስጥ ሊያካትም የሚችልበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ አጥኚዎቹ ይተነብያሉ፡፡ ለዚህም አስተዋጽኦ የሚያደርገው ሐረር የምትገኝበት የከፍታ መጠን እንደሆነ ያብራሩት ምሁራኑ፣ ለቡና ተስማሚ የሚባለው የከፍታ መጠን ከባህር ወለል በላይ ከ1,200 እስከ 2,200 ሜትር ድረስ እንደሚገመት አስፍረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለቡና ተስማሚ የሚባለው ዓመታዊ የዝናብ መጠንም ከ1,300 ሚሊ ሊትር መሆን እንዳለበት ተጠቅሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚታየው ዓመታዊ አማካይ የሙቀት መጠን ጭማሪ ከ50 ዓመታት በኋላ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2060 ከ1.1 ወደ 3.1 ዲግሪ ሴልሺየስ እንደሚጨምር ይገመታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2090 ደግሞ እስከ 5.1 ዲግሪ ሴልሺየስ ሊጨምር እንደሚችል ሣይንሳዊ ትንበያዎች እያመላከቱ ይገኛሉ፡፡ በዚህ አግባብ መሠረት በኢትዮጵያ የሚታየው የሙቀት መጠን ጭማሪ ለቡና ማሳያዎች የሥጋት ደውል እየተስተጋባበት ይገኛል፡፡ ዘ ጋርዲያንን ጨምሮ የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን ያሰራጩትን ይህንን የጥናት ውጤት አጥኝዎቹ ይፋ ያደረጉት ‹‹ኔቸር ፕላንትስ›› በተባለው የሳይንስ ጆርናል አማካይነት ነው፡፡

ዓምና ለውጭ ገበያ ከቀረበው 180 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና ከ800 ሚሊዮን ዶላር በመገኘቱ የአገሪቱን ሲሦ የውጭ ምንዛሪ ድርሻ የያዘው ቡና እንደሆነ አጥኚዎቹ ዘክረዋል፡፡ አራት ሚሊዮን ቡና አምራቾችን ጨምሮ 15 ሚሊዮን ሕዝብ የሚተዳደርበት የቡና እርሻ ላይ የተደቀነው አደጋ ወለል ብሎ የሚታይ በመሆኑ፣ የመንግሥትና የሚመለከታቸውን አትኩሮት እንደሚሻ ተጠቅሷል፡፡

 

Standard (Image)

ብርሃን ባንክ የምርት ገበያን የክፍያ ሥርዓት ተቀላቀለ

$
0
0

 

ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚካሄዱ ግብይቶችን በዘመናዊ የባንክ የክፍያ ሥርዓት ለማስተናገድ ከምርት ገበያው ጋር ስምምነት በመፈረም አሥራ አንደኛው ባንክ ሆነ፡፡

ብርሃን ባንክ ከምርት ገበያ ጋር ዘመናዊ የክፍያ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችለውን ስምምነት ሰኔ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. በምርት ገበያው ዋና መሥሪያ ቤት ተፈራርሟል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንደገለጸው፣ ከብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር የተደረሰው ስምምነት የምርት ገበያውን የክፍያ ሥርዓት ለማቀላጠፍና ለማዘመን የሚያደርገውን ጥረት ለማሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን፣ የግብይት ፈጻሚዎችም ተጨማሪ የክፍያ ባንክ እንዲኖራቸው ዕድል ይሰጣል ብሏል፡፡

ብርሃን ባንክን ጨምሮ እስካሁን ከ11 ባንኮች ጋር ተመሳሳይ ስምምነቶችን በማድረግ ተገበያዮች ግብይት በፈጸሙ ማግሥት አቅራቢዎችና ሻጮች የተገበያዩበትን ገንዘብ በቀጥታ ገዥውን ከፈጸመው የባንክ ሒሳብ፣ ሽያጩን ወደ ፈጸመው የባንክ ሒሳብ እንዲዛወር በማድረግ አገልግሎት የሚሰጥበት አሠራር ነው፡፡ ከምርት ገበያው ጋር እንዲህ ዓይነቱን አገልግሎት ከስምንት ዓመታት በፊት በመፈረም ቀዳሚው ዳሽን ባንክ ነው፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ከምርት ገበያው ጋር ስምምነት የፈጸሙት ባንኮች በዓመት በቢሊዮን የሚቆጠረውንና በግብይቶች አማካይነት የሚመነጨውን ገንዘብ ከገዥ ወደ ሻጭ የባንክ ሒሳብ እንዲዘዋወር በማድረግ ሲሠሩ  ቆይተዋል፡፡ ምርት ገበያው በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት ብቻ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ግብይቶችን አስፈጽሟል፡፡

እንዲህ ያለው በባንኮች ላይ የተመሠረተ የክፍያ ሥርዓት ገበያውን በመተማመን ላይ የተመሠረተ እንዲሆን እንደሚያደርገው የሚገልጸው የምርት ገበያው መረጃ ለዘመናዊ የክፍያ አገልግሎቶች መጎልበት የራሱ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

ሐሙስ፣ ሰኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. በብርሃን ባንክና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ መካከል የተደረገውን ስምምነት የፈረሙት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና አስፈጻሚ አቶ ኤርሚያስ እሸቱና የብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም አላሮ ናቸው፡፡ 

Standard (Image)

ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የዘመናይ አምራችነት በር ከፋች

$
0
0

 

በሳምንቱ መጀመሪያ የሐዋሳ ከተማ ከወትሮው ለየት ያለ ድባብ ታይቶባታል፡፡ የከተማዋ የንግድ ቤቶች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ደጃፎች፣ በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች ዙሪያ የተለያየዩ መልዕክቶችን ያነገቡ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችና ማሳያዎች ተሰቅለዋል፡፡ የሲዳማን ባህላዊ አልባሳት የተጎናፀፉ ወጣቶችና ጎልማሶች በከተማው ወዲህ ወዲያ እያሉ ሲንጎማለሉ ማየት የሰሞኑ የሐዋሳ ከተማ አክራሞት ነበር፡፡

የንግድ ድርጅቶች ትላልቅ የድምፅ ማስተጋቢያ ሳጥኖችን ከደጆቻቸው አስቀምጠው የሲዳማን ባህላዊ ዝማሬዎችና የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችን ጨዋታዎች አጉልተው ሲያሰሙ የተመለከተ ከተማዋ ውስጥ የተለየ ነገር መኖሩን እየተከናወነ እንዳለ ያሳብቃል፡፡  

ይህ ሁሉ የሲዳማ ዘመን መለወጫ የሚከበርበትን የፍቼ ጫምባላላ ክብረ በዓል ለመቀበል ከዋዜማው ጀምሮ ሲደረግ የነበረው ዝግጅት የፈጠረው ነበር፡፡ ከዚህ በዓል የዋዜማ ዕለት ጎን ለጎን ሐዋሳን ሊያጎላ የሚችል ሌላ ትልቅ ዝግጅት እየተደገሰ ስለነበር ከተማዋ እንቅስቃሴ የበዛባት ሆና እንድትሰንብት አድርጎታል፡፡

ይህም በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች እየተገነቡ ካሉና ግንባታቸው ከተጠናቀቁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ የሆነው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሙሉ በሙሉ ሥራ መጀመሩን በማስመልከት የተዘጋጀው ክብረ በዓል አንዱ የድምቀቷ ምክንያት ነበር፡፡

የጫምባላላ በዓል ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ መጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ጋር በመገጣጠሙ፣ ፓርኩን ለመመረቅ ሐዋሳ የሔዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ስለፓርኩ ምርቃት ንግግራቸውን የጀመሩት እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰን በማለት ነበር፡፡

የግዙፉ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገፅታዎች

የኢንዱስትሪ ፓርኩ አጠቃላይ ይዞታ ሦስት ሚሊዮን ካሬ ሜትር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የፓርኩ የመጀመርያው ምዕራፍ የሸፈነው ቦታ 1.4 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ነው፡፡ ይህ የኢንዱስትሪ ፓርክ እየተገነቡ ካሉና ይገነባሉ ተብለው ከሚጠበቁት 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ትልቁ ሆኗል፡፡

35 የማምረቻ ፋብሪካዎች ያሉት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ከመግቢያው ጀምሮ ዓይነ ገብ ነው፡፡ ምድረ ግቢው ባማረ ዲዛይን የተሠራ፣ የሥራ ፍላጎትን የሚያነሳሳ ነው፡፡ ከ50 ሺሕ በላይ የተለያዩ ዛፎችና ዕፅዋት የተተከሉበት ከመሆኑም ባሻገር፣ የመኖሪያ ቤት ሕንፃዎችም አሉት፡፡ የሁለተኛው ምዕራፍ የፓርኩን ግንባታ ለማካሔድ ሰኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. መሠረት ተቀምጦለታል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኩን የገነባው ሲሲአርሲ የተባለው የቻይና ተቋራጭ ከመሆኑም ባሻገር ከዚህ ግንባታ በተጨማሪ ከ14ቱ ፓርኮች የሦስቱን ሥራ ተረክቧል፡፡ የዚህን ፓርክ የግንባታ ወጪ ለየት የሚያደርገው ልዩ ሒደት ያለው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ  በሸጠችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቦንድ ሽያጭ አማካይነት ከተገኘ ገንዘብ የድርሻውን ተመድቦለት መገንባቱ ነው፡፡

የፓርኩን ግንባታ የኋላ ታሪክ በተመለከተ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዕቅድ ውጤታማነት ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሊቀመንበር ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የገለጹት ነጠብ ይጠቀሳል፡፡ ፓርኩን  ለየት የሚያደርገው አንዱ ነጥብ ግንባታው በዘጠኝ ወራት ውስጥ መጠናቀቁ ነው፡፡ ቀጥሎም በፓርኩ ውስጥ ወደ ተገነቡት ማምረቻዎች የሚገቡ በዓለም የታወቁ ኩባንያዎች እንዲመጡ ለማድረግ ብዙ አድካሚ ሥራዎች መሠራታቸውንም ዶ/ር አርከበ ጠቅሰዋል፡፡ ጥያቄ ከቀረበላቸው ታዋቂ ኩባንያዎች ውስጥ 18ቱ በመምጣት ሥራ ጀምረዋል፡፡ ይህም ሆኖ ወደ ፓርኩ የገቡት ኩባንያዎች የማምረት ሥራቸውን የጀመሩት ዘግይተው ነበር፡፡

ዶ/ር አርከበ እንደገለጹት ይህ የሆነው በመስከረምና ጥቅምት ወራት በተፈጠረው የፖለቲካ ግርግር ሳቢያ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ምርት በጀመሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ አንዳንዶቹ ወደ ውጭ ለመላክ በቅተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በፓርኩ ውስጥ የተገነቡት ሁሉም ማምረቻዎች ኩባንያዎች አልገቡባቸውም፡፡ ለዚህ የቀረበው ምክንያትም ምርጥ ኩባንያዎች ተመልምለው እንዲገቡ መንግሥት ከመለፈጉ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ሐዋሳን ያነጋገረው የፓርኩ ፍሳሽ ማስወገጃ

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአካባቢ ብክለትን እንዳያስከትል ከዲዛይን ጀምሮ ታስቦበታል፡፡ የፓርኩ ዲዛይን ብክለትን የሚከላከለው ልዩ መሠረተ ልማትም አስተማማኝነቱ በተነገረለት ቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የጠየቀ ሥርዓት ያለው ነው፡፡ ከፓርኩ የሚወጣውን ፍሳሽ በመቀበል አጣርቶ መልሶ ለፋብሪካ ሥራ ለማዋል የሚያስችለው ቴክኖሎጂ የሚያስፈልጉት መሠረተ ልማቶች ተሟልተውለት በተንጣለለ ቦታ ላይ ታንጿል፡፡ በቀን ከፋብሪካዎቹ ሊመነጭ የሚችለውን 11 ሚሊዮን ሊትር ፍሳሽ ይማጥራት አቅም አለው፡፡ ስለዚህ ለብክለት የሚያጋልጥ ሥጋት እንደሚኖር ቴክኖሎጂውንና ተዛማጅ መሠረተ ልማቶችን የገነባው የህንዱ ኩባንያ ኦርቪንድ ኤንቪሶል ኩባንያ አስታውቋል፡፡  

ይህ ይባል እንጂ በተለያዩ ማኅበራዊ ድረገጾች በቅርቡ ሲስተጋባ እንደታየው ከፓርኩ የሚለቀቅ ፍሳሽ ወደ ሐዋሳ ሐይቅ እንዲገባ የሚያመቻች ግንባታና የቦይ ቁፋሮ እየተካሄደ እንደሚገኝ የሚገልጹ ትችቶች የበርካቶችን ቀልብ በመሳብ ሲያነጋግሩ ከርመዋል፡፡ እንዴት እንዲህ ይደረጋል? የሚለው ጥያቄም ተስተጋብቷል፡፡ ይሁንና የተባለው ሁሉ ሐሰት እንደሆነ የፍሳሽ ማጣሪያው ይመስክር ተብሏል፡፡ በፓርኩ ሥራ መጀመሪያ ዕለትም በርካቶች ይህንኑ መሠረተ ልማት እንዲጎበኙት ተደርጓል፡፡ ከፓርኩ የሚወጣው ፍሳሽ ኢንዱስትሪዎች የሚያመነጩት ሳይሆን፣ ከእያንዳንዶቹ ማምረቻ የሚወርደውን የዝናብ ውኃ የሚከማችበትና በአግባቡ የሚስተናገድበት ሥርዓት ስለመሆኑ ማበራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክም ሆነ ከዚህ በኋላ የሚገነቡት ፓርኮች የሥራ ሒደት ሲነደፍ፣ የበርካታ አገሮችን ልምድ ለማየት ተሞክሯል ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ ልምድ ከተቀሰመባቸው ዋና ዋና አገሮች መካከል ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር፣ ቬትናምና ቻይና ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከተጠቀሱት የሩቅ ምሥራቅ አገሮች በተጨማሪ ከአፍሪካ የሞሪሺየስና የናይጄሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ታይተዋል፡፡ ይህ ቅኝት የፓርኮች ልማት፣ የሚታዩ ችግሮችንና ምርጥ ልምዶችን ለመመልከት ያስቻለ ነበር ብለዋል፡፡ በእስያም ሆነ በአፍሪካ በተመረጡ አገሮች ልምድ ለመቅሰም በተደረገው ቅኝት፣ ኢትዮጵያ የምትገነባቸው ፓርኮች ምን መምሰል እንዳለባቸው ለመገንዘብ እንደተቻለ ዶ/ር አርከበ ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌ በአብዛኛዎቹ የእስያ አገሮች የተሳካ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልምድ ስለመኖሩ መረዳት ቢቻልም ከአካባቢ ጥበቃ ረገድ ጥሩ የሚባል ልምድ እንደሌላቸው ያስረዱት ዶ/ር አርከበ፣ እነዚህ አገሮች ፈጣን የኢንዱስትሪ ልማት ቢያሳዩም አካባቢን ሲጎዱ በመቆየታቸው አሁን ላይ የጎዱትን አካባቢ በማከም ሥራ መጠመዳቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹እንዲህ ዓይነቶቹን ጉዳዮች በመመልከታችን የኢትዮጵያ ምርጫ አካባቢን እየጠበቅን በሺዎች የሚቆጠሩ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎችን ማስፋት የሚለውን አማራጭ ለመከተል የመወሰን ዕድል ሰጥቷታል፡፡ ኢንዱስትሪዎቹ ብከላ የሚያስከትሉ መሆን እንደሌለባቸው ታምኖ ከአገሪቱ የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲ ጋር በተጣጣመ መልኩ እንዲገነቡ ተደርጓል፡፡ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከብከላ ነፃ በሆነ መንገድ የተገነባ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮችም በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚገነቡ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የወጪ ንግድና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሚና

የፓርኮች ግንባታ አስፈላጊነትና ጠቃሚ የሚሆንበት ሌላው አንኳር ጉዳይ፣ ከወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን ጋር ስለሚያያዝ ነው፡፡

የአገሪቱን የወጪ ንግድ ለማሳደግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚኖራቸው ጠቀሜታ የላቀ ስለመሆኑ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሙሉ ለሙሉ ሥራ ሲጀምር ከዚህ ፓርክ ብቻ አንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ይገኛል ተብሏክል፡፡ ይህ ውጥን ምን ያህል ይሳካል የሚለው አነጋጋሪ መሆኑ አልቀረም፡፡ ዶ/ር አርከበም እንዲህ ያለው ጥያቄ ብዙ ጊዜ እንደሚነሳ አልሸሸጉም፡፡ ፓርኩ አንድ ቢሊዮን ዶላር ስለማስገኘቱ ለማስረገጥ ወደ ፓርኩ የገቡት የውጭ ኩባንያዎች አቅም ማሳያ ተደርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር እነዚህ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራች ኩባንያዎችን ከነባር የአገሪቱ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ጋር በማነፃፀር ልዩነቱን ለማሳየት ተሞክሯል፡፡

ዶ/ር አርከበ እንደሚጠቅሱት፣ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው የፈጠረው የሥራ ብዛት ለ53 ሺሕ ሰዎች ብቻ እንደነበር በማስታወስ፣ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግን 60 ሺሕ ሠራተኞች መቅጠር መቻሉ ከብልጫዎቹ አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በሁለት ዓመት ውስጥ 60 ሺሕ ሰዎችን መቅጠር መቻል በራሱ በፓርኩ ያሉ ፋብሪካዎችን አቅም ያሳያል ብለዋል፡፡ አያይዘውም የወጪ ንግዱን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ የነባሮቹ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ዓመታዊ የወጪ ንግድ ገቢ 180 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር ብለዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ግን የኢንዱስትሪ ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ሲያመርት የጨርቃጨርቅን የወጪ ንግድ ገቢ በአሥር እጥፍ በማሳደግ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚያደርሰው ተናግረዋል፡፡

በሌሎች ፓርኮች የሚመረቱት ሲታከሉበት የአገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ በከፍተኛ መጠን ስለሚያድግ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለአገሪቱ የወጪ ንግድ ማደግ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ድርሻ ከአምስት በመቶ በታች በመሆኑ፣ በአሥር ዓመት ውስጥ በአራት እጥፍ ማደግ እንዲችል ታቅዷል፡፡

ከ12 በመቶ ያልበለጠውን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በአራት እጥፍ ለማሳደግ ይፈለጋል፡፡ ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንግድ ሚኒስቴር የ11 ወራት ሪፖርትም የወጪ ንግዱ አፈጻጸም 41 በመቶ ጉድለት አሳይቷል፡፡ ዶ/ር አርከበ ግን እነዚህ ፓርኮች ይህንን መለወጥ ይችላሉ እያሉ ነው፡፡

‹‹በወጪ ንግድ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ሰብረን ላለመግባታችን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በሚገባ አለማደጉ የፈጠረው ማነቆ ነው፤›› ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ ዘርፉ ብዙ ፈተናዎች ያሉበት ከመሆኑም በተጨማሪ አምራቾች አሉባቸው ያሉቸውንም ጉድለቶችና ችግሮችም አብራርተዋል፡፡ አንድ አምራች የንግድና የኢንቨስትመንት የምዝገባ ሠርተፍኬት ወስዶ፣ ቦታ አግኝቶ፣ ግንባታ ጀምሮ ወደ ማምረቱ ሥራ እስኪገባ ድረስ በትንሹ አምስት ዓመት እንደሚወሰድበት ገልጸዋል፡፡ የምዝገባ ሠርተፍኬት ካገኙ በኋላ መሬት ለማግኘት ቢያንስ ሁለት ዓመት እንደሚፈጅ፣ መሬት ለማግኘት ያለው ሒደትም ሙስና እንዳለበት አስታውሰዋል፡፡

‹‹መሬት ካገኙ በኋላ ፋይናንስ ማፈላለግ ስለሚኖርባቸው፣ ለሕንፃ ግንባታውና ለማሽነሪ ጭምር የሚፈልጉትን ገንዘብ አግኝተው ወደ ግንባታ ለመግባት ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ይፈጅባቸዋል፤›› በማለት አንድ አምራች ከምዝገባ እስከ ማምረት ሥራ ድረስ የሚገጥሙትን ውጣ ውረዶች አስቀምጠዋል፡፡  

ግንባታው ከተጠናቀቀም በኋላ ቢሆን የኤሌክትሪክና የቴሌኮም አገልግሎት ለማግኘት፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎችን ለማስተካከል ተጨማሪ ጊዜ ይጠይቀዋል ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ አንድ አምራች ወደ ምርት ሥራ ለመግባት አምስት ዓመት ይፈጅበታል ብለዋል፡፡ መንግሥት ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እንዲገባ ውሳኔ ላይ ከደረሰባቸው ምክንያቶች አንዱም ይህ ችግር ነው ተብሏል፡፡ ስለዚህ አምራቾች እንደ ሐዋሳ ባሉ ፓርኮች ውስጥ ገብተው የሚሠሩ ከሆኑ፣ ሁሉም ነገር ተመቻችቶ ስለሚጠብቃቸው፣  ስለመሠረተ ልማት ግንባታ ወጪ ሳያስቡ፣ ማሽነሪ ተክለው በአምስት ወይም በስድስት ወራት ውስጥ ወደ ምርት ሥራ መግባት ያስቻለቸዋል፡፡

በፓርኩ ውስጥ መሬት በነፃ የሚሰጥ መሆኑም አንዱ ማበረታቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ያለ ምንም ውጣ ውረድና ከሙስና በነፃ ሁኔታ ሥራቸውን እንዲሠሩ ያስችላቸዋል፡፡ በሐዋሳና በሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚያመርቱ ኩባንያዎች ሌላ ልዩ ዕድል መሰጠቱንም ገልጸዋል፡፡ ይኸውም ያመረቱትን ወደ ውጭ ለመላክም ሆነ ለማስገባት ሲጥሩ ይገጥሟቸው የነበሩ ማነቆዎችን ለማስቀረት የሚያስችሉ አሠራሮች በፓርኮቹ ውስጥ ይዘረጋሉ፡፡

በዚህ ረገድ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡ እንደ ምሳሌ የተነሳው ደግሞ በአንድ ማዕከል ለውጭ ዜጎች በፓርኩ ውስጥ ቪዛ መስጠት ማስቻሉ ነው፡፡ በፓርኩ ውስጥ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሙያዎችና ባለሀብቶች ረዘም ላለ ጊዜ የሚገለገሉበት ቪዛ ይሰጣቸዋል፡፡ ለሙያተኞችና ለማኔጅመንት አባላት የሦስት ዓመት፣ ለባለሀብቶች ደግሞ እስከ አምስት ዓመት የሚያገለግል ቪዛ ይሰጣል ተብሏል፡፡ ከሎጂስቲክስና ከፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት አንፃርም የታሰበበት አካሔድም ተወጥኗል፡፡ በምን መልኩ የሚለውን በግልጽ ባያብራሩም፣ በመንግሥት አገልግሎቶች ላይ መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ በሎጂስቲክስ፣ በጉምሩክና በብሔራዊ ባንክ አሠራሮች ላይ ለውጥ ይደረጋል ብለዋል፡፡

‹‹ያለ ተደራሽ የፋይናንስ አገልግሎት ኢትዮጵያ ተመራጭና ተወዳዳሪ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ልትሆን አትችልም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ባንኮች ራሳቸውን በአዲስ መልክ በማደራጀት፣ ዓለም ከደረሰበት ዘመናዊ አገልግሎት ጋር ማስተዋወቅ አለባቸው በማለት አሳስበዋል፡፡ መንግሥት በእነዚህ ዘርፎች አሠራር ላይ ያሰበውን ለውጥንና የተመቻቸ የቢዝነስ ኢንቨስትመንት የመፍጠር ዓላማ እንደያዘና ከዋናው የመንግሥት ዓላማ ጋር ማስተሳሰር እንደሚኖርበት የጠቀሱት ዶ/ር አርከበ ሲሆኑ፣ በተለይ እ.ኤ.አ. በ2025 ኢትዮጵያ ዋነኛ የአፍሪካ ማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ የሁሉም አካላት ርብርብ እንደሚሻም ተናግረዋል፡፡

የአገር ውስጥ ባለሀብቶችና ፓርኮቹ

መንግሥት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰማሩ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ ነበር፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የንግድ ኅብረተሰብ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በእጅጉ በመራቁና ፍላጎቱ የተቀዛቀዘ በመሆኑ፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች ብቻ የተተወ አስመስሎታል፡፡ የዕውቀትና የፋይናንስ እጥረት እንደምክንያት ቢጠቀስም፣ አቅሙም ኖሯቸው ወደ ማኑፋክቸሪንግ መስክ ለመግባት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች አቅማምተዋል፡፡ መንግሥት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደዚህ ዘርፍ እንዲገቡ በሚፈለገው ደረጃ እገዛ አላደረገም የሚለው ወቀሳም ይሰነዘራል፡፡  

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የገቡት በሙሉ የውጭ ኩባንያዎች ብቻ መሆናቸው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ በምን ደረጃ እንደሚገኝ ያሳየ ነው ቢባልም ዶ/ር አርከበ ግን ኢትዮጵያውያን ወደዚህ ሥራ ዘርፍ እንዲገቡ ለማድረግ  የተለያዩ አቅጣጫዎች መታሰባቸውን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ወደ ማኑፋክቸሪንግ የማይገቡበት ዋነኛ ምክንያት ግን ማኑፋክቸሪንግ አክሳሪ በመሆኑ ነው በማለት ያከሉት ዶ/ር አርከበ፣ አክሳሪ የሚሆኑበትም ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው ብለው ካስቀመጡት ውስጥ የፋብሪካ ምርት ሲጀምሩ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ የሚያጋጥማቸው መሆኑ አንዱ ነው፡፡ ከባንክ በቀላሉ ብድር ማግኘት የማይቻል መሆኑም ወደ ኪሳራ ከሚገፋቸው ምክንያቶች ውስጥ ተካቷል፡፡ የሚፈልጓቸውን መሠረተ ልማቶች የሚያገኙ በመሆኑም እኚህ ኢትዮጵያውያን የምርት ሒደታቸውን አስፋፍተው በማኑፋክቸሪንግ ሊያድጉ አይችሉም በማለት አብራርተዋል፡፡

ሆኖም የቀደሙት ልምዶችን በማየት እንዲህ ያለውን ሒደት ለመፍታት አንዱ ዘዴ ነባሮቹም ሆኑ አዳዲሶቹ አምራቾች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ እንዲገቡ ማድረግ ተብሏል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ከገቡ የኤሌክትሪክ ችግር አያጋጥምም፡፡ የጉምሩክ መጓተትና ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥማቸው ወደ ፓርኩ መግባት አንድ መፍትሔ ይሆናል ተብሏል፡፡ ስለዚህ ከ15 እስከ 30 በመቶ የሚሆነው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ቦታ ለኢትዮጵያውያን እንዲሆን ስለመታሰቡ ተገልጿል፡፡

ለአገር ውስጥ ባለሀብቶችም ተጨማሪ ልዩ ድጋፍ በማድረግ በፓርኩ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደ ዋነኛ ማነቆ ሆኖ የቆየውን የፋይናንስ፣ የክህሎትና የቴክኒክ አቅም እንዲሁም የገበያ ልማት ናቸው፡፡ እነዚህን ሦስት ጉዳዮች ለመፍታት መንግሥት በሁለት መንገድ ችግሩን ለማቃለል እንዲያስብ ከተደረገው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህም በአንድ በኩል መሠረተ ልማት የተሟላለት ማምረቻ ሕንፃ ስለሚያገኙ እስከ ስልሳ በመቶ የሚሆነው ካፒታል ኢንቨስትመንት ይቀንስላቸዋል፡፡ ለማሽነሪና ለሥራ ማስኬጃ የሚያስፈልጋቸው ገንዘብ እስከ 85 በመቶ በብድር ተመቻችቶላቸዋል፡፡

ይህ አዲስ ፖሊሲ እንደሆነ የጠቀሱት ዶ/ር አርከበ፣ ሌሎች አገሮች በዚህን ያህል ደረጃ ድጋፍ እንደማያደርጉም ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ይህንኑ ሐሳብ በማጠናከር በዘርፉ ለሚሳተፉ ባለሀብቶች ያልተለመደ ልዩ ዕድል ማመቻቸቱን  ተናግረዋል፡፡ የቴክኒክና የክህሎት ችግሮቻቸውን እንዲፈቱም ሥልጠና ወሳኝ በመሆኑ፣ መንግሥት ውሳኔ ላይ ከደረሰባቸው አበረታች ዕርምጃዎች መካከል በማኑፋክቸሪንግ ወደ ፓርኩ የሚገቡ አገር በቀል ኩባንያዎች ለሥራቸው የሚያስፈልጓቸውን ብቁ የሰው ኃይል እንዲያገኙ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለማሠልጠን ከፈለጉ የሚያስፈልጋቸው ወጪ፣ (የውጭ ምንዛሪን ጨምሮ) በመጀመሪያው ዓመት 85 በመቶን መንግሥት ለመሸፈን የተዘጋጀ መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ዓመት ላይ 75፣ በሦስተኛው ዓመት 50 በመቶ በአራተኛው ዓመት 25 በመቶ የሚሆነውን ወጪ መንግሥት እንዲሸፍንላቸው ተወስኗል ተብሏል፡፡ በአምስተኛው ዓመት ግን አምራቾቹ ለሠልጣኞቻቸው የሚያወጡትን ወጪ ሙሉ በሙሉ ይሸፍናሉ፡፡ እንደ ሥልጠና ወጪው ሁሉ ኢትዮጵያውያን አምራቾች የውጭ ባለሙያ ሲቀጥሩ በተመሳሳይ ለአራት ዓመታት ከ25 እስከ 85 በመቶ የሚደርሰውን ወጪያቸውን ይሸፍናል፡፡  

18ቱ ጀማሪዎች

ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ኢትዮጵያ አግኝታዋለች ያሉን ከፍተኛ ውጤት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ዕድገትን በማሳካት ረገድ የውጭ ኢንቨስትመንት የማይተካ ሚና ያለው ዓይነተኛ መሣሪያ እንደሆነ፣ ይህም የመንግሥታችን ጽኑ ቅኝት መሆኑን ላስገነዝብ እወዳለሁ፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ላይ ምንም ብዥታ ሊኖር እንደማይገባ ያስመዘገቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይ በእነዚህ ፓርኮች ውስጥ ምርጥ የሚባሉ የውጭ ኩባንያዎች እንዲገቡ ማድረግ ላይ መንግሥት ብዙ መልፋቱንና ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ወደ ሥራ የገቡት ከ18ቱ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች መረጣ ምርጥ የሚባሉ ኩባንያዎችን ከማግኘት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በእርግጥም በፓርኩ ውስጥ የገቡት ኩባንያዎች በዓለም ደረጃ የሚታወቁ ምርቶችን የሚያቀርቡ ናቸው፡፡

እንደ ዶ/ር አርከበ ገለጻ ፒቪኤች የተባለው የአሜሪካ ኩባንያ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ከ130 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው ፒቪኤች ኩባንያ፣ በዓለም ምርጥ አልባሳት ከሚያመርቱ ትልልቅ ኩባንያዎች አንዱ ነው፡፡ በ40 አገሮች ውስጥ ከ30,000 በላይ አምራቾች ጋር ይሠራል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 ከ8.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስመዘገበ ኩባንያም ነው፡፡ ፒቪኤች ታዋቂ የሆኑት ካልቪን ክሌን፣ የቶሚ ሃልፊገር፣ የቫን ሂውን፣ የአሮው፣ የስፒድ፣ የዋርነርስና ኦልጋ ብራንዶችን ጨምሮ የበርካታ ምርቶች ባለቤት ስለመሆኑ የኩባንያው ታሪክ ያሳያል፡፡

ፒቪኤች በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመሥራት ዘርፉን ለማገዝና ወደፊት ለማራመድ ስለመነሳቱ የኩባንያው ማኔጅመንት አባል፣ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ባለንብረቶች ማኅበር ሊቀ መንበር ሚኒስትር ቢል ማክሬን ተናግረዋል፡፡ ፒቪኤች በፓርኩ የተመረተውን የመጀመሪያውን ምርቱን በግንቦት ወር ለውጭ ገበያ አቅርቧል፡፡

የሐዋሳ ፓርክን የተቀላቀለው ሌላው ስመ ጥር ኩባንያ ደግሞ ሬይመንድ ሲልቨርስፓርክ አፓረል ኩባንያ የተባለው ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1925 በሕንድ የተመሠረተው ይህ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ከ25,000 በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡ የህንድ ምርጥ ኩባንያ በመባል በተደጋጋሚ ለመመረጥ የበቃው ሬይመንድ፣ በእስያም ምርጥ የሥራ ቦታ አላቸው ተብለው ከተመረጡ ኩባንያዎች አንዱ ነው፡፡ ራይመንድ፣ ራይመንድ ፕሪምየም፣ ፓርክ አቬኑ፣ ፓርክ አቬኑ ከለር ፕላስ፣ ፓርክስና በመሳሰሉት ብራንዶች ይታወቃል፡፡

ዉሺ የተባለው የቻይና ኩባንያ በጨርቃ ጨርቅ፣ በስፌትና በመሳሰሉት ይታወቃል፡፡ ከኩባንያው ደንበኞች መካከል ፒቪኤች፣ ጋፕ፣ ጃክ ፔነር፣ ታርጌት የተባሉት በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡

ሃይድራማኒ ጋርመንት ኩባንያ ዋና መሥሪያ ቤቱ በሲሪላንካ ሲሆን፣ ከ100 ዓመት በላይ ልምድ አለው፡፡ በስድስት አኅጉራት ውስጥ ግንባር ቀደም ልብስ አምራች ሲሆን፣ ለትልልቅ ብራንዶችም ያቀርባል፡፡ በተለይ የሴቶችን ፖሎ ቲሸርቶችና የውስጥ አልባሳት እያመረተ ይገኛል፡፡ እስካሁንም ከፓርኩ 25 ኮንቴነር ምርትን ኤክስፖርት አድርጓል፡፡

ኢንዱስትሪ ፓርኩና የሰው ኃይል

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለሰው ኃይል ቅጥር ሰፊ ዕድል ይሰጣሉ ተብሏል፡፡ ዶ/ር አርከበ እንደገለጹትም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አስተማማኝ የሆነ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ የሥራ ዕድል እንዳለውም የሚታመንበት በመሆኑ እየተሠራበት ነው፡፡

ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ዕድገት የሚኖራት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እያደገ የሚመጣውን የሥራ ፍላጎት ለማሟላት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ አስፈላጊነት ጎልቶ ይታያል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በየዓመቱ 100 ሺሕ የሚሆኑ ምሩቃን የሚያወጡ ሆነዋል፡፡ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ የ12ኛ የቴክኒክ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ይመረቃሉ፡፡ ለእነዚህ ሁሉ የሥራ ዕድል መፈጠር ካለበት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ዶ/ር አርከበ አስረድተዋል፡፡ በግብርና ብቻ ይህንን የሥራ ፍላጎት መሸፈን የማይቻል ስለሆነ በማኑፋክቸሪንግ በአሥር ዓመት ለሁለት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡

ይህ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር 60 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ አሁን እስከ አሥር ሺሕ የሚደርሱ ሠራተኞችን ይዟል፡፡ ሠራተኞችን ለመቅጠር የተቋቋመ አላክም ወደ 30 ሺሕ የሚጠጉ ዜጎችን መዝግቦ እየጠበቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ስመ ጥር ኩባንያዎች የከተሙበት ይህ የኢንዱስትሪ ፓርክ ከሠራተኞች ደመወዝ ጋር ተያይዞ ከሠራተኞች አንዳንድ ጥያቄዎች እየተሰሙ ነው፡፡

ብዙ ወጣቶች በተለይም ሴቶች በዚህ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ሥራ በጀመሩ ኩባንያዎች ውስጥ እየሠሩ ቢሆንም ለሠራተኞች ዝቅተኛ እየተባለ ነው፡፡ ስሟን ያልገለጸችው የ19 ዓመት ወጣት በህንዱ የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥራ እየሠራች ነው፡፡ ሥራውን ከጀመረች ሁለተኛ ወሯ ነው፡፡ ሥራዋ አድካሚ ቢሆንም ሥራ በመገኘቱ መደሰቷን ትገልጻለች፡፡ ነገር ግን የሚከፈላት ደመወዝ ሕይወቷን ለመምራት የሚያስችል ስለመሆኑ ያሳስባታል፡፡

እንደ እሷ ገለጻ ደመወዟ 650 ብር ነው፡፡ ከአንዳንድ ጥቅማ ጥቅሞች ጋር ተደምሮ በወር 1,002 ብር ይደርሳታል፡፡ ገንዘቡ እጅግ በጣም ትንሽ በመሆኑ በዚህ ደመወዝ እንዴት መቀጠል እንዳለባትና ምን ማድረግ እንደሚኖርባት ግራ ስለመጋባቷም ጠቅሳለች፡፡ ነዋሪነቷ ሐዋሳ ከተማ ውስጥ ባለመሆኑ ቤት መከራየት ስላለባትና በዚህ ደመወዝ ደግሞ ለብቻዋ መከራየት ስላልቻላት እሷ ጋር በተመሳሳይ ሥራ ላይ ከሚኖሩ ሁለት ጓደኞቿ ጋር በ600 ብር በጋራ በተከራዩት ቤት እየኖሩ ነው፡፡ የተከራዩት ቤት ከፓርኩ የሚርቅ በመሆኑ ረዥም ጉዞ ይጠብቃቸዋል፡፡ ጉዞውም ወጪ እንዳለው የጠቀሰችው ይቺ ወጣት ክፍያው ሊስተካከል ይገባል ትላለች፡፡ በአብዛኛው ዝቅተኛ የሥራ መደብ ላይ ያሉ ሠራተኞች ተመሳሳይ አስተያየት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ 650፣ 750፣ 1,002 እና 1,200 ብር የሚከፈላቸው ሠራተኞችም አሉ፡፡ ይህ ክፍያ ለምንም አሁን ካለው የመኖር ዋጋ ጋር አልተጣጣመላቸውም፡፡ ሰርቪስ የሚያቀርቡ ኢንዱስትሪዎች የመኖራቸውን ያህል ለሠራተኞች ማጓጓዣ ያላዘጋጁም እንዳሉ ካነጋገርናቸው የፓርኩ ሠራተኞች ለመረዳት ተችሏል፡፡ በእርግጥ የትራንስፖርት የሚከፍሉም አጋጥመውናል፡፡ ደመወዙ በቂ ባለመሆኑ ኢንዱስትሪው በተገነባበትና በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ አጥር ይዘው በላስቲክ የተሠሩ ምግብ ቤቶች ከዚያ ያማረ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚወጡ ደንበኞቻቸውን በአቅማቸው ያስተናግዳሉ፡፡

ቀጣዮቹ ፓርኮች

እነዚህም ከሁለት ዓመት በፊት ለአገልግሎት የበቃው ቦሌ ለሚ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሲሆን፣ ወደ አገልግሎት የገባ ሁለተኛው የኢንዱስትሪ ፓርክ ሆኗል፡፡ የመቐለና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው የተጠናቀቁ በመሆኑ በዚህ ወር መጨረሻ ይመረቃሉ፡፡ የአዳማና የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ መስከረም 2010 ግንባታቸው እንደሚጠናቀቁ ዶ/ር አርከበ ተናግረዋል፡፡ በፋርማቲውካል ዘርፍ ላይ የሚሠራው የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጥር 2010 ዓ.ም. ለምርት ዝግጁ ይሆናል ተብሏል፡፡

የቦሌ ለሚ (ሁለት) በግንባታ ላይ ሲሆን፣ በጥር 2010 ወደ ምርት ይገባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በጅማና ባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ግንባታ የገቡ ሲሆን፣ በሚያዚያ 2010 ይጠናቀቃሉ፡፡ የአራርቲ የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ በቅርቡ የግንባታቸው ኮንትራት ይፈረማል፡፡ አላጌ (ዝዋይ) አይሻ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም ደግሞ ሁናን የተባለውና በአዳማ የታሰበው ሌላ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በቀጣዩ የበጀት ዓመት ግንባታቸው ይጀመራል፡፡ ከእነዚህ ውጭ በሰመራ አካባቢ ይገነባል ተብሎ የሚጠበቀው አዲስ የኢንዱስትሪ ፓርክ ጥናት እንደሚጀመር ከዶ/ር አርከበ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

Standard (Image)

የቦብ ማርሌይ አደባባይ ፈረሰ

$
0
0
  • በተሰጠው ምትክ ቦታ ላይ ምስለ ቅርፁ እንዲቆም ይደረጋል ተብሏል

በታዋቂው የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝ ቦብ ማርሌይ ስም የተሰየመውና በአዲስ አበባ ከተማ ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ የሚገኘው አደባባይ ፈረሰ፡፡ ለቦብ ማርሌይ ምስለ ቅርፅ ማቆሚያና በስሙ ለሚጠራ አደባባይ ተለዋጭ ቦታ እንደተሰጠ ታውቋል፡፡

ለአዲስ አበባ መንገዶች የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ ምክንያት ሆነው ከሚጠቀሱ አደባባዮች መካከል አንዱ የሆነው የቦቦ ማርሌይ አደባባይ የፈረሰው ቅዳሜ፣ ሰኔ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲሆን፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በፈረሰው አደባባይ ምትክ መንገዱን በትራፊክ መብራቶች ለማስተናገድ የሚያስችል ግንባታ ጀምሯል፡፡  

በባለሥልጣኑ ውሳኔ መሠረት ከሚፈርሱት አደባባዮች አንዱ መሆኑ ቀድሞውኑ የታወቀው የቦብ አደባባይ እስካሁን ሳይፈርስ የቆየው የአቀንቃኙን ምስለ ቅርፅ ማሳረፊያ ተተኪ ቦታ ለማግኘት ጊዜ በመውሰዱ ነው፡፡ ይሁንና ለምስለ ቅርፁ ማኖሪያ የሚሆን ቦታ የከተማው አስተዳደር በማዘጋጀቱ፣ ምስለ ቅርፁ ከነበረበት ቦታ ተነስቶ አደባባዩን በማፍረስ የአስፓልት ኮንክሪት ግንባታ ሥራ መካሔድ ጀምሯል፡፡

ለምስለ ቅርፁ ማዛወሪያና በቦብ ስም የሚጠራ ተለዋጭ ቦታ ለማግኘት በተደረገው ሙከራ ስድስት አማራጭ ቦታዎች ቀርበው በመጨረሻው፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የሚገኝበት እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ያለ ቦታ ተመርጧል፡፡ በዚህ ቦታ አዲስ አደባባይ በመገንባት ምስለ ቅርፁ እንዲያርፍ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ምስለ ቅርፁን የማስቀመጡ ሥራ በልዩ ሥርዓት የቦብ ማርሌ ቤተሰቦች ወዳጆች በሚገኙበት በክብር እንደሚፈጸም ምስለ ቅርፁን አሠርተው በኢምፔረያል አካባቢ ካኖሩት ሦስት ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው አርቲስት ዘለቀ ገሠሠ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ለከተማው የትራፊክ መጨናነቅ መንስዔ ነበሩ ካላቸው አደባባዮች ውስጥ እስካሁን ስድስተኛውን አፍርሷል፡፡

በተለይ በቀለበት መንገዱ ጋር የተያያዙ አደባባዮች መፍረስ እንደሚኖርባቸው በማመን እስካሁን የጀሞ አደባባይ፣ 18 ማዞሪያ፣ የቦሌ ሚካኤል፣ ለቡ መብራት ኃይልና የጃክሮስ አደባባዮች ፈርሰው ለተሽከርካሪዎች ምቹ ይሆናል በተባለ መንገድ ተገንብተው የትራፊክ መብራት እንዲተከልላቸው ተደርጓል፡፡ የጃክሮስ አደባባይ የፈረሰው ባለፈው ሳምንት ነው፡፡

ባለፈው ቅዳሜ የፈረሰው የቦብ አደባባይም የአስፓልት ሥራው በሚቀጥሉት ቀናት ተጠናቅቆ በአራት አቅጣጫ የሚተላለፈውን የትራፊክ ፍሰት በመብራት ለማስተናገድ በሚያስችለው ደረጃ እየተገነባ ነው፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን አደባባዮችን በማፍረስ ለትራፊክ ምቹ ይሆናል ባለው መንገድ እየሠራ ያለው ሥራ በጊዜያዊነትም ቢሆን የከተማዋን የትራፊክ መጨናነቅ በማስተንፈስ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ተብሏል፡፡ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጥኡማይ ወልደ ገብርኤል ለሪፖርተር እንደገለጹት ከስድስቱ አደባባዮች ሌላ ቀሪ አራት አደባባዮች በአዲሱ በጀት ዓመት ይፈርሳሉ፡፡

ከእነዚህም መካከል የሳሪስ አቦና የጀርመን አደባባዮች እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለሥልጣኑ ለከተማዋ የትራፊክ ፍሰት እንቅፋት ናቸው ከተባሉት አደባባዮች ሌላ የተጎዱ መንገዶች ጥገናም በማካሄድና ምቹ የትራፊክ ፍሰት እንዲፈጠር እያደረገ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡  

በዚህም መሠረት አደባባዮችን በማፍረስና መልሶ በመብራት እንዲስተናገድ የማድረጉ ሥራና በከተማዋ ውስጥ ላካሄዳቸው የመንገድ ጥገናዎች እስካሁን ከ330 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 130 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው መንገድ ጠግኗል፡፡ በበጀት ዓመቱ ለመጠገን ታቅዶ የነበረው 90 ኪሎ ሜትር እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

አደባባዮችን በማጥፋት በመብራት የማስተናገዱ ዘላቂ ይሆናል ተብሎ ስለማይታመን አደባባዮቹ በነበሩባቸው ቦታዎች ላይ ተላላፊ መንገዶችን ወደመገንባት ይገባል፡፡ ተላላፊ መንገዶች ያስፈልጋቸዋል ለተባሉ አደባባይ የነበረባቸው መንገዶች ላይ ለሚገነቡት ተላላፊ መንገዶች የሚሆን ዲዛይን እየተሠራ ሲሆን የሚካኤል አደባባይ አልቋል፡፡ በሚቀጥለው በጀት ዓመት ግንባታቸው ይጀመራል ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥም ቀዳሚው ይኸው የሚካኤል አደባባይ ነው፡፡ 

Standard (Image)

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ምክር ቤትን የምርጫ ሕግ በመጣስ ያገዳቸውን ዳግመኛ በምርጫ ሒደት ማካተቱ ጥያቄ አስነሳ

$
0
0

ሕግ በመጣሳቸው ምክንያት ያካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔም ሆነ የምርጫ ውጤት የታገደባቸውና በምትኩ ዳግመኛ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያካሂዱ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከተወሰነባቸው የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች መካከል የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አንዱ ነው፡፡ ሆኖም በሕጋዊ መንገድ ዳግመኛ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያካሂድ ለማድረግ የተዋቀረው ኮሚቴ የታገዱ ሰዎችን ዳግመኛ በምርጫ አመቻችነት ማካተቱ እያነጋገረ ነው፡፡ በድጋሚ ይካሄዳል የተባለው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫም ከአንድ ዓመት በኋላ በሐምሌ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊካሄድ እንደሚችል ታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር የተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ የታገደው በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ውሳኔ ሲሆን፣ ዳግመኛ እንዲጠራ የተባለውን ጠቅላላ ጉባዔም ሆነ የምርጫ ሒደት እንዲያካሂድ የተዋቀረው ኮሚቴ ጥያቄ የተነሳበት ለጉባዔው መታገድ ምክንያት የሆኑ አመራሮች አሁንም በምርጫ ሒደቱ ውስጥ እንዲካተቱ በመደረጋቸው ነው፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሁለት ወራት በፊት በአገር አቀፉ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ የወሰደው ዕርምጃ ትክክል እንደሆነ ለሪፖርተር የገለጹ ወገኖች እንዳሉት፣ በውሳኔው መሠረት ምርጫው እንዲደገም ሰበብ በመሆን ጥሰዋል ተብለው  ተጠያቂ የተደረጉ ሰዎችን ከማስገባት ይልቅ ገለልተኛ አካላት የሚሳተፉበት የምርጫ አመቻች ኮሚቴ መዋቀር ነበረበት፡፡

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በድጋሚ የሚካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ ለመጥራት ያስችላል ብሎ ባዋቀረው ኮሚቴ ውስጥ የታገዱ አመራር አባላት እንዲካተቱ ማድረጉ አግባብ እንዳልሆነ እየተገለጸ ነው፡፡ ከሕግ ውጭ ተመርጠዋል የተባሉ የዘርፉ አባላትን አካቶ የቀረበው የምርጫ አመቻች ኮሚቴ ቀድሞ የተፈጸሙ ስህተቶችን ላለመድገሙ እርግጠኛ አይደለንም የሚሉ ወገኖች የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ውሳኔ ብዥታ እንደፈጠረባቸው ይጠቅሳሉ፡፡

ከሚፈቀድላቸው የምርጫና የአገልግሎት ዘመን ውጭ ሕግ በመተላለፍ ተመርጠዋል ከተባሉና ምርጫ ውጤታቸው ከታገደባቸው ግለሰቦች መካከል በአዲሱ ምርጫ አመቻች ኮሚቴ ውስጥ የተካተቱት፣ ባለፉት አሥር ዓመታት የዘርፍ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት የመሩት አቶ ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር  እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡ ከአቶ ገብረ ሕይወት ባሻገር በትክክለኛው የሕግ አግባብ ተወክለው ወደ አገር አቀፉ የዘርፍ ምክር ቤት የአመራር መዋቅር አልመጡም የተባሉት የአዲስ አበባ ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መኮንንም በአዲሱ የምርጫ አመቻች ኮሚቴ ውስጥ ተካተዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሪፖርተር መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ኮሚቴው ሰባት አባላት ያሉት ሲሆን፣ ሦስቱ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አራቱ ደግሞ ከዘርፍ ምክር ቤቶች የተወከሉ ናቸው፡፡

ለሕግ ጥሰቱ ተጠያቂ ናቸው የተባሉ የታገደው የአመራር አባላት መልሰው ለአዲሱ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ የምርጫ አመቻች ኮሚቴ አባል እንደሆኑ ከተፈቀደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ቀድሞስ ለምን አገደ? እየተባለ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በዚህ አመቻች ውስጥ የንግድ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቢካተት የድጋሚ ምርጫው ላይ የተፈጠረውን ብዥታ ይቀንሰው ነበር ያሉም ወገኖች አሉ፡፡

ለወራት እየተጓተተ የመጣውና በድጋሚ እንዲካሄድ የተወሰነው የዘርፉ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ለኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ምርጫ መዘግየትም ምክንያት መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ምርጫውን ማካሄድ የነበረበት መስከረም 2009 ዓ.ም. ቢሆንም፣ የአገር አቀፍ ዘርፍ ምክር ቤትና የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት አካሂዶት የነበረው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ የሕግ ጥሰት አለበት በሚል ድጋሚ ምርጫ እንዲያካሂዱ ተወስኖ የአማራው አካሂዷል፡፡

እንደ ዘርፍ ምክር ቤቱ ሁሉ ዕገዳ ተጥሎበት አዲስ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ እንዲያካሂድ የተወሰነበትን የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውንና ምርጫውን ያካሄደው የታገደውን አመራር አባላትን ባላካተተ ሁኔታ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የአማራ ንግድ ምክር ቤትን አዲስ የተጠራ ጠቅላላ ገባዔና ምርጫ ለማካሄድ በአስተባባሪነት የተሰየሙት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራትን ጨምሮ በታገደው አመራር ውስጥ ያልነበሩ የከተማና የወረዳ ንግድ ምክር ቤቶች አባላት ሲሆኑ የአማራ ንግድና ኢንዱስትሪ ገበያ ልማት ቢሮ ነበር፡፡

በተመሳሳይ መንገድ የታገደው የኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት በድጋሚ እንዲካሄድ የተወሰነበትን ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫም አሳማኝ እንዲሆን በአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እንደተካሄደው ከቀድሞ አመራር ጋር ንክኪ በሌለው መንገድ ሊሆን ይገባው እንደነበር አመልክተዋል፡፡

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አንድ የሥራ ኃላፊ  እንደገለጹት ደግሞ የዘርፉ ምክር ቤት ምርጫ ከአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በተለየ የሚደረግ ነው፡፡

‹‹እኛ ያሰብነው ሁሉም ቦርዱም ቢሆን ችግሩን በጋራ እንዲፈቱ የማድረግ ነው፤›› ያሉት እኚህ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊ ምርጫው የሕግ ስህተቶች ሊኖሩት ቢችሉም አሁን የሚደረጉ ይህንን ለማስተካከል በጋራ ለመሥራትና ሁሉም አጋዥ እንዲሆን ነው የተወሰነው፡፡

እንዲህ መወሰኑ እንዲታገድ ለተደረገው ምርጫ ተጠያቂ ናቸው እየተባሉ ግለሰቦችን መልሶ ለአዲሱ ምርጫ የኮሚቴ አባል ማድረጉ ምን ያህል ተገቢ ነው? ተመሳሳይ ዕርምጃ የተወሰደበት የአማራ ንግድ ምክር ቤት ገለልተኛ ኮሚቴ ነበር ያዋቀረውና ለምን እንደዚያ ማድረግ አልተቻለም? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው እኚሁ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኃላፊ ‹‹የሁለቱ ምክር ቤቶች አካሄድ የተለያየ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህንንም ሲያብራሩ የአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት ይዞት የነበረው ፈቃድ (የዕውቅና ሰርተፊኬት) ሙሉ ለሙሉ ታግዶ እንደ አዲስ ነው የተመሠረተው፡፡ ይህ ግን እንደ አዲስ ምሥረታ ሳይሆን ምክር ቤቱ እንዳለ በመሆኑና አመራሩም ስላለ የሚደረገው የምርጫ ማስተካከያ ነው፡፡ የተጣሱ ሕጎች ተስተካክለው ምርጫው እንዲደገም የማድረግ ሥራ ነው፡፡ የዘርፍ ምክር ቤቱ ደንብም የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጁም ሁሉንም የሚያስማማና በዚህ መሠረት የሚካሄድ ስለሆነ ችግር አይኖረውም፡፡ ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የተዋቀረውም ኮሚቴ በዚሁ መንፈስ በጋራ ለመሥራት በማለት ተናግረዋል፡፡

 

 

Standard (Image)

በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ለገበያ ቀረቡ

$
0
0

በዳዊት እንደሻው

ሮዝ ቢዝነስ ግሩፕ የተባለው ኩባንያ አካል የሆነው ሮዝ የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን ለኢትዮጵያ ገበያ አቀረበ፡፡

ከጃፓን እንደሚመጡ የተነገረላቸውና ‹‹የዋይ ፎር ግላስ›› ሥሪት የሆኑት እነዚህ መኪኖች፣ ገበያው ላይ ከሚገኙትና በነዳጅ ኃይል ከሚሠሩት ተመሳሳይ ተሽከርካሪዎች አኳያ በዋጋ እንደሚቀንሱ የድርጅቱ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡ ይሁንና የድርጅቱ ኃላፊ አቶ ሮቤል እስጢፋኖስ፣ የመኪኖቹን ትክክለኛም ሆነ ተቀራራቢ የመሸጫ ዋጋ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

መኪኖቹ በሳፋየር አዲስ ሆቴል በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ባለፈው ሳምንት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) ለገበያ ዝግጁ መሆናቸው ይፋ ተደርጓል፡፡

ከአካባቢ ብክለት ነፃ እንደሆኑና ባትሪያቸው ለአንድ ሰዓት በኤሌክትሪክ ኃይል ተሞልቶ ከ80 እስከ 100 ኪሎ ሜትር መጓዝ እንደሚችሉም የፋብሪካው ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

በቢሾፍቱ ከተማ በ10 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ላይ የተገነባው መገጣጠሚያ ፋብሪካ፣ በሰዓት አንድ የኤሌክትሪክ መኪና የመገጣጠም አቅም እንዳለው ተገልጿል፡፡

መኪኖቹን ለመገጣጠም በቂ ዝግጅት ተደርጎ ለገበያ ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን የኩባንያው መሥራች አቶ ሮቤል ተናግረዋል፡፡

ከ15 ዓመታት በፊት በደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ፅዳትና ማንሳት ሥራ የተጀመረው ሮዝ ቢዝነስ ግሩፕ በአሁን ወቅት ወደ ስምንት የሚጠጉ በማሽን ኪራይ፣ በፅዳትና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎች በሥሩ ይገኛሉ፡፡

በአሁን ወቅት ስምንቱ ኩባንያዎች ወደ 80 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል አላቸው፡፡

በተለይም ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ እንደ ባህርዳር፣ ድሬደዋ፣ እንዲሁም ሐዋሳ ከተሞች ውስጥ በብዛት የሚታወቁት ባለሦስት እግር መኪኖች፣ ሰፊ ተፈላጊነት ሲኖራቸው፣ በአሁን ወቅት እንደ ቲቪኤስ፣ ታግሮ ባጃጅና የመሳሰሉት በነዳጅ ኃይል የሚሠሩ ባለሦስት እግር መኪኖች ገበያውን መቆጣጠራቸው ይታወቃል፡፡   

 

Standard (Image)

የቻይናው መሪ ለአፍሪካውያን ቢጤያቸው ‹‹እንዳገኛችሁ አትገልብጡ›› ይላሉ

$
0
0

- ለቻይና ያደላው የንግድ ሚዛን እንዲመጣጠን ኢትዮጵያ ትጠይቃለች

የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢፒንግ በቻይና የድህነት ቅነሳ ላይ ያጠነጠነ መጽሐፍ ከወራት በፊት ለንባብ ያበቁ ሲሆን፣ በዚህ ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በተካሔደው የቻይና-አፍሪካ ከፍተኛ የምክክርና የምሁራን ፎረም ከመጽሐፉ አንቀጾች እየተጠቀሱለት ሲብራራ ታይቷል፡፡ አንደኛው ነጥብም በጥሬው ‹‹ያገኛችሁትን አትገልብጡ›› (Don’t copy everything…) የሚል መልዕክት እንደሚገኝበት ተጠቅሷል፡፡

በዚሁ ፎረም እገረ መንገዳቸውን የተገኙት የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ፣ ይህንኑ መልዕክት ለአፍሪካውያኑ አስተጋተዋል፡፡ ፖሊሲዎችን ከየትም ቦታ እንዳሉ ከነነፍሳቸው ከመገልበጥ ይልቅ ለአገርና ለሕዝብ ነባራዊ ሁኔታዎች እንደሚስማማ፣ ከአገርና ከሕዝብ አንገብጋቢ ችግሮች አኳያ የሚስማማ የፖሊሲ ሐሳብ ብትጋሩ ይሻላችኋል የተባለበት መድረክ ነበር፡፡ ከቻይናውያኑ ባሻገር ስለመጽሐፉ በጨረፍታ እያጣቀሱ ማብራሪያ ከሰጡት መካከል፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የኢኮኖሚ ዕቅድ ውጤታማነትና ክትትል ድጋፍ ዘርፍ ሚኒስትር ኃላፊው ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ይጠቀሳሉ፡፡

ዶ/ር አርከበ የኢትዮጵያን የድህነት ቅነሳ ውጤቶች ባብራሩበት የቻይና አፍሪካ ከፍተኛ የምክክር ፎረም ወቅት በዓበይትነት የተጠቀሰው ጉዳይ ከቻይና በርካታ የልማት ፖሊሲዎች ልምድ መቀሰሙ ነው፡፡ ቻይና ለአፍሪካ የልማት ፖሊሲ ዓቢይ ሞዴል ነች ያሉት ዶ/ር አርከበ፣ በፖሊሲ ረገድ ኢትዮጵያ ከቻይና በተማረችው መሠረት 60 በመቶ ዓመታዊ በጀቷን ለመሠረተ ልማት አውረታሮች እንደምታውል ለታዳሚው አብራርተዋል፡፡ እርግጥ ነው ቻይና ብቻም ሳትሆን አብዛኛው የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች በተለይም እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ቬትናም እና ሲንጋፖር ያሉ አገሮች ለአፍሪካውያን የልማት ተምሳሌቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከእነዚህ አገሮች በተገኙ ተሞክሮዎችና በተቀሰሙ ልምዶች ኢንዱስትሪ ተኮር ኢኮኖሚ ለመገንባት ስለተነሳው መንግሥታቸው ያብራሩት ዶ/ር አርከበ፣ በኢኮኖሚ መስክ ብቻም ሳይሆን በማኅበራዊ መስኮች የተገኙ ለውጦችን ጠቃቅሰዋል፡፡ ዋቢ ሲያደርጉም፣ በ1983 ዓ.ም. የአገሪቱ ሕዝብ አማካይ የመኖር ዕድሜ ወይም የዕድሜ ጣሪያ 45 ዓመታት እንደነበር አንስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ይህ ወደ 65 ዓመታት በማሻቀቡ፣ በአማካይ የ20 ዓመታት የዕድሜ ጭማሪ የታየው በአገሪቱ ተደራሽ የጤና መሠረተ ልማት በመስፋፋታቸው፣ የትምህርት መሠረተ ልማት አውታሮች በመጨመራቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በሩብ ክፍለ ዘመን ውስጥ ለታየው ለውጥ መንግሥት 70 በመቶውን በጀት ደሃ ተኮር ለሆኑ ሥራዎች በመመደቡ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሦስት መሠረታዊ ችግሮችን ይፈታል የተባለውን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ መንግሥት እያስፋፋ እንደሚገኝ ሲጠቅሱም አንደኛው የሥራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ በሰው ጉልበት የሚታገዙ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ እየተደረገ መሆኑ፣ ሁለተኛው አገሪቱ የሚታይባትን የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ለመቅረፍም የሚስፋፉት ማምረቻዎችና ምርቶቻቸው ለውጭ ገበያ በገፍ የሚቀርቡባቸው መሆናቸውን ከዶ/ር አርከበ ማብራሪያ መጨለፍ ይቻላል፡፡

በኢትዮጵያ የሚስፋፋው ኢንዱስትሪ ትልቅ የተባለውን የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን እያሳበ መሆኑም የኢትዮጵያ የልማት ፖሊሲ ከትክክለኛው ምንጭ ለመቀዳቱ አስረጅ ተደርጓል፡፡ በቅርቡ ይፋ የተደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ ሪፖርት ከአምስት የዓለም ዋና ዋና የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ አገሮች ተርታ ኢትዮጵያ አንጎላን ተከትላ በሁለተኛነት እንደምትጠቀስ አስነብቧል፡፡ በሪፖርቱ መሠረት ኢትዮጵያ ባህር አልባ፣ እንደ ነዳጅ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ከሌላቸው አገሮች ተርታ የምትመደብ ሆና ሳለ፣ ሁለቱም ሀብቶች ካላቸው አገሮች ይልቅ ኢትዮጵያ የ3.2 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገበ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን እንደበቃች ይፋ አድርጓል፡፡

እነዚህ ነጥቦች ያነሱት ዶ/ር አርከበ ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢፒንግ መጽሐፍ ሲያጣቅሱ ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹አፕ ኤንድ አውት ኦፍ ፖቨርቲ›› ብለው በሰየሙት መጽሐፋቸው ውስጥ የታሪክ ዳራ ያደረጉት እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ ይኖሩባት ከነበረችውና በፉጂያን ግዛት ውስጥ በምትገኘው ኒግዴ በተባለችው የትውልድ መንደራቸው ውስጥ የነበረውን አስከፊ ድህነት እንዴት እንዳሸነፉ፣ ሐሳባቸውና ልምዳቸው የተካተቱበት መጽሐፍ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

ቻይና ለአፍሪካ ከምትሰጠው ድጋፍ አኳያ ከፖሊሲ ሞዴልነት ባሻገር በምታቀርበው ከፖለቲካ ጫናዎች ነፃ የሆነ የፋይናንስ አቅርቦት ረገድም ተወድሳለች፡፡ በዚህ ወቅት እንደ ዶ/ር አርከበ ሁሉ፣ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሕመትም ተመሳሳይ ነጥብ አንስተዋል፡፡ ቻይና የአፍሪካ የቀኝ አጋር ካሰኟት ምክንያቶች ሚዛን የሚደፋውም ይኸው ግራና ቀኝ የሌለው፣ ይህን አድርጉም አታድርጉም የሌለበት፣ የፖሊሲ ነፃነታችንን ያከበረ ብድር መስጠቷ ትልቅ ቦታ አለው ብለዋል፡፡

ይህም ሆኖ ግን አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ከቻይና ጋር ያላቸው ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በቻይና የበላይነት የሚቃኝ መሆኑም በግልጽ ተጠቅሷል፡፡ አፍሪካ የቻይና የጥሬ ዕቃና የተፈጥሮ ሀብት ማዕከል ብቻ መሆን እንደሌለባት ያሳሰቡት ዶ/ር አርከበ፣ ‹‹የተፈጥሮ ሀብት ላኪዎች ሆነን መቀጠል የለብንም፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሳይገደቡ በቻይና እና በአፍሪካ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ሚዛኑ ይስተካከል በማለትም ቻይናን ጠይቀዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 በቻይና እና በአፍሪካ አገሮች መካከል የነበረው የንግድ ልውውጥ 230 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር አርከበ፣ የዚህን አሐዝ አብዛኛውን ድርሻ የያዘችው ቻይና ስትሆን፣ የአፍሪካውያኑ ድርሻ ግን አምስት በመቶ ገደማ በመሆኑ ይህ ሊሻሻል ይገባዋል ብለዋል፡፡

ምንም እንኳ የቻይና ኢንቨስትመንት በአፍሪካ ከአምስት በመቶ ያልበለጠ ቢሆንም በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ ግን በአፍሪካ ትልቁን የኢንቨስትመንት ድርሻ በመያዝ ቻይና ትልቋ እንደምትሆን የአሜሪካውን አማካሪ ኩባንያ፣ የማኬንዚን ይፋ ያልወጣ ጥናት ዋቢ ያደረጉት ዶ/ር አርከበ፣ በጠቅላላው ከቻይና የሚገኘው ድጋፍም ሆነ የሚካሔዱ የትብብር ግንኙነቶች ጠቀሜታን አብራርተዋል፡፡

አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቶች ምንጭ ሆና ሳለ ለምን ደኸየች ሲሉ ሙሳ ፋኪ ላቀረቡት ጥያቄ፣ አፍሪካ የባሪያ ንግድ ማዕከል ሆና መቆየቷና የቅኝ ግዛት ሰለባ መሆኗ ለድህነቷ አስተዋጽኦ ያበረከቱ እውነታዎች ናቸው ሲሉ ምላሻቸውን አቅርበዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ከቻይናው ኢንስቲትዩት ኦፍ አፍሪካን ስተዲስ ኦፍ ዚያንግ ኖርማል ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ያሰናዱት ይህ የምክክር ፎረም፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰናዳው በሁለቱ ተቋማት ትብብር ቢሆንም ሰሞኑን ሲካሔድ ግን ለስድስተኛ ጊዜው እንደሆነ ታውቋል፡፡

  

Standard (Image)

የንግድ ምክር ቤቱ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ዲዛይን እንዲለወጥ ተወሰነ

$
0
0

 

  • የአዲሱ ሕንፃ ዲዛይን ቦርዱን አሟግቷል

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዋና መሥሪያ ቤቱን ሕንፃ ለማስገንባት በማሰብ ከዚህ ቀደም ያወጣውን ዲዛይን በሌላ እንዲቀየር ተወሰነ፡፡

ከንግድ ምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት፣ ከሦስት ዓመታት በፊት ለመገንባት የወጠነውን የሕንፃ ዲዛይን እንዲሠሩለት የሥነ ሕንጻ ኩባንያዎችን በማወዳደር ከአሸናፊው ድርጅት ጋር የተዋዋለበትን የዲዛይን ሥራ በመረከብ ለግንባታ ሲዘጋጅ ቆይቶ ነበር፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ የዲዛይን ለውጥ ለማድረግ የሚያስገድደውን ውሳኔ የወሰነው፣ ቀደም ብሎ ያሠራው ዲዛይን ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ ለግንባታ የሚውል ቦታ እንደሚሰጠው በገመተው ቦታ ላይ ለሚገነባ ባለዘጠኝ ወለል ሕንፃ የሚስማማ ዲዛይን በማሠራቱ ነበር፡፡

ሆኖም ቀደም ብሎ ለግንባታ እንዲሰጠው ጥያቄ ያቀረበበትን ቦታ የከተማው አስተዳደር ሳይቀበለው በመቅረቱና በምትኩ በሌላ አካባቢ ቦታ ስለተሰጠው በዚሁ አግባብ ዲዛይኑን ለመቀየር እንደተገደደ ታውቋል፡፡ በመሆኑም አዲስ ዲዛይን በድጋሚ ለማሠራት ወስኗል፡፡

ዲዛይኑን በመለወጥ አዲስ ለማሠራት የሚያስቸለውን ውሳኔ ለማስተላለፍ የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ አባላት እርስ በርስ ሙግት ውስጥ ገብተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአዲስ መልክ ይሠራል የተባለውን ዲዛይን ማን ይሥራው የሚለው ጉዳይ የቦርድ አባላቱን ለሁለት ከፍሎ እንዳከራከረ የገለጹት የሪፖርተር ምንጮች፣ አንደኛው ወገን አዲስ በተሰጠው ቦታ ላይ ለሚገነባው ሕንፃ ሌላ ዲዛይን ለማሠራት ሥራውን ለሚሠሩ አማካሪዎች ጨረታ እናውጣ የሚል አቋም አራምዷል፡፡ ሌላኛው የምክር ቤቱ አመራር አካል በበኩሉ አዲሱን ዲዛይን ከዚህ ቀደም ለንግድ ምክር ቤቱ የባለዘጠኝ ወለል ሕንፃ ዲዛይን ለሠራው ኩባንያ በድጋሚ ይሰጠው በማለቱ፣ በሁለት ሐሳቦች መካከል በተነሳው የሐሳብ ልዩነት ለውሳኔ ተቸግረው እንደነበር ታውቋል፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት ንግድ ምክር ቤቱ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ እንዲሰጠው አመልክቶ የነበረውን ቦታ ታሳቢ በማድረግ ባለዘጠኝ ፎቅ ሕንፃ ለማስገንባት አሸናፊ የሆነውን ዲዛይን የሠራው አማካሪ ድርጅት ለዲዛይኑና ለማማከሩ ሥራ የሁለት ሚሊዮን ብር ኮንትራት ተፈራርሞ ነበር፡፡ እንደ አዲስ ዲዛይኑ ይሠራ የሚሉት የቦርድ አባላት፣ ሥራው አዲስ በመሆኑ ጨረታ መውጣት አለበት ብለው ቢሟገቱም በድምጽ ተበልጠው የቀድሞውን ዲዛይን ለሠራው ኩባንያ ተሰጥቷል፡፡

በመሆኑም ለአዲሱ ባለ 12 ወለል ሕንፃ ዲዛይን ጨረታ ማውጣት ሳያስፈልግ የዲዛይን ሥራውን ከሦስት ዓመት በፊት እንደሚገነባ ለታሰበው ባለዘጠኝ ወለል ሕንፃ ዲዛይን በመሥራት አሸናፊ ለሆነው ኩባንያ ይሰጥ የሚለው ቡድን በአብላጫው በማሸነፉ በዚሁ መሠረት ስምምነት ላይ እንደተደረሰ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በዚህ ውሳኔ ያልተስማሙት ወገኖች፣ ሥራው አዲስ በመሆኑ ጨረታ ሊወጣ ይገባል፣ ያለ ጨረታ ቀድሞ ለሠራው ኩባንያ ዳግም ይሰጥ መባሉ ትክክል አይደለም በማለት ሞግተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አንጋፋ ከሚባሉት የአገሪቱ ንግድ ምክር ቤቶች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን የራሱ የሚለው ሕንፃ ባለመኖሩ አዲሱን ሕንፃ በቶሎ ለማስጀመር ፍላጎት ያለው መሆኑ ታውቋል፡፡ እስከ 500 ሚሊዮን ብር ይፈጃል የተባለውን ይህን ሕንፃ በመስከረም 2010 ለመጀመር ያቀደ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን አዲሱ ዲዛይን ለውጥ ግን ሥራ ሊያዘገየው ይችላል የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡ 

Standard (Image)

በቡና ግብይት ሒደት ውስጥ አዳዲስ አሠራሮች ከመጪው ወር ጀምሮ ይተገበራሉ ተባለ

$
0
0

 

ውስብስብ ችግሮች ጠፍንገው እንደያዙት ሲገለጽ የቆየውን የአገሪቱን የቡና ግብይት ሥርዓት በማስያዝ በተሻለ መንገድ እንዲጓዝ ያስችላሉ የተባሉ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ ከማሳ እስከ ግብይት ከዚያም አልፎ የወጪ ንግዱ ላይ የሚታየው የእሴት ሰንለሰት ላይ መሠረታዊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ የሚያሰረዱ አዳዲስ አሠራሮችን ለመቅረጽም እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሰፊው ሲመከርበት የቆየው የቡና ጉዳይ ችግሮቹ ተለይተው መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉ ውሳኔዎች ተወስነው ወደ አፈጻጸም እንዲገባም ተደርጓል፡፡ እንደ መፍትሔ የተቀመጡ በርካታ የአሠራር ለውጦችን ያካተተ፣ የአገሪቱን የቡና ግብይት ሥርዓት በበላይነት የሚመራና የሚገዛ አዲስ አዋጅ መቅረፅ አንዱ ዕርምጃ ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት ለቡና ሪፎርም ሥራዎች አንጓ ይሆናል የተባለው የቡና ግብይትና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ሰሞኑን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ይህንን ረቂቅ ሕግ ሲገመግም የቆየው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቁን በያዝነው ሳምንት አጋማሽ በማፅድቁ፣ ለተወካዮች ምክር ቤት ተልኮ ሕግ ሆኖ የሚወጣበት ቀን እየተጠበቀ ይገኛል፡፡

እስካሁን የነበረውን የቡና ግብይት መሠረታዊ ነው በተባለ መንገድ ይለወጣል የተባለውን ይህንኑ ረቂቅ አዋጅ ያፀደቀው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ እንደላከው ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

አዲሱ ረቀቅ አዋጅ አጠቃላይ ከምርት ጀምሮ ወደ ውጭ እስኪላክ ድረስ መከወን ይገባዋል የተባሉ አዳዲሶቹን የታመነባቸውን አሠራሮችና እነዚህ አሠራሮች ተፈጻሚ የሚሆኑበትን ድንጋጌ የያዘ ነው፡፡

የቡና ባለድርሻ አካላት በጋራ ስምምነት የደረሱባቸውን ነጥቦች አካቶ የተረቀቀው ይህ አዋጅ ከዚህ በኋላ በአገሪቱ የቡና ግብይት ውስጥ ከፍተኛ ሚና በሚኖረው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ነው፡፡ እንደ ባለሥልጣኑ መረጃ ከሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የደረሰው ረቂቅ አዋጅ በቅርቡ ፀድቆ በአዲሱ በጀት ዓመት ተግባራዊ እንደሚሆን እየተጠበቀ ነው፡፡

ባለሥልጣኑ እንደሚጠቅሰው፣ የረቂቅ አዋጁ መፅደቅ በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ሕግ ሆኖ የሚወጣበት ሒደት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከአዋጁ የማይቃረኑና የአዋጁን ድንጋጌዎች የማያፋልሱ አዳዲስ አሠራሮች ግን ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡

በሪፎርሙ መሠረት ከቡና ግብይት ጋር ተያይዘው ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት አሠራሮች ውስጥ ቡናን በመኪና ላይ ሳለ መገበያየት መቻል አንዱ ነው፡፡

በአዲሱ አዋጅ ውስጥ የሚካተቱ ሆነው የአዋጁን መፅደቅ ሳይጠብቁ ይተገበራሉ ከተባሉት ሌሎች አዳዲስ አሠራሮች ውስጥ ቡና አቅራቢዎች ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ውጭ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡበት አሠራር ይገኝበታል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያም ቢሆን በአዲሱ አሠራር መሠረት ራሱን ያደራጀ በመሆኑ፣ አዳዲሶቹን አሠራሮች ይተገብራል ተብሏል፡፡ በአዲሱ በጀት ዓመት በአዲስ አሠራሮችና የግብይት ሒደቱም በጠቅላላው በአዲሱ አዋጅ የሚመራበት የቡና እሴት ሰንሰለት እንደሚፈጠር የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከግብይት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የሚሠሩ ተቋማትም ለአዲሱ አሠራር በሚመች መንገድ ዝግጅት እንዳደረጉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

እንደ ትልቅ ለውጥ የሚጠበቀው ሌላው ጉዳይ፣ በምርት ገበያው ወንበር ገዝተው በአገናኝነት በሚሠሩ አባላት በኩል ግብይት የሚፈጸምበት አሠራር የግድ መሆኑ ቀርቶ ተገበያዮች ከፈለጉ ብቻ የሚገበያዩባቸው እንዲሆኑ ይደረጋል የሚለው ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ቀድሞው አካሄድ የቡና ግብይት በምርት ገበያው ባለወንበሮች አገናኝነት ይፈጸም የሚለው አስገዳጅ አሠራር ይቀራል፡፡ የቡና ግብይት ተዋናዮች ምርቶቻቸውን ከፈለጉ ብቻ በምርት ገበያ ውስጥ ባሉ አገናኞች መሸጥ የሚችሉ ሲሆን፣ ካላስፈለጋቸው ግን ቡና አቅራቢዎቹ በቀጥታ በምርት ገበያ ውስጥ የራሳቸውን ምርት ለመሸጥ የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡ እስካሁን ግን ቡና አቅራቢም ሆነ ላኪ በቡና ግብይት ውስጥ ተገበያይቶ ቡናውን መሸጥና መግዛት የሚችለው በምርት ገበያው ወንበር ባላቸው አገናኞች አማካይነት ብቻ እንደነበር ይታወሳል፡፡  

በዚሁ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቀጥታ ይገበያዩ የነበሩ የቡና ዓይነቶች ውስጥ የልዩ ጣዕም ወይም የስፔሻሊቲ ቡናዎች ተብለው የሚታወቁትን ቡናዎች የሚገበያዩም በሚያመቻቸው መንገድ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚችሉበትን አሠራር አዋጁ ይደነግጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ በቡናው ዱካ ወይም በአካባቢው ስም የመሸጥ መብትም የዚህ ድንጋጌ አካል እንደሚሆን ታውቋል፡፡

ቀድሞ ብልሹ አሠራር ይታይባቸዋል የተባሉ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት አሠራር ላይ ለውጥ ያመጣል የተባለው አዲሱ ቡና ከምርት ጀምሮ ለውጭ ገበያ እስኪቀርብ ድረስ ያለውን ረዥም ሰንሰለት ለማስቀረት የሚያስችሉ ድንጋጌዎች እንደሚኖሩት ተጠቁሟል፡፡

የቡና ዘርፍን የተመለከተው ሪፎርም ከአዋጁ ቀደም ብለው የተወሰዱ ዕርምጃዎች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ከነዚህ ዕርምጃዎች ውስጥ የኢትዮጵያ የምርት ገበያ ባለሥልጣን ተጠሪነት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ወደ ንግድ ሚኒስቴር መዛወሩ አንዱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያና የመጋዘን አገልግሎት ድርጅት እንዲዋሃዱ መወሰኑም የዚህ የሪፎርም አካል ነው፡፡ የአገሪቱን የቡና ዘርፍ በበላይነት የሚመራ ብሔራዊ ምክር ቤት እንዲቋቋም መወሰኑም ይታወሳል፡፡

ይህ ለውጥ በተለይ የአገሪቱን የቡና የወጪ ንግድ ከማሳደግ አንፃር ጠቀሜታ የሚኖረው ሲሆን፣ የቡና ምርትን ለማሳደግ፣ እሴት የተጨመረበት የቡና ምርት ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ ጭምር ዕድል ይሰጣል፡፡ አዲሱ ድንጋጌ እሴት የተጨመረባቸው የቡና ምርቶችን የሚልኩ ኩባንያዎች እንደማንኛውም ተገበያይ ቡናን ከምርት ገበያው ተጫርተው የሚገዙበት አሠራር ይፈቅድላቸዋል፡፡

 

Standard (Image)

በግብርና ንግድ ሥራ የተሠማሩ ወጣቶች ለመሠረቷቸው የግብርና ማዕከላት ድጋፍ አገኙ

$
0
0

 

በኦሮሚያ ክልል በአነስተኛ ገበሬዎች ላይ ያተኮሩ የግብርና ንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩት ወጣቶች ጽጌሬዳ ሰሎሞንና አብርሃም እንድሪያስ ይባላሉ፡፡ ሁለቱም በግብርና መስክ ለአነስተኛ ገበሬዎች አገልግሎት ከዚህ ቀደም ሲሰጧቸው የነበሩ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት የግብርና ማዕከላት የሚመሠርቱባቸውን ድጋፎች ከጀርመን መንግሥት አግኝተዋል፡፡

ጽጌረዳ ሰሎሞን በሙያዋ ላቦራቶሪ ቴክኒሻን ብትሆንም፣ በግብርና ግብዓቶች አቅርቦት ንግድ መስክ በ1999 ዓ.ም. የሚንቀሳቀስና ጽጌሬዳ የግብርና ግብዓቶች አቅራቢ ድርጅት የተባለውን መደብር በኦሮሚያ፣ ሉዴ ሒጦሳ ወረዳ ውስጥ ከባለቤቷ አቶ ታደሰ ፀጋዬ ጋር በመሆን ስትሠራ ቆይታለች፡፡

የጀርመን መንግሥት በጂአይዜድ አማካይነት ከሚሰጣቸው ድጋፎች መካከል የግብርና አግልግሎት ማዕከላት ፕሮጀክት የተሰኘው አንዱ ሲሆን፣ ይህንን በሚያስፈጽመው፣ ‹‹ከልቲቬቲንግ ኒው ፍሮንታየርስ ኢን አግሪካልቸር- ሲኤንኤፍኤ›› በተባለ ተቋም አማካይነት ፕሮጀክቶችን እያስፋፋ ይገኛል፡፡ በዚህ ተቋም አማካይነት ድጋፍ ካገኙ መካከል የሆነችው ጽጌሬዳ፣ በኬሚካል፣ በዘር አቅርቦት መስክ ስታከናውን በቆየችው ሥራ በኩል የ30 ሺሕ ዩሮ ግምት ያለው የዓይነት ድጋፍ አግኝታለች፡፡ ለዚህ ድጋፍ መጠይቅ ከሆኑት ዋናው ተመጣጣኝ የገንዘብ መጠን ያለው መዋጮ ማድረግና ቀጣይነቱ የሚያስተማምን የግብርና ንግድ ሥራ ውስጥ መገኘት እንደሆነ ያብራራችው፣ የተቋሙ የፕሮግራም ኃላፊ ወይዘሪት ርብቃ አምሃ ነች፡፡ እንደ ወይዘሪት ርብቃ ማብራሪያ ከሆነ እኩል መጠን ያለውና በዓይነት የሚደረገው መዋጮ ለወደፊቱም ዘላቂነት ያለው የግብርና ንግድ ሥራ እንዲኖር፣ አነስተኛ ገበሬዎችም ከዚህ አገልግሎት በዘላቂነት መጠቀም እንዲችሉ ታስቦ የዘተረጋ ፕሮግራም እንደሆነ ገልጻለች፡፡

በመሆኑም ጽጌሬዳና ባለቤቷ በሚሠሩበት ከተማ የፕሮጀክቱ ዕድል በመጣበት ወቅት ተወዳድረውና እንዲያሟሉ የተጠየቋቸውን መስፈርቶች አሟልተው በመገኘታቸው የ30 ሺሕ ግምት ያለው ሙሉ የግብርና ግብቶች፣ መለዋወጫዎችና ሌሎችም እንደሚሟሉላቸው ጽጌሬዳ አብራርታለች፡፡ የዕቃዎቹ ርክክብም በመጪው ዓመት ህዳር ወር እንደሚደረግ ከተደረገው ስምምነት ለመረዳት ተችሏል፡፡

ወጣት አብርሃም እንድርያስ በበኩሉ ግሪን አግሮ ሶሉሽን የተባለ ኩባንያ መሥራች ሲሆን በዲጋሉ ጢጆ ወረዳ ውስጥ የሳጉሬ ግብርና አገልግሎት ማዕከልን በመመሥረት ለገበሬዎች የሜካናይዜሽን አገልግሎት፣ ለዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ለቴክኒክና ሙያ ተመራቂዎች በሜካናይዜሽን እርሻ መስክ ሥልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ልዩ ልዩ የእርሻ መሣሪዎችን በማከራየትም ይቀሳቀሳል፡፡

አብርሃም የያንግ አፍሪካ ሊደርስ ኢኒሺዬቲቭ የአምና ተሳታፊ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከታዋቂው የአሜሪካው ፐርዱ ዩኒቨርሲቲ ጋር ለግብርና ግብዓቶችና ምርት ማጓጓዣ፣ ብሎም ለሜካናይዜሽን እርሻ የሚረዳ ተሽከርካሪ በአገር ውስጥ ለማምረት ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር አብሮ እየሠራ ይገኛል፡፡ እሱም የ30 ሺሕ ዩሮ ግምት ያላቸው ለሥልጠና የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችለውን ቅድመ ሁኔታ በማሟላቱ የዕድሉ ተሳታፊ ለመሆን በቅቷል፡፡

ይህ ፕሮጀክት በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን እስካሁን ዋና መዳረሻውን በአርሲ ዞን በማድረግ የሮቤ፣ የኢተያ፣ የአሰላ፣ የሳጉሬ እንዲሁም የሁሩታ ግብርና አገልግሎት ማዕከላት የተባሉትን አምስት አነስተኛ የግል ድርጅቶች ለመመሥረት ለእያንዳንዳቸው 30 ሺሕ ዩሮ መጠን ያላቸው ልዩ ልዩ የቁሳቁስ ድጋፎችን አቅርቧል፡፡

ፕሮግራሙ ለመጪዎቹ አራት ዓመታት ሊቆይ እንደሚችል ከወይዘሪት ርብቃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በእስካሁኑ የሙከራ ሒደት ድጋፍ ባገኙት አምስት የግብርና አገልግሎት ማዕከላት አማካይነት የ375 ሺሕ ዩሮ ግምት ያላቸው ሸያጮችን ማከናወን እንደተቻለ፣ ለ25 ሺሕ ደንበኞችም ምርቶችና አገልግሎቶችን ማዳረስ እንደተቻለ፣ ከ1,600 በላይ ገበሬዎችንም ለማሠልጠን እንደተቻለ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

በጀርመን መንግሥት በአነስተኛ ግብርና መስክ ድጋፍ ከሚደረግበት የማዕከላት ማቋቋሚያ ድጋፍ ባሻገር፣ በአሜሪካ መንግሥት የሚደገፉ 26 ፕሮጀክቶችም በአገር አቀፍ የተቋቋሙ ሲሆን፣ እነዚህን ማዕከላት የሚመሠርቱ ሰዎችም ከ40 እስከ 50 ሺሕ ዶላር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ እንደተደረገላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

 

Standard (Image)

ደቡብ ኮሪያ ለኢትዮጵያ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ማስተር ፕላን ድጋፍ እንደምትሰጥ አስታወቀች

$
0
0
  • የከተማ የውኃ ፍሳሽ አወጋገድና ሳኒቴሽን ተዘንግቷል ተብሏል

በደቡብ ኮሪያና በኢትዮጵያ መካከል በበርካታ መስኮች ጠንካራ የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚና የባህል ግንኙነቶች በመሠረትም፣ በአካባቢ ጉዳይ ላይ ያን ያህል የጠበቀ ግንኙነት ባለመኖሩ በዚህ መስክ በተለይም በፍሳሽ ውኃ ማጣሪያ ፕሮጀቶች ላይ የማስተር ፕላን ዝግጅት ላይ ድጋፍ ለመስጠት መዘጋጀቷን አስታወቀች፡፡

የደቡብ ኮሪያ የንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ያዘጋጀውና የኮሪያ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲሁም የኮሪያ የአካባቢ ጥበቃ፣ የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተወካዮች የታደሙበት የኮሪያ ኢትዮጵያ የአካባቢ ፎረም በዚህ ሳምንት አጋማሽ ሲካሔድ እንደተገለጸው፣ ለውኃ ፍሳሽ ማጣሪያ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ዝቃጭ አወጋገድ ሥርዓት ማስተናገጃ የሚውል ማስተር ፕላን በማዘጋጀት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ይደረጋል፡፡

ዶ/ር ሊ ቻንግ ሒም፣ በደቡብ ኮሪያ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ሥር ለሚገኘው የአካባቢ ጥበቃ፣ የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲ ቢሮ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ዶ/ር ቻንግ ሒም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የውኃ ፍሳሽ ማጣሪያ ማስተር ፕላን ፕሮጀክቱ በሁለቱ አገሮች መካከል ለሚደረግ የአካባቢ ጥበቃ የሁለትዮሽ ግንኙነት መመስረቻ ይሆናል፡፡

 

በመጪው ዓመት ሥራው ይጀመራል ያሉት የማስተር ፕላን ዝግጅት ሥራው ሦስት የተመረጡ ከተሞችን ሊያካልል እንደሚችል ዶ/ር ቻንግ ሒም አስታውቀዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ምን ያህል ገንዘብ ሊጠይቅ እንደሚችል ለማወቅ በአገሪቱ በፍሳሽ አወጋገድ መስክ ያሉ መረጃዎችን ማጠናቀር እንደሚጠይቅና በርካታ ዝርዝር ሥራዎችም እንደሚካሔዱ ገልጸዋል፡፡ ሥራው ገና ጅምር ላይ በመሆኑ ኮሪያውያኑ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ለማወቅ የመረጃ ልውውጥ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሥራው እንደሚጠናቀቅ የተጠቀሰው ይህ ፕሮጀክት፣ ኮሪያ በየዓመቱ ለአገሮች የምታደርገው የአካባቢ ጥበቃ ድጋፍ አካል ሲሆን፣ በአፍሪካ ከሞዛምቢክ በመከተል ኢትዮጵያ የዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ እንደምትሆን ዶ/ር ቻንግ ሒም ጠቅሰዋል፡፡

ከኮሪያ መንግሥት ባሻገር የኮሪያ ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ የውኃ አቅርቦትና የፍሳሽ ማጣሪያ ሥራዎች ውስጥ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው በፎረሙ አስታውቀዋል፡፡ ከመንግሥትና ከግል የተውጣጡ 20 ተሳታፊዎች በተሳተፉበት መድረክ፣ ልምዳቸውን ያካፈሉ ኩባንያዎች በደረቅና በፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ መስክ ስለሚሠሯቸው ሥራዎች አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል የግል ኩባንያዎችን ጨምሮ የመንግሥት ተወካዮችም ተገኝተዋል፡፡ በውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ሥር የውኃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን አገርአቀፍ ፕሮጀክቶች አስባባሪ አቶ ታምሩ ገደፋ እንዳብራሩት፣ በዚህ ዓመት ይፋ የተደረገውና ከዓለም ባንክ በተገኘው የ500 ሚሊዮን ዶላር ብድር (የመንግሥትን የ60 ሚሊዮን ዶላር መዋጮ ይጨምራል)፣ በአዲስ አበባና በ22 ሁለተኛ ደረጃ ከተሞች የሚተገበረው የውኃና የሳኒቴሽን ፕሮግራም ከ3.3 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦችን በውኃ አቅርቦትና በሳኒቴሽን ሥራዎች ተጠቃሚ ለማድረግ ለመጪዎቹ ስድስት ዓመታት እንደሚተገበር ገልጸዋል፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት የተጀመረው ሌላኛው የአምስት ዓመት ፕሮጀክትም በዓለም ባንክ፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ በመንግሥትና በሌሎችም አበዳሪዎችና ለጋሾች የሚደገፈው አገር አቀፉ የውኃ፣ የሳኒቴሽንና የሃይጂን ፕሮግራም (ዋን ዋሽ ናሽናል ፕሮግራም) የ485 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት 382 ወረዳዎች፣ 124 አነስተኛና 20 መካከለኛ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ስድስት ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ እንሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

ይህም ሆኖ መንግሥት በአምስቱ ዓመት ዕቅዱ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የያዘላቸው ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም፣ ከፍተኛ የፋይናንስ ችግሮች እንዳጋጠሙት አቶ ታምሩ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በከተማና በገጠር አካባቢዎች የውኃ አቅርቦትና የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓቶችን ለመገንባት እየጣረ ቢሆንም፣ በተለይ የከተማ ፍሳሽ ውኃ አወጋገድ በእጅጉ የተረሳ መስክ እንደሆነ አቶ ታምሩ ገልጸዋል፡፡ አብዛኞቹ ፋብሪካዎችም የፍሳሽ አጋገድ ሥርዓት የጎደላቸውና ተገቢውን ሥርዓት ያልተከተሉ በመሆናቸው፣ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር አኳያ ትልቅ ሥጋት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

የምግብ አምራቾች ቅደመ ምዝገባን የሚደነግግ ረቂቅ መመርያ እየተዘጋጀ ነው

$
0
0
  • ምግብ ማቀናበሪያዎች መመርያው እንዲስተካከል ባሏቸው ነጥቦች ላይ ሐሳብ አቅርበዋል

የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ሰሞኑን ባዘጋጀው መድረክ የምግብ አምራቾች በምግብ አቀነባባሪነት ለመመዝገብ ከመጠየቃቸው በፊት ሊያሟሉ ይገባቸዋል የተባሉ ዝርዝር ነጥቦችን የሚደነግግ ረቂቅ መመርያ ለውይይት አቅርቧል፡፡

ባለሥልጣኑ ባለፈው ሳምንት በጠራው የውይይት መድረክ ወቅት ይፋ የተደረገው ረቂቅ መመርያ፣ ምግብ አምራቾች ፈቃድ ከማግኘታቸው በፊት ሊያሟላ ይገባቸዋል በማለት የዘረዘራቸውን መጠይቆች ከአዋጅ ቁጥር 661/2002 እንዲሁም ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 299/2006 ጋር በማዛመድ አቅርቧል፡፡ ‹‹የምግብ ማምረቻ ተቋማት የቅድመ ፈቃድ መመርያ›› የተሰኘው አዲሱ ረቂቅ መመርያ፣ ምግብ አምራቾችን በአምስት ምድብ በማስቀመጥ ትርጓሜ ሰጥቷቸዋል፡፡ ለልዩ የምግብ ንጥረ ነገር ፍላጎት የሚዘጋጁ ምግቦች አምራች፣ በከፍተኛ ደረጃ ለብልሽት ተጋላጭ ምግቦች አምራች፣ የዝቅተኛ ደረጃ ለብልሽት ተጋላጭ ምግቦች አምራች፣ አነስተኛ ምግብ አምራች እንዲሁም ከፍተኛ ምግብ አምራች በማለት መድቧቸዋል፡፡

በዚህ መሠረት ልዩ የምግብ ንጥረ ነገር ፍላጎትን ለማሟላት የሚዘጋጁ ምግቦች አምራች የሚባሉት በልዩ የቅንብር ሁኔታ ለተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚቀርቡ ሆነው ተጨማሪ ምግብ፣ የጨቅላ ሕፃናት ምግቦች፣ የታዳጊ ሕፃናት፣ የጨቅላና ታዳጊ ሕፃናት ማሟያ ምግብ፣ ምግብ ንጥረ ነገር እጥረት ለተጎዱ ሰዎች የሚቀርቡ እንዲሁም ጤናቸው በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት ለተጎዳ ሰዎች ታስበው የሚመረቱና ከዚህ ዓይነት ምግቦች ጋር ተመሳሳይ ምግቦችን የሚያመርቱ በዚህ መስክ ተደልድለዋል፡፡  

በከፍተኛ ደረጃ ለብልሽት ተጋላጭ ምግቦች አምራች የሚባሉት ተቋማት ከምግቦቹ ተፈጥሯዊ ይዘት አንፃር በቀላሉ ለበሽታ አምጪ ተዋስያን ዕድገት ተስማሚ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ የወተት፣ የወተት ተዋፅኦ፣ የሥጋና የሥጋ ውጤቶች፣ ዓሣና የባህር ምግቦች፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ውጤቶችና ሌሎችንም የሚያመርቱ ድርጅቶች የሚጠቃለሉበት ይህ ምድብ ሲሆን፣ በዝቅተኛ ደረጃ ለብልሽት ተጋላጭ ምግቦች አምራቾች የተባሉት ደግሞ የሚያመርቷቸው የምግብ ይዘቶችና ባህርያት ለበሽታ አምጪ ተዋስያን ዕድገት የማይመቹ እንደ አልኮል መጠጦች፣ እንደ ጥራጥሬ፣ የሻይ ቅጠል፣ ቡና እና ቅመማ ቅመም፣ ዘይትና ቅባት፣ ስኳር፣ ማር ስታርች፣ የባልትና ውጤቶች፣ ኮምጣጤ፣ እርሾና ሌሎች ተመሳሳይ የምግብ ዓይነቶች የሚያመርቱ ሁሉ በዝቅተኛ ደረጃ ለብልሽት ተጋላጭ የሆኑ ምግቦች አምራቾች ተብለዋል፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ሁለቱ የምግብ አምራቾች ላይ የቀረቡ የማሻሻያ ጥያቄዎች ቢኖሩም በተለይ በአነስተኛና በከፍተኛ ምግብ አምራችነት የተመደቡት ላይ የተቀመጡት ትርጓሜዎች ላይ አንኳር ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ይኸውም አነስተኛ የምግብ አምራች ተብለው የተደለደሉት ማቀናበሪዎች የሚጠየቁት ካፒታል ከግማሽ ሚሊዮን ብር በታች የሆኑና ከ50 ሰው በታች የሰው ኃይል እንዲኖራቸው የሚጠይቅ በመሆኑ የማሻሻያ ጥያቄ ቀርቦበታል፡፡

ከፍተኛ የምግብ አምራቾች በአንፃሩ ካፒታላቸው ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ እንዲሁም በሥራቸው የሚተዳደረው የሰው ኃይል ከ50 ሰው በላይ የሆኑ ከፍተኛ ምግብ አምራቾች ተብለው በረቂቅ መመርያው መቅረባቸው ተቀባይነት አላገኘም፡፡ አብዛኞቹ ተሳታፊዎች በመመርያው በዚህ አግባብ የቀረበው መጠይቅ፣ በምግብ የማምረት አቅም መጠን ላይ እንዲመረኮዝና የቀረበው የግማሽ ሚሊዮን ብር የካፒታል አቅም በገንዘብ መሆኑ ቀርቶ በሚመረተው የምግብ መጠን ብዛት አምራቾች እንዲፈረጁ ተዋዋዮቹ ጠይቀዋል፡፡ የምግብ ደኅንነትን ለማስፈን ካፒታል ዋናው መጠይቅ መሆን የለበትም ብለዋል፡፡

በመመርያው ክልል ተሻጋሪ አምራቾችን እንደሚመለከት ሲያስቀምጥ፣ ክልል ተሻጋሪ አይደሉም ተብለው የሚለዩት በምን ይዳኛሉ ያሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ ክልል የማይሻገሩ ኩባንያዎች ተብለው የሚጠቀሱት አምራቾቹ ቢሆኑም ምርቶቻቸው ግን ክልል መሻገራቸው የማይቀር በመሆኑ፣ ይህ የመመርያው አተረጓጎም እንዲሻሻል ጥያቄ ቀርቧል፡፡ በመመርያው መካተት ሲገባቸው አልተካተቱም ከተባሉት ውስጥ የሚጠቀሱት ደግሞ የአካባቢ ደኅንነት ባለሙያዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር የምግብ ቸርቻሪዎችና አከፋፋዮች በእሴት ሰንሰለቱ ውስጥ ጉልህ ሚና ቢኖራቸውም፣ በመመርያው ውስጥ አለመካተታቸውም እንዲታይ ተጠይቋል፡፡ ምግብ አምራቾች ያመረቱት ምርት በሥርጭት ወቅት ለሚገጥመው ችግርና ብልሽት አምራቾችን ተጠያቂ የሚያደርግ አካሔድ ያለው መመርያ በመሆኑ ይሻሻል በማለት ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

ምግብ በሚመረትበት አካባቢ ለምግብ ብክለት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ እንደ ሲሚንቶ ማምረቻ ያሉ ፋብሪካዎች በሚከፈቱበት ወቅት፣ ከምግብ ደኅንነት መሥፈርት አኳያ የግንባታ ፈቃድ ሰጭ፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲሁም የመሬት አስተዳደር አካላት እንዲህ ያለውን የአመራረት ሒደት በሚገባ ሊያጤኑ እንደሚገባና ይህ አካሔድም እንዲስተካከል ጥያቄ ቀርቧል፡፡ በቆሻሻ አወጋገድ፣ በተለይም ቆሻሻ መቃጠል እንደሚኖርበት የሚጠይቀው የመመርያው ክፍል እንዲሻሻል ተወያዮቹ ሲጠይቁ፣ ካቀረቧቸው መከራከሪያዎች አንዱ ማቃጠል ብክለትን እንደሚያባብስ የጠቀሱበት አካሔድ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር ለሠራተኞች የደንብ ወይም የማምረቻ አልባሳት ስቴራላይዝ ማድረግንም መመርያው የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ይህ አግባብ አይደለም ያሉት አምራቾች ስቴሪያላዝ የሚደረግባቸው ማሽኖች ምግብ ለማቀነባበር ከሚተከለው ፋብሪካ ያልተናነሰ ወጪ ስለሚጠይቁ፣ ከዚህ ይልቅ በእጥበትና በመሳሰሉት መንገዶች ንፅህናቸውን ማስጠበቅ የሚቻሉባቸው ስልቶች በመመርያው እንዲቀርቡ የጠየቁም አልታጡም፡፡

በቡድን ተከፋፍለው ባደረጉት ውይይት ከተለያዩ የምግብ ማምረቻ ኩባንያዎች ተወክለው የተሰባሰቡ ሰዎች ባደረጉት ውይይት፣ እነዚህን ሌሎችም መሠረታዊ ያሏቸውን ማሻሻያዎች በረቂቅ መመርያው እንዲካተቱላቸው ጠይቀዋል፡፡ ባለሥልጣኑ በበኩሉ ለውይይት ባቀረበው ረቂቅ መመርያ ላይ የተነሱትን ነጥቦች በግብዓትነት በማካተት እንደሚያስተካክል አስታውቋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የምግብ ምዝገባ አፈጻጸም መመርያ የተባለ ረቂቅ ሰነድም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ይሁንና መመዝገብ ሳያስፈልጋቸው ለሽያጭ መዋል ይችላሉ ተብለው የተለዩ የምግብ ዓይነቶችም በመመርያው ተዘርዝረዋል፡፡

በአገር ውስጥና በውጭ የተመረቱ፣ ተጠቃሚው ጋር ከመድረሳቸው በፊት በአምራቹ የታሸጉ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን የሚያመርቱ ተቋማት፣ ምርቶቻቸውን ማስመዝገብና ማሳወቅ እንዳለባቸው መመርያው ይጠይቃል፡፡ ለሰብዓዊ ዕርዳታ፣ ለግለሰብ ጥቅም፣ ለሳይንሳዊ ምርምሮች፣ ለተለያዩ ሆቴሎችና ምግብ አምራች ድርጅቶች እንደ ግብዓትም ሆነ እንደ ጥሬ ዕቃነት ጥቅም ላይ የሚውሉ፣ በ24 ሰዓታት ውስጥ ጥቅም ላይ መዋል የሚኖርባቸው፣ በልዩ ሁኔታ ለተለዩ የኅብረሰተቡ ክፍሎች ጥቅም ላይ የሚውሉትን ምግቦች ምዝገባ ሳያስፈልጋቸው ለገበያ መዋል የሚችሉ መሆናቸውን ባለሥልጣኑ በረቂቅ ሕጉ አስፍሯል፡፡ እነዚህ መመርያዎች ማሻሻያ ከተደረገባቸው በኋላ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

Standard (Image)

የ50 ሚሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ድርሻ የሚኖራቸው የቻይና ኩባንያዎች የቻይና ንግድ ሳምንት በተሰኘው ዓውደ ርዕይ እየተሳተፉ ነው

$
0
0

የቻይና መንግሥት ይፋ ካደረገው ‹‹ዋን ቤልት ዋን ሮድ›› ከተሰኘውና አኅጉራትን እንደሚያስተሳስር ከሚነገርለት መጠነ ሰፊ የመሠረተ ልማት አውታር ዝርጋታ ዕቅድ ጋር የተገናኘው፣ የቻይና የንግድ ሳምንት የኢንቨስትመንትና የንግድ ዓውደ ርዕይ በአዲስ አበባ መካሔድ ጀምሯል፡፡ በዓውደ ርዕዩ እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉ ኩባንያዎች መሳተፋቸው ተነግሯል፡፡

 ማክሰኞ፣ ሰኔ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ የተከፈተው የቻይና ንግድ ሳምንት የኢንቨስትመንትና የንግድ ዓውደ ርዕይ፣ ከንግድ ግንኙነት ባሻገር የቻይናን የጎደፈ ስም የማደስ ዓላማም እንዳነገበ ተጠቅሷል፡፡ በመላው ዓለም የቻይና ዕቃዎች እርባናቢስ፣ በቶሎ የሚበላሹና የማያስተማምኑ እንደሆኑ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የሰረፀ አመለካከት ተንሰራፍቷል ያሉት፣ ሚድል ኢስት ኢንተርናሽናል ግሩፕ የተባለው የዓውደ ርዕዮች አዘጋጅ ኩባንያ፣ የዓለም አቀፍ ዝግጅቶች ዳይሬክተር ሚሼል ሜሪይክ ናቸው፡፡ ሚሼል እንዳሉት ብቃት ያላቸውና የተመረጡ የቻይና ኩባንያዎች በሰታፉበት በቻይና የንግድ ሳምንት ተሳታፊዎች ታድመዋል፡፡ የቻይና ኩባንያዎችን ጨምሮ 400 ተሳታፊዎች በዓውደ ርዕዩ እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡

በኬንያ ሲካሔድ በቆየው የቻይና ንግድ ሳምንት ዓውደ ርዕይ፣ ከ35 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ የኬንያን የውጭ ኢንቨስትመንት መስክ የተቀላቀሉ እንዳሉ ይህም በዓውደ ርዕዩ ምክንያት በተፈጠረ ግንኙነት ሳቢያ እንደሆነ ያብራሩት ሚሼል ሜይሪክ፣ በኢትዮጵያም በዚሁ አኳኋን እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ሊያደርጉ የሚችሉ ኩባንያዎች መምጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

37 የቻይና ኩባንያዎች የተሳተፉበት ይህ ዓውደ ርዕይ ሐሙስ ሰኔ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ በዓውደ ርዕዩ የታደሙት በሙሉ በዘርፋቸው ተመርጠው የመጡና ከኢትዮጵያ ወገንም በዘርፍ የተመረጡ ይገኙበታል ተብሎ እንደነበር የፕራና ፕሮሞሽን ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነቢዩ ለማ ገልጸዋል፡፡

የዓውደ ርዕዩ አንዳንድ ጎብኚዎች ግን በዓውደ ርዕዩ የጠበቁትን እንዳላገኙ፣ የቀረቡትም ምርቶች ብዙም እንዳልማረካቸው የገለጹ ነበሩ፡፡ ስለ ጎብኚዎቹ አስተያየት ተጠይቀው ምላሽ የሰጡን አቶ ነብዩ፣ በዘርፍ በተለዩ መስኮች ላይ በማተኮር የተሰናዳ እንደሆነና ለዚሁም ሲባል የታዳሚዎች ቁጥር ውሱን እንዲሆን መደረጉን አቶ ነብዩ ተናግረዋል፡፡

በኢነርጂ፣ በኤሌክትሮኒክስ መሣሪዎች፣ በግንባታ ዕቃዎች፣ በማሽነሪዎች፣ በእርሻ መሣሪዎች፣ በኮስሞቲክስ፣ በማተሚያና ማሸጊያ ዕቃዎች፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍና በሌሎችም አምራችነት የተሠማሩ ኩባንያዎች በዓውደ ርዕዩ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ ኩባንያዎቹ ከ4,500 በላይ ልዩ ልዩ የፋብሪካ ውጤቶችን የሚያመርቱ እንደሆኑም ተጠቅሷል፡፡

በየዓመቱ በቋሚነት በአዲስ አበባ እንደሚዘጋጅ የሚጠበቀው ይህ ዓውደ ርዕይ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ከኬንያ፣ ከጋና፣ ከሞሮኮ፣ ከኦማን፣ ከደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ከኢራን ባሻገር በኢትዮጵያም ዓመታዊ የቻይና የንግድ ሳምንት የተሰኘውን ዓውደ ርዕይ በማዘጋጀት እንደሚቀጥል አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ዓውደ ርዕይ የቻይና ኩባንያዎች ከሚፈጥሩት የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኙነት ባሻገር፣ የቻይናን ገጽታ በበጎ ጎኑ ለመገንባት ያለመ ነው የተባለ ሲሆን፣ ቻይና ርካሽና በቶሎ የሚበላሹ፣ የማይረቡ ምርቶችን ታመርታለች የሚለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለመለወጥ የታሰበበት ነው ያሉት ሚሼል ሜይሪክ፣ ከዚህ ይልቅ ግን ቻይና እንደ ምርትና አገልግሎት ፈላጊው የመክፈል አቅም ለዚያ የሚመጥን ነገር እያቀረበች እንደምትገኝ መገንዘብ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

ከ16 ዓመታት በፊት በዱባይ የተመሠረተው ሚድል ኢስት ኢንተርናሽናል ኩባንያ፣ ዓውደ ርዕዮችን ከማዘጋጀት ባሻገር የንግድና የቱሪዝም መስኮችም ላይ የሚንቀሳቀስ ኩባንያ ነው፡፡ በአዲስ አበባ የተሰናዳውን የቻይና የንግድ ሳምንት ኩባንያው ከአገር በቀሉ ፕራና ፕሮሞሽን ጋር በመሆን አሰናድቶታል፡፡

ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የተመሠረተው ፕራና ፕሮሞሽን በአራት ወጣቶች የተቋቋመ ሲሆን፣ በጤና፣ በግብርና እና ምግብ፣ በዶሮ እርባታ እንዲሁም በቁም እንስሳት መስክ ያተኮሩ ዓውደ ርዕዮችን በማዘጋጀት ይታወቃል፡፡ ከዓውደ ርዕይ ዝግጅት ባሻገርም ዝግጅቶችን በገበያና ግብይት እንዲሁም በዝግጅት ማስተዳደር ሥራዎች ውስጥ እየተሳተፈ የሚገኝ ኩባንያ ነው፡፡

                                          

Standard (Image)

ንብ ባንክን ያስፈነደቀው የ680 ሚሊዮን ብር ሕንፃ ለዋና መሥሪያቤትነት ታጭቷል

$
0
0

አራት ኪሎ አካባቢ፣ ከቱሪስት ሆቴል አጠገብ በሚገኝ ቦታ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ግንባታው ተጀምሮ በማጠናቀቂያው ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ባለ ስምንት ወለል ሕንፃ፣ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሐራጅ እንዲሸጥ በመወሰኑ፣ ጨረታው ሰኔ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ተካሂዶ አሸናፊው አካል ታውቋል፡፡

በ2000 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው የዚህ ሕንፃ ባለቤት በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ከበደ ተሠራ ወይም በቅጽል ስማቸው ‹‹ወርልድ ባንክ›› የሚባሉት ግለሰብ ናቸው፡፡ መከታ ሪል ስቴት በተሰኘው ኩባንያቸው የገነቡት ይህ ሕንፃ፣ በሐራጅ እንዲሸጥ የተወሰነው በአራጣ አበዳሪነት በተመሠረተባቸው ክስ ጥፋተኛ በመባላቸው ነበር፡፡ በእስራትና በገንዘብ ከተጣለባቸው ቅጣት ባሻገር በስማቸው የተመዘገበው ይህ ሕንፃ እንዲወረስ ተበይኗል፡፡ በዚሁ የፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረት በፍርድ አፈጻጸም ንብረታቸው በ72.7 ሚሊዮን ብር የጨረታ መነሻ ዋጋ ለጨረታ ቀርቦ ነበር፡፡

በጨረታ ሒደቱ ተወዳዳሪዎች ሕንፃውን የሚገዙበትን ዋጋ በሰም በታሸገ ፖስታ ዋጋ የሰጡበት ሳይሆን፣ መነሻ ዋጋውን መሠረት በማድረግ በግንባር ቀርበው ዋጋ እየጠሩ የሚፎካከሩበት ነበር፡፡ በመሆኑም ሕንፃውን ለመግዛት በዕለቱ የቀረቡት አምስት ተጫራቾች አንዱ በሰጠው ዋጋ ላይ ሌላው እያከለ የተፎካከሩበት ሒደት ነበር፡፡

ከተፎካከሩት ውስጥ እስከ 350 ሚሊዮን ብር ድረስ በየተራ የሚጫረቱበትን ዋጋ በመጥራት ሁሉም ቢጓዙም፣ ከ350 ሚሊዮን ብር በኋላ ግን አቢሲኒያና ንብ ባንክ ብቻቸውን ተፎካካሪ ሆነው ሊቀጥሉ ችለዋል፡፡ አንዱ በሚሰጠው ዋጋ ላይ ሌላው እየጨመረ ውድድሩን አክርረው ዘልቀዋል፡፡ ይሁንና በሁለቱ ተቀናቃኞች መካከል የነበረው ፉክክር የተገታው አቢሲኒያ ባንክ የመጨረሻ ዋጋውን 672 ሚሊዮን ብር በላይ በማድረጉ ነበር፡፡ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በበኩሉ 680 ሚሊዮን ብር በማቅረብ የጨረታውን ውርርድ በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ በቅቷል፡፡

አራት ባንኮችን ባፎካከረው የጨረታ ሒደት፣ በተለይ ንብ ባንክ ሕንፃውን ለመግዛት ያሳየው ፍላጎት ከሌሎች እንደሚለይ ያሳየበት ነበር፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ክብሩ ፎንጃ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህንን ሕንፃ ለመግዛት በብርቱ የታገልንበት በርካታ ምክንያቶች ነበሩን ብለዋል፡፡

ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የሕንፃው ግንባታ ሲጀመር፣ ለግንባታው የዋለውን ፋይናንስ ያቀረበው ንብ ባንክ ነበር፡፡ ባንኩ የሰጠው ብድር በወቅቱ ሊመለስለት ባለመቻሉ፣ ብድሩን ለማስመለስ እልህ አስጨራሽ ሒደቶችን ማለፉም ከሕንፃው ግዥ ጋር እንደሚተሳሰር ጠቅሰዋል፡፡ በአቶ ከበደ ባለቤትነት እየተገነባ ለነበረው ሕንፃ የ55 ሚሊዮን ብር ብድር መስጠቱ፣ የባንኩና የሕንፃው ግንኙነት ከሌሎች ተወዳዳሪዎች እንደሚለየው፣ በከፊልም ባለቤት የሚያደርገው ትስስር እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥም ንብ ባንክ የሰጠውን ብድር ለማስመለስ ብዙ ውጣ ውረዶችን እንዳለፈ፣ ለዓመታት የዘለቀ የፍርድ ቤት ክርክር ውስጥ እንደቆየም የባንኩ ኃላፊዎች ይጠቅሳሉ፡፡ የባንኩ ባለአክሲዮኖችም ለዚህ ሕንፃ ግንባታ የተሰጠው ብድር ሳይከፈል መዘግየቱን በማሳሰብ፣ በየዓመቱ በሚያካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት እያነሱ ገንዘባችን የት ደረሰ? የሚል ጥያቄ በማንሳት ማኔጅመንቱንና ቦርዱን ከመጠየቅ እንዳልቦዘኑ አስታውሰዋል፡፡

በዚህም ሳይወሰን ለባንኩ የተበላሸ ብድር መጠን መጨመር ዋነኛው ምክንያት ለዚህ ሕንፃ የተሰጠው ብድር አለመመለስ አስተዋጽኦ እንደነበረው ባንኩ አስታውቋል፡፡ እንደ ባንኩ ኃላፊዎች ገለጻ፣ ብድሩን ለማስመለስ መከተል ያለባቸውን ሕጋዊ መንገድ ተከትለው ቢጓዙም፣ ብድሩን ለማስመለስ እንቅስቃሴ ሲጀመር ግን ጋሬጣ አጋጥሟል፡፡ ይኸውም መከታ ሪል ስቴት ብድሩን ከወሰደ በኋላ መክፈል ባለመቻሉ፣ ባንኩ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሕንፃውን ለመሸጥ ማስታወቂያ አውጥቶ ወደ ዕርምጃ ለመግባት መንቀሳቀስ ሲጀምር፣ ኩባንያው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቱ ሕንፃውን ሽጦ ገንዘቡን ለማስመለስ ሳይችል ይቀራል፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዓቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው አቤቱታም ንብረቱ ወይ ሕንፃው በአራጣ የተያዘ፣ ሕጋዊ ባልሆነ የገንዘብ ልውውጥ የተገኘና ይወረስ የሚል ጥያቄ የቀረበበት በመሆኑ ንብ ባንክ ሊሸጠው አይችልም በማለቱ ነው፡፡ ይህ አቤቱታ የቀረበው በመጋቢት ወር 2003 ዓ.ም. ሲሆን፣ በገቢዎችና በጉምሩክ ባለሥልጣንና በባንኩ መካከል ለዓመታት ለዘለቀው ክርክርም መነሻ ሆኖ ቆይቷል፡፡

በባለሥልጣኑ አቤቱታ መሠረት፣ ባንኩ ንብረቱን ለመሸጥ ያደረገው እንቅስቃሴ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ይታገዳል፡፡ የዕግድ ትዕዛዝ ሲወጣም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔን በመቃወም ባንኩ በበኩሉ ዕግዱን በመቃወም ንብረቱን ለመሸጥ መብት እንዳለው ተከራክሯል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አስተያየት የሰጡት የንብ ባንክ የሕግ አገልግሎት መምሪያ ዳይሬክተር አቶ በየነ ዓለሙ፣ ‹‹ንብረቱን ሸጦ ገንዘባችንን ለማግኘት መብታችን የሚመነጨው ከውል እንደሆነም ጭምር አስረድተናል፡፡ ብድር አበድረናል፡፡ የመያዣ ውል አለን፡፡ ማስያዣውን አግባብ ባለው አካል አስይዘናል፡፡ ይህንን ሁሉ ስናደርግ ስለሕገወጥነቱም ሆነ ስለሌላው ነገር የምናውቀው ነገር አልነበረም በማለት ተሟግተናል፤›› ብለዋል፡፡  

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ‹‹እንዲህ ያለ መብት ካላችሁ የሊዝ መብቱ እንዲወረስ በማለት ውሳኔ ያሳለፈው ከፍተኛው ፍርድ በመሆኑ፣ መብት አለን ካላችሁ መብታችሁን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጠይቁ፤›› በማለት ዕግዱን እንደማያነሳ ማስታወቁን አቶ በየነ ያስታውሳሉ፡፡

‹‹ከዚህ በኋላ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር ክርክሩ ቀጠለ፡፡ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ሄደን መብት ያለን መሆኑን መረጃዎች አቀረብን፤ የሰጠነው ብድር መጠንም እያደገ ነው ይከፈለን ብለን ጠየቅን፤›› የሚሉት አቶ በየነ፣ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ረዥም ጊዜ ወስዶ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መልስ እንዲሰጥበት አደረገ፡፡ የመከታ ሪል ስቴት ሥራ አስኪያጅ አቶ ከበደ ስለሆኑ እሳቸውም ከእስር ቤት እየቀረቡ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ጭምር ይደረግ እንደነበር አቶ በየነ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ መሠረት ክርክሩ ሲደረግ ከቆየ በኋላ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሰኔ 2007 ዓ.ም. ይወረስ የተባለው የሊዝ መብቱ ነው፡፡  

የሊዝ መብቱና ሕንፃው አሁን ባለው በኢትዮጵያ ሁኔታ የተለያዩ ዋጋዎች ሊወጣላቸው እንደሚችል ይገለጻል፡፡ በመሆኑም የፍርድ አፈጻጸም መምሪያው የሊዝ ዋጋውን ዓይቶና አውቆ ሕንፃውን ለብቻ አስገምቶ ሐራጅ አውጥቶ ሸጦ ባንኩም የሚያገኘውን ገንዘብ ያግኝ፡፡ ሌላው በመንግሥት እንደተያዘ ይቆይ የሚል ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ገቢዎችና ጉምሩክ በዚህ ውሳኔ ባለመደሰት ይግባኝ ይጠይቃል፡፡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ግን ውሳኔው ፀና፡፡ ባለሥልጣኑ እንደገና ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከዚያም ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት በመሄድ ውሳኔውን ለማስቀልበስ ቢያመለክትም፣ ጉዳዩ እንደገና በሰበር ችሎት ብዙ ካከራከረ በኋላ ‹‹ለመጨረሻ ጊዜ የሥር ፍርድ ቤት የባንኩ መብት በተጠበቀ መልኩ አፈጻጸሙ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ባንኩ ያበደረው ገንዘብ ማጣት የለበትም ብሎ ታኅሳስ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጠ፤›› በማለት የፍርድ ሒደቱን ገልጸዋል፡፡

ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ትዕዛዝ መሠረትም አፈጻጸሙ ይቀጥል፣ የእኛም መብት ይከበርልን ብለን ሕንፃው ተገምቶ በተሰጠው ግምት መሠረት ጨረታው እንዲካሄድ ትዕዛዝ ሊሰጥ ችሏል፡፡ ሕንፃው በሐራጅ እንዲሸጥ ሊወሰን የቻለውም በዚህ መንገድ ነው፡፡ ውሳኔው ደግሞ የባንኩንም ሆነ በዚህ ሕንፃ ላይ ያልተከፈለ ገንዘብ አለኝ የሚልም ኮንትራክተር ስለነበር የሱም ጉዳይ የሚታይበት ይሆናል፡፡ እንደ አቶ በየነ ገለጻ እንዲያውም ከባንኩ ቀድሞ የኮንትራክተሩ ፍላጎት እንጠብቅ፣ ከዚያ ቀጥሎ ባንኩ ገንዘቡን እንዲያገኝና ሌላው በሞዴል 85 ተይዞ እንዲቀመጥ ነው የተወሰነው፡፡ ከዚህ ውሳኔ ጎን ለጎን ግን ባንኩ ለፍርድ ቤቱ በሕንፃው ጨረታ ላይ እንዲሳተፍ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ይህንን ጥያቄ ያቀረቡትም ‹‹በጨረታ ሒደቱ የተወሰኑ ቡድኖች ገብተው ገበያውን አፍኖ የመያዝ ልምድ ስላለ፣ የባንኩም ሆነ የመንግሥትን ፍላጎት ለመጠበቅ ባንኩ በጨረታው ውስጥ እንዲሳተፍ ይፈቀድለት፤›› በሚል ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ጥያቄያችንን በመቀበሉም በሕንፃ ጨረታው ላይ ለመሳተፍ መቻላቸውን የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡  ከዚህ ውሳኔ በኋላ ንብ ባንክ ሕንፃውን ለመግዛት አንዱ ተፎካካሪ ሆኖ ቀረበ፡፡

ሰኔ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. የሕንፃ ሽያጩ ጨረታ ሲካሄድ ከተወዳደሩት  ከአምስቱ መካከል አራቱ ተጫራቾች ባንኮች ሲሆኑ፣ ጨረታው በተካሄደበት ወቅትም የተወዳዳሪ ባንኮቹ ኃላፊዎች፣ የቦርድ አባላትና ባለአክሲዮኖች ተገኝተው ነበር፡፡ ንብ ባንክ የጨረታው አሸናፊ ይሁን እንጂ ሕንፃውን መግዛት ያወጣው ገንዘብ  ሲታይ፣ ‹‹ሕንፃው የቱንም ያህል ዋጋ ቢኖረው 680 ሚሊዮን ብር ማውጣቱ በምን አግባብ ትክክለኛ ነው?›› የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ በመሆኑም ስለዚሁ ጉዳይ የተጠየቁት የባንኩ ፕሬዚዳንት ‹‹ያዋጣል ብለን ነው የገዛነው፤›› በማለት ፈርጠም ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ይህንን ስናደርግ ብዙ አውጥተንና አውርደን በመወሰን ነው፤›› ያሉት አቶ ክብሩ፣ ጥሩ ስም ስላለው፤ ምናልባትም የትርፍና የገንዘብ ብቻም ሳይሆን፣ በዚህ ሕንፃ ጉዳይ ከስምንት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ በክርክር የቆየንበትና በብዙ ባለአክሲዮኖች አዕምሮ ውስጥ የሚብላላ ጥያቄ ስለነበርና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም ታይቶ የተገባበት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የዓመታት ድካማችን ውጤት አድርገን እናየዋለን፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም ቀሪ ሥራዎቹን አጠናቆ በጊዜያዊነት ለቢሮ አገልግሎት ሊውል እንደሚችል አቶ ክብሩ አስታውቀዋል፡፡ ሕንፃው ሰፊ ከመሆኑ ባሻገር አራት ኪሎ ስትራቴጂካዊ በሆነ ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ ለባንኩ መገልገያነትም ሆነ ለኪራይ እንዲውል በማድረግ የገቢ ምንጭ እንዲሆን ስለሚደረግ የወጣበት ገንዘብ አዋጭ ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

የሕንፃ ርክክቡና የገንዘብ አከፋፈሉን በተመለከተም፣ ሕንፃውን ለመግዛት የተጠቀሰውን ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ በማድረግ ከዚህ ውጭ ባንኩ ተበዳሪው ያልከፈለውንና ከወለዱ 120 ሚሊዮን ብር የደረሰውን ገንዘብ እንደሚያገኝ ሆነም በሕግ አግባብ ተይዞ እንዲቆይ የሚደረገው ገንዘብ ተይዞ እንደሚቆይ አብራርተዋል፡፡

ባንኩ በ15 ቀን ውስጥ የሚጠበቅበትን ክፍያ በመፈጸም፣ ሕንፃውን ከተረከበ በኋላ በባንኩ ዕቅድ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሕንፃውን የማጠናቀቂያ ሥራዎች መሥራት እንደሚጀምር የገለጹት አቶ ክብሩ፣ ሥራው እንደተጠናቀቀ የባንኩን ዋና መሥሪያ  ቤትም ወደዚያ የማዞር ሐሳብ እንዳለ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት እያስገነባነው ያለው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ሦስት ወይም አራት ዓመት ሊፈጅ ስለሚችል አሁን የገዛነው ሕንፃ ወደ ዋናው መሸጋገሪያ መሥሪያ ቤት ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹17 ዓመታት ሙሉ ቆይተን አዲስ አበባ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ሕንፃ የለንም፡፡ ሕንፃውን በዋና መሥሪያ ቤትነት ተጠቀምንበትም፣ አከራየነውም በንብ ባንክ ስም የተያዘ ሕንፃ በከተማው ውስጥ በባለቤትነት መያዛችን ትልቅ ስኬት ነው፤›› በማለት አቶ በየነ ገልጸዋል፡፡

የሕንፃው ግዥ ሲፈጸም ማኔጅመንቱ፣ ቦርዱና ባለአክሲዮኖች ሳይቀሩ አምነውበት ስለሆነ የግዥ ዋጋው የቱንም ያህል ትልቅ ቢሆን አዋጭ መሆኑ ተረጋግጦ እንደሆነ የባንኩ ኃላፊዎች ያስረዳሉ፡፡ የሕንፃው ግዥ ከተፈጸመ በኋላም በባንኩ ማኅበረሰብ ዘንድ ደስታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት የደንበል ሕንፃ ውስጥ የተወሰነ ክፍል ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ለኪራይ ብቻ በዓመት 20 ሚሊዮን ብር እያወጣ በመሆኑ፣ ሕንፃውን ገዝቶ ዋና መሥሪያ ቤቱን ማዞር ይችላል የሚለው ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱን ያሳያል አስብሎታል፡፡ ይህ የማኔጅመንትም ሆነ የቦርዱ ፍላጎት ነበር ያሉት አቶ ክብሩ፣ ‹‹ይህን ሕንፃ እስከ መጨረሻው ተፋልመን መግዛት እንዳለብን ስንወስን ከዋና መሥሪያ ቤት አገልግሎቱ ባሻገር ባንኩን ከኪራይ ከማውጣት ባለፈም የተወሰኑትን ክፍሎች በማከራየት ገቢ ሊገኝ ይችላል በሚል ነው፤›› ብለዋል፡፡

በጨረታው ውጤት መሠረት አሸናፊው ንብ ባንክ ገንዘቡን በ15 ቀናት ገቢ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ለጨረታ መወዳደሪያ 18 ሚሊዮን ብር አስይዟል፡፡ ስለዚህ ቀሪውን ከ572 ሚሊዮን ብር ውስጥ ክፍያ ሲፈጽም፣ በፍርድ አፈጻጸም መመርያው መሠረት ሕንፃውን ይረከባል ተብሏል፡፡

በመከታ ሪል ስቴት ሲገነባ የነበረው ሕንፃ፣ ሦስት የሲኒማ አዳራሾች፣ ሁለት የመኪና ማቆሚያዎች፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ በተለያየ መጠን የተሠሩ ክፍሎች አሉት፡፡ በ2,926 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሕንፃ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ንብ  ባንክ ከ17 ዓመታት በፊት ሲቋቋም ወደ ሥራ የገባው 27 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የተፈቀደ ካፒታሉ ከ3.5 ቢሊዮን ብር፣ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 2.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የባለአክሲዮኖቹም ቁጥር ከ4,000 በላይ ሲሆን፣ የባንኩ ሀብት በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 17.6 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ (አሁን የገዛውን ሕንፃ ሳይጨምር) ከ21.3 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን የባንኩ መረጃ ያመለክታል፡፡ ባለፈው ዓመት 2008 ከታክስ በፊት 458 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡

 

 

Standard (Image)
Viewing all 720 articles
Browse latest View live