በ1995 ዓ.ም. አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) የአዲስ አበባከተማን ቁልፍ ከአቶ አሊ አብዶ ሲረከቡ በከተማው የነበሩ ቤቶች ቁጥር 387,000 ብቻ ነበር፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ1996 ዓ.ም. ባደረገው የጂአይኤስ ዳሰሳ ጥናት፣ በከተማው ውስጥ ከነበሩ ቤቶች መካከል 238,000 (61.5 በመቶ) መኖሪያ ቤቶች ሲሆኑ፣ የተቀሩት የተለያዩ አገልግሎቶች ይሰጡ ነበር፡፡
በዚህ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ የ500 ሺሕ ቤቶች እጥረት እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህንን የከፋና ሲከማች የቆየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ከመሠረቱ ለመፍታት የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር ከንቲባ አርከበ ሁለት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አደረጉ፡፡
የመጀመሪያው ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላለው የኅብረተሰብ ክፍል በየዓመቱ 50 ሺሕ ኮንዶሚኒየም ቤቶች በ1.5 ቢሊዮን ብር ወጪ መገንባት፣ ሁለተኛው ደግሞ ከፍተኛና መካከለኛ ገቢ ላለው የኅብረተሰብ ክፍል የሚሆኑ የሪል ስቴት ቤቶችን በግሉ ዘርፍ እንዲገነባ ዕድሉን ማመቻቸት ነው፡፡
በዚህ መሠረት በተለይ በ1996 ዓ.ም. በተካሄደው የጂአይኤስ ዳሰሳ ጥናት በከተማው ከሚገኙ ቤቶች 80 በመቶ ያህሉ ያረጁ፣ ለመኖሪያ ምቹ ያልሆኑና አሮጌ መንደሮችን በማፍረስ በመሀል ከተማ አዲስ ግንባታ ማካሄድ ነው፡፡ ለዚህም መንግሥት ነባር ነዋሪዎችን አንስቶ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ በማቆየት፣ ቤቶቹን ከገነባ በኋላ መልሶ ለማስፈር ዕቅድ አውጥቶ ነበር፡፡
በዚህም የማይናቅ መንገድ ከተሄደ በኋላ በታሪካዊው ምርጫ የ1997 ዓ.ም. ከተማውን ለማስተዳደር ምርጫውን ያሸነፈው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በተለያዩ ምክንያቶች ሥልጣኑን መረከብ አልቻለም፡፡ መረከብ ባለመቻሉም በአቶ ብርሃነ ደሬሳ የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ ባለአደራ አስተዳደር ሥልጣኑን ተረክቧል፡፡
የአቶ ብርሃነ ካቢኔ ባለአደራ አስተዳደር እንደመሆኑ የተጀመረው የመኖሪያ ቤት ልማት በተጀመረበት መንገድ ማስቀጠል ሳይቻል ቀርቷል፡፡ ራሱንም ‹‹ፋየር ብርጌድ›› በማለት ሲጠራ ቆይቷል፡፡
በወቅቱ የተጀመረውን የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለማግኘት ከ453 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች የተመዘገቡ ቢሆንም፣ ከ13 ዓመታት በኋላም ከእነዚህ ነዋሪዎች መካከል አብዛኛዎቹ ቤታቸውን ማግኘት አልቻሉም፡፡ አሁንም ቢሆን የተወሰኑ ነዋሪዎች በመጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ልብ ይሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ የበጀት ዓመቱን ሪፖርት ለምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ የከተማው የቤት ልማት ሥራ በእስካሁኑ ጉዞ 175 ሺሕ የሚሆኑ ቤቶችን ለተጠቃሚ አስተላልፏል፡፡ 40/60 ፕሮግራምን ጨምሮ 132 ሺሕ ቤቶች ደግሞ ግንባታቸው እየተካሄደ ነው፡፡
ከ13 ዓመታት በኋላ የቀድሞ ተመዝጋቢዎች ጭምር መኖሪያ ቤታቸውን ማግኘት ካለመቻላቸው በላይ፣ በሐምሌ 2005 ዓ.ም. በተካሄደው የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች ዳግም ምዝገባ የከተማው የመኖሪያ ቤት ፍላጎት (እጥረት) አንድ ሚሊዮን ደርሷል፡፡
የግንባታ ፍጥነቱ ከአንገብጋቢው የመኖሪያ ቤት ፍላጎት አንፃር ሲታይ ከፍተኛ አለመጣጣም ይስተዋልበታል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መንግሥት 750 ሺሕ ቤት የመገንባት ዕቅድ ይዟል፡፡ በዓመት ሲታይ 150 ሺሕ ቤት መገንባት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ይህንን ግንባታም ለማካሄድ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል፡፡ በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማቅረብ የቻለው 15 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡
በፋይናንስ በኩል ካለው የአቅርቦት ችግር በተጨማሪ ግንባታውን በተያዘው ዕቅድ ማካሄድም ሆነ የፕሮጀክት አስተዳደር ችግር በመኖሩ የመኖሪያ ቤት አቅርቦቱ አሁንም ችግር ውስጥ ይገኛል፡፡
የቀድሞ የአዲስ አበባ ከንቲባ አርከበ የመኖሪያ ቤት እጥረቱን ለመፍታት ትኩረት ያደረጉበት ሌላኛው ዕቅድ የሪል ስቴት ፕሮግራም ነው፡፡ ከንቲባ አርከበ በዚህ ግዙፍ ዕቅዳቸው በዘርፉ ለመሰማራት አቅም ላላቸው ለ105 ሪል ስቴት ኩባንያዎች በአማካይ 50 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥተዋል፡፡ በድምሩ በሚሊዮን ካሬ ሜትር የሚቆጠር መሬት ለሪል ስቴት ልማት በጀት ተደርጓል፡፡
ለሪል ስቴት ኩባንያዎች ሰፋፊ መሬት ከማቅረብ ባሻገር በተለይ መካከለኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችም እንደየፍላጎታቸው እንዲስተናገዱ 70 በመቶ አፓርታማና 30 በመቶ ደግሞ ቪላዎች እንዲገነቡ ዕቅድ ወጥቶ ነበር፡፡
ይህንን ተግባራዊ ለሚያደርጉ የሪል ስቴት ባለሀብቶች ለተሰጣቸው መሬት ዝቅተኛ የሊዝ ክፍያ እንዲፈጽሙና በሚገነቡት ቤት መጠን ለአንድ ቤት 50 ካሬ ሜትር ቦታ በማበረታቻ መልክ እንዲሰጣቸው ጭምር ተደርጓል፡፡
ነገር ግን የሪል ስቴት ልማት ዘርፉ ከመጀመርያው ጀምሮ በበርካታ ማነቆዎች መተብተብ በመጀመሩ በታሰበው መንገድ መጓዝ ሳይችል ቀርቷል፡፡
በወቅቱ ብዙዎቹ የሪል ስቴት አልሚዎች የተሰጣቸው መሬት በከተማው ዳርቻ ላይ በመሆኑ መንግሥት በተፈለገው መጠን እንደ መንገድ፣ ኤሌክትሪክና ውኃ ያሉትን የመሠረተ ልማቶች ማሟላት አልቻለም፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሪል ስቴት ኩባንያዎች ግንባታ የሚያከናውኑት ከደንበኞቻቸው በተወሰነ ደረጃ ቅድሚያ ክፍያ በማሰባሰብ በመሆኑ፣ በተለይ አፓርትመንቶች ለመገንባት በቂ አቅም አልነበራቸውም፡፡ ባንኮች ለሪል ስቴት ግንባታ የሚሆን የረዥም ጊዜ ብድር የማያቀርቡ በመሆኑ፣ ግንባታቸውን በወቅቱ አካሂደው ለማስረከብ ችግር ተፈጥሯል፡፡
በሪል ስቴት አልሚዎች በኩልም መረር ያለ ችግር ታይቷል፡፡ በተለይ በትንሽ የሊዝ ገንዘብ የወሰዱትን መሬት ምንም ዓይነት ግንባታ ሳያካሂዱ ለሦስተኛ ወገን የሊዝ መብትን አሳልፎ መሸጥ፣ አፓርታማ ለመገንባት የወሰዱትን ቦታ ቪላ ገንብቶ መሸጥ፣ ለማኅበራዊ አገልግሎት መዋል ያለበትን መሬት ለቤት ግንባታ ማዋል፣ ከተሰጣቸው ማበረታቻ አንፃር በተመጣጣኝ ዋጋ መኖሪያ ቤቱን መሸጥ ሲገባቸው ዋጋ ማናር፣ ከደንበኞች ገንዘብ ከሰበሰቡ በኋላ ቤቱን በወቅቱ አለማቅረብና ጭራሽኑ ገንዘቡን ይዞ መጥፋት የተወሰኑት ችግሮች ናቸው፡፡ በነዚህ ውስብስብ ችግሮች ተፈትነው የወጡ ሪል ስቴቶች ቢዘገዩም ለደንበኞቻቸው መኖሪያ ቤት ያስረከቡም መኖራቸው የሚዘነጋ ሀቅ አይደለም፡፡
ባለፉት አሥር ዓመታት በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ በማለፍ ግንባታቸውን አጠናቀው፣ ለደንበኞች ካስረከቡና እነሱም በቂ ልምድ የያዙ ሪል ስቴቶች፣ በቀጣይ በሰፊው ግንባታ ውስጥ ለመግባት የመሬት አቅርቦት አለመኖር አሳስቧቸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሥረኛው ማስተር ፕላን በመሀል ከተማ የሚካሄዱ የሕንፃ ግንባታዎች እስከ 60 በመቶ ድረስ መኖሪያ ቤቶች ማካተት እንዳለባቸው አስገዳጅ በማድረጉ፣ አዳዲስ የሪል ስቴት ኩባንያዎች መፈጠራቸውና በየጊዜው እየጨመረ በመሄድ ላይ የሚገኘው የዋጋ ግሽበት፣ ገንዘብን ሁነኛ ቦታ ለማስቀመጥ የሪል ስቴት ቤቶች አማራጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
ጊፍት ሪል ስቴት በ1998 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሦስት ሳይቶች 16 ሔክታር መሬት ለሪል ስቴት ልማት ተረክቧል፡፡
ጊፍት ሪል ስቴት 1,500 ደንበኞችን ማፍራት የቻለና በሦስቱም ሳይቶች አፓርትመንቶች፣ ታውን ሐውሶችንና ቪላ ቤቶችገንብቶ ለደንበኞቹ አስረከቧል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ ቤቶችን በመገንባትም ላይ ይገኛል፡፡
የጊፍት ግሩፕ ኩባንያዎች መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ገብረ ኢየሱስ ኢጋታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ድርጅታቸው በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፎ በርካታ ልምድ አካብቶ የሪል ስቴት ግንባታውን አገባዷል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት ለሪል ስቴት ልማት መሬት በድርድር እየቀረበ አይደለም፡፡ በመሆኑም ይህንን ሁሉ ሥራ ከሠራን በኋላ ዘርፉን ለቆ የመውጣት ጉዳይ ያሳስበኛል፤›› በማለት አቶ ገብረ ኢየሱስ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ኅዳር 2009 ዓ.ም. የወጣው የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721 ለአገልግሎት መስጫ ተቋማት ለአብነት ለሪል ስቴት፣ ለባለኮከብ ሆቴል፣ ለትምህርት ቤትና ለጤና አገልግሎት የሚውሉ ግንባታዎች ለማካሄድ መሬት የሚቀርበው በጨረታ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡
‹‹የሪል ስቴት ልማትን በጨረታ በሚገኝ መሬትም ሆነ ከባለይዞታዎች ላይ እየገዙ ግንባታ ማካሄድ አዋጪ አይደለም፣ በዚህ ዓይነት ግንባታ የመኖሪያ ቤት ችግሮችን መቅረፍ አይቻልም፤›› የሰንሻይን ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ለዓለም ተሰራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከሪል ስቴት ልማት መሬት አቅርቦት ጋር ተያይዘው ያሉ ችግሮች የተፈጠሩት በሊዝ አዋጅ ነው፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት የሊዝ አዋጅ እየተሻሻለ በመሆኑ በሚቀጥለው ዓመት ተሻሽሎ ይወጣልተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሊዝ አዋጅ ሲወጣ ችግሮቹ ይፈታሉ፤›› በማለት አቶ ለዓለም አብራርተዋል፡፡
ከዚህም የሊዝ አዋጅ ባሻገር በሪል ስቴት ዘርፍ ያሉ የግብይትና የአሠራር ችግሮችን ለመፍታት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የሕግ ረቂቅ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ረቂቅ ሕጉ ከተዘጋጀ አራት ዓመታት ቢሆኑትም፣ የሪል ስቴት ኩባንያዎች ረዥም ጊዜ የወሰደ ውይይት ቢያደርጉትም እስካሁን ሕግ ሆኖ አልወጣም፡፡
በአሁኑ ወቅት በሪል ስቴት ልማት ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን እያካሄዱ ከሚገኙ ኩባንያዎች መካከል ፍሊንት ስቶን ሆምስ አንዱ ነው፡፡ የፍሊንት ስቶን ሆምስ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ፀደቀ ይሁኔ፣ በሪል ስቴትና በአጠቃላይ በመሬትና ተያያዥ ዘርፎች የተዘጋጁ የሕግ ማዕቀፎችበአፋጣኝ ፀድቀው ሥራ ላይ መዋል አለባቸው ብለዋል፡፡
‹‹ነገር ግን ሕጉ ከተዘጋጀ አራት ዓመት በማስቆጠሩና አዳዲስ ክስተቶች በመኖራቸው፣ በድጋሚ ሊታይ ይገባል፤›› በማለት አቶ ፀደቀ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባወጣው መረጃ፣ በአጠቃላይ 117 ኩባንያዎች በሪል ስቴት ዘርፉ ለመሥራት ፈቃድ ወስደዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች 56 ፕሮጀክቶችንም አስመዝግበዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 43 የሚሆኑት በአዲስ አበባ የሚካሄዱ ናቸው፡፡
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በ2009 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት ባወጣው ሪፖርት፣ 35 ሪል ስቴቶች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የግንባታ ፈቃድ ወስደው በግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡
የሪል ስቴት መኖሪያ ቤቶች ግብይት በሒደት በመጠኑ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም፣ የሪል ስቴት ኩባንያዎች ግን ዘርፉን እየተቀላቀሉ የሚገኙት አሥረኛው ማስተር ፕላን በከተማው መሀል የሚካሄዱ ሕንፃዎች እስከ 60 በመቶ የሚሆነው ግንባታ ለመኖሪያ ቤቶች አፓርታማ እንዲያውሉ አስገዳጅ በመሆኑ ሊሆን እንደሚችል ይጠረጠራል፡፡
ሆኖም ግን የግንባታው ወጪ እየናረና ግንባታ ለማካሄድ የሚያስፈልጉ ሕጋዊ ሒደቶች ረዥም ውጣ ውረዶች በሚጠይቁበት፣ ባንኮች የረዥም ጊዜ ብድር በማያቀርቡበት በዚህ ወቅት፣ ቤቶችን በውድ ዋጋ የሚገዙ ደንበኞች እየተበራከቱ መምጣታቸው አነጋጋሪም ሆኗል፡፡
ለዚህ ጉዳይ እየቀረበ የሚገኘው ምክንያት ምናልባት የብር የመግዛት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መሄዱና ገንዘብ በባንክ ማስቀመጥ የተሻለ አማራጭ ባለመሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም ሕጋዊ ያልሆነ ገንዘብን ሕጋዊ አድርጎ ለማቅረብ አማራጭ ሊሆን በመቻሉ ምክንያት ወይም የመንግሥት የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች አፈጻጸም ደካማ በመሆኑ፣ ውዱን የግል ሪል ስቴት በርካቶች እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ መላ ምቶች እየቀረቡ ነው፡፡ አቶ ለዓለም በዚህ ጉዳይ ላይ አስተዳደሩ እንደዳልመከረ ገልጸዋል፡፡
ሰንሻይን ሪል ስቴት በተለያዩ ቦታዎች መለስተኛ ቤቶችን እየገነባ የሚገኝ ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡ የሰንሻይን ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በመሀል ከተማ ከግለሰብ እየገዙ የሪል ስቴት ልማት ማካሄድ አዋጭ አይደለም፡፡ የመኖሪያ ቤት ችግሩን ይፈታል ብለውም አያምኑም፡፡
‹‹እኛ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ግንባታ የምናካሂድበት ቦታ አለን፣ ከዚያ በኋላ ግን ቦታ የማይቀርብ ከሆነ ወደ ሌሎች ዘርፎች ትኩረት እናደርጋለን፤›› በማለት አቶ ሳሙኤል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሀል ከተማ በሚያካሂዳቸው የመልሶ ማልማት ፕሮግራሞች ቦታ ቢያቀርብ፣ የግሉ ዘርፍና ለመኖሪያ ቤት እጥረት ብቻ ሳይሆን በከተማ ልማት ረገድ ትልቅ እገዛ ሊያበረክት እንደሚችል አቶ ሳሙኤል ለሪፖርተር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ እስከ 1995 ዓ.ም. ድረስ በስፋትየመኖሪያ ቤት ግንባታ አልተካሄደም፡፡ በዚያ ወቅት እንኳ በተካሄደው የመኖሪያ ቤቶች ፈላጊ ሕዝብ በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ነበር፡፡
በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያ ችግሮች ምክንያት የከተማ አስተዳደሩ ባቀደው መንገድ የቤቶች ግንባታ መካሄድ ባለመቻሉ ቀውስ እየተፈጠረ ይገኛል፡፡
ቁጥራቸው የማይናቅ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከ40/60 ፕሮግራም ወደ ሪል ስቴት ኩባንያዎች መሄዳቸው እየተገለጸ ነው፡፡
ከግለሰቦች ይዞታ እየገዛ ግንባታ በማካሄድ ላይ የሚገኘው የፍሊንት ስቶን ሪል ስቴት፣ የተወሰኑ ገዥዎች ከ40/60 ቤቶች ፕሮግራም አቋርጠው ወይም ተስፋ ቆርጠው ወደ እነሱ እየመጡ መሆኑን አቶ ፀደቀ አረጋግጠዋል፡፡