Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

ተስፋ የተጣለበት የሰሊጥ የእርሻ መሬት 17 በመቶ ቀነሰ

$
0
0

ተስፋ የተጣለበት የሰሊጥ የእርሻ መሬት 17 በመቶ ማሽቆልቆሉን፣ ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ አመለከተ፡፡

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የጥናት ውጤት በ2009 ዓ.ም. በሰሊጥ የተሸፈነው የእርሻ መሬት 17 በመቶ ማሽቆልቆሉን ይገልጻል፡፡ በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የንግድ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊ፣ የሰሊጥ በዓለም ገበያ ዋጋው ማሽቆልቆል ለምርትና ለእርሻ መሬት ማሽቆልቆል ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ የሰሊጥ የምርት መጠን በዘጠኝ በመቶ እንዲያሽቆለቁል ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዓለም የሰሊጥ ዋጋ 2008 ዓ.ም. ከነበረበት በሁለት በመቶ መቀነሱን የተናገሩት የሥራ ኃላፊው፣ ይህ ዋጋ የሰሊጥ ኤክስፖርት ከተጀመረ ወዲህ በጣም ዝቅተኛ የሚባል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

አንድ ቶን ሰሊጥ እስከ 2,200 ዶላር ይሸጥ እንደነበር ያስታወሱት የሥራ ኃላፊው፣ በ2009 ዓ.ም. የተገኘው ዋጋ ግን 1,111 ዶላር እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰሊጥ የምርት መጠን በመጨመሩና የቻይና ገበያ በመቀዛቀዙ ዋጋው ሊወርድ እንደቻለም አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰሊጥ ምርት እ.ኤ.አ. በ2016/17 450 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እንደነበር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ቀደም ብሎ በነበረው ዓመት 487 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እንደነበር ታውቋል፡፡

በሰሊጥ የተሸፈነው የእርሻ መሬት 537,000 ሔክታር እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰሊጥ ዋጋ በመውረዱ በሰሊጥ ዘር የሚሸፈነው መሬት ቢቀንስም፣ በ2010 ዓ.ም. ይሻሻላል የሚል እምነት እንዳላቸው የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች አዘጋጅቶ ላኪ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ዮሐንስ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በሰሊጥ ምርት ላኪነት የሚሳተፉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነጋዴዎች በበኩላቸው፣ የንግድ ሰንሰለቱ መራዘም ከዓለም የሰሊጥ ዋጋ ማሽቆልቆል ጋር ተዳምሮ የአገር ውስጥ አምራቾችን ትርፍ በመጉዳቱ፣ ከሰሊጥ ምርት ወደ ገብስ በመሸጋገር ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም ተፈላጊ የጥራት ደረጃ ያለው የሰሊጥ ምርት ቢኖራትም፣ ምንም ዓይነት እሴት ሳትጨምር ለገበያ በማቅረቧ ጉዳት እየደረሰባት መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር ባለሙያዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰሊጥ 62 በመቶ የሚላከው ወደ ቻይና ሲሆን፣ ቀሪው 13 በመቶ ወደ እስራኤል፣ እንዲሁም ስድስት በመቶው ወደ አሜሪካ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ቻይና ከኢትዮጵያ የምታገኘውን የሰሊጥ ምርት ከራሷ ምርት ጋር አደባልቃና እሴት ጨምራ ወደ ታይላንድና ደቡብ ኮሪያ በመላክ፣ ከፍተኛ ተጠቃሚነትን ማትረፏንም ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ ግን ገበያዋን ማስፋት ባለመቻሏና እሴት ባለመጨመሯ ብቻ በዓለም ገበያ ዋጋ ማሽቆልቆል ተመታለች ብለዋል፡፡ 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles