በዳዊት እንደሻው
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ያወጣውን የ1.3 ሚሊዮን ቶን የማዳበሪያ ግዥ ጨረታ ለማሸነፍ፣ ከ11 ዓለም አቀፍ አቅራቢዎች እየተፎካከሩ ነው፡፡
ከሳምንት በፊት የተከፈተው ጨረታ በአራት ተከፋፍሎ የወጣ ነው፡፡ አቅራቢዎች ዩሪያ፣ ኤንፒኤስ፣ ኤንፒኤስቢ፣ እንዲሁም ኤንፒኤስ ዚንክ ቦሮን የተባሉ የማዳበሪያ ዓይነቶችን ለማቅረብ ይወዳደራሉ፡፡
በዚህ መሠረት ከአጠቃላዩ አቅርቦት 550 ሺሕ ቶን ዩሪያ፣ 500 ሺሕ ቶን ኤንፒኤስቢ፣ 200 ሺሕ ቶን ኤንፒኤስ፣ እንዲሁም 50 ሺሕ ቶን ኤንፒኤስ ዚንክ ቦሮን ማዳበሪያዎች ናቸው፡፡
በዚህ በተለያዩ ሎቶች ተከፋፍሎ በወጣው ጨረታ ሁለት አቅራቢ ኩባንያዎች የአብዛኛውን አቅርቦት ዝቅተኛውን ዋጋ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሳምሰንግ ሲኤንድቲ የተባለ የሲንጋፖር ኩባንያ ለዩሪያ ማዳበሪያ ለአንድ ቶን 314.34 ዶላር ዋጋ አቅርቧል፡፡ ይህም ኩባንያው ለጠቅላላ የዩርያ አቅርቦት የሰጠውን ዝቅተኛ ዋጋ 172.8 ሚሊዮን ዶላር ያደርሰዋል፡፡
ከ1.3 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ውስጥ 750 ሺሕ ቶን ኤንፒኤስ፣ ኤንፒኤስቢና ኤንፒኤስ ዚንክ ቦሮን ማዳበሪያ ለማቅረብ፣ ኦሲፒ የተባለው የሞሮኮ የማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ዝቅተኛውን ዋጋ ሰጥቷል፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት በነበረ ተመሳሳይ የማዳበሪያ ግዥ ይህ የሞሮኮ ኩባንያ 70 በመቶ የሚሆነው ማዳበሪያ ማቅረብ ችሎ ነበር፡፡ ከሁለቱ ኩባንያዎች በቀረበው አነስተኛ ዋጋ መሠረት አጠቃላዩ የማዳበሪያ ዋጋ 417 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡
የ11 አቅራቢዎች ዋጋ ተከፍቶ ካለቀ በኋላ የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚና የጨረታ ኮሚቴው ሰብሳቢ ታፈሰ ገብሩ (ዶ/ር)፣ የጨረታውን ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተገመገመ በኋላ እንደሚያሳውቁ ለተጫራቾች አስታውቀዋል፡፡
