ካፒቴን አበራ ለሚ የናሽናል አየር መንገድ ኢትዮጵያ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ ናሽናል አየር መንገድ (የቀድሞው ኤር ኢትዮጵያ) ከአሥር ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ የግል አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ ከሚጠቀሱ ኩባንያዎች መካከል ይመደባል፡፡ ኩባንያው በበርካታ ችግሮች ውስጥ በማለፍ የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ የሚጠባበቅበት አቋም ላይ እንደሚገኝ ካፒቴን አበራ ይናገራሉ፡፡ ኩባንያቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ በተከሰተው ፖለቲካዊ ትኩትና በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ያሳለፋቸው ጊዜያት ከባድ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት ለግሉ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆን፣ በግል አየር መንገዶች ላይ የተቀመጡት የመደበኛ በረራ እንዲሁም የአውሮፕላን መቀመጫ ገደቦች እንደልብ አላሠራ ብለው የቆዩ ቁልፍ ችግሮች እንደነበሩም ያስታውሳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት እነዚህን ገደቦች እንደሚያሻሽል ተስፋ የተጣለበት ሕግ እንደሚፀድቅ ሲጠበቅ፣ ኩባንያው በራሱ በኩል የሚያከናውናቸው እንቅስቃሴዎች በአገሪቱ አቪዬሽን ዘርፍ ውስጥ ትርጉም ያለው ሥራ ለመሥራት የተነሳበት ዓመት መሆኑን ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ አብራርተዋል፡፡ ተቋማቸው ከአዲሱ ዓመት ጀምሮ አዳዲስ አካሄዶችን እንደሚከተል ሲገልጹም፣ በአቪዬሽን ኮሌጁ የማስተርስ ዲግሪ ሥልጠና ፕሮግራሞች መካተታቸውን፣ አውሮፕላኖችን መግዛት ስለማሰቡና ስለመሳሰሉት ጉዳዮች ብርሃኑ ፈቃደካፒቴን አበራ ለሚን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በኢቬዬሽን ኮሌጃችሁ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚያገለግሉ ሠልጣኞችን በማውጣት በየዓመቱ ለገበያ ስታቀርቡ ቆይታችኋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአቪዬሽን ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪ መርሐ ግብሮችን አዘጋጅታችኋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ቢነግሩን?
ካፒቴን አበራ፡-አቪዬሽን ኮሌጁ በሚገባ እየሠራ ነው፡፡ በጥራት ላይ ትልቅ ኢንቨስትመንት አካሂደናል፡፡ ዘንድሮ በአቪዬሽን ማኔጅመንት በማስተርስ ዲግሪ ማስተማር እንጀምራለን፡፡ በኤሮናውቲካል ኢንጂነሪንግና በኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ በመጀመርያና በሁለተኛ ዲግሪ፣ በአቪዬሽን ሳይንስ በመጀመርያ ዲግሪ እንዲሁም በሆቴልና ቱሪዝም መስክ በዲግሪ ፕሮግራሞች ማሠልጠን እንጀምራለን፡፡ የራሳቸውን ሳተላይት ማምጠቅ የሚችሉ ሰዎችን ማፍራት የምንችለው በዚሁ መልኩ ስንሠራ ነው፡፡ ትምህርት የሚያፈራው ጭንቅላቱ የተሞረደ ሰው ነው፡፡ ሰው የአገር ሀብት ነው፡፡ የአገር ሀብት የሆነን ሰው ደግሞ እንደ ማንኛውም ሸቀጥ አይደለም የምታፈራው፡፡ የሰዎችን አስተሳሰብ በሚገባ ቀርፀህ ካላቀረብክ በቀር፣ ራሳቸውን ጠቅመው ሌሎችንም አገርንም እንዲጠቅሙ መጠበቅ ይከብዳል፡፡ በመሆኑም አብዛኛውን ትኩረታችን በምንሰጠው የትምህርት አገልግሎት ላይ ጥራትን ቀዳሚ ያደረግነው፡፡ ስለዚህ እ.ኤ.አ. በ2015 እና በ2016 የአፍሪካ ከፍተኛ ተቋም ሆነን የተመረጥንበት ምክንያቱም ይኼው ነው፡፡ አስተማሪዎችን ከውጭ በማስመጣት ተማሪዎች እንዲታገዙ እናደርጋለን፡፡ የሥነ ልቦናና የተግባቦት ትምህርትን በማካተት ማስተማራችን ተማሪዎቻችን በሥነ ልቦና ረገድ ትልቅ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ እየረዳቸው ነው፡፡ የእኛ ተማሪዎች የነበሩ ልጆች በሌሎች አገሮች የዓመቱ ምርጥ ሠራተኞች እየተባሉ በሚሠሩባቸው አየር መንገዶች ሲሸለሙ እያየን ነው፡፡ እዚህ አገር ውስጥም የራሳቸውን ሥራ ጀምረው ጥሩ ሕይወት የሚመሩ ልጆች ስናይ፣ የሰውን አዕምሮ በሚገባ በማዳበር የሚታየው ለውጥ ነው የእኛ ስኬት፡፡ ውጭ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠርና መምህራኖቻቸውን በማስመጣት አመለካከት ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችን እንዲሰጡልን ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ በፊት ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ደረጃ የሠለጠኑ ባለሙያዎችን የሚያቀርብ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም አልነበረም፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የአቪዬሽን ኮሌጁ በተለይ በማስተርስ ደረጃ ተማሪዎችን የመቀበል አቅሙ ምን ያህል ነው? በአንድ ጊዜ ምን ያህል ተማሪዎችን ትቀበላላችሁ?
ካፒቴን አበራ፡-የቅበላ አቅማችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥራትና ቁጥጥር ኤጀንሲ ያስቀመጠልን ቁጥር አለ፡፡ ይሁንና በአሁኑ ደረጃ የሚኖረን አቅም በ200 ገደማ የሚቆጠር ነው፡፡ አሁን ላይ ብዛት ሳይሆን በጥራት ላይ ነው ራሳችንን ለመገንባት የምንፈልገው፡፡ የምናሠለጥናቸው ተማሪዎች ከአገር አልፈው በውጭ ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ እንዲሆኑ ነው የምንፈልገው፡፡ ሆኖም በመንግሥት ደረጃም ቢሆን ለትምህርት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው፡፡ ለኢንዱስትሪና ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ለትምህርት ዘርፉም መሰጠት አለበት፡፡ ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙት 27 ሚሊዮን ልጆች ናቸው ይባላል፡፡ ከ27 ሚሊዮኑ ደግሞ ምን ያህሉ ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ? የተቀሩትስ ምን ይሆናሉ? ብለህ ስታስብ እነዚህ ዜጎች ብዙ ሥራ የሚያስፈልጋቸው ሆነው ታገኛቸዋለህ፡፡ ዩኒቨርሲቲ የገቡትም ቢሆኑ የሕይወትን ቁልፍ ጨበጡ ማለት አይደለም፡፡ የአስተሳሰብ ዘዴያቸው በሚገባ የተቃኘ መሆን አለበት፡፡ ከራሱ አልፎ ማሰብ የሚችል ትውልድ መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡ በዚህ አገር ውስጥ የተፈጠረው ሀብት አብዛኛው መጠን ከአንዱ ወደ ሌላ በማሻገር እንጂ በአዲስ ነገር ፈጠራ ላይ የተመሠረተው ጥቂት ነው፡፡ የሌላው ሰው ሀብት ወደ ራስ በማዞር፣ የመንግሥትን ሀብት ወደ ራሳቸው በማዛወር የሚገኘው ሀብት ከሰው አዕምሮ ከሚመነጨው አዲስ ሀብት አኳያ ሲታይ ከፍተኛ መጠን አለው፡፡ እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ በመቀየር አዳዲስ ሀብት መፍጠር የሚችሉ ልጆችን ለመፍጠር እየጣርን ነው፡፡ ሰውን አበላሽተህ ካወጣህ፣ ገንዘብ እንዲሠሩ ብቻ የሚገፋፋ አካሄድ ከተከተልክ አገርን ነው የምታበላሸው፡፡ ከአገሪቱ ዕድገት ጋር የሚጣጣም ነገር ካልፈጠርን፣ ስማችን ወደላይ ወጥቶ ሥራችን ግን ታች የሚገኝ ከሆነ ማንነታችንን ያበላሽብናል፡፡ ይህንን ለመቅረፍ ዋጋ እየከፈልን ነው፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች እየመጡ የሚማሩ ልጆችም አሉን፡፡
ሪፖርተር፡- በአቪዬሽኑ መስክ፣ ተዛማጅ በሆኑ የሆቴልና ቱሪዝም መስክም ሰዎችን አሠልጥናችሁ እያወጣችሁ ነው፡፡ ሆኖም እነዚህ ዘርፎች ከፍተኛ የሠለጠነ የሰው እጥረት የሚታይባቸው ናቸው፡፡ በዘርፉ ስለሚታየው ችግር ምን ታዝባችኋል? ምንስ ያህል አስተዋጽኦ አድርጋችኋል?
ካፒቴን አበራ፡-የታዘብነው ነገር ቢኖር ሰዎች ስሙን እንጂ ከስማቸው ጋር ሊሄድ የሚችል ጥራት ያለው የሙያ ዕውቀት እጥረት እንዳለባቸው ነው፡፡ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ሳይንሱን ተምረውና አውቀው የሚሠሩ ሰዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ከሌላ የሙያ መስክ እያመጣን እናሠለጥናለን እንጂ ከመነሻው የአቪዬሽን ትምህርት ተምረው ወደ ሥራ የሚገቡ ሰዎች ብዙም አልነበሩም፡፡ እስካሁን አጫጭር ሥልጠናዎችን ስንሰጥ ቆይተናል፡፡ በዚህም ጥሩ ሠርተናል ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ በሆቴልና ቱሪዝም መስክ በምንሰጠው ሥልጠና ሳቢያ ገና ትምህርት ሳይጨርሱም የሥራ ዕድል የሚያገኙ ሠልጣኞች አሉን፡፡ እየሠሩ የሚማሩም አሉ፡፡ ምንም እንኳ በተፈጥሮ ኢትዮጵያውያን ትሁት መሆናችን ለቱሪዝምና መስተንግዶ ዘርፉ አጋዥ ሆነልን እንጂ የምንሰጠው አገልግሎት ብዙ ድክመት ይታይበታል፡፡ አስተናጋጆች ሰውን ማንበብ መቻል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በጭብጨባ ወይም በሌላ ዘዴ መጥራት ተገቢ አይደለም፡፡ አንድ ነገር ፈልገህ ዞር ስትል ከተፍ ብሎ አጠገብህ የሚገኝ አስተናጋጅ መኖር አለበት፡፡ አገልግሎት ተኮር መሆን አለባቸው፡፡ በሌሎች አገሮች ይህ የተለመደ ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ቱሪዝም መስክ ላይ የተደረገ ጥናት የሚያመላክተው ዝቅተኛ የአገልግሎትና የመስተንግዶ ችግር ለዘርፉ ዕድገት ማነቆ መሆኑን ነው፡፡ ይህን ለማምጣት ሥልጠና ያስፈልጋል፡፡ ስለሚሰጡት መስተንግዶ ተገልጋዩ ማግኘት የሚፈልገውን ነገር በቅልጥፍና የሚያቀርቡ ባለሙያዎች የሚፈጠሩት በክህሎትና በትምህርት ነው፡፡ ይህንን ለማምጣት እየሠራን ነው፡፡ ጥሩ ግብረ መልስም እያገኘን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከቻይና፣ ከእንግሊዝና ከሌሎች ተቋማት ጋር ግንኙነት እንዳላችሁ ይታወቃል፡፡ ሌሎች የጨመራችኋቸው አገሮች አሉ?
ካፒቴን አበራ፡-በካናዳ ከሚገኘው ከዓለም አቀፉ የአየር ትራስፖርት ማኅበር (IATA) ዕውቅና በማግኘት ሥልጠና የምንሰጥ ተቋም ነን፡፡ በእንግሊዝ ከሚገኘው አይሲኤል ጋር አብረን እየሠራን እንገኛለን፡፡ በቻይና ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችም ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ ብዙ ሰው ወደ ቻይና ሄዶ ዕቃ ያስመጣል፡፡ እኛ ግን እዚህ ደረጃ የደረሱበትን ዕውቀት መጋራት ነው የምንፈልገው፡፡ አስተሳሰባቸውን፣ እነሱን እዚህ ደረጃ ያደረሰውን ነገር ለመውሰድ ነው ከዩኒቨርሲቲዎቻቸው ጋር እየሠራን የምንገኘው፡፡ በዚህ ዓመት አዳዲስ የምንሠራቸውም ይኖራሉ፡፡ እንግሊዞችም በሚሰጣቸው ትምህሮችና አስተሳሰባቸው ከእኛም ከሌሎችም ጋር ለየት ያለ ነገር ስላላቸው፣ ከእነሱም ጋር እየሠራን ነው፡፡ የአስተሳሰብ ልዩነት አለ፡፡ በረንዳ በሚተኛውም ሆነ በእኛ መካከል ያለው ልዩነት የአስተሳሰብ ነው፡፡ አንዳንዱ ራሱን ለመቻል የሚቸግረው፣ አንዳንዱ ደግሞ ከራሱ አልፎ ለአገርም የሚተርፍ ሥራ ለመሥራት የሚሯሯጠው በአስተሳሰብ ልዩነት ምክንያት ነው፡፡ ለዚህም ነው ከሌሎች አገሮች ጋር አብሮ በመሥራት አስተሳሰባቸውንም ጭምር ለመቅሰም የምንጥረው፡፡
ሪፖርተር፡- እስካሁን ምን ያህል ተማሪዎችን አሠልጥናችኋል?
ካፒቴን አበራ፡-እስካሁን ከ1,000 በላይ ተማሪዎችን አሠልጥነን አስመርቀናል፡፡ ይሁንና በአቪዬሽን መስክ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሰው አሠልጥነህ ማውጣት አይታሰብም፡፡ ምክንያቱም መሟላት የሚገባቸው ጥብቅ ጉዳዮች ስላሉ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ገበያው የሚፈልገው ከፍተኛ የሙያ ብቃትና ክህሎት ያላቸውን ሠልጣኞች ነው የምታወጣው፡፡ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውም ቢሆን ጥቂት ነው፡፡ በዚያም ላይ ትምህርት ጀምሮ የሚያቋርጠውም አለ፡፡ ይሁንና ጥቂትም ቢሆኑ፣ በየዓመቱ የምናስመርቃቸው ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከአቪዬሽን ኮሌጁ ባሻገር በግል አቪዬሽን መስክም በትራንስፖርትና በሌላውም አገልግሎት ዘርፍ ትሠራላችሁ፡፡ የግል አየር መንገዶች የቻርተር በረራ አገልግሎት ብቻ እንዲሰጡ ተገድበዋል፡፡ ከዚህ አኳያ በገበያው ውስጥ የምታደርጉት እንቅስቃሴስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ካፒቴን አበራ፡-በግል የአየር መንገድ አገልግሎት መስክ የተቀመጡ ገደቦች ሥራችን ላይ ጫና አድርገዋል፡፡ መደበኛ የበረራ አገልግሎት መስጠት ለግል አየር መንገዶች አለመፈቀዱ፣ ከዚህ ባሻገር ከ50 ወንበሮች በላይ ያላቸውን አውሮፕላኖች መጠቀም አይቻልም መባሉና የመሳሰሉት ገደቦች ሁሉም የግል አየር መንገዶች የቻርተር በረራ ብቻ እንዲሠሩ፣ የአንዱን ደንበኛ ሌላው እየተሻማ እንዲሠራ ብቻ የሚያስገድዱ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል፡፡ ሆኖም ግን በ2009 ዓ.ም. በተወካዮች ምክር ቤት እንደሚፀድቅ ሲጠበቅ የነበረ አዲስ ፖሊሲ ተነድፏል፡፡ ምናልባት በአዲሱ ዓመት መጀመርያ ወራት ይፀድቃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ይህ ሕግ ለግል አየር መንገዶች መደበኛ በረራን እንደሚፈቅድ ሲጠበቅ፣ ከዚህ ቀደም የተቀመጠው ከ50 መቀመጫ በላይ ያላቸው አውሮፕላኖችን መጠቀም አይቻልም የሚለውን ሕግ የሚያሻሽል ስለሚሆን ሕጉ ከፀደቀ በኋላ የሚመጣውን ለውጥ እናያለን፡፡ እንደ ተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ያሉ አንድ ክፍለ አገር ብቻ የሚያክሉ አገሮች የሚያስተዳድሯቸውን አየር መንገዶች ብዛት ሳይ ይገርመኛል፡፡ ኤምሬትስን ጨምሮ ፍላይ ዱባይ፣ ኤር ዓረቢያ፣ ኢታሃድ፣ ራካልሴማ የሚባሉትን ጨምሮ በርካታ ትልልቅ አየር መንገዶች በዚያች ትንሽ አገር ውስጥ መኖራቸው ይደንቀኛል፡፡ ሕዝባቸው ትንሽ ነው፡፡ የሚበሩበት ክፍለ አገር፣ የሚያመላልሱት ሕዝብ የላቸውም፡፡ ነገር ግን ከአገራቸው ባሻገር ዓለምን የማዳረስ ራዕይ ያላቸው ናቸው፡፡ እኛ ግን የምናመላልሰው 100 ሚሊዮን ሕዝብና የምንበርበት አገር አለን፡፡ ብዙ ማድረግ የምንችልበት ዕድል አለ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባደገበት ደረጃ የእሱን አምስት ስድስት ያህል ተጨማሪ አየር መንገዶች ቢኖሩ ለአገሪቱ ጥቅም እንጂ ጉዳት አይሆኑም፡፡ የግድ የአገሪቱ ገበያ ብቻም አይደለም መዳረሻው፡፡ በኬንያ ያሉ በአብዛኞቹ ኦፕሬተሮች ማለትም 80 በመቶዎቹ የሚሠሩት ከኬንያ ውጭ ነው፡፡ አፍሪካን የተቆጣጠሩት የግል ኦፕሬተሮች የኬንያና የደቡብ አፍሪካዎቹ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥጋት አንሆንበትም እያሉ ነው?
ካፒቴን አበራ፡-አንሆንም፡፡ የምንሠራበት አግባብ ይለያያል፡፡ የከተማ አንበሳ አውቶቡስና ላዳ ታክሲ የቱ ጋ ነው ውድድር ውስጥ የሚገቡት? የእኛም ሥራ የዚያን ያህል የተራራቀ ነው፡፡ እንደውም ትልቁን አየር መንገድ ልንመግበው እንጂ ሥጋት ልንሆንበት የምንችልበት አጋጣሚ የለም፡፡ ሥራችንም የቢዝነስ ሞዴላችንም ይለያያል፡፡ ፖሊሲ አውጪዎቹም ይህንን በሚገባ ተረድተው ኢንዱስትሪው እንዲያድግ መሥራቱ ለሁሉም ጥቅም ነው፡፡ የአሜሪካ ቻርተርድ አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎች ብቻ በዓመት 150 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛሉ፡፡ ለአንድ ኢኮኖሚ 150 ቢሊዮን ዶላር የሚያስገኝ ያን ያህል ብዙም ዕውቅና ከሌላቸው ኩባንያዎች የሚመጣ ከሆነ ምን ያህል ድርሻ እንዳላቸው የሚያሳይ ነው፡፡ ኬንያ ያሉትም በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገቢ እያስገኙ ነው፡፡ ማደጋችን ጥቅም አለው ለማለት እፈልጋለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በመደበኛ የበረራ መርሐ ግብርና በመቀመጫ ቁጥር ላይ ለበርካታ ዓመታት አቤቱታ ስታሰሙ ቆይታችኋል፡፡ አሁን ላይ ማሻሻያ የሚደረግ ከሆነ ለእስካሁኑ ችግራችሁ መፍትሔ ተገኘለት ማለት ይቻላል?
ካፒቴን አበራ፡-ችግሩ እንደ ችግርነቱ በወቅቱ ሲፈታ ነው ጥሩ፡፡ ችግር መሆኑ ለታወቀ ጉዳይ ከዓመታት ቆይታ በኋላ መፍትሔ ስታመጣ፣ ችግሩ መልኩን ሊቀይር ይችላል፡፡ መፍትሔ ያልከው ነገር መፍትሔ መሆኑ ሊቀር ይችላል፡፡ ምክንያቱም ችግሩ ተቀይሯልና ነው፡፡ አሁን ላይ ውኃ እያስፈለገህ፣ ውኃ የምታገኘው ግን ከሳምንት በኋላ ከሆነ፣ ምናልባት ያኔ ውኃ ሳይሆን ግሉኮስ ሊሆን ይችላል የምትፈልገው፡፡ ያኔውኑ ውኃ በጠማህ ወቅት ባለማግኘትህ የተባባሰ ችግር ስለመጣብህ ውኃ ሳይሆን ሌላ ሕይወት አድን ነገር ይሆናል የምትፈልገው፡፡ ይህ መሆኑም የማያባራ ቅሬታና ስሞታ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል፡፡ ላለፉት አሥር ዓመታት ያህል ቅሬታና ችግር ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የባለድርሻ አካላት ስብሰባ ላይ ሁሌ ተሰብስበን የምናወራው ችግር ብቻ እየሆነ በመምጣቱ እያሳፈረኝ ነው፡፡ ችግር ብቻ ለማውራት መሰብሰብ ምንም አይጠቅምም፡፡
ሪፖርተር፡- በቱሪዝም መስክ በቻርተርድ መርሐ ግብር በርካታ አገልግሎት ትሰጣላችሁ፡፡ ትልቅ ስም ያላቸው ጎብኝዎችን፣ ባለሙያዎችን፣ ባለሥልጣናትና ሌሎችንም ከቦታ ቦታ ታመላልሳላችሁ፡፡ ያለፉት ሁለት ዓመታት ሁኔታችሁ ምን ይመስላል? በአገሪቱ የነበረው የፀጥታ ችግር ሥራችሁ ላይ ያሳደረው ጫና እንዴት ይገለጻል?
ካፒቴን አበራ፡-በአገሪቱ የነበረው የፀጥታ ችግር ጎድቶናል፡፡ ሰዎችን የምናመላልሰው በጣም ገጠራማ ወደሆኑ ቦታዎች ነው፡፡ በፀጥታው ችግር ምክንያት ግን ትልቅ ጉዳት አጋጥሞናል፡፡ የግል አቪዬሽን ኢንዱስትሪው የመጀመርያ ተጎጂ ነው ብል አላጋነንኩም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጆ መቆየቱም ትልቅ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ እንደ አገር፣ እንደ ግለሰብና እንደ ኩባንያ በአገር ላይ በሚደርሱ ከባድ ሁኔታዎች ሳቢያ ውጠህ ለማለፍ የምትገደድባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ፡፡ የሚፈጠሩት ከባድ ችግሮች አንዳንዴ ኩባንያህን እስከ መክሰም ሊደርሱትም ይችላሉ፡፡ እንደምንም በአንድ እግርህ ቆመህም ልታልፍም ትችላለህ፡፡ አንድ የእንግሊዝኛ አባባል አለ፡፡ ‹‹Quitters never win and Winners Never Quit›› ይባላል፡፡ አሸናፊዎች አያቋርጡም፣ የሚያቋርጡ ደግሞ አያሸንፉም እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይኼ ነገር ዓላማዬ ነው፣ ለዚህ ነገር ነው መኖር አለብኝ ብለህ ካልክ እንደምንም ብለህ ለማለፍ ትጥራለህ እንጂ አታቆምም፡፡ በተፈጠረው ችግር ምክንያት በጣም ብዙ ዋጋ ከፍለናል፡፡ ብዙ ነገሮች ከብደውናል፡፡ ነገር ግን እንደምንም እያለፍን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የፀጥታ ችግር በነበረባቸሁ ዓመታት ውስጥ መንግሥት ምን ድጋፍ አደረገላችሁ? የደረሰባችሁን ጉዳትስ ምን ያህል ተገንዝቦታል?
ካፒቴን አበራ፡-ለአንድ ነገር ትኩረት የምትሰጠው ጥቅም አለው ብለህ ስታስብ ነው፡፡ እንደማስበው የግል ኦፕሬተሮችን ጥቅም ብዙም የተረዱት አልመሰለኝም፡፡ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ እንዲህ ይደረግን፣ እንዲህ ያለ ነገር እንፈልጋለን ብለን ብንጠይቅም የሚደረግልን ነገር የለም፡፡ ገንዘብ ስጡን አንልም፡፡ ሆኖም ሥራችን ቀለል የሚያደርጉልንን ነገሮች አድርጉልን ነው ጥያቄያችን፡፡ በሥራ ላይ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ፍቱልን ስንል ብዙም መፍትሔ አናገኝም፡፡ የግንዛቤ ችግር አለ፡፡ እንደማንኛውም ኩባንያ የሥራ ዕድል እንፈጥራለን፡፡ የውጭ ምንዛሪ እናስገባለን፡፡ በርካታ ቱሪስቶችን እናገለግላለን፡፡ ብናድግ ትልቅ ቀዳዳ ልንሞላ የምንችልበት አቅም አለን፡፡ ሆኖም የተሰጠን ትኩረት ዝቅተኛ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የኦፕሬሽን አቅማችሁ ምን ይመስላል? የምታሰማሯቸው አውሮፕላኖች፣ ያላችሁ ሀብት፣ ወዘተ ምን ያህል ደርሷል?
ካፒቴን አበራ፡-አቅም የምታዳብረው እኮ በሥራ ውስጥ ነው፡፡ የውጭ ኩባንያዎች ሥራ ሊሰጡን ይመጡና አቅም የላችሁም ይሉናል፡፡ አቅም የሚዳብረው ግን ከሥራ ነው፡፡ እየሠራን የምናካብተው ነገር ነው፡፡ ከቁስ ይልቅ የሰው አቅማችንን በሚገባ አጠናክረናል፡፡ የአውሮፕላን ኦፕሬሽን ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቅ ነው፡፡ አሥር ሚሊዮን ዶላር ለሌላ ሥራ በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ፋብሪካ ለመገንባት ጭምር ሊበቃ ይችላል፡፡ ለአቪዬሽን ግን ምንም ትርጉም የለውም፡፡ ምናልባት አንድ አውሮፕላን ትገዛበት ይሆናል፡፡ በዚህ ሳቢያ በቂ አቅም ፈጥሬለሁ አያሰኝህም፡፡ ነገር ግን ብዙ ከመቆየትና ሥራውን በሚገባ ከማወቅ የተነሳ ትልቅ አቅም ፈጥረናል፡፡ በጥቂት ነገር እንዴት ብዙ መሥራት እንደሚቻል አውቀናል፡፡ አጋጣሚዎችን በምን መልኩ እንደምንጠቀም የሚያስችሉ ክህሎቶችን ስላዳበርን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ብዙ ርቀን እንደምንሄድ ተስፋ አለን፡፡ ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ድጋፍም ማበረታቻም ብዙ የለም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብዙ ድጋፍ ያገኛል፡፡ እሱ ሌላ ዓለም ላይ የሚገኝ ነው፡፡ የጉዞና አስጎብኝ ድርጅቶችም ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ በመሀል ያለነው ትናንሽ የግል አየር መንገዶች ግን ምንም እያገኘን አይደለም፡፡ ሁሉንም ነገር በራሳችን ነው የምንወጣው፡፡ ይኼ ነው ፈተና ሲሆንብን የቆየው፡፡ ኢንዱስትሪው ማደጉ አይቀርም፡፡ እኛም እየጠራን ነው፡፡ በሁለትና ሦስት ዓመት ውስጥ የተለየ ኢንዱስትሪ እንፈጥራለን ብለን እናስባለን፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ያህል አውሮፕላኖችን ታሰማራላችሁ? የግላችሁ አውሮፕላኖች አፍርታችኋል?
ካፒቴን አበራ፡- እስካሁን ተከራይተን ነው ስንሠራ የቆየነው፡፡ ሲያስፈልግም ትመልሳለህ፡፡ እስካሁንም ለመቆየት ያህል ነው ስንሠራ የነበረው፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ትልቅ ለውጥ ይኖረናል፡፡ የራሳችን አውሮፕላኖች ይኖሩናል፡፡ ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ ይፋ እናደርጋለን፡፡ ከነበረን አካሄድ በመውጣት ትልቅ ውጤት ማምጣት እንፈልጋለን፡፡ እናድጋለን፡፡ ለአገራችን ዕድገትም ተገቢውን አስተዋጽኦ የምናደርግበት አጋጣሚ በሦስት ዓመታት ውስጥ እንፈጥራለን፡፡ ሁሌም በምትሄድበት መንገድ ስለሄድክ ብቻ አዲስ መንገድ የለም ማለት አትችልም፡፡ ከምናውቀው ነገር ወጣ ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሥራ ያስተዋልኩት ሰዎች ከለመዱት ነገርና አሠራር መውጣት ፍዳ እንደሚሆንባቸው ነው፡፡ አዳዲስ መንገዶችን እንከፍታለን፡፡
