- 51 በመቶ ድርሻውን በ48 ሚሊዮን ብር ሸጧል
በኢትዮጵያ የመነፅር ውጤቶች አምራችነቱና አከፋፋይነት የሚታወቀው ሳን ኦፕቲካል ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ለግዙፉ ዓለም አቀፍ የመነፅር አምራች ኩባንያ 51 በመቶ ድርሻውን በመሸጥ ምርቱን በአሥር እጅ ለማሳደግ ማቀዱን አስታወቀ፡፡ ሳን ኦፕቲካል በኢትዮጵያ በሕግ የተደገፈ የፍራንቻይዝ አሠራርን በመተግበር 200 ቅርንጫፎችን እንደሚከፍት አስታውቋል፡፡
በሳን ኦፕቲካል ቴክኖሎጂና በፈረንሣዩ ኤሲሎር ኢንተርናሽናል መካከል የተደረሰውን ስምምነት በማስመልከት ሐሙስ፣ መስከረም 4 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ወቅት ይፋ እንደተደረገው፣ የፈረንሣዩ ኩባንያ የሳን ኦፕቲካል የ51 በመቶ ድርሻን የገዛው በ48 ሚሊዮን ብር ነው፡፡
በመነፅርና ተያያዥ ሥራዎች ላይ ከ22 ዓመታት በላይ የቆየው ሳን ኦፕቲካል፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የተረጋገጡ ከ44 ሺሕ በላይ መነፅሮችን በዓመት የማምረት አቅም አለው፡፡ የሳን ኦፕቲካል ባለድርሻና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኔ አብርሃ እንደገለጹት፣ የአገሪቱን የመነፅር ገበያ ሲመራ ቆይቷል፡፡
ሳን ኦፕቲካል በኢትዮጵያ የመጀመርያውን የሌንስ ማምረቻ በመገንባት አዲስ ምዕራፍ እንደከፈተም ለመረዳት ተችሏል፡፡ በዚህ ዘርፍ በኢትዮጵያ ገበያ ስሙን የተከለው ሳን ኦፕቲካል፣ ከፈረንሣዩ ኩባንያ ጋር ተጣምሮ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ለማሰር ከሁለት ዓመት በላይ የወሰደ ድርድርና ዝግጅት ማድረጉን አቶ ብርሃኔ አስታውሰዋል፡፡
ሰን ኦፕቲካል ላለፉት 22 ዓመታት በዓይን መነፅር ምርት ቀዳሚ ሆኖ ቢዘልቅም፣ በሚፈልገው ፍጥነት ማደግ ስላልቻለ የውጭ አጋር በማፈላለግ የተሻለ ለመሥራት መነሳቱ ተጠቅሷል፡፡ ኤሲሎን የዓለምን 60 በመቶ የዓይን መነፅር ገበያ የተቆጣጠረ ከመሆኑ አንፃር፣ ከዚህ ኩባንያ ጋር ተጣምሮ መሥራቱ ለዕውቀት ሽግግር እንዲሁም ኩባንያው ያለውን የገንዘብ አቅም በመጠቀም ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ ይችላል ተብሏል፡፡
እንደ አቶ ብርሃኔ ገለጻ፣ ሳን ኦፕቲካል በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ያለውን ተቀባይነት ከማሳደግ በላይ ጥራት ያለውን የዓይን ሕክምና በመስጠትና መነፅሮችን በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ብሎም በአገር ውስጥ የሚታየውን የአቅርቦት ክፍተት ለመሙላት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም የመነፅርና የመነፅር አካላትን ከሚያመርተው ኤሲሎር ኢንተርናሽናል ጋር የስትራቴጂ ጥምረት መፈጸሙ፣ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያስገኝለት ያምናሉ፡፡
ኤሲሎርን በመወከል መግለጫ የሰጡት የኩባንያው የምሥራቅ አፍሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚ/ር ኒቦል ሚቼልስ፣ ከሳን ኦፕቲካል ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት በአጭር ጊዜ አገልግሎቱን ለማስፋት ተጨማሪ መዋዕለ ንዋዮችን እንደሚያፈስ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያን የዓይን መነፅር ፍላጎት ለማሟላት የሚችልበት የቴክኖሎጂና የገንዘብ አቅም እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡
ኤሲሎር ኢንተርናሽናል በዓለም የዓይን መነፅር ገበያ ውስጥ እንደ እ.ኤ.አ. በ2015 ብቻ 8.7 ቢሊዮን ዩሮ ሽያጭ ያከናወነ ግዙፍ ኩባንያ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚሁ ዓመት ከ500 ሚሊዮን በላይ ሌንሶችን ለገበያ ያቀረበው ይህ ኩባንያ፣ ከሳን ኦፕቲካል ጋር የፈጠረው ጥምረት የኢትዮጵያን የዓይን መነፅር ገበያ እንደሚቀይረውም ይጠበቃል፡፡
አቶ ብርሃኔ እንደገለጹት፣ የፍራንቻይዝ አሠራሩን ለመተግበር የሚያስችለው የመጀመርያው ስምምነት በሰነዶችና በውል ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤት እንደተፈረመ አስታውሰው፣ የፍራንቻይዝ አሠራሩን ተግባራዊ ለማድረግ በአሁኑ ወቅት ሳን ኦፕቲካል የሚያስተዳድራቸውን 12 ማዕከሎች ጨምሮ በተያዘው ዓመት 22 የሕክምና መስጫና የመነፅር መሸጫዎችን መክፈት ያስችለዋል፡፡ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የማዕከሎቹን ብዛት 200 እንደሚያደርስም ይጠበቃል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 97ቱ በአዲስ አበባ ከተማ የሚከፈቱ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ በተለያዩ የክልል ከተሞች ይከፈታሉ ተብሏል፡፡
በሁለት ሳምንታት ውስጥ በአዲስ አበባ 22 ቅርንጫፎችን ለመክፈት ስምምነት መደረጉን የገለጹት አቶ ብርሃኔ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዓይን ሕክምና መስጫና የመነፅር ማምረቻ ላብራቶሪዎችን ለመክፈት ስምምነት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
‹‹በውልና ማስረጃ በፍራንቻይዝ ስምምነት ስፈራረም እኛ የመጀመርያዎቹ ነን፤›› ያሉት አቶ ብርሃኔ፣ በፍራንቻይዝ ሕጉ መውጣት ምክንያት ሌሎች ታዋቂ ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ውስጥ እንዲሳተፉ ያስቻላል ብለዋል፡፡
የሁለቱ ኩባንያዎች የፍራንቻይዝድ ስምምነት ሦስት ደረጃዎች ያሉ ሲሆን፣ ለአገልግሎቱ የሚከፈለው አንደኛው የፍራንቻይዝ ዓይነት፣ መነፅር ብቻ የሚሸጥበት ነው፡፡ ሁለተኛው ሕክምናና የመነፅር ሥራውን ያጣምራል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ከሆስፒታሎች ጋር በሚደረግ ስምምነት በየሆስፒታሉ ውስጥ የዓይን መነፅር መሸጫ ማዕከሎችን ለማቋቋም የሚያስችል ነው፡፡ቱbault
የፍራንቻይዝ ሥርዓቱን ለመዘርጋት ሳን ኦፕቲካል ቴክኖሎጂና ኤሲሎር ኢንተርናሽናል ከኅብረት ባንክ ጋር በመሆን፣ በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉና የኩባንያዎቹን መመዘኛዎች የሚያሟሉ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በየከተሞቻቸው የፍራንቻይዝ ሱቆችን እንዲከፍቱ የሚያስችሉ የብድርና የሥልጠና ዕድሎች ይመቻችላቸዋል፡፡ ለሥራው የሚያስፈልገውን 30 በመቶ የመነሻ ገንዘብ የሚያቀርቡ ወጣቶች፣ ሥራውን ለመጀመር የሚያስችላቸውን ቀሪውን ገንዘብ በብድር መልክ ከኅብረት ባንክ እንደሚያገኙ ተጠቅሷል፡፡
ከአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር ከሚደረገው የፍራንቻይዝ ትስስር በተጨማሪ ሳን ኦፕቲካል በግል ድርጅቶችና በመንግሥት ተቋማት የአጋርነትን አሠራር መሠረት፣ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በ50 የመንግሥት የጤና ተቋማት ውስጥ የዓይን ሕክምናና የመነፅር መሸጫ ማዕከላት የማቋቋም ዕቅድ አለው፡፡ በኮሪያ ሆስፒታል ውስጥ ከሁለት ወራት በፊት በከፈተው ማዕከል ይህንን ሥራ እንደጀመረ ታውቋል፡፡
በሁለቱ ኩባንያዎች መጣመር ከሚጠበቁ ለውጦች መካከል የሳን ኦፕቲካል ዓመታዊ መነፅር የማምረት አቅም አሁን ከሚገኝበት 44,000 መጠን፣ ከሁለት ዓመት በኋላ 500,000 እንደሚደርስ መታቀዱ አንዱ ነው፡፡ የድርጅቱ የመነፅርና የመንፅር አካላት የማምረት አቅም በየዓመቱ በዕጥፍ እያደገ እንደሚሄድም ይጠበቃል፡፡
በፍረንቻይዝ ስምምነት የሚከፈቱት አዳዲሶቹ 200 የዓይን ሕክምናና የመነፅር መሸጫ ማዕከላትን በአዲስ አበባ፣ በአዳማና በመቐለ ከተሞች አዳዲስ ማምረቻዎችን የማደራጀት ሥራውን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚያስፈልገው የዓይን ሕክምናና የመነፅር አቅርቦት ላይ ብዙ እንዳልተሠራ ይታመናል፡፡ በዓለም የጤና ድርጅት የተደረጉ ጥናቶች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የዕይታ ችግር ያለባቸውና መነፅር የሚያስፈልጋቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዳሉ ማመላከቱ በአስረጅነት ያቀርባል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያውያን የዓይን ጤናቸው በከፍተኛ ሁኔታ ካልታወከ በቀር፣ የዓይን የጤና ምርመራ የማድረግ ልምድ የሌለ በመሆኑ፣ መነፅር የመጠቀምና ተያያዥ የዓይን ሕክምና የማድረግ ባህላቸው ደካማ ነው ተብሏል፡፡
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ፣ በግንዛቤ ማነስና ተገቢውን ሕክምና በማግኘት ሳቢያ ከ4.5 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ለዓይነ ሥውርነት ተዳርገዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ግማሾቹ በዓይን መነፅር መስተካከል የሚችል ችግር ነበረባቸው፡፡
ሳን ኦፕቲካል በ1987 ዓ.ም. የተመሠረተ የመነፅር ውጤቶች አምራችና አከፋፋይ ድርጅት ሲሆን፣ የአሁኑ ስሙን ያገኘው ከምሥረታው አሥር ዓመታት በኋላ ነው፡፡ ሲመረት ጀምሮ ይጠቀምበት የነበረው የንግድ ስያሜው ሳን ኦፕቲክስ የሚል ነበር፡፡ ድርጅቱ ሥራውን የጀመረው ምኒልክ ሆስፒታል ፊት ለፊት በሚገኝ አነስተኛ ሱቅ ውስጥ ነበር፡፡ በወቅቱ በቀን የሚያመርተው መነፅር ብዛት ከ25 እንደማይበልጥ ተጠቅሷል፡፡
