በነሐሴ 2009 ዓ.ም. በአንድ ወር ውስጥ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ለዓለም ገበያ የሚቀርብ የኢትዮጵያ ቡና ግብይት መጠን በ66 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ ተገለጸ፡፡ ምርት ገበያው በአንድ ወር 1.7 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶች እንዲያገበያይ በቡና እና በምርት ገበያ ላይ የተደረገው ሪፎርም አስተዋጽኦ ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡
ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወርኃዊ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ በነሐሴ 2009 ዓ.ም. ለግብይት የቀረበው አጠቃላይ የቡና መጠን 21,159 ቶን ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ለውጭ ገበያ የተዘጋጀ ቡና መጠን 15,817 ቶን ነው፡፡ ይህ በነሐሴ ወር ለውጭ ግብይት የተዘጋጀው ቡና በሐምሌ ወር ከተላከው በ66 በመቶ በልጧል፡፡
በቡና ብቻ ሳይሆን የምርት ገበያው ከሚያገበያያቸው ምርቶች በጥቅል ሲታይም፣ በቀዳሚው ወር ከነበረው በ52 በመቶ ሲጨምር በዋጋ ደረጃም የታየው ዕድገት 66 በመቶ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የምርት ገበያው እንደገለጸው በተለይ የቡና ግብይት ይህንን ያህል ደረጃ እንዲያድግ ከምክንያቶች አንዱ፣ ከቡና ሪፎርም ጋር ተያይዞ የቡና መገኛ ባለቤትነትን የተመረኮዘ የመኪና ላይ ግብይት ሥርዓት በምርት ገበያው መጀመሩ ነው፡፡ ምርት ገበያው በአዳዲስ አሠራሮች እንዲደራጅ መደረጉም ለግብይቱ መጨመር ምክንያት እንደሆነም እየተለገጸ ነው፡፡ በቡና ግብይት ገበያ የተፈጠረው ለውጥ በ2010 በጀት ዓመት ከቡና የሚገኘው ገቢ እስከ 30 መቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በነሐሴ ወር በ23 የግብይት ቀናት በአጠቃላይ 1.7 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው 33,528 ቶን ቡና፣ ሰሊጥና ቦለቄ ማገበያየት ችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሐምሌ ወር ካገበያያቸው ምርቶች መካከል ቡና ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል፡፡ በአጠቃላይ በነሐሴ ወር ብቻ 1.40 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው 21,159 ቶን ቡና ግብይት ተካሂዷል፡፡ ይህ የግብይት መጠን በዋጋ 82 በመቶ፣ በመጠን 63 በመቶ ይይዛል፡፡ ከዚህ የቡና ግብይት ውስጥ ለውጭ ገበያ የተዘጋጀ ቡና 15,817 ቶን፣ ለአገር ውስጥ ፍጆታ 4,152 ቶን፣ ስፔሻሊቲ ቡና 1,190 ቶን ድርሻ እንዳላቸው ምርት ገበያው አስታውቋል፡፡ እያንዳንዱ የቡና ዘርፍ በፈረሱላ የተሸጠበት ከፍተኛ ዋጋ ስፔሻሊቲ ቡና 2,807 ብር ሲሆን፣ የታጠበ ቡና ደግሞ 1,550 ብር ዋጋ ነበረው፡፡ ያልታጠበ ቡና 2,753 ብር ሲሆን፣ ዝቅተኛ ዋጋ ደግሞ ስፔሻሊቲው 950 ብር፣ የታጠበ ቡና 810 ብር፣ ያልታጠበ ቡና 800 ብር እንደሆነም መረጃው አሳይቷል፡፡ በቀዳሚው ወር ግን ተገበያይቶ የነበረው የቡና መጠን 13,972 ቶን የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ለውጭ ገበያ የቀረበው 68.4 በመቶ ድርሻ ነበረው፡፡ በሐምሌ ወር 7,841 ቶን ያልታጠበ ቡና በ467 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ የነቀምት ቡና ከአጠቃላይ የግብይት መጠን 32.54 በመቶ በመያዝ በግብይቱ በከፍተኛ ሆኖ ተሸጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በሐምሌ 2009 ዓ.ም. የስፔሻሊቲ ቡና ግብይት መጠን 1,761 ቶን የደረሰ ሲሆን፣ የግብይት ዋጋውም 131 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውለው ቡና ደግሞ 2,635 ቶን መጠን የነበረው ሲሆን፣ አጠቃላይ ሽያጩም 129 ሚሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡
በነሐሴ ወር ከተካሄደው ግብይት ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ ግብይት የያዘው ሰሊጥ ሲሆን፣ 303 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው 11,479 ቶን ሰሊጥ በምርት ገበያው ማገበያየት ተችሏል፡፡ ከአጠቃላይ ግብይቱ በመጠን 34 በመቶ፣ በዋጋ 18 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ በኩንታል የነበረው ዋጋም ከፍተኛው 2,906 ብር፣ እንዲሁም ዝቅተኛው 2,200 ብር አውጥቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 205 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው 7,455 ቶን ነጭ የሑመራ ጎንደር ሰሊጥ ግብይት በመፈጸም ቀዳሚ ሆኗል፡፡ ባለፈው ወር የሰሊጥ ግብይት መረጃ እንደሚያመለክተው፣ 12,660 ቶን ቡና መገበያየቱ ነው፡፡ ይህም 317 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ነበር፡፡
