በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ፋብሪካ በመትከልም ሆነ ምርቱን ለአገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ቀዳሚ የሆነው ቢኤንድሲ የተባለው የአሉሚንየም አምራችና አከፋፋይ ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ ስም ያመረታቸውን የአሉሚንየም ምርቶች ወደ ውጭ መላክ ጀመረ፡፡
ባለፉት ዓመታት ኩባንያው ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን የአገር ውስጥ የአሉሚንየም ፍላጎት ሲያቀርብ መቆየቱም ተገልጿል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አማራጭ ተጨማሪ ገበያ በማፈላለግ ቅዳሜ ጳጉሜን 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ምርቱን ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ግብፅ መላኩን ኩባንያው ይፋ አድርጓል፡፡
በኢትዮጵያ መመረታቸውን የሚያሳይ መረጃ የታተመባቸውን የአሉሚንየም ፕሮፋይሎች ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ለማብሰር በፋብሪካው ውስጥ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ ኩባንያው መንግሥት ትኩረት ከሰጠው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከመሳተፍ ባሻገር አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቷ አንገብጋቢ ደረጃ በደረሰበት ወቅት ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ፈር ቀዳጅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቢኤንድሲ ፋብሪካ ምርት የሆኑት የአሉሚንየም ፕሮፋይሎች በሁለት ኮንቴይነሮች ተጭነው ሲላኩ ሚኒስቴር ዴኤታው፣ ሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች፣ የፋብሪካው ባለቤቶችና የተጋበዙ እንግዶችን በሥፍራው ተገኝተው ነበር፡፡
የኩባንያው ባለቤትና ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ብሩክ ኃይሌ ከሥነ ሥርዓቱ በኋላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የግብፅ ኩባንያ ከተለያዩ አገሮችና አምራቾች ጋር ባደረገው ውድድር የኢትዮጵያ ምርት የተሻለ ጥራት እንዳለው በማረጋገጡ ምርታቸውን ለመጀመርያ ጊዜ ለውጭ ገበያ አቅርበዋል፡፡
ከግብፅ ኩባንያ ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ቢኤንድሲ እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ 600 ቶን የአሉሚንየም ምርት ይልካል፡፡ በመጀመሪያው ዙር 30 ቶን የሚደርስ ምርት መላኩንም አቶ ብሩክ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት ኩባንያው ከ1.6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከሽያጩ ገቢ እንደሚያገኝ፣ በየሁለት ሳምንት ደግሞ ምርታቸውን እንደሚልኩም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ፋብሪካው ተጨማሪ የውጭ ገበያ ዕድል ለመፍጠር ሌላ ጥናት እያስጠና መሆኑም አክለዋል፡፡
ለዚህም ጥረት ከ300 ሚሊዮን በላይ በሆነ ወጪ ፋብሪካውን ለማስፋፋት ከአዲስ አበባ አስተዳደር 7,000 ካሬ ሜትር የማስፋፊያ ቦታ ማግኘታቸውንም አቶ ብሩክ አስረድተዋል፡፡ የማስፋፊያ ግንባታውን በስድስት ወራት ጨርሰው ወደ ምርት ለመግባት እንዳቀዱም ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለሕንፃ ግንባታዎች የሚገጣጣሙ የአሉሚንየም ፕሮፋይሎችን በማምረት ላይ የሚገኘው ቢኤንድሲ ኩባንያ፣ የምርት ዓይነቶችን የማስፋፋት ዕቅድ መያዙም ተገልጿል፡፡
