በዳዊት እንደሻው
የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚደረጉ የግልና የመንግሥት ፕሮጀክቶች፣ በአንድ ዓመት 12 ቢሊዮን ብር ብድር ለመስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡
ብድሩ በዚህ ዓመት ለተበዳሪዎች ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህም መሠረት ባንኩ ከግል ባለሀብቶችና ከመንግሥት የቀረበለትን ብድር ጥያቄ እየገመገመና በጥልቀት እያየ እንደሚገኝ፣ የባንኩ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ኅብረት ተወካይ ክሪስቶፈር ሊት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በባለፈው ዓመት ብቻ 76 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ መንግሥት መስጠቱ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ፓዋ ቫን ባልኮም ብድሩን የተፈራረሙ ሲሆን፣ ብድሩም የአገሪቱን የጥቃቅንና የመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለመደገፍ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተገልጾ ነበር፡፡
የአሁኑ 12 ቢሊዮን ብር ብድር ባንኩ ከዚህ ቀደም ሰጥቶት ከነበረው የብድር መጠን የተሻለ መሆኑን፣ ከሌላው ጊዜ በተለየም በዛ ላሉ የግልና የመንግሥት ፕሮጀክቶች ብድር እንደሚሰጥ ሚስተር ሊት አስታውቀዋል፡፡
ይህም ባንኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚያሰፋው ተገልጿል፡፡ ባንኩ ለኢትዮጵያ ዕገዛ ማድረግ ከጀመረ 40 ዓመታት ያሳለፈ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በፊት ቢሮውን አዲስ አበባ መክፈቱ ይታወሳል፡፡
ባንኩ ለማበደር እያያቸው ከሚገኙ የብድር ጥያቄዎች ውስጥ በትውልደ ኢትዮጵያውያን ለተቋቋመው ሴፈስ የተባለ ኩባንያ፣ በቅርቡ የአሥር ሚሊዮን ዶላር ብድር ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ለኩባንያው የሚሰጠው አሥር ሚሊዮን ዶላር ብድር ከሳምንት በኋላ በባንኩ ቦርድ ይፀድቃል ተብሏል፡፡
ከዚህ ብድር በተጨማሪ ባንኩ ለመቀሌና ለድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ቁጥር ሁለት ግንባታ፣ እንዲሁም ደቡብ ክልል ውስጥ ለሚከናወነው የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርክ ግንባታ እንዲውል 200 ሚሊዮን ዶላር ለማበደር የቀረበለትን ጥያቄ እያየ ይገኛል፡፡
ይህ የ200 ሚሊዮን ዶላር የብድር ጥያቄ ቅድመ ጥናት እየተደረገበት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሌላው ባንኩ የቀረበለት የብድር ጥያቄ ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር ይወስዳል ለተባለው ሞጆ ለሚቋቋመው የቆዳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የሚውል ነው፡፡
ይህ የቆዳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአሁኑ ጊዜ በሞጆ ከተማ የሚገኙ ብዛት ያላቸው የቆዳ ፋብሪካዎችን አንድ ላይ አሰባስቦ ይይዛቸዋል ተብሏል፡፡ ፓርኩ በአሁኑ ጊዜ የከተማዋን አየር እየበከለ ላለውና ከፋብሪካዎቹ ለሚወጣው መርዛማ ፈሳሽ ማከሚያ ዘመናዊ ሥርዓት እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡
በግል ባለሀብቶች እንዲከናወኑ ለታቀዱ ኢንቨስትመንቶች ባንኩ ከፍ ያለ ትኩረት እንደሰጠም ታውቋል፡፡
ባንኩ ኤምብር ከተባለ የግል ኩባንያ የቀረበለትን የብድር ጥያቄ እየተመለከተ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የብቅል ፋብሪካ ለማቋቋም የሚያስችላቸውን የብድር ጥያቄ ተመልክቶ መልስ ይሰጣል ተብሏል፡፡
ከታዳሽ ኃይል ልማት ጋር በተያያዘ 100 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ብድር ለኮርቤቲ የጂኦተርማል ፕሮጀክት፣ 50 ሚሊዮን ዶላር ለመተሐራ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የመተሐራ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ለመገንባት መንግሥት ዓለም አቀፍ ጨረታ ያወጣ ሲሆን፣ አምስት ኩባንያዎች እየተሳተፉ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ሃምሳ ሚሊዮን ዶላር ብድሩም በአሁኑ ወቅት በጨረታው እየተሳተፉ ያሉትን ኩባንያዎችን ለማገዝ ይውላል ተብሏል፡፡ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ እስካሁን ለአገሪቱ ወደ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብድር አበድሯል፡፡
