Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

ለንግድ ምክር ቤቱ የተያዘው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ እንዲራዘም ጥያቄ ቀረበ

$
0
0

 

.እስካሁን ተወዳዳሪ ዕጩዎች አልቀረቡም

ከአንድ ዓመት በላይ ሲንከባለል የቆየውና መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ጠቅላላ ጉባዔና የቦርድ አመራሮች ምርጫ፣ ለተጨማሪ ሁለት ሳምንታት እንዲራዘም ጥያቄ ቀረበ፡፡ ንግድ ምክር ቤቱን ለመምራት አዲስ ዕጩ እስካሁን አልቀረበም፡፡

ከንግድ ምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀን ተቆርጦለት የነበረው ጠቅላላ ጉባዔ ለ15 ቀን እንዲራዘም ጥያቄ የቀረበው በራሱ በንግድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔው የሁለት ሳምንት የጊዜ ማራዘሚያ የጠየቀበት ምክንያት፣ የዓመታዊ ጉባዔና የምርጫው ሥነ ሥርዓት ንግድ ምክር ቤቱ በየዓመቱ ከሚያካሂደው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ጋር አብሮ እንዲካሄድ ለማድረግና ለወጪ ቅነሳ እንዲረዳው በማሰብ እንደሆነ የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ከጽሕፈት ቤቱ የቀረበውን የጊዜ ማራዘሚያ ጥያቄ ያረጋገጡ የንግድ ምክር ቤቱ አንድ ኃላፊ፣ እስካሁን ግን በቀረበው ጥያቄ ላይ የምክር ቤቱ ቦርድ እንዳልወሰነ ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ለቀረበው ጥያቄ የቦርዱ ምላሽ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡

ጥያቄው ተቀባይነት ካገኘም፣ ከአንድ ዓመት በላይ ሳይካሄድ የቆየው ጠቅላላ ጉባዔ ጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲካሄድ ተስፋ ሲደረግ፣ በዚሁ ወቅትም በንግድ ትርዒቱ ለመሳተፍ ከሞሮኮ ብቻ 82 ኩባንያዎች እንደሚመጡ ተጠቅሶ፣ ለምርጫው መራዘም የቀረበው ጥያቄ አንዱ ምክንያት ተደርጓል፡፡ በጥቅምት አጋማሽ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የንግድ ምክር ቤቱ ዓለም አቀፍ የንግድ ዓውደ ርዕይ ከሚካፈሉ አገሮች መካከል ሞሮኮ አንዷ መሆኗ ተጠቅሷል፡፡

ለአንድ ዓመት ያህል ከሞሮኮ ጋር በተደረገ ድርድር በዘንድሮው የንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ትርዒት ላይ በ82 ኩባንያዎች እንደምትወከል አስታውቃለች፡፡ በአንድ የንግድ ትርዒት ላይ ከአንድ አገር ይህንን ያህል ተሳታፊ እንደሚመጣ ሲታወቅ የሞሮኮ ኩባንያዎች የመጀመርያዎቹ በመሆናቸውና ከኢትዮጵያውያን ጋር የአቻ ለአቻ የንግድ ግንኙነት መፍጠር የሚችሉባቸው መድረኮች እየተመቻቹ በመሆኑ፣ ጠቅላላ ጉባዔውን ለ15 ቀናት እንዲራዘም የተጠየቀው፣ የጠቅላላ ጉባዔው ተሳታፊዎች በእንዲህ ያለው መድረክ እንዲካፈሉ ለማመቻቸት ሲባል እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውን ከንግድ ትርዒቱ ጋር ማስተሳሰሩ ሌላ ጠቀሜታ እንዳለው የተገለጸው ወጪ ለመቀነስ እንደሚያስችል በመታመኑ እንደሆነ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ይጠቅሳል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አባልነት የተመዘገቡ የተወሰኑ ንግድ ምክር ቤቶች ከዚህ ቀደም ባካሄዷቸው የጠቅላላ ጉባዔና የቦርድ አባላት ምርጫ ወቅት የሕጋዊነት ጥያቄ መነሳቱ ይታወሳል፡፡ ምክር ቤቶቹ ትክክለኛውን የሕግ አካሄድ ባለመከተላቸው ሳቢያ እንዲሁም በትክክለኛ የምርጫ ሒደት የተወከሉ አመራሮችን  ባለመላካቸው ሳቢያ በተፈጠረ ውዝግብ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ እንደተስተጓጎለ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በሕጋዊ መንገድ ምርጫ አላካሄዱም በተባሉት ንግድ ምክር ቤቶች ላይ መንግሥት ጣልቃ በመግባት ጭምር ዳግመኛ ምርጫ አካሂደው አመራሮቻቸውን የመረጡ ሲሆን፣ ለውዝግቡ ምክንያት የሆኑ ችግሮችም መፈታታቸው ተነግሯል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ እንዳጋጠመው ሲገልጽ በቆየው ችግር ምክንያት ከአንድ ዓመት በላይ ለዘገየው ጠቅላላ ጉባዔ፣ ከአምስት ጊዜ በላይ መርሐ ግብር ቢወጣለትም አንዱንም ማካሄድ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ እንቅፋት የሆኑትን ጉዳዮች ሲከታተል የነበረው ንግድ ሚኒስቴር፣ ንግድ ምክር ቤቱ ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠርቶት የነበረውን ጠቅላላ ጉባዔ ማገዱም አይዘነጋም፡፡

በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫን ተከትሎ ንግድ ምክር ቤቱ አዳዲስ አመራሮችን እንደሚያገኝ ሲጠበቅ፣ በአሁኑ ወቅት በአመራር ላይ ከሚገኙት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት መካከል የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት በመጪው ምርጫ እንደማይወዳደሩ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ እስካሁን ባለው መረጃ አወዛጋቢ ሆኖ የቆየውን የንግድ ምክር ቤቱ የአመራር ቦታ ለመረከብ የቀረበ ዕጩ የለም፡፡ ሪፖርተር ባደረገው ማጣራትም ንግድ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትና በምክትል ፕሬዚንትነት ለመምራት የሚወዳደር ዕጩ አልቀረበም፡፡

ከዚህ ቀደም ሲካሄዱ በመጡ ምርጫዎች ወቅት፣ የተወዳዳሪ ዕጩዎች ማንነት ቀድሞ ይታወቅ ነበር፡፡ በዘንድሮው ምርጫ ግን በግልም ሆነ በንግድ ምክር ቤት ደረጃ ለፕሬዚዳነትነትና ለምክትል ፕሬዚዳንትነት የሚወዳደር ዕጩ አለመቅረቡ ሒደቱን ከወዲሁ አሳሳቢ አድርጎታል ተብሏል፡፡ አባል ምክር ቤቶች ለፕሬዚዳንትነትና ለምክትል ፕሬዚንትነት ሊወዳደሩ የሚችሉ ዕጩዎቻቸውን እስካሁን አለማቅረባቸውም አዲሱ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ማን እንደሚሆን ለመገመት እንዳላስቻለ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የንግድ ምክር ቤቱ አባላት ይገልጻሉ፡፡

መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ወይም ጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት፣ ከተመደበለት የምርጫ ዘመን (ሁለት ዓመት) በላይ በኃላፊነት የቆየው ተሳናባቹ ቦርድ የሦስት ዓመት ሪፖርት እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት መተዳደሪያ ደንብ ውጪ የአመራር አባላት ምርጫ አካሂዷል፣ አንዳንድ አመራሮችም ከመተዳደሪያ ደንብ ውጪ በተደጋጋሚ በአመራርነት ቦታው ላይ ቆይተዋል በማለት ክስ ተመሥርቶባቸው ከነበሩበት መካከል የቀድሞ የኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት አመራሮች፣ በሐምሌ 2009 ዓ.ም. ለተመረጡት አዲስ አመራሮች ቦታውን ማስረከባቸው ታውቋል፡፡ በቅርቡ በተካሄደ ምርጫ ወደ አመራርነት የመጡ አዳዲሶቹ ተመራጮች የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኃላፊዎች በተገኙበት ከተሰናባቹ አመራር የቢሮ ርክክብ ማድረጋቸውንና አዲሱ አመራርም ሥራውን እንደጀመረ ከኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ይገልጻል፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles