በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ከሚገኙ 16 የግል ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ፣ መለያ አርማን በአዲስ መቀየሩን አስታወቀ፡፡ እስካሁን አምስት የግል ባንኮች የአርማ ለውጥ አድርገዋል፡፡
የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ላለፉት 12 ዓመታት ሲገለገልበት የቆየውን አርማ መለወጡንና በአዲሱ አርማው መንቀሳቀስ እንደጀመረ ያስታወቀው ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡
የአርማ ለውጡን ማድረግ ያስፈለገው ባንኩን በተገቢው መንገድና የኮርፖሬት ማንነቱን በቀላሉ ለመግለጽ ታስቦ እንደሆነ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ድርቤ አስፋው ገልጸዋል፡፡ ባንኩ ከቀረፀው ስትራቴጂ ጋር የሚተሳሰር፣ ደንበኞች ዓይተው በቀላሉ እንዲለዩት በማሰብ ጭምር ባንኩ ‹‹ሪ-ብራንድ›› መደረጉን አውስተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊኖር የሚችለው የወደፊት ውድድር ውስጥ ባንኩን በቀላሉ መግለጽ የሚችል አርማ በማስፈለጉ የተወሰደ ዕርምጃ ነው ብለውታል፡፡ አርማውን ለመለወጥ ከወሰነ በኋላ ባንኩ ለዘጠኝ ወራት ያህል የተለያዩ አማራጮች ቀርበውለት ሲመለከት መቆየቱንና፣ ከቀረቡት አማራጮች ውስጥም ተቀባይነት ያገኘው አዲሱ አርማ ለሥራ ዝግጁ መደረጉ ታውቋል፡፡ አዲሱ አርማ የተሠራው በባንኩ የግራፊክ ዲዛይን ባለሙያዎች መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡ የአርማ ለውጡ ባንኩ ለጀመረው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ መገለጫው እንደሚሆንም ተጠቅሷል፡፡ ከአርማ ለውጡ በተጨማሪ ባንኩ የቀረፀው አዲስ የአሠራር ስትራቴጂም ተብራርቷል፡፡
የአዲሱ አርማ ይዘትና ፍቺን በተመለከተ ባንኩ ካሠራጨው መረጃ መረዳት እንደተቻለው፣ ባንኩ ከዓለም አቀፍ የኅብረት ሥራ ትብብር ጋር ተዛማጅነት ያለው አርማ በመምረጥ፣ አብሮ የመሥራትንና የጠንካራ ትስስርን መርሆዎች ለማራመድ ያለውን መነሳት ያሳየበት የለውጥ መንገድ ነው፡፡ በመሆኑም የባንኩ አዲሱ አርማ በእንግሊዝኛው ‹‹ሲ›› ፊደል የሚጀመር፣ በመካከሉ ሁለት የተጠላለፉ (የኦሜጋ ወይም የኢንፊኒቲ ቅርፅ የሚሠሩ) የእንግሊዝኛ ‹‹ኦ›› ፊደላት ያሉበት፣ እንዲሁም በመክፈቻ ቁልፍ ቅርፅ አምሳያ የተጻፈ የ‹‹ፒ›› ፊደል ተካተውበት ‹‹COOP Bank of Oromia›› የሚል አዲስ አርማ ሥራ ላይ አውሏል፡፡
አርማው የሚወክላቸውን ቁም ነገሮች በተመለከተ ባንኩ እንደሚገልጸው፣ ሁለቱ የተጠላለፉት የ‹‹ኦ›› ፊደላት የባንኩን ቁርጠኝነትና ትጋት ብሎም በከተማና በገጠር መካከል አካታች የፋይናንስ ሥርዓት እንዲዘረጋ ስትራቴጂካዊና ቁልፍ አጋርነቱን እንዲያመላክትለት የተዋቀሩ ናቸው፡፡ የተጠላለፉት ፊደላት ገደብ ወይም ወሰን የለሽ የሆነውን የ‹‹ኢንፊኒቲ›› ቅርፅ መያዛቸውም ለባንኩ ትልሞችና ፍላጎቶች ገደብ እንደሌለበት፣ አቅምና ዕድሎቹም እንደ ሰማይ ርቀት ከፍተኛ መሆናቸውን ለማመላከት የተጠቀሙት ሆኗል፡፡ በቁልፍ አምሳል የተቀረፀው ‹‹ፒ›› ፊደልም በፋይናንስ ረገድ ከታች ጀምሮ ያሉ ማኅበረሰቦች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ያለውን ተልዕኮ እንደሚወክልለት ባንኩ አስታውቋል፡፡
ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ ከተቋቋሙ 16ቱ የግል ባንኮች ውስጥ ወደ ኢንዱስትሪው በመግባት ሰባተኛው ተቋም ሆኖ የተመዘገበው የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ፣ በአዲስ መልክ የሚመራበት የስትራቴጂ ዕቅዱ በ2025 ዓ.ም. የአገሪቱ ቀዳሚ ባንክ ለመሆን እንደሚሠራ ያመለክታል፡፡
የባንኩን ወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ከተሰጠው ማብራሪያ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ በ2009 ዓ.ም. በጥንካሬ ከሠራባቸው መስኮች መካከል የቅርንጫፍ ማስፋፋት ዋናው ነው፡፡ በዚሁ ዓመት ብቻ 82 ቅርንጫፎችን በመክፈት፣ ጠቅላላ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 256 እንዳደረሰ የጠቀሱት አቶ ድርቤ፣ ይህ የቅርንጫፍ ማስፋፋት ተግባሩ፣ ከአዋሽና ከዳሸን ባንክ በመከተል በርካታ ቅርጫፎች ያሉት ባንክ እንዲሆን አብቅቶታል፡፡ በሌሎች የባንክ እንቅስቃሴዎቹም ጥሩ ውጤት ያስመዘገበበት ዓመት እንደነበር ያመለከቱት አቶ ድርቤ፣ የባንኩ የሀብት መጠን በ2008 ዓ.ም. ከነበረው የ10.6 ቢሊዮን ብር ወደ 17.7 ቢሊዮን ብር ማደጉ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ባንኩ የሰጠው የብድር መጠን 7.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን በመጥቀስም፣ ከዚህ የብድር መጠን ውስጥ 2.6 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ለአርሶ አደሮች የብድር ማስያዣ የተሰጠ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ መስክ የኅብረት ሥራ ባንኩ የሚሰጠው አገልግሎት ከሌሎች ባንኮች የተለየ ያደርገዋል ያሉት አቶ ድርቤ፣ የደንበኞቹ ቁጥርም 1.06 ሚሊዮን እንደደረሰና የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑም ወደ 5.08 ቢሊዮን ብር እንዳደገ ጠቅሰዋል፡፡
ከ12 ዓመታት በፊት በ300 ሚሊዮን ብር በተፈቀደ ካፒታልና በ112 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ወደ ሥራ የገባው ባንኩ፣ በተለይ ከ2005 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም በነበረው ጊዜ ውስጥ ከአገሪቱ የግል ባንኮች ከፍተኛ ትርፍ በማስመዝገብ በሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻለ ባንክ ነበር፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በ2007 ዓ.ም. 604 ሚሊዮን ብር በማትረፍ በወቅቱ ከግል ባንኮች ሦስተኛው ባንክ ለመሆን መብቃት ችሎ ነበር፡፡ በ2008 እና 2009 የሒሳብ ዓመት ግን የትርፍ መጠኑ ከቀዳሚዎቹ ዓመታት እጅጉን እንዳነሰ ለመገንዘብ ይችላል፡፡
በ2003 ዓ.ም. 68 ሚሊዮን ብር፣ በ2004 ዓ.ም. 140 ሚሊዮን ብር፣ በ2005 ዓ.ም. ደግሞ 268 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም በ2006 ዓ.ም. 478.9 ሚሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቦ ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም. ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ 371.5 ሚሊዮን ብር እንደነበር የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት ያሳያል፡፡ በ2009 ዓ.ም. የባንኩ ትርፍ 326 ሚሊዮን ብር አካባቢ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ድርቤ እንደገለጹትም በትርፍ መጠንና በውጭ ምንዛሪ ግኝት ረገድ፣ ባንኩ ባቀደው ልክ መፈጸም አልቻለም፡፡ በ2009 ዓ.ም. 326 ሚሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ 82 ቅርንጫፎች መክፈታቸው የባንኩን ወጪዎች ከጨመሩ መካከል ስለሚመደቡ ትርፉን ቀንሰውታል፡፡ አንድ ቅርንጫፍ ሲከፈት የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ‹‹እንዲህ ባሉ ምክንያቶች የበጀት ዓመቱ ትርፍ ባቀድነው ልክ ባይደርስም በመጪዎቹ ዓመታት የባንኩን የትርፍ መጠን ለማሳደግ የሚችል መሠረት በመጣሉ ባንኩ ከዚህ በኋላ የትርፍ ዕድገቱን እየጨመረ ይሄዳል፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ የወደፊቱን የባንኩን ጉዞ አመላክተዋል፡፡
ባንኩ በአሁኑ ወቅት የተከፈለ ካፒታሉን አንድ ቢሊዮን ብር በማድረስ፣ የተፈቀደ ወይም የተመዘገበ ካፒታሉ ደግሞ ሦስት ቢሊዮን ብር እንዳደገ የባንኩ መረጃ ያሳያል፡፡
ከ62 በመቶ በላይ የባንኩ ባለአክሲኖች የተለያዩ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኒየኖች ሲሆኑ፣ አጠቃላይ የግል አክሲዮኖች ቁጥር ደግሞ ከ13 ሺሕ በላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
እንደ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ሁሉ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት አዋሽና ወጋገን ባንኮችም ላለፉት 20 ዓመታት ያህል ሲገለገሉባቸው የነበሩትን አርማዎች መለወጣቸው ይታወሳል፡፡ ከሁለቱ ባንኮች ቀደም ብሎ አርማውን በመለወጥ የሚጠቀሰው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ነው፡፡ ዳሸን ባንክም የአርማ ማስተካከያ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
የግል ባንኮቹ የአርማ ለውጥ እያደረጉ የሚገኙት ወደፊት የሚጠብቃቸውን ውድድር ታሳቢ በማድረግ፣ በቀላሉ በደንበኞቻቸው ዘንድ ሊታወስና ሊገናዘብ የሚችል አርማ መጠቀሙ እንደሚሻል በማመናቸው እንደሆነ ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡
