አዲስ አበባ የአፍሪካ የፖለቲካ ማዕከል ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ ኢኮኖሚ እቅስቃሴ እንብርት እንድትሆን ለማድረግ እንደሚያግዝ ታምኖበት ከአንድ ሳምንት በፊት የመሠረት ድንጋዩ ተቀምጦ ግንባታው የተጀመረው የአዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንፌዴሬሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል የተጠነሰሰው ከ13 ዓመታት በፊት ነበር፡፡
የኋላ ታሪኩ ሲፈተሽ ለማወቅ እንደሚቻለው፣ የማዕከሉ ግንባታ ጠንሳሾች የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት (አሁን የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት) የወቅቱ አመራሮች ነበሩ፡፡
ለዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ማካሄጃ እንዲሁም ለተዛማጅ አገልግሎቶች ማስተናገጃ የሚለው እዚህ ግባ የሚባል ማዕከል የሌላት አዲስ አበባ፣ ከአሁን በኋላ ከራሷ አልፎ በአፍሪካ ደረጃ የሚዘጋጁ ትርዒቶችን የምታስተናግድበት የንግድ ማዕከል ባለቤት ያደርጋታል የተባለውን ይህንን ማዕከል የመገንባት ሐሳብ ከውጥኑ ጀምሮ የበርካቶችን ቀልብ ገዝቶ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የወቅቱ ከንቲባ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ በነበሩበት ወቅት፣ ለማዕከሉ መገንቢያ የሚውል 110 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ንግድ ምክር ቤቱ ተርክቧል፡፡
በወቅቱ ለንግድ ምክር ቤቱ ትልቅ እመርታ ሆኖ የተቆጠረው የቦታ ርክክቡ በተከናወነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከንቲባ አርከበ፣ በዚያን ወቅት የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ከነበሩት ከአቶ ብርሃነ መዋ ጋር በመሆን ለዘመናዊው የንግድ ትርዒት ማዕከል ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠው ነበር፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በራሱ የሚያስተዳድረው ትልቅ ማዕከል ለመገንባት መነሳቱ ብሎም ቦታ መረከቡ ለተቋሙ ዳግመኛ መነቃቃትን የፈጠረ ክስተት ስለነበር በርካቶች እንደየ ምርጫቸው አጋጣሚውን ለመግለጽ ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡ የመጀመርያው የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሥርዓት ሲከናወን፣ አቶ ብርሃነ መዋ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችን በሚወክል ባህላዊ ልብስ ተሸልመው እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ይኸው ሥነ ሥርዓት ሲካሄድ ንግድ ምክር ቤቱና የንግዱ ኅብረተሰብ ተቀናጅተው በወቅቱ ዋጋ ከ350 እስከ 400 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ የተገመተውን የንግድ ማዕከል በጋራ እንደሚገነቡ ተነግሮ ነበር፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ ባለቤትነት ተይዞ በአባላቱ ርብርብ ግንባታው ይካሄዳል ተባለ፡፡ በዚሁ ተስፋና ወኔ አዲስ አበባ ዘመናዊና ግዙፍ የንግድ ማዕከላት እንዲኖራት ለማድረግ ደፋ ቀና ማለት ተጀመረ፡፡ በጋለ ስሜት የተጀመረው የማዕከሉ ግንባታ፣ ከመሠረት ድንጋዩ በኋላ ወደ ተግባር ለመግባት ግን የአነሳሱን ያህል ግን ሊራመድ አልቻለም፡፡ ከሦስት እስከ አራት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል የተባለው የንግድ ማዕከሉ ግንባታ ዕውን ሊሆን አልቻለም፡፡ መደበኛው የማዕከሉ ግንባታ በቁሙ መቅረቱ ብቻም ሳይሆን፣ ለግንባታ የተፈቀደው ቦታ የረባ አጥር ሳይኖው ዓመታት መቆጠር ጀመሩ፡፡ ምንም ግንባታ ሳይካሄድባቸው ታጥረው ከተቀመጡ ቦታዎች አንዱ በመሆንም የንግድ ምክር ቤቱ ቦታ በከተማው አስተዳደር ይጠቀስ ጀመረ፡፡ የማዕከሉ ግንባታ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ በቆመበት ወቅት ንግድ ምክር ቤቱ አራት ፕሬዚዳንቶችን አፈራረቀ፡፡ በልዩ ሁኔታ የግንባታ ቦታውን ለምክር ቤቱ በሊዝ የሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም አቶ አርከበን ጨምሮ አራተኛ ከንቲባውን አፈራረቀ፡፡
የፕሮጀክቱ አዝጋሚ ጉዞ
ብዙ የተባለለትና ተስፋ የተጣለበት ይህ ፕሮጀክት፣ እንደታሰበው ሳይራመድ ለመቆየቱ የተለያዩ ምክንያቶች ሲጠቀሱለት ቆይቷል፡፡ ይሁንና በተጓተተው የግንባታው ፕሮጀክት ሒደት ውስጥ ዳግመኛ እንደ አዲስ የሚታይበት መንገድ ተከፈተ፡፡ ይኸውም ንግድ ምክር ቤቱ ግዙፉን ግንባታ ለብቻው ለመወጣት አቅም የሌለው መሆኑ አንዱ አጋጣሚ ነበር፡፡
የንግድ ማዕከሉ በንግድ ምክር ቤቱ ብቸኛ ባለቤትነት መያዙ ቀርቶ ሌሎችም እንዲሳተፉበት ለማድረግ ከሌሎች ተቋማት ጋር አብሮ መሥራት የሚቻልበትን ሐሳብ በማንሳት ለዚሁ የሚያግዝ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ጊዜ መውሰዱ አልቀረም፡፡ ቀድሞ የታሰበው ቀርቶ በአዲስ አደረጃጀት እንዲመራ ሲታሰብ፣ የንግድ ምክር ቤቱ አዲሱ አካሄድ ማዕከሉ የሚገነባበት ሥርዓት ቢዝነስ ቀመስ እንዲሆን፣ በአክሲዮን ኩባንያነት ተደራጅቶ የአክሲዮን ድርሻዎች መሸጥ ጀመሩ፡፡ በዚሁ አነሳሽነትም መጠነኛ እንቅስቃሴ ይደረጉ ጀመር፡፡
ጥቂት ቆይቶ ግን የፕሮጀክቱን አካሄድ የቀየረ ሌላ አመለካከት ተፈጠረ፡፡ ግንባታው በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ጥምረት ይካሄድ የሚል አዲስ አካሄድ ይንፀባረቅ ጀመረ፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ ስምምነት ከማድረጋቸው በፊት ንግድ ምክር ቤቱና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለብዙ ጊዜ እንደመከሩበት ይገለጻል፡፡ በመጨረሻውም የአዲስ አበባ የባላደራ ቦርድ ከንቲባ የነበሩት አቶ ብርሃኑ ደሬሳና የወቅቱ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ የንግድ ማዕከሉ ግንባታ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ጥምረት እንዲካሄድ የሚያስረግጥ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡፡ ስምምነቱ የተፈረመበት ብዕርም ‹‹ወርቃማ›› ነች ተባለ፡፡ በዚህም ሳይገታ የፕሮጀክቱን ዓላማ የሚተነትነው ሰነድም ተለወጠ፡፡ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በመጣመር መሥራት እንደሚችሉ ማሳያ ፕሮጀክት ስለመሆኑ ተጠቅሶም፣ በ20 መሥራች አባላት የአዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከል አክሲዮን ማኅበር እንደ አዲስ ተቋቋመ፡፡ የአክሲዮን ማኅበሩ መመሥረትና የማዕከሉ ግንባታ አስፈላጊነትን ከተመለከቱ አምስት ዋነኛ ዓላማዎች ውስጥ ሁለቱ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ በጥምረት የመሥራታቸውን ፋይዳ የሚያትቱ ነበሩ፡፡ አንደኛው ሐሳብ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ልማት ተሳታፊነቱ እንዲጨምር ያግዛል የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነትን ለማጠናከር ይጠቅማል በሚል የተቃኘ ነበር፡፡
ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ባለቤትነት እንዲተዳደር ታልሞ በዚህ አኳኋን የተጓዘው የአክሲዮን ኩባንያው ታሪክ፣ ሁለቱንም ወገኖች ሚዛናዊ የባለቤትነት ድርሻ ኖሯቸው ፕሮጀክቱን በጋራ የማስተዳደር መብት እንዲኖራቸው ጭምር ያስቻለ ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡
ከአክሲዮን ኩባንያው ምሥረታ በኋላ ዋናዎቹ ባለአክሲዮኖች የሆኑት እነዚሁ የአዲስ አበባ አስተዳደርና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ናቸው፡፡ የተቀሩት ባለአክሲዮኖች 18ቱ የግል ኩባንያዎችና ሌሎች የግል ኩባንያ ኃላፊዎች ነበሩ፡፡ ወደ አክሲዮን ሽያጩ በተገባ በመጀመርያው ዙር፣ 300 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለገበያ ቀረበው ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ 150 ሚሊዮን የሚያወጡ አክሲዮኖችን የከተማ አስተዳደሩ ገዛ፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በበኩሉ አሥር ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖችን ወሰደ፡፡ ቀሪዎቹ ባለአክሲዮኖችም ከ25 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖችን ገዙ፡፡ ለሕዝብ የቀረቡ አክሲዮኖች ግን እንደተፈለገው መጠን ሊሸጡ አልቻሉም፡፡ ይህም ለፕሮጀክቱ መጓተት አንዱ ምክንያት ሆኖ ቀረበ፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደ የአክሲዮን ሽያጭም፣ ከቀረቡት የአንድ ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ውስጥ አስተዳደሩ የግማሽ ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን ገዛ፡፡ ከዚህ ውስጥ 415 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች የገዛው የከተማ አስተዳደሩ በሥሩ በሚተዳደሩ አምስት ተቋማት በኩል ነበር፡፡ በከተማው አስተዳደር አክሲዮን የተገዛላቸው ተቋማትም ሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ኩባንያ፣ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት፣ አዲስ ብድርና ቁጠባ እንዲሁም አዲስ ኢንተርፕራይዝ ናቸው፡፡ 85 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን ደግሞ በአንበሳ አውቶብስ ስም ተገዝተዋል፡፡ ይህ በመሆኑም አስተዳደሩ ትልቁን የአክሲዮን ድርሻ ይዞ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡ በሁለት ዙር ከተሸጡት አክሲዮኖች ውስጥ 97 በመቶውን አስተዳደሩ ይዞ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ግን በያዘው አክሲዮን ብቻ ተወስኖ የ1.68 በመቶ ድርሻ ይዞ ይገኛል፡፡ ቀሪዎቹ 18 መሥራች ባለአክሲዮኖች ድርሻ ሁለት በመቶ ያልሞላ ድርሻ ይዘው የአክሲዮን ሽያጩ በድጋሚ ቀጠለ፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ አሁንም ድረስ ይዞ የቆየው አሥር ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለውን አክሲዮን ብቻ ነው፡፡
ለፕሮጀክቱ እንደ አዲስ ምዕራፍ የሚቆጠረው ሌላው ታሪክ የሚጀምረው ባለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄዱ እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ በተለይ አስተዳደሩ በሁለቱ የአክሲዮን ሽያጮች ወቅት የአንበሳውን ድርሻ የያዘባቸውን አክሲዮኖች ከገዛ በኋላ ወደ ግንባታ ሊያሸጋግር የሚችል ሥራ ተሠርቷል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ ከተፈቀደ 1.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ውስጥ የመጨረሻዎቹን 669.255 አክሲዮኖች በዚህ ዓመት አጋማሽ ለሽያጭ አቅርቧል፡፡ በዚህን ወቅት ግን ከ20ዎቹ መሥራቾች በተጨማሪ አዳዲስ የገቡትን ጨምሮ በአጠቃላይ 747.255 ሚሊዮን ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖችን ለመሰብሰብ ችሏል፡፡
አዲሱ ምዕራፍ
የፕሮጀክቱ አዲሱ ምዕራፍ የሚጀምረው የማዕከሉን ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችለው አዲስ የመሠረት ድንጋይ ከመቀመጡ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በተገኙበት፣ ለሁለተኛ ጊዜ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት አዲስ ምዕራፍ የሆነው የግንባታውን የመጀመርያ ምዕራፍ ለማካሄድ የግንባታ ስምምነት መፈረሙና ወደ ተግባር ሥራ መገባቱም ጭምር ነው፡፡
የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ለማካሄድ ከፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ጋር ስምምነት የፈረመው ሲጂሲኦሲ ግሩፕ የተባለው የቻይና ኩባንያ ነው፡፡ ነገር ግን በሁለት ዙሮች ከተደረገው የአክሲዮን ሽያጭ መገንዘብ የተቻለው፣ ከ13 ዓመታት ቆይታ በኋላ የዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት የባለቤትነት ድርሻ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ተመጣጣኝ ድርሻ ገና እንዳልተያዘበት ነው፡፡
የ595.9 ሚሊዮን ብር ዋጋ ካላቸው አክሲዮኖች ውስጥ የከተማ አስተዳደሩ 583.3 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች በመግዛት የ97.9 በመቶ ድርሻ መያዙ ያልተመጣጠነ የባለቤትነት ድርሻ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ከዚህ በኋላ 658 ሺሕ ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለሽያጭ ቢቀርቡም፣ እነዚህ አክሲዮች ተሽጠውም እንኳ ዋናው የኩባንያው ባለቤት የከተማው አስተዳደር ሆኖ መቅረቱን የሚያረጋግጥ አካሄድ እየታየ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ ግን እስካሁን በነበረው የአክሲዮን ሽያጭ ከፍተኛውን አክሲዮን የገዛው አስተዳደሩ ቢሆንም፣ ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት አስተዳደሩ ፕሮጀክቱን በፍጥነት ለማስጀመር ካለው ፍላጎት አኳያ ነው ብለዋል፡፡
ለሥራው ማስጀመሪያ የሚሆን ገንዘብ በማዋጣት ግንባታ እንዲጀመር በማድረግ፣ በቀሪዎቹ አክሲዮኖች ግዥ ላይ ግን የንግድ ኅብረተሰቡ እንዲሳተፍ ለማድረግ ብቻም ሳይሆን፣ አስተዳደሩ የግል ዘርፉን ለመደገፍ ብሎም ፕሮጀክቱ እንዳይቋረጥ በማሰብ የወሰደው ዕርምጃ እንደሆነ በመጥቀስ አቶ ጌታቸው ይሞግታሉ፡፡ ይህ የአስተዳደሩ ዕርምጃ ከዚህ በኋላ ለሚካሄደው የአክሲዮን ሽያጭ ትልቅ ድጋፍ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ጌታቸው፣ በአሁኑ ወቅት ወደ አስተዳደሩ ሚዛኑ ያጋደለው ኢንቨስትመንትም፣ ወደፊት በሚሸጡት አክሲዮኖች እየተመጣጠነ እንደሚሄድ ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ፍላጎት ይህ ብቻ እንዳልሆነ ተናግረው፣ ቀሪዎቹን አክሲዮኖች ለመግዛት መነሳሳት መታየቱ ፕሮጀክቱን በፍጥነት ዕውን ለማድረግ እንደሚያግዝም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ዋናው ነገር ግንባታውን መጀመራችን ነው፡፡ አዋጭ በመሆኑ ሁሉም ይረባረብበታል፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ እንዲህ ያለው ቢዝነስ ውስጥ የንግድ ኅብረተሰቡ የሚሳተፍ በመሆኑ፣ መንግሥት ከገዛቸው አክሲዮኖች ውስጥ ወደ ወደፊት ወደ ግሉ ዘርፍ የሚያዛውር በመሆኑ የባለቤትነት ድርሻውን እየተመጣጠነ ይሄዳል ብለው ያምናሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በርካታ የግሉ ዘርፍ አባላት አክሲዮን እየገዙ በመሆኑ፣ ሥጋቱ እንደሚፈታ ያስረዳሉ፡፡
የፕሮጀክቱ አዋጭነት መረጋገጡ ብቻም ሳይሆን የግንባታ ሥራውም በመጀመሩ በርካቶች አክሲዮን ለመግዛት እንደሚቀርቡ ይታሰባል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ በጋራ የመሥራት ዓላማውን ለማሳካት ያስችላል በማለት አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱም አባላቱ በዚህ ፕሮጀክት ባለቤት ለመሆን እንዲችሉ ቅስቀሳዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረው፣ ቀሪዎቹን አክሲዮኖች ለመግዛት የታየው መነሳሳት ፕሮጀክቱ በታሰበው ጊዜ ለማጠናቀቅ ያስችላል ብለዋል፡፡ ‹‹ዋናው ነገር ግን ግንባታውን መጀመራችን ነው፡፡ አዋጭም በመሆኑ ሁሉም ይረባረብበታል፤›› ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ይፈጃል የተባለው ይህ ፕሮጀክት፣ በጥንስሱ ወቅት ዲዛይኑ ሲሠራ 1.8 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ ታስቦ ነበር፡፡ ይህ ልዩነት የተከሰተው ግን የግንባታ ሒደቱ በመዘግየቱና ወጪውም በመጨመሩ ነው፡፡ ሆኖም ማዕከሉ ሥራ ሲጀምር፣ በመጀመርያው ዓመት ብቻ 220 ሚሊዮን የተጣራ ትርፍ እንደሚያስገኝ ይገመታል፡፡ በየዓመቱ የሚያስመዘግበው ትርፍም ከ16 እስከ 46 በመቶ የሚገመት ዕድገት ይኖረዋል ተብሏል፡፡
የማዕከሉ ዋና ዋና ክፍሎች
ይህ ማዕከል አንድ ባለአራት ኮከብ ሆቴል፣ በአዳራሽ ውስጥ 20,600 ካሬ ሜትር እንዲሁም ከአዳራሽ ውጭ 6,700 ካሬ ሜትር፣ በጠቅላላው 27,300 ካሬ ሜትር የቦታ ስፋት ያለው የኤግዚቢሽን ማሳያ ሥፍራ፣ በአንድ ጊዜ 5000 ሰዎችን የሚያስተናግድ አዳራሽ፣ 3000 መቀመጫዎች ያሉት ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች የሚስተናገዱበት አዳራሽ፣ እያንዳንዳቸው 500 ሰዎችን የሚይዙ ሁለት የቴአትርና የፊልም አዳራሾች፣ ከ50 እስከ 100 ሰዎችን የሚያስተናግዱ ስድስት አነስተኛ የመሰብሰቢያ ክፍሎች፣ ባለአራት ኮከብ ሆቴል፣ ዘመናዊ የገበያ ሥፍራ፣ ሬስቶራንት፣ ካፍቴሪያዎች፣ የሕፃናትና የአዋቂዎች መዝናኛ ሥፍራዎች ወዘተ. እንደሚገነበቡበት ከማዕከሉ መመሥረቻ ጽሑፍ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ለቻይናው ሲጂሲኦሲ የሚከፈለው ገንዘብ 1.2 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ሲታወቅ፣ እስካሁን ከ830 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው አክሲዮኖች መሸጣቸውም ተረጋግጧል፡፡
