በዓለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ በሚገነባው የቦሌ ለሚ ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ለጃፓን አምራቾች የሚውል ልዩ የኢንዱስትሪ ዞን ለመመሥረት የሚያግዝ የመግባቢያ ስምምነት ይፈረማል፡፡
ረቡዕ ሰኔ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በጃፓን ወገን የሚፈረመው የመግባቢያ ስምምነት፣ በቦሌ ለሚ ሁለት ውስጥ ለጃፓኖች ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለማምረት የሚውል ልዩ የኢንዱስትሪ ዞን ለመመሥረት እንደሚያስችል ይጠበቃል፡፡
ስምምነቱን በጃፓን ወገን የሚፈርሙት ተሞኒየስ የተባለው የጃን የኢንቨስትመንት ኩባንያ ሲሆን፣ ዘፊር የተሰኘውና በካምቦዲያ የፕኖም ፔን ልዩ ኢኮኖሚክ ዞን ባለድርሻ የሆነው የዚህ ኩባንያ ወኪሎች እንደሚሆኑ ከጃፓን ኤምባሲ እንዲሁም ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2012 የተመሠረተው ቶሞኒየስ ኩንያ፣ በጃፓን የሪል ስቴት ዘርፍ እንዲሁም የደረቅ መርፌ ሕክምና ማዕከል በሰፊው ይንቀሳቀሳል፡፡ ከዚህም ባሻገር በካምቦዲያ ትልቁ እንደሆነ የሚነገርለት፣ የፕኖም ፔን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ባለድርሻ በመሆን ያስተዳድራል፡፡
መንግሥት የጃፓን ባለሀብቶች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ለማድረግ በብዙ ሲወተውት ከርሟል፡፡ የዚህ ልዩ ዞን ስምምነት ወደ ተግባር መሸጋገር ከቻለም ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ደረጃ ያላቸውን ምርቶች የሚያመርቱ ጃፓናውያን አምራቾች እንደሚሳተፉበት የሚጠበቅ፣ መንግሥትም በጉጉት የሚጠብቀው ፕሮጀክት ነው፡፡
ይሁንና እስካሁን ባለው ሒደት መንግሥት እንደሚፈልገው መጠን የጃፓን ባለሀብቶችን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት አልተቻለውም፡፡ ጃፓናውያኑ የኢትዮጵያ መንግሥት የጃፓንም ሆነ የሌሎች ያደጉ አገሮች አምራቾች የሚፈልጓቸውን የመሠረተ ልማት አውታሮች ማሟላት አልቻለም ይላሉ፡፡ ለአብነትም እንደ ሐዋሳ ወይም እንደ ቦሌ ለሚ አንድ ያሉ ሰፋፊ የማምረቻ ሼዶችን መደርደሩን አይቀበሉትም፡፡ ጃፓኖች ባለሀብት ከአንድ ሔክታር በታች፣ አነስተኛ መሬት ላይ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው፣ በራሳቸው የዲዛይንና የማምረቻ ቦታ አገባብ ሥርዓት መሠረት መሥራት እንደሚፈልጉ ደጋግመው ይገልጻሉ፡፡
ጃፓኖቹ በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት በኢንቨስትመንት ሕግ፣ በቀረጥ ነፃና በኢንቨስትመንት ሕጎችና በሌሎችም መስኮች የሚደጉ ማሻሻያዎችና ለውጦች ጥያቄ እንደሚፈጥሩባቸው ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ መንግሥት የሚያወጣቸው መመርያዎችና ደንቦች ተለዋዋጭነት ሥጋት እንደፈጠሩባቸው ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ ቢባልም ግን ለጃፓኖች በሚያመቻቸው መንገድ፣ በራሳቸው ዲዛይንና የግንባታ ፍላጎት መሠረት የኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት የሚችሉበትን ቦታ ማዘጋጀቱን ይፋ ካደረገ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ፣ የጃፓን አፍሪካ የኢንቨስትመንት ፎረም በሚል ርዕስ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ነበር የኢትዮጵያ መንግሥት ለጃፓኖቹ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የሚውል መሬት ማዘጋጀቱን ይፋ ያደረጉት፡፡
በጃፓኖች የተቀዛቀዘ ምላሽ የመንግሥት ባለሥልጣናት ያን ያህል ደስተኞች እንዳልሆኑ እየታየ ነው፡፡ ይሁንና እንደ ፒቪኤች ያሉ የአሜሪካ ኩባንያዎች መምጣታቸው ግን የጃፓኖቹን ፍላጎት ሳይቀስቀስ እንዳልቀረ ይገመታል፡፡
ምንም እንኳ የጃፓን ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት ለማድረግ ያሳዩት ፍላጎት የተቀዛቀዘ ይሁን እንጂ የጃፓን መንግሥት ግን በኢትዮጵያ የሚታዩ የውጭ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታቱ እንቅስቃሴዎችን እየተከታተለ መረጃውን እንደሚያደርስ የጃፓን ኤምባሲ ሲያስታውቅ ቆይቷል፡፡
ከዚህ ባሻገር የጃፓን ንግድና ኢንቨስትመንትን በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ለማድረግ የሚሠራ ተቋም ጽሕፈት ቤትም ሥራ ከጀመረ ወራትን ማስቆጠሩ፣ ጃፓን በኢትዮጵያ ስላላት የወደፊት ፍላጎት ማሳያ ሆኖ እየቀረበ ነው፡፡ የጃፓን ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋም (ጄትሮ) ጽሕፈት ቤቱን የከፈተው በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ተደጋጋሚ ጥያቄ እንደሆነ ቢታወቅም፣ ይኸው ተቋም የጃፓን ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ለማድረግ ተገቢውን መረጃ በመተንተን የማሠራጨት ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡
የዓለም ባንክ የቦሌ ለሚ ምዕራፍ ሁለት ግንባታን ጨምሮ የቅሊንጦ ኢንዲስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት የሚያስችል የ250 ሚሊዮን ዶላር ብድር መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ፓርኩ በ186 ሔክታር መሬት ላይ የሚገነባ ሲሆን፣ ምንም እንኳ ረጅም ጊዜ ቢፈጅም በቅርቡ ይጠናቀቃሉ ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥ አንዱ ነው፡፡
እስካሁን የተገነቡትን ቦሌ ለሚ አንድና የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ኤኮ ፓርክን ጨምሮ 13 የኢንዱትሪ ፓርኮች ግንባታ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የኮምቦልቻና የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ተጠናቆ በሰኔ ወር መጨረሻ እንደሚመረቁ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
