Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

ዘመናዊ የጤፍ ዱቄት ማዘጋጃና የእንጀራ መጋገሪያ ፋብሪካ ሥራ ሊጀምር ነው

$
0
0

 

ሐጂ ቱሬ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ከ60 ዓመታት በላይ የሚታወቅ ስም ነው፡፡ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በአስመጪና ላኪነት ቀዳሚ የሆኑት ስመጥሩ ነጋዴ፣ ለአገሪቱ አዳዲስ ምርቶችን ከውጭ በማስገባትና በማከፋፈልም ይታወቃሉ፡፡ በተለይ ከቻይና ጋር የነበራቸው የንግድ ግንኙነትም በጉልህ የሚጠቀስ ነው፡፡ የዱቄት መፍጫ ማሽኖችንና ሌሎችንም በማስመጣት ዘርፉ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ስለእሳቸው ከሚነገሩት ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡

ሐጂ ቱሬ ለዓመታት ሲመሩት የነበረውን ቢዝነስ ወደ ልጆቻቸውና ወደ ልጅ ልጆቻቸው በማስተላለፍ ዛሬም ድረስ ሥር የሰደደ ኩባንያ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል፡፡ ወ/ሮ ሙና መሐመድ ሦስተኛ ትውልድ ላይ የሚገኙ የሐጂ ቱሬ የልጅ ልጅ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ሙና የአያትና የወላጆቻቸውን ቢዝነስ ብቻም ሳይሆን፣ ልክ እንደነሱ እኛም የራሳችንን አሻራ ማኖር አለብን በማለት አዳዲስ ቢዝነሶችን በማስተዋወቅ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

‹‹አያቴ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹን የዱቄት ማሽኖች አስመጥቶ ከ300 በላይ ማሽኖች እንዲተከሉ አድርገዋል፡፡ ሌሎች በወቅቱ አዳዲስ የሚባሉ ቢዝነሶች አስተዋውቀዋል›› በማለት ያብራሩት ወ/ሮ ሙና፣ ‹‹እኛም ከአያታችን መነሻውን በመያዝ አዲስ ነገር ለማበርከት የምንችለውን ነገር እያደረግን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ወ/ሮ ሙና አዲስ እንደሆነ የገለጹትና አሁን ላይ ወደ ተግባር ያሸጋገሩት ቢዝነስ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ እንደሆነ የሚጠቅሱት ዘመናዊ የጤፍ ዱቄትና የእንጀራ ማምረቻ ፋብሪካቸውን ነው፡፡

ቃሊቲ አካባቢ የኢትዮጵያ ቆርኪ ፋብሪካ ፊት ለፊት በሚገኘው ይዞታቸው ላይ የተተከለው የጤፍ ዱቄት ማምረቻ ማሽን፣ ዛሬ ላይ ለአገልግሎት ይብቃ እንጂ የዚህ ቢዝነስ ውጥን የተጠነሰሰው ከአሥር ዓመት በፊት እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በተለምዶ ለዘመናት ያገለገለውን የድንጋይ ወፍጮ እንደሚተካ የሚጠበቀው አዲሱ መፍጫ ዕውን ለማድረግ፣ ላለፉት አሥር ዓመታት ጤፍ ብቻ ሊፈጩ የሚችሉ ዘመናዊ የጤፍ ማሽኖችን ለማሠራት ወደ ቻይና በተደጋጋሚ መመላለስ ነበረባቸው፡፡

ማሽኑን ለመፈብረክ የሚያስችላቸውን ዲዛይን በመንደፍ ደፋ ቀና ሲሉ የከረሙ የቻይና ባለሙያዎች፣ በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ዲዛይን ንድፍ ከመሥራት ጀምሮ ማሽኑን ከሚያመርተው የቻይና ኩባንያ ጋር በመዋዋል በርካታ ሙከራዎች ከተደረጉ በኋላ ቢግባል የተባለ የቻይና ኩባንያ መሐንዲሶች የኢትዮጵያ ጤፍ በሚፈለገው ደረጃ ፈጭቶ ማውጣት የሚችል ማሽን ሠርተው በማስረከባቸው የሙከራ ሥራ ተካሂዶ ውጤታማነቱ መረጋገጡን ወ/ሮ ሙና አብራርተዋል፡፡

ከወ/ሮ ሙና ጋር በሽርክና የሚሠሩት ወንድማቸው አቶ ኤልያስ ወይብም ይህንን ሥራ ወደ ተግባር ለመለወጥ በርካታ ውጣ ውረዶች ታልፈው ወደ ተግባር ለማሸጋገር እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡ ጤፍን ከወፍጮ ቤት ባሻገር በዘመናዊ ማሽን አማካይነት ማስፈጨት የቻለበት ማሽን፣ በቀን 600 ኩንታል ጤፍ የመፍጨት አቅም አለው፡፡

የጤፍ ዱቄት ማምረቻ ፋብሪካ ንፁህ የጤፍ ዱቄት ገበያ ላይ እንደ ልብ እንዲገኝ ከማስቻሉም በተጨማሪ፣ በተለያዩ መጠኖች ታሽጎ በሱፐር ማርኬቶች ጭምር በቀላሉ ለገበያ ለማቅረብ የሚቻልበትን አሠራር አምጥቷል፡፡ ዱቄት ዋጋውን ተመጣጣኝ ለማድረግም ጤፍ በቀጥታ ከአምራቾች በመግዛት ያመርቃል፡፡ ጤፍ ወይም ደላላ ሳይገባበት በቀጥታ ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር በመደራደር የመረከብ ዕቅድ በመያዝ፣ የአቅርቦት ችግር እንዳይኖር፣ ዋጋውም እንዳይንር ለማድረግ እንደሚጥሩ አስታውቀዋል፡፡ የተፈጨ የጤፍ ዱቄት ዋጋ በዚህ አግባብ ተመጣጣኝ ይሆናል ብለዋል፡፡

ማሽኑ ጤፉን ከማበጠርና ከማንፈስ ጀምሮ የተለያዩ መጠን ባላቸው ወንፊቶች ውስጥ እየተንዘረዘረ በማለፍ የጥራት ደረጃዎችን በማለፍ ለመጨረሻው ደረጃ ሲበቃ የሚፈጭ ሲሆን፣ በተለያየ መጠን ዱቄቱን አሽጎ የሚያመጣ ማሽንም ከመፍጫው ጋር አብሮ የሚሠራ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ተያያዥ በሆነው ሒደት የሚወጣው ንጹህ ጤፍ፣ በቀላሉ በሱፐር ማርኬት መደርደያ እንደልብ የሚገኝበትን ሒደት የሚያቀላጥፍ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ከሁሉም በላይ በቤት ውስጥ በተለይ በሴቶች ላይ የሚታየውን አድካሚ የማዕድ ቤት ሥራ በማቃለል ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የሚታመንበት ይህ የአመራረት ሥርዓት፣ ደንበኞች የፈለጉትን ዓይነት የጤፍ ዱቄት እንደምርጫቸው ለማግኘት እንደሚያስችልም ወ/ሮ ሙና አስረድተዋል፡፡

የእነ ወ/ሮ ሙና ውጥን ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከጤፍ መፍጫው ማሽን ጎን ለጎን ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ ማሽን በመትከል ላይ ናቸው፡፡ ይህኛውም ማሽን በተመሳሳይ መንገድ ዲዛይኑ ተዘጋጅቶ ለቻይናውያን በመስጠት የተሠራ ነው፡፡ ማሽኑ እንጀራ ለመጋገር የሚያስችሉትን ግብዓቶችና ቅድመ ዝግጅቶች አጠቃለው የያዙ መሣሪያዎች ያሉት እንደሆነ ከእነ ወ/ሮ ሙና ገለጻ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሰዓት 500 እንጀራ የሚጋግረው ማሽን፣ በትኩሱ የወጣውን እንጀራ በማቀዝቀዝ ለአያያዝ በሚያመች አስተሻሸግ ጠቅልሎ ያወጣል፡፡ በዚህ ማሽን የሚጋገረው ግን የጤፍ እንጀራ ብቻ አይደለም፡፡ ከሌሎች ሰብሎች የሚዘጋጅ የእንጀራ ዓይነትም ይጋገርበታል ተብሏል፡፡ ለምሳሌ የዘንጋዳ እንጀራ ከሚጋገሩት ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ ጤፍን ከስንዴና ከሌሎች ሰብሎች ጋር በመቀላቀል በተፈጨ ዱቄት የሚዘጋጅ እንጀራም ይኖራል፡፡

ይህ ሲደረግ እያንዳንዱ እንጀራ ከምን እንደተዘጋጀ የሚገልጽ ዝርዝር የምርት መረጃና መግለጫ በማሸጊያው ላይ ስሚኖር፣ ተጠቃሚው የሚመርጠውን የእንጀራ ዓይነት በመግዛት የመጠቀም ዕድል ይኖረዋል ተብሏል፡፡ የእንጀራ ማምረቻው ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡ በሁለቱም ማምረቻዎች ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ዱቄትና እንጀራም ይመረትበታል፡፡

እነዚህን ዘመናዊ ማሽኖች በማስፈብረክ ሥራ ለማስጀመር ረጅም ጊዜ ከመውሰዱ አንፃር ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ለዚህ ሥራ ተብሎ የወጣው ወጪ ምን ያህል ነው ለሚለው ጥያቄ በተጨባጭ ለመናገር የሚያስችል አሐዝ ይህ ነው ተብሎ በተጨባጭ ባይጠቀስም በግምት ግን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሥራ እንደሆነ ባለቤቶቹ ገልጸዋል፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles