Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የኬንያን በመብለጥ ከስምንት በመቶ በላይ እንደሚያድግ ይጠበቃል

$
0
0

 

  • የውጭ ኢንቨስትመንት በብዛት ከሚመጣባቸው አምስት አገሮች ተርታ ተመድባለች

ከሰሞኑ የኬንያ መገናኛ ብዙኃን የኬንያ የኢኮኖሚ የበላይነት በኢትዮጵያ መወሰዱን ሲዘግቡ ከርመዋል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ የዓለም ባንክ ይፋ ባደረገው ትንበያ መሠረት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) በ8.3 በመቶ እንደሚያድግ ባንኩ ይፋ አድርጓል፡፡

ኬንያውያኑ የዜና አውታሮች እንዳስተጋቡት ከሆነ የኬንያ የምሥራቅ አፍሪካ የበላይነት አክትሟል፡፡ ጊዜው የኢትዮጵያ ሆኗል ብለዋል፡፡ የዓለም ባንክን መረጃ መሠረት ያደረጉት መገናኛ ብዙኃኑ፣ ኢትዮጵያ የኬንያን ኢኮኖሚ በ3.6 ቢሊዮን ዶላር በመብለጥ በቀጣናው ግዙፉን የኢኮኖሚ አቅም ለመፍጠር የቻለችው በየዓመቱ ያስመዘገበችው ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ያወጣውን መረጃ ዋቢ በማድረግም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፈው ዓመት በ73 ቢሊዮን ዶላር የሚለካ አቅም እንደነበረው፣ ከካቻምናው የ64.7 ቢሊዮን ዶላር ይልቅም በተያዘው ዓመት (እ.ኤ.አ. 2017) ወደ 78.3 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያድግ ትንበያውን በማውጣቱ፣ ኢትዮጵያን ከኬንያ ብልጫውን ለመውሰድ እንዳበቃት ሲዘገብ ሰንብቷል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ አውራነቷን ከሁለት ዓመት በፊት ለኢትዮጵያ ያስረከበችው ኬንያ በበኩሏ፣ ካቻምና ያስመዘገበችው የኢኮኖሚ መጠን ግዝፈቱ በገንዘብ ሲተመን 64 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነበር፡፡ ዓምና የ69 ቢሊዮን ዶላር ግምት የነበረው ኢኮኖሚዋ፣ በዘንድሮው እንቅስቃሴው 75 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ የሚገመት በመሆኑ ከኢትዮጵያ አኳያ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በታች ሆኗል፡፡

ኬንያውያን ተንታኞች በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግዙፍ መንሳት አስተዋጽኦ አድርገዋል ያሏቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር መብዛት፣ የሕዝቡ መብዛትም ለአገር ውስጥ ገበያ የፈጠረው አቅም እንዲሁም ለውጭ ባለሀብቶች እንደልብ የቀረበው ርካሽ የሰው ኃይል ይገኙበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ከኬንያ በእጥፍ ይበልጣል፡፡

ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግዙፍ ሆኗል፣ ዓመታዊ ዕድገቱም ፈጣንና አብላጫ ያለው ቢባልለትም የኢትዮጵያን ሕዝብ ሀብታም የሚያሰኝበት ደረጃ ላይ ግን አልደረሰም፡፡ ኬንያውያንም ይህንኑ በመጥቀስ ከኢትዮጵያ እንደሚበልጡ ይናገራሉ፡፡ ይኸውም የኬንያ የነፍስ ወከፍ ገቢ (የአንድ አገር የኢኮኖሚ አቅም ለጠቅላላው ሕዝብ ሲካፈል የሚገኝ አሐዝ) ኬንያውያን ከኢትዮጵያውያን ይልቅ ሀብታሞች እንደሆኑ ያረጋግጣል፡፡ በዚህ ዓመት እንደሚኖር በሚታሰበው የኢኮኖሚ ዕድገትና በሕዝቡ ብዛት መሠረት (92 ሚሊዮን እንደደረሰ ታስቦ)፣ የኢትዮጵያውያን አማካይ የነፍስ ወከፍ ዓመታዊ ገቢ 848 ዶላር ወይም 18,650 ብር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ማለት ነው፡፡

በአንፃሩ ኬንያውያን የሚያገኙት ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ1,650 ዶላር በላይ፣ በብር ሲገለጽ 36,300 ብር ስለሚደርስ ከኢትዮጵያውያን ይልቅ በእጥፍ የሚበልጥ የገቢ ብልጫ ያላቸው፣ ሀብታሞች ኬንያውያኑ እንደሆኑ አሐዞቹ ያረጋግጣሉ፡፡ ኬንያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ የምትመደብ አገር መሆኗም የታወቀ ነው፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ መመደቧም እውነት ነው፡፡

ይህም ቢባል ግን በኬንያና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት ልዩነት የሚያሰፉ የኢንቨስትመንት ሁናቴዎችም ይስተዋላሉ፡፡ አንደኛው አብነት በመንግሥት የሚካሄዱ ልዩ ልዩ የመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ የሚጠቀስ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ያህል ፈርጀ ብዙ አይሁን እንጂ የኬንያ መንግሥትም በመንገድ፣ በባቡር፣ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በትምህርትና ጤና በሌሎችም መስኮች የሚጠቀሱ አንኳር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ያከናውናል፡፡

ከመንግሥት ኢንቨስትመንት በተጨማሪ ግን በውጭ ባለሀብቶች የሚካሄዱ ኢንቨስትመንቶችም ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መበራከት ወሳኙን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም መሠረት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ የዚህ ዓመት የኢንቨስትመንት ሪፖርት እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚጠቀሱ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች አንዷ ሆኗለች፡፡ በአንጎላ የ14 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን ከሚመራው ጎራ የተሰለፈችው ኢትዮጵያ፣ ከግብፅ፣ ከጋና እና ከናይጄሪያ በመከተል በአፍሪካ ዋና ዋና የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ተብለው ከተደለደሉ አገሮች አንዷ መሆኗን የተመድ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 የተመዘገበው የውጭ ኢንቨስትመንት 3.2 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር የጠቀሰው ይኸው ሪፖርት፣ እንዲህ ያለው የኢንቨስትመንት መጠን የተመዘገበው የዓለም የሸቀጥ ንግድ እጅጉን እየተቀዛቀዘ በቀጠለበት፣ የውጭ ኢንቨስተሮችም ወደ አፍሪካ በተለይም ከሰሃራ በታች ወዳሉት አገሮች ለመምጣት መነሳሳቱን ባጡበት ወቅት መሆኑ ግምት እንደሚሰጠው የሚያስገድድ የኢንቨስትመንት መጠን መሆኑን አመላክቷል፡፡

 በዚያም ላይ በኢትዮጵያ የሚገነቡ መሠረተ ልማቶችና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሚያሳየው ለውጥ ኢትዮጵያ ላስመዘገበችው የውጭ ኢንቨስትመንት ዕድገት አስተዋጽኦ አድርገዋል ያለው ይህ ሪፖርት፣ ኢንስትመንቱ የ46 በመቶ ዕድገት እንደነበረውም አትቷል፡፡

ምንም እንኳ በኢንቨስትመንትም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ዕድገት የኢትዮጵያ ግስጋሴ ይህን ያህል ቢነገርለትም በሕዝቡ የዕለት ኑሮ መንጻበረቅ መጀመሩ ላይ ብዙ  ይቀረዋል፡፡ የኑሮ ውድነት በተለይም የምግብና የሌሎች ሸቀጦች ዋጋ በየጊዜው መናር፣ የከተማም ሆነ የገጠር ነዋሪውን የድህነት መጠን፣ የሥራ አጥነት ወዘተ ችግሮችን በመቀነስ ዕድገቱ የሚያደርገው አስተዋተዋጽኦ በብዙ የሚጠበቅ ይጠበቃል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ ደጋግሞ የሚከሰተው የድርቅ አደጋ፣ ውዝፍ የብድር ዕዳ ክፍያ፣ ዕምና እንደተከሰተው ያለ የፖለቲካ ትኩሳት የሚያጋጥም ከሆነ በኢንቨስትመንቱም ሆነ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ምሁራን ይስማሙበታል፡፡ የዕድገቱም ዘላቂነት እንዚህና መሰል አንገብጋቢ ጉዳዮች እንደሚወስኑት ኬንያውያኑም ሆኑ የአገር ቤት ሰዎች ይስማማሉ፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles