Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

ለሕክምና ባለሙያዎች የሥራ ላይ አደጋ የመድን ሽፋን መስጠት ተጀመረ

$
0
0

 

ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጄነራል ኢንሹራንስ አክስዮን ማኅበር፣ በአገሪቱ የመጀመሪያውን ለሕክምና ባሙያዎች እንዲሁም በመስኩ ለተሠማሩ የተለያዩ አካላት የመድን ሽፋን የሚሰጥ አዲስ አገልግሎት ማቅረብ ጀመረ፡፡

ኩባንያው ይህንን አገልግሎት መጀመሩን በማስመልከት ሐሙስ ሰኔ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሔደው ሥነ ሥርዓት ወቅት፣ ‹‹ዶክተርስ ኤንድ ፕራክትሺነርስ ፕሮፌሽናል ኢንደሚኒቲ፤›› በሚል መጠሪያ አዲስ የኢንሹራንስ አገልግሎት ለገበያ ማቅረቡን ያስታወቀው ኩባንያው፣ ዶክተሮችና ሌሎችም የሕክምና ባለሙያዎች የሙያ ግዴታቸውን በሚወጡበት ወቅት በሚፈጠር ችግር ምክንያት ሊመጣባቸውን የሚችል የሕግ ተጠያቂነት ሥጋትን ለማቃለል የሚያስችል እንደሆነ ገልጿል፡፡

አገልግሎቱ በሌሎች አገሮች የተለመደ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ፣ ከተጠቃሚዎች ፍላጎትና ከመግዛት አቅም ጋር ተገናዝቦ ለመጀመሪያ ጊዜ ለገበያ መቅረቡን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽመልስ ገብረጊዮርጊስ ገልጸዋል፡፡

አዲሱ የኢንሹራንስ አገልግሎት ታካሚዎች በሐኪሞችና በጤና ባለሙያዎች ላይ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት የሚቀርብባቸውን የሕግ ተጠያቂነት የሚሸፍን ሲሆን፣ በወንጀል የሚቀርብ ተጠያቂነት ግን በመድን ሽፋኑ እንደማይካተት ኩባንያው አስታውቋል፡፡

የሐኪሞችም ሆነ ሌሎች የጤና ባለሙያዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን የሚጠቀሰው ኩባንያው፣ በአሁኑ ጊዜ  ከ11,000 በላይ ሐኪሞች፣ 4,460 አዋላጅ ነርሶች፣ 668 ሰመመን ሰጪ ባለሙያዎች፣ 1,042 የጥርስ ሐኪሞች፣ 682 የጨረር ሕክምና ባለሙያዎች እና 628 የባዮ ሚዲካል ሳይንቲስቶች በኢትዮጵያ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጀነራል ኢንሹራንስ አክስዮን ማኅበር፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሕክምና ዘርፍ ውስጥ እየታየ ያለውን አወንታዊ ለውጥ እንዲሁም የባለሙያዎች ቁጥር መጨመርን ግምት ውስጥ በማስገባት አዲስ የመድን አገልግሎት ለመስጠት መነሳቱን አስታውቋል፡፡ በተለይ ከሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ እየታዩ ያሉ ጉዳቶች እየጨመሩ በመምጣታቸው ሳቢያ፣ አገልግሎት ሰጭዎችንም ሆነ ተገልጋዮችን በመድን ሽፋን ለማገዝ የሚረዳ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ የሕክምና ዶክተሮችና ሌሎች የጤና ባለሙያዎች ለኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት አገልግሎቶችን በሚሰጡበት ሒደት የሚያጋጥማቸውን ያልተጠበቀ የአደጋ ሥጋት መታደግ ስለሚቻልበት መንገድ ጥናት ሲያካሂድ ከቆየ በኋላ ለመተግር የተነሳበት የመድን ዓይነት እንደሆነም ከኩባንያ ኃላፊዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

 የኢንሹራንስ አገልግሎቱን ለመጀመር ያካሔደው ጥናትም የሕክምና ዶክተሮችና የጤና ባለሙያዎች ከአቅም በላይ በሆነ ያልታሰበ ክስተት በታካሚዎች ላይ በሚያደርሱት ጉዳት አለያም ስህተት ምክንያት ሕጋዊ ተጠያቂነት ሲመጣባቸው   ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት ሲያመራ ይታያል፡፡ በዚህ አግባብ የሚቀርብባቸውን ክስ ለመከላከል ታሳቢ  ያደረገ የመድን ሽፋን ነው፡፡ እንደሚደርሰው ጉዳት ሁኔታ ለተጎጂ ታካሚዎች ካሳ የመፈጸም ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑም በፋይንንስ አቅማቸው ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ ለመገንዘብ እንደተቻለም ኩባንያው ያስረዳል፡፡

የካሳ ክፍያ ጣሪያው ኢንሹራንስ በሚገቡት የሕክምና ባለሙያዎች ውሳኔ መሠረት እንደሚፈጸም የኩባንያው ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ ብሥራት ኃይለሥላሴ ገልጸዋል፡፡ የመድን ካሳው እስከ ምን ያህል መጠን ሽፋን ይሰጣል?  ለሚለው ጥያቄ፣ የሕክምና ባለሙያው ከሚያጋጥመው የአደጋ ሥጋትና ከሥራው ባህሪይ፣ ከመክፈል አቅሙና ከፍላጎቱ ጋር እንደሚያያዝ ገልጸዋል፡፡ የመድን ውሉ እንደ ማንኛውም ሕይወት ነክ ያልሆነ ኢንሹራንስ በየዓመቱ የሚታደስ በመሆኑ፣ በዓመት ለምን ያህል ጉዳቶች የመድን ሽፋን እንደሚያስፈልጋቸው አስበው የሚገቡበት እንደሆነም አቶ ብሥራት ተናግረዋል፡፡

የአገልግሎቱን መጀመር አስመልክቶ ከሕክምና ባለሙያዎች ስለተሰጠው ግብረ መልስ በተሰጠው ማብራሪያም አገልግሎቱን ፈልገው እስካሁን ሊያገኙ እንዳቻሉ የሕክምና ባለሙያዎቹ እንደገለጹላቸው ያመለከቱት ኩባንያው ኃላፊዎች፣ የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበራትም የአገልግሎቱን መጀመር በእጅጉ እንደሚፈልጉት መናገራቸውን አስታውቀዋል፡፡

በዚህ መድን ሽፋን ያላቸው ባለሙዎች አማካይነት አደጋ ቢደርስ፣ አደጋው ስለመድረሱ ማረጋገጫ የሚሰጠው አካል ማን ነው ለሚለውን በተመለከተ ለኩባንያው ኃላፊዎች ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት አቶ ብሥራት ‹‹ኩባንያችን ጉዳቱን እንዴት ይወሰናል የሚለውን ቀድሞ አስቦበታል፡፡ አደጋው መፈጸሙ እንዴት ይረጋገጣል የሚለው በጣም አስፈላጊ ጉዳይ በመሆኑም ይህን የሚያጣራ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የተቋቋመ ቡድን አለ፡፡ በኢትዮጵያ ምግብ፣ መድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ውስጥ በተቋቋመ ክፍል የሚተዳደረው ይህ ቡድን በሚወሰነው መሠረት የካሳ ክፍያዎች ይፈጸማሉ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሜድኮ ሌጋል›› የሚባለው ይህ ቡድን ከተለያዩ የሕክምና ዘርፎች የተውጣጡ ባለሙያዎችን ማካተቱን የጠቀሱት አቶ ብሥራት፣ አደጋ ሲደርስ የሕክምና አሰጣጡ ወይም ሐኪሙ ጥፋት አለበት፣ የለበትም የሚለውን ውሳኔ የሚሰጡትም እነዚሁ ባለሙያዎች እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡ ስለዚህም በሕግ በተቋቋመ አካል በመኖሩ ውሳኔ አሰጣጡ እንደማያስቸግር ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያው ዘመናዊ ሆስፒታል በመሆን ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል በ1894 ዓ.ም. ገደማ በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ተቋቁሞ ሥራ ከጀመረ ጀምሮ፣ የጤናው ዘርፍ በለውጥ ሒደት ውስጥ እንደሚገኝ ያስታወሰው ኩባንያው፣ በአሁኑ ጊዜ ልዩ ልዩ የጤና አገልግሎቶች በመንግሥታዊና በግል ተቋማት እየቀረቡ፣ ተደራሽነታቸውም ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡

የሕክምና ሥልጠና የሚሰጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማስፋፋታቸውም የሐኪሞችና የጤና ባለሙያዎች ቁጥር እንዲያድግ አግዟል፡፡ ከ12 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የጤና ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ሦስት ብቻ እንደነበሩም ኩባንያው አስታውሷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ 28 የመንግሥት፣ ስምንት የግል ከፍተኛ የሕክምና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ሲኖሩ፣ በዓመት 2,000 ተመራቂዎችን የማፍራት አቅም አላቸው፡፡ በመሆኑም ይህንን ዘርፍ ከኢንሹራንስ አገልግሎት ጋር ማስተሳሰሩ ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የዶክተሮችና የታካሚዎች ምጣኔ በአሁኑ ወቅት አንድ ለ15,000 መድረሱ ተጠቁሟል፡፡ መንግሥት ይህንን ምጣኔ አንድ ለ10,000 እንደሆን የማድረግ ዕቅድ ያለው በመሆኑ፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ተከፍተው አገልግሎት እንደሚሰጡ የሚጠበቁት 13 ዩኒቨርሲቲዎች ሥራ ሲጀምሩም፣ የሐኪሞችና የታካሚዎች ምጣኔ አሁን ካለውም መጠን እንደሚቀንስ ይጠበቃል፡፡

ኩባንያው ካስተዋወቀው የኢንሹራንስ አገልግሎት በተጨማሪ በሕይወት ነክ ኢንሹራንስ ዘርፍ ‹‹የትምህርት ቤት ክፍያ ዋስትና›› እንዲሁም ‹‹ሴቶችን ያማከለ የቡድን የሕይወት ብድር ማይክሮ ኢንሹራንስ›› የተባሉትን በማዘጋጀት ለገበያ እያቀረበ የሚገኝ ኩባንያ እንደሆነም አስታውቋል፡፡

ኩባንያው የተጠቃሚዎችን የኢንሹራንስ ፍላጎቶችን በማጥናትና የባለሙያዎቹን የፈጠራ አቅም በመጠቀም አዳዲስ የኢንሹራንስ ዓይነቶችን ለገበያ በማቅረብ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ድርሻ የማስጠበቅ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ አቶ ሽመልስ ጠቅሰው፣ በቅርቡም ተጨማሪ የኢንሹራንስ አገልግሎቶችን ይፋ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles