‹‹ሳይሞከር እንዴት ነው አያዋጣም የሚባለው?››
ትራንስፖርት ባለሥልጣን
- ‹‹በማን ኪሳራ ነው የሚሞከርብን?››
የሜትር ታክሲ ማኅበራት መንግሥት ከቀረጥ ነፃ በሰጠው ዕድል አማካይነት ከ1,000 በላይ ሜትር ታክሲዎች አዲስ አበባ ከገቡ መንፈቀ ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ ታክሲዎቹን ጨምሮ ከ500 ያላነሱ አውቶቡሶችም በቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በመወሰኑ ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደተመደበም ይታወሳል፡፡
በመሆኑም ቀረጥ ሳይከፈልባቸው በገቡት ታክሲዎች ላይ የታሪፍ አገልግሎት ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል፡፡ እንደውም ከየካቲት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በአስገዳጅነት በወጣላቸው ታሪፍ መሠረት እንዲሠሩ የሚያሳስብ መመርያ ተላልፎ፣ ከገቡት 1163 ያህል ታክሲዎች ለአግልግሎት ብቁ ናቸው በተባሉት 750ዎች ላይ የስምሪት ትዕዛዝ ወጥቶ እንዲሠሩ ተብሏል፡፡ በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የወጣውን የታሪፍ መመርያ እንዲያስፈጽም ሥልጣን የተሰጠው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ከወር በፊት መግለጫ ማውጣቱም ይታወሳል፡፡ በመግለጫው መሠረት በወጣው ታርፍ የማይሠሩት ታክሲዎች ላይ ከገንዘብ ቅጣት ጀምሮ እስከ የፈቃድ ንጥቂያ የሚደርሱ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡
ከመነሻው ጀምሮ ተቃውማቸው ሲያሰሙ የከረሙት 26ቱም የሜትር ታክሲ ማኅበራት፣ መንግሥት ያወጣውን ታሪፍ እንዲያስተካክል ሲሞግቱና ሲቃወሙ ቆይተዋል፡፡ ፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ያወጣው ታሪፍ የባለንብረቶቹን ጥያቄ አላገናዘበም፣ አዋጭነትና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን አርቆ አላየም የሚሉ ትችቶች እየቀረበበት ይገኛል፡፡
በአጨቃጫቂው ታሪፍ መሠረት ለሊፋን ሥሪት 750 ታክሲዎች በኪሎ ሜትር አሥር ብር እንዲሠሩ ተወስኗል፡፡ በአንፃሩ ቶዮታ ሠራሽ አቫንዛ ሞዴል ታክሲዎች በኪሎ ሜትር 13 ብር እንዲሠሩ ተብሏል፡፡ በመሆኑም ታክሲዎቹ ከመንቀሳቀሳቸው በፊት ታሳቢ የሚደረገውን መነሻ ሒሳብ (ለሊፋን አሥር ብር፣ ለአቫንዛ 13 ብር) ታክሎበት፣ ተሳፋሪው የተሳፈረበትን ርቀት ልክ በሚለካው ሶፍትዌር አማካይነት እንዲከፍል ይጠበቅበታል፡፡ ይህም ማለት ሁለት ኪሎ ሜትር የሚጓዝ ተሳፋሪ በሊፋን ታክሲዎች ከሆነ ለተጓዘበት ርቀት 20 ብር እንዲሁም ለመነሻው የተቀመጠውን አሥር ብር አካቶ 30 ብር ይከፍላል ማለት ነው፡፡ የአቫንዛዎቹም በተመሳሳይ ስሌት እንደሚተገበር ተገልጾ ነበር፡፡
ይህ ታሪፍ ግን ከመነሻው ጀምሮ ተቃውሞ እየቀረረበበት ሲሆን፣ ታክሲዎቹም ቢሆኑ እስከቅርብ ጊዜው አስገዳጅ መመርያ ድረስ ከታሪፉ ይልቅ በድርድር መሥራቱን ሲያስቀድሙ ይታዩ ነበር፡፡ አስገዳጁ መመርያ ከወጣ በኋላ ታክሲዎቹ ከጎዳና መጥፋት አብዝተው ከርመዋል፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስም በዚሁ አኳኋን ሰነባብተዋል፡፡ ከሰሞኑ ግን በየመንገዱ መታየት ጀምረዋል፡፡ የዚህ ምክንያቱም መንግሥት በተደጋጋሚ የታክሲ ማኅበራቱ የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች ችላ በማለት መንግሥት የራሱን አቋም በማራመዱ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል፡፡
ከማኅበራቱ መካከል ሪፖርተር ያነጋገራቸው አዲስ ሜትር ታክሲ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ሙላቱ እንዲሁም የ‹‹ዚ ሉሲ›› ሜትር ታክሲዎች ማኅበር ኃላፊ አቶ አንተነህ ትሪሎ ተመሳሳይ አቋም አላቸው፡፡ መንግሥት እንዲተገበር ያደረገው አስገዳጅ ታሪፍ የታክሲዎቹን ባለንብረቶች መሠረታዊ ጥያቄዎች ከግምት ያላስገባ እንደሆነ ሁለቱም ይገልጻሉ፡፡ በቅርቡ ለሌላ ጉዳይ በተጠራው ስብሰባም ይኸው የታሪፍ ጉዳይ በታክሲ ባለንብረቶች ተነስቶ አብዛኞቹ ስሜታዊ ሆነው ሲናገሩ እንደነበረ ታውቋል፡፡
ከወር በፊት ሪፖርተር በዚህ ታሪፍ ጉዳይ ላይ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ያነጋገራቸው አቶ አንተነህ እንዲህ ብለው ነበር፡፡ ‹‹በታሪፉ ላይ ቅሬታ ነበረን፡፡ የታሪፍ አሞላሉ ቅሬታ አሳድሮ ነበር፡፡ በተለይ የተሳፋሪው ቆይታ ጊዜ ማለትም በጉዞ ወቅት ወርዶ ጉዳዩን ፈጽሞ የሚመለስ ተሳፋሪ የሚስተናገድበት አሠራር የለውም፡፡ የነዳጅ ታሪፍ ለውጥ ሲኖር፣ በዝናብ ጊዜ፣ እንደ አፍሪካ ኅብረት ያለው ስብሰባ በሚኖርበት ወቅት ለሚፈጠረው የመንገድ መዘጋጋት ምላሽ የሚሰጥ ሥርዓት አልተዘጋጀም፤›› ያሉት አቶ አንተነህ፣ አሠራሩ ከውጭ እንደ መግባቱ መጠን እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ የሚችል መሆን ሲገባው ይህን አላደረገም ብለው ነበር፡፡
ከወር በኋላ ሪፖርተር ዳግም ታክሲዎቹ ስለሚገኙበት ሁኔታ ባደረገው ማጣራት የተለወጠ ነገር እንደሌለ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ መንግሥትም በአቋሙ እንደፀና ሲሆን፣ ታክሲዎቹም በመንግሥት አካሄድና ውሳኔ ላይ ያደረባቸው ቅሬታም አልተነሳም፡፡ በመሆኑም የሁለት ጎራ ሆነው ቀጥለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ አማረ ከዚህ ቀደም በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ታክሲዎቹ በተወጣላቸው ታሪፍ መሠረት እንዲሠሩ፣ በሥራ ሒደት እየታየም መሻሻል ያለበት ነገር ይሻሻላል ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ሆኖም ታክሲዎቹ የወጣው ታሪፍ አያዋጣንም ቢሉም፣ ከአቶ ምትኩ ማብራሪያ ግን ታክሲዎቹ በቀን በአማካይ 120 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ርቀት በመጓዝና በየአቅጣጫው ገደብ ሳይኖርባቸው እንዲሠሩ የሚችሉበት ስሌት መነሻ ተደርጎ በዚሁ ስሌት መሠረት እንዲሠሩ መወሰኑን ጠቅሰው ነበር፡፡ በዚህ ስሌት መሠረት ቢያንስ 75 በመቶውን ርቀት ተሳፋሪ በማጓጓዝ ቢሸፍኑት የቀን ገቢያቸው (የሊፋን ታክሲዎች) ከ750 ብር በላይ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ይሁንና ይህንን ታሪፍ በመቃወም አነስተኛ ብቻም ሳይሆን ካለብን የባንክ ዕዳ ከመሳሰሉት ወጪዎች አኳያ አያዋጣንም ቢሉም፣ አቶ ምትኩ ግን ‹‹ታሪፉ ያንሳል ይበዛል ለማለት መሞከርና ውጤቱ መታየት አለበት፤›› የሚል አቋም አራምደዋል፡፡ በመሆኑም ‹‹አንድ ነገር ሳይሞከር እንዴት ነው አያዋጣም የሚባለው?›› በማለት የታክሲዎቹን ባለንብረቶች ጥያቄ በጥያቄ አስተናግደዋል፡፡ ይህንን ቢሉም ታሪፉ ወደፊት ማሻሻያ እንደሚደረግበትም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
ምንም እንኳ የታሪፍ ማሻሻያ ይደረጋል መባሉን አቶ አንተነህ ቢቀበሉትም፣ ‹‹እስከዚያው ግን በወጣው ታሪፍ መሠረት ሥሩ መባላችን በማን ኪሳራ ነው እኛ ላይ የሚሞከረው?›› የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ታሪፉ መሞከር ካለበት በተወሰኑ ናሙናዎች ላይ እንጂ 751 ታክሲዎች ላይ መሆኑ አግባብ አይደለም፤›› ያሉት አቶ አንተነህ፣ እንዲህ ያለው አሠራር በርካቶቹን ባለታክሲዎች ህልውና አደጋ ላይ እንደሚጥልም አብራርተዋል፡፡ በርካቶቹ ታክሲዎቹን የገዙት ባለንብረቶች የነበሯቸውን የቀደሙ ታክሲዎች ሸጠው፣ ተበድረውና ተለቅተው በመሆኑ ታሪፉ ከግንዛቤ ያላስገባቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ መንግሥት ሊገነዘብ እንደሚገባው ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ግን በተጠቃሚዎች ዘንድ የተፈጠረው ብዥታም ላለመግባባት ምክንያት እየሆነ እንደሚገኝ አቶ አንተነህ ገልጸው፣ መንግሥት ታክሲዎቹን በነፃ ያደለ እስሊመስል ድረስ የተዛባ አመለካከት እየተንፀባረቀ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ ይሁንና መንግሥት ከቀረጥ ነፃ ዕድል ከመስጠቱ ውጭ የታክሲዎቹን የ30 በመቶ ቅድሚያ ክፍያና የ70 በመቶ የባንክ ብድር ዕዳ በመክፈል የታክሲዎቹ ባለቤቶች ግለሰቦቹ እንጂ መንግሥት እንዳልሆነ መታወቅ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ታክሲዎቹ የሚመሩበት የአሠራር ሥርዓት ማኑዋል ባለመዘጋጀቱም የሜትር ታክሲዎች አሠራርና ስምሪት ችግር እንደሚታይበት ገልጸዋል፡፡
የታሪፉን ጉዳይ በሚመለከት አቶ ዮናስ እንደሚገልጹት በማኅበራቸው በኩል ለመንግሥት ቀርቦ የነበረው ዋጋ ከ20 ብር በላይ እንደነበር፣ ከዚህ በታች ቢደረግ ግን ለታክሲዎቹ የወጣውን ገንዘብ ለመመለስም ሆነ ለባለንብረቶቹ ማስገኘት የሚገባቸውን ጥቅም ሳያስገኙ በኪሳራ ለመሥራት እንደሚያስገድዱ ተገልጾ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በጠቅላላው ሜትር ታክሲዎቹ በመንግሥት ታሪፍ ለመሥራት የተገደዱት መንግሥት በ‹‹ጉልበት›› እንዲሠሩ ስላስገደዳቸው እንጂ አዋጭ ሆኖ እንዳልሆነ እየገለጹ ቢሆኑም፣ መንግሥት ወደ ሥራ ግቡ እያለ ይገኛል፡፡ በሁለቱ ወገን አለመግባባት የሜትር ታክሲዎች አገልግሎት እንደታሰበው ሊሆን አልቻለም፡፡ አሁንም ድረስ በርካቶቹ በድርድር ዋጋ ተስማምተው እየሠሩ እንደሚገኙ ታይቷል፡፡ የአቫንዛ ታክሲዎች በወጣው ታሪፍ መሠረት እንዲሠሩ ለማኅበር አባላት መገለጹንና በዚሁ መሠረት እየሠሩ እንደሚገኙ አቶ ዮናስ ቢከራከሩም፣ ተጨባጭ እውነታው ግን ይህን አያሳይም፡፡
‹‹የውበት እስረኞች›› የሚል ስያሜ የወጣላቸው የሜትር ታክሲዎች በገቡበት አግባብ አገልግሎት ሊሰጡ ባለመቻለቻው፣ በመንግሥትና በታክሲዎቹ ባለንብረቶች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት አንዳንድ ማኅበራትን ለባንክ ውዝፍ ዕዳ እንዳበቃቸው እየተነገረ ነው፡፡ ከቀረጥ ነፃ ለገቡት ሁሉም ሜትር ታክሲዎች ብድር ካቀረበው ብርሃን ባንክ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ባይሳካም፣ የዕዳ ማስጠንቀቂያ የጻፈላቸው ማኅበራት እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አንዳንድ ባለንብረቶችም ታክሲዎቹን ባንኩ እንዲረከባቸው እየጠየቁ እንደሚገኙ አቶ አንተነህ ገልጸዋል፡፡
የሳሎን ታክሲዎች ስምሪት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደር ወቅት እንደተጀመረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የታክሲ አገልግሎት ማኅበራቱ በደርግ መንግሥት ወቅት እንዲበተኑ ሲደረግ በርካታ የታክሲ ባለንብረቶችም ተወርሰው ነበር፡፡ በኢሕአዴግ መንግሥት ወቅት የቀደሙት የሥርዓቱ መሥራቾች እንዲፈቀድላቸው በመጠየቅ ተደራጅተው መሥራት እንደጀመሩና በአብዛኛውም በኤርፖርትና በሆቴሎች አካባቢ ሲሠሩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
