የሐዋሳ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃውን ለመገንባት የሚችልበትን ቦታ ከሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ የራሱን ሕንፃ ለመገንባት ቦታ እንዲሰጠው ጥያቄ ካቀረበ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ በቅርቡ ከሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምላሽ አግኝቷል፡፡ ለሕንፃ ግንባታው ምቹ በተባለ የከተማዋ ክፍል 800 ካሬ ሜትር ቦታ በአነስተኛ ሊዝ ዋጋ እንደተረከበ አስታውቋል፡፡ የቦታው የሊዝ ዋጋ 1.12 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ቦታው ላይ ይገነባል ለተባለው ሕንፃ ቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ መቀመጡን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ለሕንፃ ግንባታው የተቀመጠውን የመሠረት ድንጋይም የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ ያስቀመጡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትና የከተማው ንግድ ምክር ቤት አመራሮች በሥነ ሥርዓቱ ላይ መገኘታቸውም ተገልጿል፡፡
የሐዋሳ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሚልኪያስ አንዴቦ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ንግድ ምክር ቤቱ በተሰጠው ቦታ ላይ በአጭር ጊዜ የሕንፃ ግንባታ ሥራውን ይጀምራል፡፡ እንደ አቶ ሚልኪያስ ገለጻ፣ ሊገነባ የታሰበው ሕንፃ ስድስት ወለሎች የሚኖሩት ሲሆን፣ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሊጠይቅ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ለግንባታው የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች የሚዘጋጁ ሲሆን፣ የመሠረት ግንባታውን ግን በራሱ አቅም ለመጀመር መታቀዱን የምክር ቤቱ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡
በንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት እንዲሁም በመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ፣ በሐዋሳ ከ14 ሺሕ በላይ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች እንደሚኙ ጠቅሰዋል፡፡ ከተማው ከሚያሰባስበው ገቢ ውስጥ አንድ ቢሊዮን ብር የሚደርሰው ገቢ በአብዛኛው ከንግዱ ማኅበረሰብ እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል፡፡
የከተማው አስተዳደር ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለው የተናገሩት ከንቲባው፣ በተለይ ታማኝ ግብር ከፋዮች እንዲበራከቱ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ በትጋት መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱን ለማጠናከር የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የሚጠበቅበትን ድርሻ እንደሚወጣ አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ጥያቄ ሲቀርብበት ለነበረው የሐዋሳ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና መሥሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ አስተዳደሩ 800 ካሬ ሜትር ቦታ መስጠቱን በእማኝነት ጠቅሰዋል፡፡
ወደፊትም ለሕንፃ ግንባታው ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ከንቲባው ቃል ገብተዋል፡፡ የበርካታ ዓመታት ጥያቄ ለነበረው የጽሕፈት ቤት ሕንፃ መሥሪያ ቦታ በማቅረብ አስተዳደሩ ምላሽ በመስጠቱ፣ ከፍተኛ ውጣ ውረዶችን በማለፍ ለስኬት እንዲበቃ የሚያስችል መሆኑን አቶ ሚልኪያስ ጠቅሰዋል፡፡ የሕንፃ ግንባታው የንግዱን ማኅበረሰብ አባላት በማሳተፍና ከመንግሥት ጋር በመሆንም ጭምር እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱ ውስጣዊ አደረጃጀቱን ለማጠናከር እየሠራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሚልኪያስ፣ ለምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ሥልጠናዎች በመስጠት ላይ እንደሚገኝ፣ የንግድ ትስስሮችን የመፍጠር ሥራዎችንም እንደሚያከናውን ጠቁመዋል፡፡ ምክር ቤቱ የአባላትን ቁጥር ለማሳደግ አዳዲስ አባላትን የማፍራት ሥራ እንደሚሠራም አቶ ሚልኪያስ አስታውቀዋል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ የራሱን ሕንፃ መገንባት መቻሉ አቅሙን ከማጎልበት በተጨማሪ ለአባላቱ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማበራከት ያስችለዋል ብለዋል፡፡ የሐዋሳ ንግድ ምክር ቤት ከ600 በላይ አባላት እንዳሉት ተገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ባሻገር የክልል ከተሞች ውስጥ የራሱ የጽሕፈት ቤት ሕንፃ ያለው የአዳማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የድሬዳዋ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቀድሞ ጊዜ የተወረሰበትን ሕንፃ ለማስመለስ እየንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም የራሱን ሕንፃ ለመገንባት የሚችልበት ቦታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲሰጠው ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ከ70 ዓመታት በላይ ዕድሜ ባስቆጠረው የአገሪቱ የንግድ ምክር ቤቶች ታሪክ ውስጥ፣ አብዛኞቹ ምክር ቤቶች የራሳቸውን የጽሕፈት ቤት ሕንፃ መገንባት ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡
