Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

መንገዶች ባለሥልጣን ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ የ20 መንገዶችን ጨረታ ይፋ አደረገ

$
0
0

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ2009 ዓ.ም. ግንባታቸውን እንዲካሄድ በዕቅድ ከያዛቸው 69 ፕሮጀክቶች ውስጥ በአነስተኛ የዋጋ ግምት ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ሊጠይቁ ይችላሉ የተባሉ የ20 ፕሮጀክቶች ጨረታ ይፋ አደረገ፡፡

20ዎቹ መንገዶች በጠቅላላው የ1048 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ የ20 ፕሮጀክቶች የግንባታ ጨረታ ይፋ ሲደረግ የመጀመሪያው መሆኑም ተነግሯል፡፡

ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የዚህን ያህል የመንገድ ግንባታ ጨረታ በአንድ ጊዜ ያወጣው፣ በበጀት ዓመቱ በርካታ አዳዲስ መንገዶችን ለማስጀመር በማቀዱ ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ ግንባታቸው እንዲጀመር የታሰቡ መንገዶችን ጨረታ ከፋፍሎ ከማውጣት ይልቅ በአንድ ላይ አሰባስቦ ማውጣቱ የተሻለ ስለሆነ በዚሁ መነሻ የተወሰደ ዕርምጃ እንደሆነም ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ 

ከ20ዎቹ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ 12ቱ በዓለም አቀፍ ጨረታ መሥፈት ግንባታቸው የሚከናወን ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች ከውጭ የፋይናንስ ተቋማት በሚገኝ ገንዘብ የሚገነቡ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ስምንት ፕሮጀክቶች ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት በሚመደብ በጀት እንደሚሠሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የጨረታ ሰነዱ እንደሚያመለክተው፣ በመንግሥት በጀት የሚከናወኑት ግንባታዎች የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ተሳታፊ እንደሚሆኑባቸው የሚጠበቁ ናቸው፡፡ በእነዚህ ፕሮጀክቶች ለሚሳተፉ አገር ውስጥ ተቋራጮች ሲባልም የጨረታ ሒደቶቹ  የሚጠይቋቸው መሥፈርቶች ዝቅ መደረጋቸውም ተመልክቷል፡፡

በመሆኑም የአገር ውስጥና የውጭ ተቋራጮች የተለያዩ የመወዳደሪያ መሥፈርት የተቀመጠላቸው ሲሆን፣ ለውድድር የሚቀርብበትም በዚሁ መስፈርቶች እንደተቀመጡላቸው ከሰነዱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይኸውም ከአገሪቱ የግዥ ሥርዓት ጋር እንደሚጣጣም አመላካች ነው፡፡

ሁሉም የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ደረጃ አንድ ተቋራጮችን ብቻ የሚሳተፉ ሲሆን፣ እንደየመንገዱ ዓይነትም በጨረታ የሚሳተፉ ተቋራጮች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ነጥቦች ተመልክተዋል፡፡ ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰት መጠናቸው ምን ያህል መሆን እንደሚገባው ተቀምጧል፡፡ የአገር ውስጥ ተጫራቾች ከ98 ሚሊዮን ብር እስከ 348 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰት ሊኖራቸው እንደሚገባ በሰነዱ ሰፍሯል፡፡ ይህም ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የነበራቸውን አማካይ ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰት መጠን የሚያሳይ ነው፡፡

የውጭ ተቋራጮችም እንደየመንገዱ ፕሮጀክት ዓይነት ከ245 ሚሊዮን ብር እስከ 959 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰት ሊኖራቸው እንደሚገባ በጨረታ ሰነዱ ተመልክቷል፡፡ በዚህ ጨረታው ሒደት በሽርክና ተጣምሮ መወዳደር የሚቻል ሲሆን፣ ግንባታዎቹን ተጣምረው ለመሥራት የሚቀርቡ ተቋራጮችም ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በአማካይ ከ184 ሚሊዮን እስከ 719 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰት ማስገባታቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ጨረታው ሌሎች መስፈርቶችንም አካቷል፡፡ ለአገር ውስጥ ተቋራጮች የተቀመጠው አማካይ ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰት መጠን በዝቷል የሚሉ ቅሬታዎች እየተደመጡ ነው፡፡ የውጭዎቹ ተቋራጮች በሁሉም ጨረታዎች ውስጥ እንዲሳተፉ መፍቀዱም ጨረታው የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን የመሳተፍ ዕድል የሚያጣብብ ሊሆን  እንደሚችል ሥጋት የገባቸውም አልታጡም፡፡

ከተጠቀሱት 20 አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ግማሽ ያህሉ በቀጥታ ዲዛይንና የግንባታ ሥራቸው በጣምራ በተቋራጮች እንደሚሠሩ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ ጨረታውም ይህንኑ የዲዛይንና የግንባታ ሥራዎች አጠቃሎ የያዘ ነው፡፡ የቀሪዎቹ ፕሮጀክቶች ዲዛይን ግን ባለሥልጣኑ በሚቀጥራቸው አማካሪ ድርጅቶች እንደሚዘጋጁ ታውቋል፡፡ ለእነዚህ መንገዶች የሚፈለጉት ተጫራቾች ለግንባታ ሥራ ብቻ የሚወዳደሩ ይሆናሉ፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝና በደቡብ ክልል የሚገነቡ ሲሆን፣ 20ዎቹም መንገዶች ከአምስት እስከ 117 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ርዝመት ይኖራቸዋል፡፡

ከእነዚህ መንገዶች ውስጥ ከፍተኛ ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰት እንዲያቀርቡ ተቋራጮች ከተጠየቁባቸው አንዱ የአዘዞ ጎንደር የመንገድ ግንባታ ነው፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት የሚወዳደሩ የአገር ውስጥ ተጫራቾች ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በአማካይ 355 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰት ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የውጭ ተቋራጮች ከሆኑ 888 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ለዚሁ ፕሮጀክት በጥምረት ለሚቀርቡ ተጫራቾች የተቀመጠው ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰት መጠን 66 ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በቅርቡ እንዳስታወቀው፣ በ2009 ዓ.ም. ብቻ 18 ፕሮጀክቶችን እንዲገነቡለት በጨረታ ላሸነፉ ኩባንያዎች ሰጥቷል፡፡ አጠቃላይ የፕሮጀክት ዋጋቸው 13.7 ቢሊዮን ብር እንደሚገመትም ይጠበቃል፡፡

በአሁኑ ወቅት 29 ፕሮጀክቶች በጨረታና በግምገማ ሒደት ላይ ሲሆኑ፣ አሸናፊ ከሆኑ ተጫራቾች ጋር ስምምነት እንደሚፈረም ይጠበቃል፡፡ ከዚህም ባሻገር ባለሥልጣኑ የ97 የመንገድ ፕሮጀክቶችን የአዋጭነት፣ የዲዛይንና የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ እያካሄደ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles