በአገሪቱ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የግል ባንኮች ይልቅ ምክትል ፕሬዚዳንት ሳይኖረው የዘለቀው ደቡብ ግሎባል ባንክ፣ የመጀመሪያውን ምክትል ፕሬዚዳንት ለመሾም በእጩነት ያቀረባቸውን ባለሙያ ተቀብሎ እንዲያፀድቅለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ቀረበ፡፡
የደቡብ ግሎባል ባንክ ቦርድ ለባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ያጫቸው የባንክ ባለሙያ፣ በአሁኑ ወቅት በዘመን ባንክ የዕውቀትና የምርምር ግኝት (ኢኖቬሽን) ሥራ ክፍል ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉ የሚገኙትን አቶ ተስፋዬ ቦሩን ነው፡፡
ላለፉት 13 ዓመታት በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ተስፋዬ፣ የደቡብ ግሎባል ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ የቀረበላቸውን ጥያቄ ተቀብለዋል፡፡
በዚሁ መሠረት የደቡብ ግሎባል ባንክ የመጀመሪያው ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ዕጩ አድርጎ ያቀረባቸውን የአቶ ተስፋዬን የሥራ ልምድ ማስረጃ ያጠናከረ ሰነድ ለብሔራዊ ባንክ አቅርቦ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ከባንኩ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
አቶ ተስፋዬ በፋይናንስ ኢንዲስትሪው ውስጥ በብሔራዊ ባንክ፣ በአቢሲኒያ ባንክ እንዲሁም በሕብረት ባንክ ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት መደቦች ውስጥ ማገልገላቸው ተገልጿል፡፡ በኢኮኖሚክስና በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሦስት ዲግሪዎች እንዳሏቸው የተጠሰቀ ሲሆን፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸው ለመቀበል መቃረባቸውም ታውቋል፡፡ ይህ ሹመት በብሔራዊ ባንክ ከፀደቀላቸው፣ አቶ ተስፋዬ ወጣቱ ምክትል የባንክ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አቶ ተስፋዬ 35ኛ ዓመታቸው ላይ እንደሚገኙ የግል ማኅደራቸው ይናገራል፡፡ በደቡብ ግሎባል ባንክ የምክትል ፕሬዚዳንቱ ቦታ ሲፀድቅላቸው የባንኩን የኦፕሬሽን ዘርፍ ይመራሉ ተብሏል፡፡
ደቡብ ግሎባል ባንክ ቆየት ብለው የባንክ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀሉት ሦስት ባንኮች አንዱ ነው፡፡ ከሰባት ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉት ይህ ባንክ፣ በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከታክስ በፊት 68 ሚሊዮን ብር ማትረፉን መግለጹ ይታወሳል፡፡
