የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስቀምጦ በነበረው የጉዞ ገደብ ምክንያት ከ100,000 በላይ የውጭ ጐብኚዎች መቅረታቸው ታወቀ፡፡ ካቻምና ለጉብኝት ወደ አገሪቱ የመጡ ቱሪስቶች ቁጥር 900,000 የነበረ ሲሆን፣ በዚያው ጊዜ ውስጥ ከቱሪዝም ዘርፍ የተገኘው ገቢም 3.5 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡
ይሁንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተደነገገበት ወቅት፣ ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ አገሮች የጉዞ እገዳና ማስጠንቀቂያ ሲያወጡ ቆይተዋል፡፡ አንዳንዶቹም እስካሁን ድረስ የእገዳ ማስጠንቀቂያቸውን አላነሱም፡፡ ይህ በመሆኑ ምክንያት እ.ኤ.አ. በ2016 ወደ አገሪቱ የመጡ ጐብኚዎች ቁጥር ወደ 800,000 ዝቅ ሊል መቻሉ በጥናት ታውቋል፡፡ በአንፃሩ በወቅቱ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 128 ቢሊዮን ብር ወይም 5.6 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን፣ በኢንተርኔት ለእንግዶች የሆቴል ክፍሎችን በማስያዝ ሥራ ላይ የሚሠራው ጁሚያ ትራቭል ሐሙስ የካቲት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው ሪፖርት አመልክቷል፡፡
በበተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መዝገብ ውስጥ ከአሥር በላይ የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከቱሪዝም ዘርፍ ማግኘትና መጠቀም የሚገባትን ያህል ሳትጠቀም መቆየቷ ይታወቃል፡፡ ካሏት የቅርጾች ብዛትና የመልክዓ ምድር አቀማመጥና የተፈጥሮ መስህቦች አኳያ እጅጉን ዝቅተኛውን የቱሪስት ቁጥርና የቱሪዝም ገቢ በማግኘት ላይ ነች፡፡
ለዚህም በአገሪቱ ያለው የመስተንግዶ ኢንዱስትሪ ደካማነት በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ በቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ አለመሟላት፣ የአገሪቱ የቱሪዝም ሀብቶች እንደሚገባቸው አለመተዋወቃቸው፣ የአገር ውስጥ ጐብኚዎች የጉብኝት ልማድ ዝቅተኛ መሆንና ሌሎችም ዘርፉ የሚጠበቅበትን ያህል እንዳያስገኝ ካደረጉት መካከል ሊጠቀሱ የሚችሉ ችግሮች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል በአገሪቱ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች እንደሚፈለገው መጠን አለመኖራቸውም እንደ ችግር ይጠቀሳል፡፡ ይሁንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸው እየታየ ነው፡፡ በሪፖርቱ መሠረት 84.4 በመቶ ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢ ለመዝናናት ብለው ወደ አገሪቱ ከሚገቡ ጐብኚዎች የሚገኝ ነው፡፡ እነዚህ ጐብኚዎች እንደፍላጎታቸው ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ባሟሉ ብራንድ ሆቴሎች ለመዝናናት ፍላጎት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ ያሉት ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ብዛት በተለይም በክልል ከተሞች የሚገኙት በቁጥር ውስን በመሆናቸው ሳቢያ ጐብኚዎች ደጋግመው እንዲመጡ የማይጋብዝ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የመስተንግዶ ኢንዱስትሪው መሻሻሎችን እያሳየ በመምጣቱ ምክንያት ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢም በዚያው መጠን እየጨመረ ይገኛል፡፡ የካቻምና አኃዞች እንደሚያሳዩት፣ የጉዞና የጉብኝት ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) የ4.1 በመቶ ድርሻ እንደነበረው ነው፡፡ ይህ ኢኮኖሚያዊ ድርሻ እ.ኤ.አ. በ2026 ወደ አምስት በመቶ ከፍ እንዲል በማቀድ መንግሥት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥም ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ወደ 675 ቢሊዮን ብር ወይም ወደ 29.8 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ዕቅድ ተይዟል፡፡ ዘርፉ እስካሁን 2,326,500 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ይነገርለታል፡፡ ይህ በመሆኑም በኢኮኖሚው ውስጥ የ8.4 በመቶ የቅጥር ድርሻ እንደሚይዝ የሚያሳይ ነው፡፡
አገሪቱን ከአምስት ቀዳሚ የአፍሪካ የቱሪስት መዳረሻ አገሮች አንዷ ለማድረግ ያላትን እምቅ አቅም ከማስተዋወቅ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን በዕለቱ የተገኙት የቱሪዝም ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ታደሰ ገልጸዋል፡፡
ወደ አገሪቱ የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር ከፍ እንዲልም ከፍተኛ የማስተዋወቅ ሥራ ይጠበቃል፡፡ 31 በመቶ የሚሆኑት ጐብኚዎች ከተለያዩ የአፍሪካ አገር ሲመጡ፣ 30 በመቶ አውሮፓውያንና ሰሜን አሜሪካውያን ናቸው፡፡ ከውጭ አገር ጐብኚዎች የሚገኘው ገቢ 68.7 በመቶ ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ ጐብኚዎች የሚገኘው ደግሞ 31.3 በመቶ ደርሷል፡፡ 39 በመቶ የሚሆኑት ጐብኚዎች አዲስ አበባ ውስጥ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፣ 11 በመቶ ደግሞ በሐዋሳ፣ 8.1 በመቶ የሚሆኑት ቢሾፍቱን ይመርጣሉ፣ 7.5 በመቶዎቹ ደግሞ ባህር ዳርን የሚያዘወትሩ መሆናቸውን በሪፖርቱ ተዘርዝሯል፡፡
‹‹አገሪቱ በቱሪዝም ሴክተር ያልተነካ አቅም አላት፡፡ የመስተንግዶ ኢንዱስትሪውም ቢሆን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ይገኛል፤›› ያሉት የጁሚያ ትራቭል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፓውል ሜዲ፣ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ለማግኘት የተለያዩ ፈታኝ ነገሮች ቢኖሩም ትልቅ ተስፋ መኖሩን ተናግረዋል፡፡
በኦንላይን ሆቴል ቡኪንግ ላይ የሚሠራው ጁሚያ ትራቭል ኢትዮጵያ መጥቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ዓመት አልፎታል፡፡ በመላው አገሪቱ ከሚገኙ 600 ሆቴሎች ጋር አብሮ በመሥራት ላይም ይገኛል፡፡
የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ት ኤደን ሳህሌ እንደገለጸችው፣ ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ እንዳይሠራ አንዳንድ ችግሮች ማነቆ እየሆኑበት ይገኛሉ፡፡ ዋናው ችግር የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ ሲሆን፣ በተለይ በክልል ከተሞች ከሚገኙ ሆቴሎች ጋር አብረው ከመሥራት እያገዳቸው ይገኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ከደንበኞቻቸው ጋር በድረ ገጻቸው መገናኘት ስለማይችሉ በስልክ ለመሥራት ይገደዳሉ፡፡ ከዚህ ባሻገርም ኅብረተሰቡ ስለኦንላይን ሆቴል ቡኪንግ አገልግሎት ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ የአገር ውስጥ ጐብኚዎችን በሚፈለገው መጠን ለማግኘት እንዲቸገሩ አስገድዶናል ብላለች፡፡
