Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all 720 articles
Browse latest View live

ወጣት ባለሙያዎች ሕፃናት የኮምፒዩተር ቀማሪዎችን ለማፍራት የሚያግዝ አካዴሚ መሠረቱ

$
0
0

- የሮቦቶች እግር ኳስ ግጥሚያ አሰናድተዋል

ሕፃናትን በኮምፒዩተር ቀመርና በሶፍትዌር ፕሮግራም ፈጣሪነት እንዲያድጉ ያስችላል ያሉትን የኮምፒዩተር ፕሮግራም መቀመሪያ አካዴሚ መመሥረታቸውን ሁለት ወጣቶች ይፋ አድርገዋል፡፡

ቤተልሔም ደሴና ጌትነት አሰፋ የተጣመሩበት አካዴሚ ሕፃናትን ከለጋነታቸው ጀምሮ በኮምፒዩተር ሶፍትዌር ፈጣሪነትና በፕሮግራም ነዳፊነት ለመግራት የሚያስቸለውን አካዴሚ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ወደ ሥራ ማስገባታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሁለቱ ወጣቶች በ251 ኮሙዩኒኬሽንስ ኩባንያ ድጋፍ ባዘጋጁት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እንዳብራሩት፣ ከስድስት ዓመት እስከ 13 ዓመት የዕድሜ ክልል ላይ ለሚገኙ ሕፃናትና ታዳጊዎች ቅድሚያ በመስጠት ሥልጠና መስጠት ይጀምራሉ፡፡ በዚህ የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ልጆች በአብዛኛው በቀላሉ ውስብስብ ነገሮችን የመፍታት፣ የመፍጠርና ረቂቅ ነገሮችን ቶሎ የመረዳት ችሎታ ስለሚኖራቸው በዚህ መነሻነት ቅድሚያውን ለልጆች መስጠታቸውን ቤተልሔምና ጌትነት አብራርተዋል፡፡ ይሁንና ሥልጠናውን ወደ ፊት ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ለአዋቂዎች ለማስፋፋት እንደሚችሉም ጠቅሰዋል፡፡

ከአሥር ዓመቷ ጀምሮ የኮምፒዩተር ቀመር ማዘጋጀት እንደጀመረች የገለጸችው ቤተልሔም በአሁኑ ወቅት የ17 ዓመት ወጣት ስትሆን፣ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የሶፍትዌር ማዘጋጀትና ኮድ የማድረግ ወይም ቀመር የመፍጠር ሥራ ስትሠራ መቆየቷን ገልጻለች፡፡ በአሥር ዓመቷ በምትኖርበት ሐረር ከተማ የአባቷን ኮምፒዩተር በመነካካት የጀመረችው የኮዲንግ ሥራ ቀስ በቀስ ተሸላሚ የሆነችበትን ፈጠራ እንድታዘጋጅ አስችሏታል፡፡ እንደ ብሔራዊ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ለተወሰነ ጊዜ ተቀላቅላ እንዳገለገለች የጠቀሰችው ቤተልሔም፣ በለጋ ዕድሜያቸው ዕድሉን እንዲያገኙ ቢመቻችላቸው በርካታ ሕፃናት ብዙ መፍጠር የሚያስችላቸው የፈጠራ ሐሳብ ሊያመነጩ እንደሚችሉ ትናገራለች፡፡

በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝኛው አጠራሩ ‹‹ኤቭሪዋን ካን ኮድ›› የተባለውን ተቋም መሥርታ በፕሮጀክት ማናጀርነት እየመራች ትገኛለች፡፡ ከዚህም ባሻገር የአሜሪካ ኤምባሲ 100 ልጃገረዶችን በሶፍትዌር ፕሮግራም መስክ ለማሠልጠን በሚሰጠው ድጋፍ ውስጥ እየተሳተፈች ትገኛለች፡፡

እንደ ቤተልሔም ሁሉ ጌትነትም በኮምፒዩተር ሙያ ብዙ ዕውቀት አካብቷል፡፡ በኮምፒዩተር ምህንድስና ዲግሪውን ሠርቷል፡፡ ከዚህም በላይ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ከተማ፣ ሲልከን ቫሊ እየተባለ በሚጠራው ግዙፍ የአይሲቲ መንደር ለስድስት ወራት የቆየ ሥልጠና ተከታትሏል፡፡

 በዚህ ቆይታው ወቅት ትልቅ ጠቀሜታ ያተረፉለትን ግንኙነቶች በመፍጠር እንደተመሰ የገለጸው ጌትነት፣ ኣይኮግ ላብስ የተባለውንና በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ዘርፍ ማለትም እንደ ሮቦት ያሉ ልዩ ልዩ ማሽኖችን ለማንቀሳቀስ የሚያስችሉ ሶፍትዌሮችን ለመፍጠር የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን የሚያዘጋጅ ተቋም ከመሠረተ ሦስት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ሦስት ሆነው የመሠረቱት አይኮግ ላብስ፣ በ50 ሺሕ ዶላር ካፒታል የተመሠረተ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ፣ በጀርመን፣ በቻይና እንዲሁም በሆንግ ኮንግ የሚገኙ ደንበኞችን አፍርቷል፡፡

አይኮግ ላብስ በልዩ ልዩ መስኮች ላይ ምርምር በማድረግ ለአፍርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ የሚውሉ ሶፍትዌሮችን ከማዘጋጀትና ምርምር ከማድረግ ባሻገር ለዩኒቨርሲቲና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እንደ ማኅበረሰብ አገዝ ያለ ሥልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ወጣት ጌትነት ገልጿል፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል በሮቦቶች አማካይነት የሚካሄድ የእግር ኳስ ውድድር ለማዘጋጀት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውቆ፣ በተለይም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ሮቦቶችን ለመግዛት የሚያስችል ድጋፍ በማድረጋቸው ውድድሩ በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል እንደሚደረግም አስታውቋል፡፡ እስካሁን በፊፋ ዕውቅና የተሰጠውና አሥር ዓመታት ያስቆጠረ የሮቦቶች የእግር ኳስ ውድድር ሲካሄድ መቆየቱን የጠቀሰው ጌትነት፣ በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታሰበው ውድድር ግን በአፍሪካም የመጀመሪያው እንደሚሆን አስታውቋል፡፡

በርካታ ወጣቶች በአይሲቲ መስክ ልዩ ልዩ ፈጠራዎችን እያሳዩ ቢሆኑም፣ ተገቢውን ድጋፍ ማግኘት እንዳልቻሉ ግን እየታየ ነው፡፡ በአገር ውስጥ የሞባይል ስልኮችን ለሚገጣጥሙ ኩባንያዎች አፕሊኬሽኖችን የፈጠሩ፣ የስልክ መስመር በነፃ የአየር ሞገድ ተጠቅመው መፍጠር የቻሉ ወጣቶች ብቅ ቢሉም ተገቢው ዕገዛ ቢደረግላቸው ግን ከእነዚህም የላቁ ሌሎች በርካታ ፈጣሪዎችን ማፍራት እንደሚቻል የኢትዮጵያ አይሲቲ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሥዩም በረደድ ጠቅሰዋል፡፡ በአፍሪካ በየዓመቱ በሚካሄዱ የአይሲቲ ፈጠራ ሥራዎች ላይ በተደጋጋሚ አሸናፊ በመሆን የሚጠቀሱት የኬንያና የናይጄሪያ ወጣቶች እንደሆኑ አቶ ሥዩም ገልጸው፣ በእነዚህ አገሮች ለወጣቶች የሚደረጉ ድጋፎች በኢትዮጵያም ቢደረጉ ፈጣሪ ጭንቅላቶችን እንደልብ ማፍራት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

የ251 ኮሙዩኒኬሽንስ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አዲስ አለማየሁ በበኩላቸው በአይሲቲ መስክ ለሚሰማሩ ወጣቶች መንግሥት የሚሰጠውን ድጋፍ ማስፋፋት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡ በተለይም በቅርቡ መንግሥት ካፀደቀው የአሥር ቢሊዮን ብር የወጣቶች ፈንድ ውስጥ ምን ያህሉ ለአይሲቲ ዘርፍ እንደሚውል መንግሥት ይፋ ማድረግ እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የአይሲቲ ፓርክ የሚባለውን የፈጠራና የፋብሪካዎች መንደር የገነባው የመገናኛና ኢንፎሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ በአይሲቲ ፈጠራ መስክ ለሚሠሩ ወጣቶች በፓርኩ በነፃ የመሥሪያ ቦታ ከማመቻቸት ጀምሮ፣ የምርምር ሥራዎችን፣ ሶፍትዌርና ሌሎችም አፕሊኬሽኖችን ለሚያዘጋጁ ወጣቶች ድጋፍ እንደሚሰጥ ይፋ ካደረገ ሰነባብቷል፡፡ ይሁንና በርካታ ወጣቶች ግን ከዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ይታያል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለፈጠራ ሥራቸው የሚያውሏቸው ልዩ ልዩ መገልገያዎችን ከውጭ የሚያመጡ ጀማሪ ወጣቶች የሚመሯቸው አነስተኛ ኩባንያዎች በቀረጥና በሌሎች ጫናዎች መቸገራቸውም ሲገለጽ ይደመጣል፡፡   

እንዲህ ባሉ ችግሮች ውስጥ እንዳለፉ የገለጸው ወጣት ጌትነት፣ የእሱ መሰል ወጣቶች ዕድሉን እንዲያገኙ ለማገዝ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን እንዳዘጋጀ ይጠቅሳል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የሚደረገው ውድድር አምስት ዩኒቨርሲቲዎችን በቅርቡ በማሳተፍ የሮቦት ውድድሩን በቋሚነት እንደሚካሄድ ጠቅሷል፡፡ ከ36ቱ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ከ20 የበለጡት ከአይኮግ ላብስ ጋር ስምምነት መፈረማቸውን ያስታወሰው ጌትነት፣ ወደ ውጭ ከመሸጥ ባሻገር በአገር ውስጥ የሶፍትዌር ምርቶችን ለማቅረብም ሆነ ኢንቨስትሮችን በማግኘት ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለማውጣት ሐሳብ እንዳለው ተናግሯል፡፡

 

 

Standard (Image)

የቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ ወደ ግል ከተዛወረ በኋላ

$
0
0

ወደ ግል ከተዛወሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነውና ፀሐይ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር የገዛው ቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ ቀድሞም በመንግሥት ሲተዳደር በነበረ ጊዜ በአትራፊነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ የፋብሪካው ባለንብረትነት መብት ወደ ግል ከተዛወረ በኋላም ይበልጥ አትራፊ ሆኖ መዝለቁን የፀሐይ ኢንዱስትሪ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡

ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ በጨረታዎችና በድርድር ሒደት ወደ ግል ይዞታ ከተላለፉ በመቶዎች ከሚቆጠሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል ፀሐይ ኢንዱዲስትሪ፣ ቃሊቲ ብረታ ብረትን ሲገዛው የራሱን አሻራ ያሳረፈበት ክስተት የፈጸመበት መሆኑም የሚጠቀስ ነው፡፡

ፋብሪካው ከ550 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ዋጋ ወደ ግል ይዞታነት ሲተላለፍ፣ የአክሲዮን ማኅበሩ ባለቤቶች ለቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ ሠራተኞች የሰጡት ዕድል በሌሎች ያልተሞከረ ተግባር እንደሆነም ይነገራል፡፡ ይኸውም የፋብሪካው ሠራተኞች እንደአቅማቸው በድርጅቱ የአክሲዮን ባለድርሻ እንዲሆኑ የተመቻቸው ዕድል ሲሆን፣ ይህ ክስተት በፕራይቬታይዜሽን ሒደት ያልተለመደ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ለሠራተኞች ክፍት የተደረገውን የአክሲዮን ድርሻ በግል መግዛት የቻሉ እንዳቅማቸው መጠን እንዲገዙና ባለድርሻ እንዲሆኑ ከመደረጉ ባሻገር ይህንን ማድረግ ላልቻሉትም ሁሉንም የፋብሪካውን ሠራተኞች አባል በሚያደርገው በብድርና ቁጠባ ማኅበር በኩል አክሲዮን በመግዛት ሠራተኞቹ ባለድርሻ የሆኑበትን ዕድል ፈጥሯል፡፡ የአክሲዮን ኩባንያው የቦርድ ኃላፊዎች እንደሚገልጹት፣ በወቅቱ ይህንን ያደረጉበት ዋነኛ ምክንያት ሠራተኛው የእኔነት ስሜት ተሰምቶት በባለቤትነት ተግቶ እንዲሠራ፣ ከሥራውም ተጠቃሚ እንዲሆን በማሰብ ነው፡፡

ይህ ከተደረገ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ድርጅቱ ወደ ግል ከተዛወረ በኋላም በአትራፊነት መቀጠል መቻሉ ብቻም ሳይሆን አወቃቀሩን ለውጧል፡፡ የፋብሪካው የሥራ አድማስ እየሰፋ በመምጣቱ፣ ከአራት ዓመታት በፊት ሲያስመዘግብ የነበረው ዓመታዊ ሽያጭም በአሁኑ ወቅት ከእጥፍ በላይ ለማድረስ አስችሎታል፡፡

የፋብሪካው ዓመታዊ የሽያጭና የትርፍ መጠን ይበልጥ እያደገ ስለመምጣቱ የተገለጸው፣ ቅዳሜ ጥር 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው የድርጅቱ ዓመታዊ የሠራተኞች በዓል ወቅት ነበር፡፡ የፀሐይ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ማቴዎስ አሰሌ እንደገለጹት፣ በ2008 በጀት ዓመት 31,399 ቶን ልዩ ልዩ የብረታ ብረት ውጤቶችን ለማምረት አቅዶ 23,799 ቶን ማምረት ችሏል፡፡ ይህም የዕቅዱን 77 በመቶ ማከናወን እንደቻለ የሚያሳይ ነው፡፡ ዓምና የተመረተው ምርት በ2007 ዓ.ም. ከተመረተው ጋር በንፅፅር ሲታይ፣ የ24 በመቶ ወይም ከ4,611 ቶን በላይ ብልጫ እንዳሳየ ተመልክቷል፡፡ በዚሁ ጊዜ ውስጥ 573 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ያከናወነ ሲሆን፣ ከ2007 ዓ.ም. ከነበረው የሽያጭ መጠን ጋር ሲነጻጸርም የ18 በመቶ ብልጫ እንዳለው አቶ ማቴዎስ ጠቅሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ አፈጻጸም በበጀት ዓመቱ ሊመረት ከታቀደውና ከሽያጭ ይገኛል ተብሎ ካቀደው ገቢ ያነሰ ነው፡፡ እንደ ፋብሪካው ውጥን ቢሆን ኑሮ በበጀት ዓመቱ ለማምረት ካቀደው 31,399 ቶን ውስጥ የሽያጭ ገቢው 850 ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ ይጠበቅ ነበር፡፡

የዕቅዱን ያህል ባሆንም እንኳ በአሁን ወቅት የሚታየው የፋብሪካው አፈጻጸም በፋብሪካው ታሪክ ከፍተኛውና ከምንጊዜውም ይልቅ ብልጫ እንደያዘ አቶ ማቴዎስ ገልጸዋል፡፡ በዕቅዱና በክንውኑ መካከል የተፈጠረው ክፍተት የተከሰተው ወሳኝ በሆኑ ምክንያቶች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ክንውኑ የዕቅዱን ያህል ላለመሆኑ አሳማኝ ምክንያቶች ናቸው ብለው አቶ ማቴዎስ ከጠቀሷቸው ውስጥ ቀዳሚው የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ነው፡፡ ፋብሪካው በውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ሳቢያ ለአሥር ወራት መደበኛ የቤት ቆርቆሮ ማምረት አለመቻሉን በአስረጅነት አቅርበዋል፡፡

በዓመታዊው የሠራተኞች በዓል ላይ የተገኙት የአክሲዮን ማኅበሩ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ፈንቴ ባለፉት ዓመታት ፋብሪካው ዕድገት እያሳየ ቢመጣም፣ ዕድገቱ በቂ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡ የፋብሪካውን ማኅበረሰብ የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሁኔታዎች መበራከትና መመቻቸት አለባቸው በማለት አክለዋል፡፡ በዚህ ረገድ የፋብሪካውን አቅም ለማሻሻል ይቻል ዘንድ የተሻለ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እንዲኖር ጥረት የተደረገ ቢሆንም፣ ከውጭ የሚገቡት ጥሬ ዕቃዎችን በውጭ ምንዛሪ ዕጥረት የተፈለገውን ያህል ማግኘት አለመቻል ለፋብሪካው እንቅስቃሴ ፈታኝ ችግር ሆኖ እንደቆየም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ሆኖም የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ቀስ በቀስ እየተቀረፈ እንደሚመጣና መንግሥትም ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ቅድሚያ እንደሚሰጥ በማስታወቁ፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦቱ ይሻሻል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ማቴዎስ ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካው ከሚታወቅባቸው ምርቶች አንዱ የሆነው የቤት ክዳን ቆርቆሮ ለማምረት የሚያስችለውን ጥሬ ዕቃ በውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ምክንያት እንደልብ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ያለመቻሉ ከፈጠረበት ችግር ባሻገር፣ ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ እንዳያሳካ ያደረገው ሌላው ምክንያት በበጀት ዓመቱ ይጀመራሉ የተባሉ አዳዲስ ምርቶችን ለማምረት የሚያስችሉ መሣሪያዎችን ለማስገባትና ለማምረት አለመቻሉ ነው፡፡

ምርት ይጀምራሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩት ባለቀለምና ባለጌጥ የጣሪያ ልባስ እንዲሁም የፈርኒቸር ቱቦ ማምረቻ መሣሪያዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህን ምርቶች ለማምረት የሚያስችሉትን መሣሪያዎች የሚያቀርብ ባለመገኘቱ መሣሪያዎቹ ሊገዙ አልቻሉም፡፡ በዚህ ምክንያትም ፋብሪካው ዓምና በያዘው ዕቅድ መሠረት ምርቶቹን በፈለገው መጠን ማምረት ሳይችል ቀርቷል፡፡ ይህም በዓመታዊ የምርትና የሽያጭ ዕቅዱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮበታል ተብሏል፡፡ በገበያው ውስጥ ተፈላጊነት ያላቸው ምርቶች በጥሬ ዕቃ ዕጥረትና በማምረቻ መሣሪያዎች ጉድለት ምክንያት ፋብሪካው የበለጠ ዕድገት ለማስመዝገብ የተነሳበት ዕቅድ ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠርበት ማድረጋቸው ተብራርቷል፡፡

አቶ ማቴዎስ እንደገለጹት፣ እንዲህ ያሉ ችግሮች ባያጋጥሙ ኑሮ የፋብሪካውን አፈጻጸም በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል ይቻል ነበር፡፡ በ2009 በጀት ዓመት ግን የተለያዩ ዕርምጃዎችን በመውሰድ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉን ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡ በተለይ ከሥራ ውጭ የነበሩ መሣሪያዎች በፈጠራ  ተሻሽለው እንዲሠሩ በማድረግና በማንቀሳቀስ አዳዲስ ምርቶችን ለማምረት አስችለውታል፡፡ እንዲህ ያሉት ተግባራት ተደማምረው በ2009 የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ወቅት፣ የምርት አፈጻጸሙ ወደ 86 በመቶ እንዲደርስ አስችለውታል፡፡ በግማሽ ዓመቱ አክሲን ማኅበሩ አገኘዋለሁ ብሎ ካቀደው የሽያጭ ገቢ 76 በመቶ ማከናወን መቻሉን አቶ ማቴዎስ ጠቅሰዋል፡፡ ለሠራተኞችም የሁለት ወራት የደመወዝ ቦነስና የአንድ ዕርከን ዕድገት እንዳደረገ አስታውቀዋል፡፡ ፋብሪካው ወደ ፀሐይ ኢንዱስትሪ ከተሸጋገረ በኋላ የተለያዩ አዳዲስ ምርቶችን ያካተተ ሲሆን፣ በተለይ የከባድ ተሽከርካሪ አካላትና ተሳቢዎችን ማምረት መጀመሩ አንዱ ነው፡፡

በ2009 በጀት ዓመት ባለቀለም የጣሪያ ልባሶችን ማምረት እንደሚጀምርና ለዚህ የሚሆነውን የማሽነሪ ግዥ ፈጽሞ መሣሪያው ወደብ መድረሱ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የብረት መዋቅር ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችለውን ጥናት እንዳጠናቀቀም ተገልጿል፡፡

የብረት መዋቅር ማምረቻ ፋብሪካው የሚያመርታቸው ምርቶች በብረት መዋቅር አማካይነት የሚሠሩ ትላልቅ ግንባታዎች የሚከናወኑባቸው ሲሆን፣ ይህንን ማምረቻ በደብረ ብርሃን ከተማ ለመትከል የቦታ ጥያቄ መቅረቡም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፋብሪካው በመደበኛነት ከሚያመርታቸው ምርቶች በተጨማሪ የጭነት ተሳቢ ተሽከርካሪ አካላትን የማምረት ሒደቱን የሚያሳድጉ ተጨማሪ ሦስት የማምረቻ ሕንፃዎች ግንባታን እያካሄደ ሲሆን፣ የፈሳሽ ጭነት ተሳቢ አካላትን ማምረትም በበጀት ዓመቱ ለመጀመር እንዳቀደ ከኩባንያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

Standard (Image)

ብርሃንና ሰላም 600 ሚሊዮን ብር የወጣባቸውን ፕሮጀክቶች ለሥራ ዝግጁ አደረገ

$
0
0

አንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ደርጅት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የወጣበቸውን ሦስት ፕሮጀክቶች ቅዳሜ ጥር 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሥራ ማብቃቱን ይፋ አረገ፡፡

ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት በዕለቱ ተገኝተው ፕሮጀክቱን መርቀዋል፡፡ የ95ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በዕለቱ ያከበረው ማተሚያ ደርጅት ለኅትመት ቴክኖሎጂ አካዴሚው ያስገነባቸውን ባለ ሰባት ፎቅ ሕንፃን ጨምሮ በሚስጥራዊ ኅትመት ዘርፍ በአገራችን ቀዳሚ ያደረገውን የቼክ ፐርስናላይዜሽን ፕሮጀክት እንዲሁም ቀደም ብሎ ያስተከለውን ባለስምንት ዩኒት የኅትመት ማሽን አስመርቋል፡፡

በዕለቱ ፕሮጀክቶቹን የመረቁት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ‹‹ድርጅቱ እያደገ የመጣውን  የደንበኞቹን ፍላጎት በማሟላት ለኅትመት ቴክኖሎጂ አካዴሚው ቅድሚያ በመስጠት ኢንዱስትሪውን ማስፋት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በተጨማሪም የደንበኞቹን ፍላጎት በበለጠ ለማርካት በዘርፉ ተወዳዳሪ በመሆን መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ አገሪቱ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር የሚጓዝና ጥራት ያለው ኅትመት የሚሰጥ ማተሚያ ቤትም ሆነ ባለሙያ ክፍተትን ለመሸፈንና እንዲሁም ዓለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ ለመድረስ መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የኅትመት ቴክኖሎጂ አካዴሚ የድርጅቱን የሰው ኃይል ችግር ከማቃለሉ ባሻገር፣ ለአገራችን ኅትመት ኢንዱስትሪ አልፎም ተርፎ ለምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የሥልጠና ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተካ አባዲ አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ተካ ገለጻ፣ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰበት የቼክ ፐርሰናላይዜሽን ፕሮጀክት የውጭ ምንዛሪ ወጪ ለማስቀረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የተመሠረተበትን 95ኛ ዓመት ባከበረበት ወቅት ለረዥም ዘመን ደንበኞቹና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሠራተኞች ሽልማት አበርክቷል፡፡

ወደ 1,000 የሚሆኑ ሠራተኞች ያሉት ማተሚያ ቤቱ፣ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና መስክ ከደረጃ አንድ እስከ ሦስት ባለው እርከን የኅትመት ቴክኖሎጂ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ እስካሁንም 125 ሠልጣኞችን ያስመረቀ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም 80 ሠልጣኞችን ተቀብሎ እያሠለጠነ ይገኛል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ድርጅታቸውን በቅርቡ በኅትመት አገልግሎት ዋጋ ላይ ቅናሽ ማድረጉን ጠቁመው፣ በተለይ በጋዜጣና በሌሎችም የኅትመት አገልግሎቶች ላይ በየደረጃው ተመሳሳይ ቅናሽ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

አቶ ተካ ጨምረው ባለፈው ቅዳሜ የተመረቀው የቼክ ፐርሰናላይዜሸን ፕሮጀክት የግዙፉ የሚስጢራዊ ኅትመት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ንዑስ ዘርፍ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይኽም ፕሮጀክት በአገር ውስጥ የሚገኙት 19ኙም ባንኮችን ተግባራዊ የተደረገውን አዲሱን ቼክ ፐርሰናላይዝ የማድረግ ሥራ እንደሚያከናውን አስረድተዋል፡፡ ይኽም ሥራ ሙሉ ለሙሉ ኮምፒውተራይዝድ በሆነ ዲጂታል ኅትመት ቴክኖሎጂ የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሥራውንም ሙሉ ለሙሉ ለመጀመር የብሔራዊ ባንክን እየጠበቁ መሆኑን አቶ ተካ ገልጸዋል፡፡ የመጀመርያው ወጥ ቼክ ኅትመትና ፐርሰናላይዜሽን ከአገር ውጭ እንደተሠራ ጠቁመው፣ በዚህኛው ንዑስ ፕሮጀክት የፐርሰናላይዜሽን ሥራውን ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ መሥራት ያስችላል ብለዋል፡፡

 

 

Standard (Image)

ሦስት አሥርታትን የዘለቁ የኢንቨስትመንት ፋናዎች

$
0
0

ስለኩባንያዎቻቸው እንቅስቃሴ እንጂ ኩባንያቹን በባለቤትነት ስለመምራታቸው ብዙም ሲናገሩ ከማይደመጡ ባለሀብቶች መካከል አቶ ብዙአየሁ ታደለ አንዱ ሆነው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ከ35 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ የተለያዩ የንግድ ሥራ ዘርፎችን በመፍጠር እየሠሩ የሚገኙት አቶ ብዙአየሁ፣ ከእሳቸውና ካሏቸው ድርጅቶች ብዛት ይልቅ የፈጠሯቸው ኩባንያዎች ማንነት ጎልተው ሲነገርላቸው ቆይተዋል፡፡ አቶ ብዙአየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከእሳቸው ስምና ማምነት የተሻለ ቢታወቅ ውጤት ሊኖረው የሚችለው ቢዝነሱ በመሆኑ፣ ስለራሳቸው ከመግለጽ መቆጠብን ይመርጣሉ፡፡

የጎልማሳ ዕድሜ ያስቆጠረው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴያቸው በጋራም በተናጠልም ከ30 በላይ ኩባንያዎችን እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል፡፡ ይህን ያህል ኩባንያ የፈጠሩት እኝህ ሰው፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብም ኢንቨስት አድርገዋል፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ባገኙት ውርስ የቢዝነሱን ዓለም የተቀላቀሉት አቶ ብዙአየሁ፣ የመጀመርያ ሥራቸው ወላጆቻው ይታወቁበት የነበረውን አነስተኛ የቡና ንግድ  ሥራ  በመጀመር ነበር፡፡ ከ35 ዓመታት በፊት ወደ ቡና ንግድ ሲገቡ ሦስት ሠራተኞችን ይዘው ሲሆን፣ ዛሬ ላይ የፈጠሯቸው በርካታ ኩባንያዎች ከ6,000 በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል አስገኝተዋል፡፡ ለዓመታት ስለገነቡት የቢዝነስ መጠንና ትልቅነት ይህ ነው በሚባል ደረጃ ሲገልጹ አልታዩም፡፡

 

ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በተሰናዳ ፕሮግራም ወቅት ግን  የአቶ ብዙአየሁ ሥራዎችንና ማንነት ለማወቅ የሚያስችል አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ ስለማንነታቸው ብዙ ያልተነገረላቸው እኚህ ባለሀብት፣ ብዙ ሊባልላቸው ያበቃቸው መድረክ የተፈጠረው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ውስጥ ላበረከቱት አስተዋጽኦ፣ ከአሜሪካው ሊንከን ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ያገኙበት አጋጣሚ ነው፡፡ ሊንከን ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ከዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ጋር አብሮ በመሥራት ላይ የሚገኝ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ለአገር ልማትና ዕድገት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ዜጎች ዕውቅና ለመስጠት በራሱ ተነሳሽነት ሰዎችን መልምሎ በሚያደርጋቸው ግምገማዎች አማካይነት አቶ ብዙአየሁ ታደለ አንዱ በመሆን የዓመቱ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እንዲያገኙ የመረጣቸው መሆኑን፣ የሊንከን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርና ባላደራ ቦርድ አባል ዶ/ር ጂን ሲብል ይፋ አድርገዋል፡፡

የክብር ዶክትሬቱን በዕለቱ ከተገኙት የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የቦርድ አመራሮች እንዲሁም በፕሮግራሙ ወቅት በክብር እንግድነት ከተጠሩት የአርብቶ አደሮችና የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃን እጅ ተቀብለዋል፡፡ አቶ ብዙአየሁን ለዚህ ያበቃቸውን ተግባር የሚገልጸው የግለ ታሪካቸው ረዥም ጉዞ የጀመረው፣ ወታደራዊው ደርግ ሥልጣን ሲቆናጠጥ በተከተለው የርዕዮተ ዓለምና ፖሊሲ ምክንያት ቤተሰቦቻቸው ያፈሩትን ሀብትና ንብረት በመውረሱ ምክንያት ባዶ እጃቸውን በቀሩበት ወቅት እንደነበር ይጠቅሳል፡፡

በዚህ ቁጭት በመነሳሳትና የተሳካ ሥራ በመሥራት የቤተሰቦቻቸውን ጅምር ሥራ ማስቀጠል እንዳለባቸው በማመን ከአባታቸው በተሰጣቸው መነሻ ካፒታል በአፍላ የወጣትነት ዕድሜያቸው ወደ ግል ንግድ ሥራ እንደተሠማሩ ይኸው ታሪካቸው አስፍሯል፡፡

ወደ ቢዝነሱ ዓለም ሲገቡም ከአባታቸው ሲሰሙ የቆዩትን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ በመሞከር እንደነበር ዶ/ር ጂን ገልጸዋል፡፡ የአባታቸውም ምክር ‹‹ንፁህ ያልሆነ ገንዘብ ይዘህ ወደ ቤት እንዳትመጣ፡፡ የማታ ማታ ይጎዳሃል፤›› የሚል እንደነበር ስለታሪካቸው ከተወሳው ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ አቶ ብዙአየሁም ይህንን አባባል አስታውሰው፣ ይህ ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር እስከዛሬ አብሯቸው እንደሚኖር በዕለቱ ባረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡

የቢዝነስ እንቅስቃሴያቸውን በማጠናከርና በማሳደግ ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ወደ ጎረቤት አገሮች ማለትም ኬንያና ጂቡቲ፣ ከዚያም አልፎ ወደ ተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችና ወደ ሲንጋፖር ሲጓዙ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ቀደም ሲል የነበራቸው ህልም በአገራቸው በማምረቻና በአግሮ ኢንዱስትሪው ዘርፍ መሰማራት ስለመሆኑም ተነግሯል፡፡ ደርግ ከወደቀ በኋላ ሥልጣነ መንበሩን የተከበረው መንግሥት ለግሉ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት በውጭና በአገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ ያፈሩትን ጥሪት በመያዝ የረዥም ጊዜ ህልማቸው የነበረውን የማምረቻና የአግሮ ኢንዱስትሪን ለመቀላቀል አስችሏቸዋል፡፡

 በማኑፋክቸሪንግም ሆነ በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ውስጥ ለመሰማራት መድፈር በራሱ ከባድ ውሳኔና ወኔን የሚጠይቅ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ብዙአየሁ፣ ብዙዎች ወዳጆቻቸው አላስፈላጊ ድፍረት ነው በማለት ሲተቿቸውና ሲመክሯቸው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ በእርግጥም መስኩ እንደሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች የሚደፈር ባይሆንም እሳቸው ደፍረው በመግባት በኢትዮጵያ በግል ዘርፍ የመጀመርያ የሆነውን የኢንዱስትሪ መንደር በዱከም ገንብተው ለፍሬ እንዲበቃ አድርገዋል፡፡ በዚህ የኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ ዘጠኝ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን በመገንባት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ስኬታማ ሥራ ማከናወናቸው የክቡር ዶክትሬት ለማግኘታቸው አንዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በወቅቱ በበርካቶች ዘንድ ባልተደፈረውና ላይ ላዩን በሚፈራው ዘርፍ ውስጥ በመግባት ታግለው ማለፋቸው አሁን ለደረሱበት ውጤት አብቅቷቸዋል፡፡

በኢንዱስትሪዎች አማካይነት ሀብትን መፍጠር በሚለው የድርጅታቸው መርኅ መሠረት ፈር ቀዳጅ ለመሆን መብቃታቸው ለዕውቅናው ሌላው አስተዋጽኦ ያደረገ መመዘኛ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ከተሰጡት ውስጥ በአገሪቱ ከሚገኙ ትላልቅ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አንዱና ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ባለሀብት የተቋቋመው ናሽናል ሲሚንቶ ኩባንያ አክሲዮን ማኅበርን በመመሥረትና ፋብሪካውን በመገንባት፣ በአገሪቱ የመጀመርያው መሆኑ የሚነገርለትን ጨዋቃ የሻይ እርሻና ማቀነባበሪያ ፋብሪካን ከማቋቋም ባሻገር በማዕድናት ፍለጋና ምርት ሥራ በመሰማራትና በአገሪቱ የድንጋይ ከሰል አምራችነት በመንቀሳቀስ ረገድ ‹‹ለሌሎች ሀብትን መፍጠር›› በሚለው መርኃቸው ሠራተኞችንም ጭምር የሀብት ተጋሪ የሚያደርጉ ከ17 በላይ የጋራ ኩባንያዎችን መሥርተው ስኬታማ ለመሆን መቻላቸው ተነግሮላቸዋል፡፡ እስካሁን ከደረሱበት ስኬት ባሻገር ወደፊትም ብዙ ለመሠራት እየጣሩ ያሉ ባለሀብት መሆናቸውም ተነግሮላቸዋል፡፡  

እነዚህ ኩባንያዎቻቸው በአሁኑ ወቅት በዓመት ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ሽያጭ የሚያከናውኑ ሲሆኑ፣ ጥቅማ ጥቅሞችን ጨምሮ በየወሩ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ደመወዝ ለሠራተኞች መክፈል የቻሉ ኩባንዎችን የመሠረቱ መሆናቸው ሁሉ ዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬት ዕውቅና እንዲሰጣቸው ሚዛን እንዲደፉ ካበቋቸው መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በታክስና ግብር በዓመት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ማስገባት መቻላቸውም ተጠቅሷል፡፡

በርካቶች ስለስኬታማ ኩባንያዎቻቸው ቢያውቁም አቶ ብዙአየሁ የኩባንያዎቻቸውን ያህል ታዋቂ አለመሆናቸው ለብዙዎች ግርምት ሆኖ በመድረኩ ሲነገር ተደምጧል፡፡ እሳቸው ግን ይህን መልካም ልማድ የሚከተሉት፣ ድርጅቶቻቸውንና ምርቶቻቸውን ማስተዋወቅ እንጂ የግል ገጽታቸውን መገንባት እንደማያጓጓቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሥራን ማስቀደም፣ በጋራ መጣርና የጋራ እሴት መፍጠር ዋነኛ የኩባንያዎቹ ባህል መሆኑን ማወቅ አለብን፤›› ያሉት አቶ ብዙአየሁ፣ በጋራ ጥረት ያፈሯቸው ኩባንያዎች እንደሆኑም በአጽንኦት ተናግርዋል፡፡

የክብር ዶክትሬታቸውን ከተቀበሉ በኋላ በሥነ ሥርዓቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር መሳረጊያ ላይ ‹‹በውስጤ የተለያዩ ስሜቶች ይመላለሳሉ፡፡ በአንድ በኩል ያገኘሁት ማዕረግ ባለፉት ረዥም ዓመታት በስኬታማነት የደረስኩበትን ደረጃ የሚያመላክት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በእነዚህ ዓመታት እዚህ ለመድረስ ያሳለፍኩትን እልህ አስጨራሽ ፈተናዎች በትውስታ ተመልክቼበታለሁ፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ብዙአየሁን ለክብር የጠራው ሊንከን ዩኒቨርሲቲ ከዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን 30 ተማሪዎች በዕለቱ በማስመረቅ የትምህርት ማስረጃቻቸውን ከክብር እንግዶቹ እንዲቀበሉ አድርጓል፡፡ ከአቶ ካሳ ተክለብርሃን በተጨማሪ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አቶ ይናገር ደሴን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናትም በሥነ ሥርዓቱ ወቅት ታድመዋል፡፡

 

Standard (Image)

‹‹አግሮ ፉድ ፕላስትፓክ››

$
0
0

ከ14 አገሮች የተውጣጡ ባለሀብቶች የተሳተፉበትና ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው ‹‹አግሮ ፉድ ፕላስትፓክ›› የተሰኘው ዓለም አቀፍ የንግድ ዓውደ ርዕይ፣ ዓርብ ጥር 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከጀርመን፣ ከፈርንሳይ፣ ከእንግሊዝ፣ ከኔዘርላንድስ፣ ከኦስትሪያ፣ ከአሜሪካ፣ ከህንድ፣ ከኬንያ፣ ከታይዋን፣ ከዩክሬን፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ ከቶጎ የተውጣጡ የንግድ ዓውደ ርዕይ ተሳታፊዎች የታደሙበት ይህ ዝግጅት፣ በአገር በቀሉ ፕራና ፕሮሞሽንና በጀርመኑ ፌርትሬድ ኩባንያ አማካይነት በሚሊኒየም አዳራሽ ሲካሄድ ቆይቶ እሑድ፣ ጥር 28 ቀን ይጠናቀቃል፡፡ በየዓመቱ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው ይህ ዓውደ ርዕይ በአብዛኛው በግብርና ምርቶች፣ በግብርና ግብዓቶችና በግብርና ማቀነባበሪያ መስኮች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ከየአገሮቹ የተውጣጡ ልዩ ልዩ የማምረቻ፣ የምርት መጠቅለያና ማሸጊያ ማሽነሪዎችና መሣሪያዎችን ለዕይታ ያቀረቡ ሲሆን፣ በመክፈቻው ዕለትም በኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር መብራህቱ መለስና በዲፕሎማቶች ተከፍቶ ለሕዝብ ዕይታ ይፋ ሆኖ ቆይቷል፡፡ 

Standard (Image)

የንግድ ሚኒስቴርን ጣልቃ ገብ ውሳኔ የሚጠብቁ ንግድ ምክር ቤቶች

$
0
0

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጉባዔ ወቅቱን ጠብቆ እንዳይካሄድ ያደረጉ እንቅፋቶችን አጣርቶ ውሳኔ በመስጠት፣ ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲጠራ የሚያችለው ስምምነት ተደርሶ ነበር፡፡

ምክር ቤቱን እየመራ ያለው ቦርድ እንዳጋጠመው ባስታወቀው ችግር ላይ 18ቱን  አባል ምክር ቤቶች ጠርቶ በማማከር አጣሪ ግብረ ኃይል ተመሥርቶ ሲያካሂድ የቆውን የማጣራት ሥራ አጠናቆ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ ግብረ ኃይሉ ባካሄደው ማጣራት መሠረት ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ እንቅፋት የነበሩ ችግሮች ታውቀው ውሳኔ መተላለፉ አይዘነጋም፡፡ በዚሁ የማጣራት ሥራ የተገኙ የሕግ ጥሰቶች ላይ ግብረ ኃይሉ ዕርምጃ እንዲወስድ ኃላፊነቱን ለምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤትና ለቦርዱ ቢሰጥም፣  ውሳኔ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት ንግድ ሚኒስቴር ነገሩን ራሱ እንደሚጣራ በማስታወቅ ሊካሄድ የታቀደውን ጉባዔ ታግዶ እንዲቆይ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የሚኒስቴሩ ውሳኔ በሌሎች ዕይታ

ንግድ ሚኒስቴር ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊካሄድ የነበረውን ጠቅላላ ጉባዔ እንዳይካሄድ የሚያግድ ድምዳሜ ላይ መድረሱን ካሳወቀ በኋላ፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ለንግድ ምክር ቤቱ ቅርበት ያላቸው ወገኖች የሚኒስቴሩ ውሳኔ ቢዘገይም ተገቢ እንደሆነ ግን ያምናሉ፡፡

መንግሥት የንግድ ምክር ቤቱን ጉዳይ ለማጣራት መወሰኑ ተገቢ ነው  ከሚሉት ወገን የሆኑት የደቡብ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ከበደ ናቸው፡፡ በአባል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ውስጥ የታዩ የሕግ ጥሰቶችን የተመለከቱ አቤቱታዎች ቀርበውለት አገር አቀፉ ምክር ቤት መልስ ሳይሰጥ መቆየቱ ለችግሩ መባባስ ምክንያት እንደሆነ ለሪፖርተር የገለጹ ሌላ አስተያየት ሰጪም፣ ንግድ ሚኒስቴር ውሳኔ ለማስተላለፍ ዘገምተኛ ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

መንግሥት በግድ ምክር ቤቶች ውስጥ እጁን ላለማስገባት በመጠንቀቅ ችግሮቹን አባላቱ ራሳቸው እንዲፈቱ ዕድል መስጠቱ እንደሚደገፍ የሚገለጹት አስተያየት ሰጪዎች፣ ይሁንና በአንዳንድ ምክር ቤቶች አመራሮች አማካይነት ይፈጸሙ የነበሩ የሕግ ጥሰቶች ላይ እልባት ለመስጠት አፋጣኝ ውሳኔ አለመሰጠቱ ግን ደካማ የንግድ ምክር ቤቶች እንዲበራከቱ፣ ጥቂት ግለሰቦች ብቻ እየተፈራረቁ ወደ አመራር መንበሩ ለመምጣት የቻሉበትን በር ከፍቷል በማለት የተቹም ነበሩ፡፡

የንግድ ምክር ቤቶች አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ለመንግሥትም ጭምር መሆኑ እየታወቀ፣ አሠራራቸውን ችላ ማለቱ የፉክቻ አምባ እንዲሆኑ ማድረጉን በመገንዘብና ችላ ብሎ መቆየቱ ስህተት እንደነበር በማመን ከዚህ በኋላ መንገዳቸውን የማስተካከል ኃላፊነት አለበት በማለት የገለጹ አሉ፡፡

ንግድ ሚኒስቴር ሰሞኑን ባስተላለፈው ውሳኔ የማጣራት ሥራውን ሠርቶ ጠቅላላ ጉባዔው እንዲካሄድ፣ አዳዲስ የአመራር አባላት እንዲመረጡ በማድረግ ብቻ መገታት እንደሌለበትም እየተነገረ ነው፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት፣ ለንግድ ምክር ቤቶች መዳከም፣ ጠንካራ መሪዎች ለማግኘት አለመቻል እንዲሁም እንደሌሎች አገሮች ንግድ ምክር ቤቶች ድምፃቸው የሚሰማ ጠንካራ ተቋማት እንዳይሆኑ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅና አዋጁን ለማስፈጸም የጠሩ፣ ግልጽ ደንብና መመርያዎች አለመኖራቸው ይጠቀሳል፡፡ ንግድ ሚኒስቴር እንዲህ ያሉ ጉዳዮች እንዲጣሩ ማድረግ ይጠበቅበታል ተብሏል፡፡ ከበርካቶች አስተያየት መረዳት እንደተቻለው፣ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅና የዘርፍና የንግድ ምክር ቤቶች ሚና በግልጽ እንዲቀመጥ አዋጁ መሻሻል እንዳለበት ነው፡፡

ይህ የማይደረግ ከሆነ ጣልቃ መግባቱ ፋይዳ የሌለውና ችግሮቹ ውሎ አድሮ ዳግመኛ ስለሚፈጠሩ የማጣራቱ ሥራ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ በማካሄድ ብቻ መወሰን የለበትም የሚሉ የምክር ቤቱ አባላት ጥቂት አይደሉም፡፡ 

የአቶ አሸናፊ አመለካከትም ከተቀሩት አስተያየት ሰጪዎች ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ዘላቂ መፍትሔ ለማስፈን ንግድ ሚኒስቴር ደጋግመው ምክር ቤቶችን እየጎበኙ ለሚገኙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ይሰጣል የሚል እምነት አላቸው፡፡

ምክር ቤቱን የሚመራው ማን ነው?

የንግድ ምክር ቤቶቹ ችግር ብቁ መሪዎች ያለማግኘት እንደሆነ ይነገራል፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡን ለማገልገል ቅንነቱና ፍላጎቱ ያላቸው፣ የበቁ አመራሮች በየንግድ ኩባንያዎች ቢኖሩም ወደ ንግድ ምክር ቤት የሚመጡት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የሚመጡትም ብቃታቸው ላይ ጥያቄ እየተነሳባቸው ነው፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች አመራሮች የብቃት ጉዳይ ለችግሩ መንስዔ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሰዎች ያምናሉ፡፡

‹‹በትክክል ነጋዴ ናቸው ብዬ ለመናገር እቸገራለሁ፡፡ እጠራጠራለሁ፤›› ያሉት አስተያየት ሰጪ፣ የራሳቸው ድርጅት እያላቸው ሙሉ ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ንግድ ምክር ቤቶቹን ለመምራት እየሆነ መታየቱ ለጥርጣሬያቸው መነሻ እንደሆነ ያስቀምጣሉ፡፡ በተለያዩ የምርጫ ዘመኖች ከአንዱ ወደ ሌላኛው ንግድ ምክር ቤት እየተሸጋገሩ አንዳንዴም በሁለትና ሦስት ንግድ ምክር ቤቶች ውስጥ ራሳቸውን በአመራር ቦታ ላይ እያስቀመጡ የሚታዩ ግለሰቦች፣ በትክክል የንግዱን ኅብረተሰብ እያገለገሉ ስለመሆናቸው አፍን ሞልቶ መናገር አዳጋች እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ንግድ ምክር ቤቶችን ለመምራት የሚቀርቡ ግለሰቦች ንግድ ፈቃድ ያላቸው ነጋዴዎች ብቻም ሳይሆን በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ሊፈተሽ እንሚገባም የሚሞግቱ አልጠፉም፡፡ ከችግሮቹ ትልቁ ችግር ይኸው እንደነበር የሚገልጹት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ንግድ ሚኒስቴር በሕጋዊ መንገድም ሆነ ሕግ ጥሰው ወደ አመራር ለመሆን የሚዳክሩ ወገኖችን ትክክለኛ ነጋዴዎች ስለመሆናቸው፣ ያላቸው የንግድ ድርጅት በአግባቡ እየሠራ የሚገኝ ስለመሆኑ ማጣራት የሚቻልበትን አሠራር እንዲቀርጹ ምክር ቤቶችን እንዲያስገድድ ጠይቀዋል፡፡

 በአገር አቀፍ ወይም በክልል ደረጃ የንግዱን ኅብረተሰብ የሚመሩ ወገኖች በግል ቢዝነሳቸው ውጤታማ ሊሆኑ ስለሚገባ፣ የንግድ ሚኒስቴር የቤት ሥራም እንዲህ ያለውን ጉዳይ ማጣራት መሆን አለበት ተብሏል፡፡

ንግድ ምክር ቤቶችን ለመምራት የሚታየው ብርቱ ፍላጎት ብዙዎችን ግራ ያጋባል፡፡ ጥቂት የማይባሉና አሁንም ድረስ በአመራር ደረጃ ላይ ያሉ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት አመራሮች በያዙት ቦታ ለዓመታት ለመቆየት እንዲሁም ወደ  ኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በፕሬዚዳንትነት፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነትና በቦርድ አባልነት ለመመረጥ የሚያደርጉት ሩጫ እርስ በራሳቸው እንዲሻኮቱ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከጥቂት ወራት ወዲህ የታየው ትርምስም የጥቂት ግለሰቦች የሥልጣን ፍላጎት ጫፍ መድረስ ውጤት ነው እየተባለ ነው፡፡

በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አሠራር የሚከተል በመሆኑ፣ ለንግድ ምክር ቤቶች ኃላፊ ሆኖ መሥራት በቀጥታ የሚያስገኘው ክፍያ ወይም ደመወዝ የለም፡፡ ነገር ግን የኃላፊነት ቦታው በብርቱ ያነታርካል፡፡ ይህ መከሰቱም ነው በሕግ የተቀመጠውን የአንድ ዘመን ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ ያላስቻለው፡፡ ችግሮች የተፈጠሩት በአንድ በኩል ጥቅም የለውም እየተባለ በሌላ በኩል ግን ቦታውን ለማግኘት የሚከፈለው መስዕዋትነት ነው፡፡ ተመራጮቹ ቦታውን የግል መጠቀሚያ እያደረጉት ነው የሚል ቅሬታ የሚያሰሙ  ወገኖች ጥቂት አይደሉም፡፡ ለዚህ በተለይ የሚጠቀሰው የውጭ ጉዞዎች ጉዳይ ነው፡፡ ለንግድ ጉብኝት ወደ ውጭ የሚጓዙበትን ዕድል እያገኙ በዚያው የሚቀሩ አመራሮች መታየታቸውም ይነገራል፡፡ የውጭ ጉዞዎችን ለማይመለከታቸው ሰዎች በመስጠት ወደ ውጭ እየላኩ ገንዘብ አካብተዋል እየተባሉ ውስጥ ውስጡን ከሚወራባቸው አልፎ በአሁኑ ወቅት ይፋ የወጣ አነጋጋሪ ድርጊት መሆኑም ይገለጻል፡፡

የውጭ ጉዞው የሚመለከተው ባለሙያ ወይም አመራር እንዳይሄድ በማድረግ የቢዝነስ ጉዞዎችን ለሽርሽርና ለመሰል የግል ጉዳይ ማዋልም አመራሮች የሚታሙባቸው ድርጊቶች ሆነዋል፡፡ በቅርቡ የንግድ ምክር ቤቱን ችግሮች እንዲመረምር የተቋቋመው ግብረ ኃይል ሪፖርቱን ሲያቀርብ፣ በንግድ ምክር ቤቶች ውስጥ አጨቃጫቂ ከነበሩና ይጣሩ ከተባሉ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ይኸው የውጭ ጉዞን የተመለከተ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ እከሌ ይህንን ያህል ጊዜ የጉዞ ዕድል ተሰጥቶታል፣ አቶ እከሌ ደግሞ ገና ኃላፊነት ላይ በወጣ በወራት ጊዜ ሁለቴ አሜሪካ ሄደ የሚሉ ስሞታዎች ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት ተደምጠዋል፡፡

አጣሪ ኮሚቴው የጉዞ ፕሮግራሞች ሥርዓት ሊኖራቸው ይገባል፣ ዕድሉን አግኝቶ የሄደ አመራርም ከጉዞ መልስ ስለሄደበት ጉዳይ ማብራሪያ ያቅርብ የሚል ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ ንግድ ሚኒስቴር ይህንን አሠራር መፈተሽ አለበት ተብሏል፡፡

‹‹ሳይመረጡ የተመረጡ››

ተደጋግሞ ሲዘገብ እንደከረመው በአገር አቀፍ ንግድ ምክር ቤቱ አባል ምክር ቤቶች ሳይመረጡ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት መጥተዋል ተብለው ለንግድ ሚኒስቴር አቤቱታ ከቀረበባቸው መካከል አንዱ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ነው፡፡

ንግድ ምክር ቤቱን ላለፉት ስምንት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት የመሩትና ከጥቂት ወራት በፊት በተደረገ ምርጫ ድጋሚ የተመረጡት አቶ ጌታቸው አየነው፣ ከእሳቸው ጋር አብረው የተመረጡ ሌሎች አመራሮችም ቦታውን የያዙት ከመጡባቸው ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በሕጋዊ መንገድ ሳይወከሉ ነው የሚል አቤቱታ ከአባል ምክር ቤቶች ቀርቧል፡፡ አቤቱታው ንግድ ሚኒኒቴር ዘንድም ደርሶ ነበር፡፡  

በንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት በዋናው ንግድ አባልነት የተካተቱ ምክር ቤቶች ምርጫ አካሒደው ወደ ላይኛው ዕርከን መሄድ ይገባቸዋል፡፡ የአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ግን አቶ ጌታቸው አባል የሆኑበት የባህር ዳር ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ሲያካሂድ ከባህር ዳር መወካለቸው ተነግሮ የተመረጡ ናቸው በማለት የሕግ ጥሰት እንደተፈጸመ አስታውቋል፡፡ አቶ ጌታቸው  በወቅቱ በሰጡት ምላሽ እሳቸውና ሌሎች አመራሮች ከታች ምክር ቤት መወከል ሳያስፈልጋቸው በቀጥታ የክልሉ ጠቅላላ ጉባዔ አባል መሆን እንደቻሉ፣ ይህም ከዚህ ቀደም በተደረገ ጠቅላላ ጉባዔ የተወሰነ በመሆኑ  የሕግ ጥሰት አለመፈጸማቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤትን ለስምንት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት የመሩት አቶ ገብረህይወት ገብረእግዚአብሔር፣ የዘርፍ ምክር ቤቱ ነሐሴ 2008 ዓ.ም. ባካሔደው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ በድጋሚ መመረጣቸው አግባብ አይደለም ተብሎ ተቃውሞ ቀርቦባቸው ነበር፡፡ በዘርፍ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ ማገልገል እንደማይቻል እየታወቀ፣ በድጋሚ ስለተመረጡ የሕግ ጥሰት ፈጽመዋል ተብለዋል፡፡ ይህ አቤቱታ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ቢቀርብም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ምላሽ ሳይሰጥበት  ቆይቷል፡፡ የአማራ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትም ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥ እንደማይችሉ እየታወቀ የተመረጡ ስለሆነ፣ ይህም የሕግ ጥሰት ሆኖ ሲያከራክር ቆይቷል፡፡

የአዲስ አበባ ዘርፍ ምክር ቤትም ከኢትዮጵያው ምክር ቤት ጉባዔ በፊት ምርጫ ማድረግ ሲገባው፣ ይህንን ሳያደርግና ያለ ምርጫ ውክልና የዘርፍ ምክር ቤቱ አባል እንዲሆኑ አድርጓቸዋል የተባሉት አቶ አበባው መኮንን ናቸው፡፡ አቶ አበባው አሁን የሥልጣን ዘመኑን ያጠቃለለው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት፣ እንዲሁም በቅርቡ በተደረገ ምርጫ የአዲስ አበባ ንግና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ለሁለተኛ ጊዜ እንደተመረጡ አይዘነጋም፡፡ እነዚህ ለንግድ ሚኒስቴር በይፋ ተቃውሞ የቀረበባቸው ጉዳዮች ሲሆኑ፣ ምርመራ የሚሹ ሌሎችም የሕግ ጥሰቶች እንዳሉ በመጥቀስ ሚኒስቴሩ ሊያጣራ ይገባል ተብሏል፡፡ እንወክለዋን ወይም እንመራዋለን የሚሉትን የንግድ ኅብረተሰብ ጉዳይ እርግፍ አድርገው ትተው ዋነኛ አጀንዳቸው በምርጫው ላይ ብቻ ማድረጋቸው አመራሮቹን ጥያቄ ውስጥ እንደከተታቸው አባላት እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

ድምፅ መግዣ አባላት

በአጣሪ ግብረ ኃይሉ ይጣሩ ተብለው ከተለዩ ጉዳዮች መካከል አባል ምክር ቤቶች ስንት አባላት አሏቸው የሚለው ይገኝበታል፡፡ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአባልነት የታቀፉት 18ቱ ንግድ ምክር ቤቶች ከ500 ሺሕ በላይ አባላት እንዳሏቸው ይነገራል፡፡

የእያንዳንዱ ንግድ ምክር ቤት አባላት ብዛት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ይፈተሽ ተብሎ ሲጣራ የተገኘው ውጤት ግን ከላይ ከተጠቀሰው ቁጥር ያነሱ አባላት መኖራቸው ነው፡፡ ከ100 ሺሕ በላይ በአባልነት የተመዘገቡ ሰዎች፣ አባልነታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሊቀርቡ አልቻሉም፡፡ ምክር ቤቶቹ እንዲያቀርቡ ተጠይቀውም ሊሆን አልቻለም፡፡ ይህ ጉዳይ በንግድ ሚኒስቴር የማጣራት ሥራ ወቅት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያመለከቱ በርካቶች ነበሩ፡፡

ለዓመታት በሕጋዊ ሆነ በሕገወጥ የምርጫ ሒደት ኃላፊነቱን ይዘው የቆዩ ግለሰቦች በሥልጣን ላይ ለመቆየት ባላቸው ፍላጎት ሳቢያ ንግድ ምክር ቤቶችን ለመምራት አቅም ያላቸው አባላት እንዳይወጡ በሩን ስለዘጉ፣ ከዚህ በኋላ እንዲህ ያለው አሠራር እንዳይቀጥል ተጠይቋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን የአመራር ቦታ ለማግኘት እያንዳንዱ አባል ለምርጫ የሚኖረው ድምፅ የአባላትን ቁጥር መሠረት በማድረግ በሚሠራ ቀመር ይሁን ተብሏል፡፡

የበለጠ ድምፅ ለማግኘት ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸውን የሌሎች ንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶችን አመራሮች በመያዝ አንተ ለእኔ እከሌ ላንተ ድምፅ እንስጥ ተባብለው በመቧደን፣ በያዙት ሕገወጥ ድምፅ ከምርጫ በፊት የኃላፊነት ቦታዎችን ለየራሳቸው ደልድለው ወደ ምርጫ የሚገቡ እንዳሉም ተጠቅሷል፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ ንግድ ሚኒስቴር ጠቅላላ ጉባዔው እንዲዘገይ ከመወሰኑ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ጥቂት ግለሰቦች እርስ በርሳቸው ተመራርጠው፣ የምርጫውን ዕለት ሲጠባበቁ ነበር መባሉን በምሳሌነት ያነሳሉ፡፡

 ማን ፕሬዚዳንት? ማን ምክትል ፕሬዚዳንት? እንደሆነ እነማንስ የቦርድ አባላት ይሁኑ በሚለው ላይ ተስማምተው እንደነበር የሚገልጹት ምንጮች፣ ንግድ ምክር ቤቱን ለመምራት የሚጣደፉ ወገኖች ሕገወጥነት ምን ያህል አስቸጋሪ እየሆነ እንደመጣ ይጠቅሳሉ፡፡ ንግድ ሚኒስቴር ይህንን ጉዳይ በማጣራት ውሳኔ ለመስጠትና እንዲሁም ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ነገር እንዳይፈጸም የሚያደርግ አሠራር እንዲኖር ከፈለገ ጉዳዩን የሚያጣሩት ባለሙያዎች ጠንካራ ሊሆኑ እንደሚገባቸውም እየመከሩ ነው፡፡  

በቅርቡ በኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት ለተፈጠረው ያለመግባባት ውዝግብ አንዱ መነሻ የምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ከማካሄዱ በፊት የኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ማድረግ ይጠበቅበት ነበር፡፡ በነሐሴ 2008 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውንና ምርጫውን ሳያካሂድ፣ ይልቁንም ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሠራበት ቆይቷል የተባለውን መተዳደሪያ ደንብ በነሐሴ 2008 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ፕሬዚዳንትና ጸሐፊው ተሻሻለ የተባለውን ረቂቅ ደንብ ያፅድቅልን በማለት ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡

በወቅቱ ተሻሻለ የተባለው ደንብ ቀድሞ አባል ምክር ቤቶች ሳይወያዩበት፣ ረቂቁም ሳይደርሳቸው አፅድቁልን ብለው በመምጣታቸው የደቡብ ክልል ዘርፍ ምክር ቤት ተወካዮች ተቃውመውት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውን ረግጠው ለመውጣት ምክንያት እንደሆናቸውም ይታወሳል፡፡

ተሻሽሎ ቀረበ የተባለው መተዳደሪያ ደንብም አሻሻለ የተባለው ነጥብና የተሻሻለበት ምክንያት ምን እንደነበር በግልጽ መታየቱ ይታወሳል፡፡ በ1999 ዓ.ም. የፀደቀውና ሲሠራበት የቆየው ደንብ ውስጥ ዘርፍ ምክር ቤቱን የሚመሩ ሰዎች  የሥልጣን ዘመንን ገድቦ ቆይቷል፡፡ አንድ ተመራጭ ለሁለት የሥልጣን ዘመን ወይም ለአራት ዓመታት ብቻ ማገልገል እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡ ተሻሽሏል ተብሎ  እንዲፀድቅ በቀረበው መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ ግን የሥልጣን ዘመንን የሚገድበውን አንቀጽ እንዲወጣ መደረጉ የተመራጮች የሥልጣን ዘመን ሳይገደብ እንዲቆዩ የሚፈቅድ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይህ በመሆኑ በወቅቱ ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ዘጠኝ የቦርድ አባላት  ሕግ ከሚፈቅድላቸው በላይ በድጋሚ ለመመረጥ ያደረጉት ነው በማለት የደቡብ ዘርፍ ምክር ቤት ተቃውሞታል፡፡ የዘርፍ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ስምንተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል፡፡ ይህ በመሆኑም ለመንግሥት አቤቱታ ቀርቦበታል፡፡  

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት በ2008 ዓ.ም. በተደረገ ወደ አመራር ለመምጣት የሚደረገውን ጥረት ለማስቀረት አንድ ተመራጭ የሥልጣን ገደቡ እንዲገደብ የሚያደርገው የተሻሻለ ደንብ ደግሞ ከብዙዎች አባል ምክር ቤቶች ተቀባይነት ያለማግኘቱ ነው፡፡ በቅርቡ የተፈጠረውን ውዝግብ ሲያጣራ የነበረው አጣሪ ኮሚሽን አባል ምክር ቤቶች እንዲህ ያሉትን አንቀጾችም የተሻሻለውን መተዳደሪያ ደንብ አልተቀበሉትም ይሻሻል ብለዋል፡፡ ይህ ግን የሚያመላክተው ደጋግሞ ሊመረጥ ከመፈለግ የተነሳ ነው በሚል ሲተች ነበር፡፡

 

 

 

 

   

Standard (Image)

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ያሰበውን ያህል መጓዝ እንዳልቻለ ገለጸ

$
0
0

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በሁሉም የባንክ የአገልግሎት ዘርፍ ዕድገት እያስመዘገበ፣ የገበያ ድርሻውም ከፍ እያለ ቢመጣም በተፈለገው የዕድገት ደረጃ ልክ እየተጓዘ አይደለም ሲሉ የባንኩ ቦርድ ሊቀመንበር ገለጹ፡፡

የባንኩ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አበራ ቶላ ይህንን የገለጹት፣ የባንኩ ‹‹የወጪ ንግድ ቀን›› በተከበረበት ሥነ ሥርዓት ወቅት ነው፡፡ የባንኩ ዕቅድ አሁን ከተመዘገበው ዕድገት በላይ መሆን ነበረበት ያሉት አቶ አበራ፣ ይሁንና ውጫዊ ችግሮች በሚፈለገው ደረጃ ዕድገቱን ለመጨር ወይም በፍጥነት ለመሮጥ አላስቻለውም ብለዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ፖሊሲዎችና አሠራሮች እንደተፈለገው ባንኩን ለማራመድና ከደንበኞች ጋር ሆኖ የአገር ኢኮኖሚን ይበልጥ ከመደጎም ባሻገር አሁን ባለው ዕድገት ላይ ለመጨመር ያላስቻለ አጋጣሚ ፈጥሯል ብለዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ችግሮች በሒደት ሊፈቱ የሚችሉ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አበራ፣  በተለይ ራሳችን በምናመጣቸው ፈጠራዎች ሊለወጡ ይችላሉ በማለት እየሠሩ ስለመሆኑና አሁን ባለው ሁኔታም ቢሆን ባንኩ የደረሰበት ደረጃ ጥሩ የሚባል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፖሊሲ ባለቤት የሆነው መንግሥት በፍጥነት ከመጓዝ የሚያደናቅፉ ጉዳዮችን በመመልከት ያሻሽላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የግል ዘርፉ ለአገር አለኝታ ሆኖ እንዲቀጥል ማንኛውንም ነገር ወደፊት ሊያራምድ የሚችል አቅም እንዳለውና ይህም እየሰረጸ እንዲሄድ የሚያስችል ዕድል መፍጠር ይገባል የሚል ተስፋ እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የሁላችንም ጉዞ የኤሊ የሚሆን ይመስለኛል ብለዋል፡፡

ከስምንት ዓመታት በፊት የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክን አደራጅቶ ባንኩን ለማቋቋም ሲነሱ ታሳቢ አድርገው የነበሩት በወቅቱ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ክፍተት ነበር ያሉት የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወልዴ ቡልቶ ናቸው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ባንኮች ተደራሽነታቸው ውስን ስለነበር ይህንን ክፍተት የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ አስተዋጽኦ በማበርከት ድርሻውን መወጣት ይኖርበታል በማለት  የተጀመረው እንቅስቃሴ ከዓመት ዓመት እያደገ እንደመጣ ተናግረዋል፡፡

እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ አነስተኛና መካከለኛ የኅብረተሰብ ክፍል መድረስ አንዱ ሲሆን፣ ሁለተኛ የቅርንጫፍ ተደራሽነት በቂ አለመሆን፣ ሦስተኛ በእምነታቸው ምክንያት በመደበኛ ባንክ አገልግሎት መጠቀም የማይፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስለነበሩ እነሱንም ለመድረስ የሚያስችል አገልግሎት ለመስጠት በማሰብ ለባንኩ መቋቋም መነሻ ነጥቦች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ ይህንንም ለማመልከት ባንኩ ያስመዘገባቸውን ውጤቶች ዘርዝረዋል፡፡

ባንኩ እንደ ስኬት ከሚቆጥራቸው ተግባራቱ አንዱ በቅርንጫፍ ማስፋፋት ሥራ ላይ የወሰደው ዕርምጃ ነው፡፡ ከስምንት ዓመታት በፊት ሥራ ሲገባ በመጀመሪያዎቹ ስምንት ወራት 26 ቅርንጫፎችን ይዞ ነው፡፡ ይህ የተለየ እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ከ26ቱ ቅርንጫፎች አምስቱን ብቻ በአዲስ አበባ 21ን ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጭ ብዙም የባንክ አገልግሎት ባልነበረባቸው የክልል ከተሞች መሆኑ በተለየ የሚታይ ነው ተብሏል፡፡

ባንኩ ይኼ እንቅስቃሴና በመጀመርያው የሥራ ዓመት 26 ቅርንጫፍ መክፈቱን ሌሎች ባንኮችም በተመሳሳይ መንገድ ቅርንጫፍ ወደ ማበራከት እንዲገፋ ያደረገና የባንክ ተደራሽነት የበለጠ እንዲሆን ማድረግ ችለናል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ይህ እንደ ትልቅ ስኬት የምናየውም ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የባንኩ ቅርንጫፎች 211 ደርሰዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የቅርንጫፍ ቁጥሩን ስትራቴጂክ ዕቅድ መንደፉንም አመልክተዋል፡፡

ሌላው የባንኩ ስኬት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ከሁሉም ቀድሞ መጀመሩ ነው ተብሏል፡፡ በሌሎች ባንኮች ያልተሞከሩ አዳዲስ አገልግሎት መጀመርም የባንኩ መለያ መሆኑን በመግለጽ፣ በዕለቱ ለዕውቅናና ለሽልማት የተጋበዙ ደንበኞቻቸው አብረዋቸው ቢጓዙ የበለጠ ይጠቀማሉ ብለዋል፡፡  

በባንኩ እንቅስቃሴና ዕቅዶች ዙሪያ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖም ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ባንኩ በ2008 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ የተጣራ ትርፍ 248.3 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የባንኩ ተከታታይ የትርፍ መጠን ዕድገት የባንኩን ጤናማ አካሄድ ያመላክታል ተብሏል፡፡

ባንኩ ሐሙስ፣ ጥር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. የወጪ ንግድ የዋንጫና የምሥጋና ምስክር ወረቀት ያበረከተላቸው ደንበኞቹ 22 ናቸው፡፡ በአራት ዘርፎች የተመደቡት ተሸላሚዎች የባንኩ ተበዳሪ፣ ላኪዎች፣ ከባንኩ ብድር ሳይወስዱ የወጪ ንግድ የባንክ አገልግሎትን ሲጠቀሙ የቆዩ፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ላኪዎችና ለላኪዎች ፋይናንስ የሚደረግ ከፍተኛ ገንዘብ አስቀማጮች በሚሉ ምድቦች ነው፡፡ 

Standard (Image)

የአንድ ቢሊዮን ብር ሽያጭ ያቀደው አረቄና አልኮል ፋብሪካ ቮድካ ማምረት ጀምሯል

$
0
0

 

የአረቄና አልኮል ምርት በፋብሪካ ደረጃ በኢትዮጵያ መመረት ከጀመረ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ ታሪክ እንዳለው ይነገርለታል፡፡ ምናልባትም በኢትዮጵያ ረዥም ዕድሜ በማስቆጠር በቅብብሎሽ ከ110 ዓመታት በላይ የዘለቀ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የአረቄና አልኮል ማምረቻ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ በዚህ መስክ የመጀመርያው የአልኮል ፋብሪካ እንደሆነ የሚነገርለት የሰበታ አረቄ ፋብሪካ የተመሠረተው በ1889 ዓ.ም. እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የሰበታ የአረቄ ፋብሪካን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት የተገነቡትን ሌሎች ሦስት የአረቄና የአልኮል ፋብሪካዎች በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ብሔራዊ አረቄና አልኮል ፋብሪካ የተባለው የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡

በ1969 ዓ.ም. አራቱ የአረቄና የአልኮል ፋብሪካዎች በደርግ መንግሥት ተወርሰውና በአንድ ድርጅት ተጠቃለው ብሔራዊ አልኮልና ፋብሪካ በሚል ሥያሜ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሲንቀሳቀሱና በተለይ ሦስቱ ቅርንጫፎች እስካሁን ድረስ በአትራፊነት መዝለቅ እንደቻሉ ይነገርላቸዋል፡፡

ይህ የመንግሥት የልማት ድርጅት ከአራቱ ቅርጫፎቹ በአዲስ አበባ ከተማ መካኒሳ አካባቢ የሚገኘውና በጣልያኖች እንደተገነባ የሚነገርለት ፋብሪካው በተለይ ከፍተኛ ምርት የሚመረትበት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይሁንና በ1930 ዓ.ም. የተመሠረተውና አቃቂ ቅርንጫፍ እየተባለ የሚጠራው ፋብሪካ በእርጅና ሳቢያ ከምርት ውጭ በመሆኑ አሮጌ መሣሪያዎቹ ለታሪክ መዘከሪያነት ተቀምጠዋል፡፡ ሰበታ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ፋብሪካ የምርት አቅሙ አነስተኛ ቢሆንም፣ ከ79 ዓመታት በኋላም ቢሆን ምርት በማምረት ላይ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማምረት አቅሙን ለመጨመር የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል ማይጨው ከተማ ውስጥ የሚገኘው ቅርንጫፍም በሥራ ላይ ይገኛል፡፡  

ከሌሎቹ ቅርንጫፎች ይልቅ የተሻለ የሚያመርተው የመካኒሳውን ፋብሪካ አቅሙን ለማሳደግ ለማስፋፊያ ሥራ የወጣበት የኢንቨስትመንት ወጪ የአልኮልና የአረቄ ገበያው የደራ እንደሆነ የሚያመላክት ሆኗል፡፡

እያደገ ከመጣው የምርት ፍላጎት አንፃር በመካኒሳው ፋብሪካ ሲካሄድ የቆየውና የተጠናቀቀው የማስፋፊያ ግንባታ የበለጠ ተወዳዳሪ ያደርገዋል ተብሏል፡፡ ብሔራዊ አረቄና አልኮል ፋብሪካ እስከ 1994 ዓ.ም. ድረስ በአገሪቱ ብቸኛ የአረቄና አልኮል አምራች የነበረ ሲሆን፣ ገበያውን ለብቻው ተቆጣጥሮ ቆይቷል፡፡ ከ1995 ዓ.ም. በኋላ ግን የግል ኩባንያዎች ወደዚህ ዘርፍ እየገቡ ሲመጡ፣ መንግሥታዊውን ድርጅት ተወዳዳሪ ወደሚያደርገው የአቅም ግንባታ ሥራ በማካሄድ ተጨማሪ የማስፋፊያ ሥራዎች ውስጥ ገብቷል፡፡

ቅዳሜ፣ ጥር 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በመካኒሳ የሚገኘው ፋብሪካ የማስፋፊያ ግንባታ መገባደዱን በማስመልከት የመንግሥት የልማት ድርጅትን ሚኒስቴር ዶ/ር ግርማ አመንቴ በተገኙበት ወቅት እንደተገለጸው፣ አዲስ ለተተከለው ማምረቻ 193 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጠናቀቁ የሚጠበቁት ሌሎች ግንባታዎችንም እያካሄደ ነው፡፡ የሰበታው ፋብሪካ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ሲታከልበትም የድርጅቱ አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ወጪ 450 ሚሊዮን ብር ይደርሳል ተብሏል፡፡

የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለ ማርያም ግደይ እንደገለጹት፣ አዲስ የተተከለው የመካኒሳው ማምረቻ ብቻውን በቀን 18 ሺሕ ሊትር አረቄና አልኮል የማምረት አቅም አለው፡፡ ከማስፋፊያ ግንባታው በፊት በአሮጌ መሣሪያዎች እየታገዘ በቀን ያመርት የነበረው 5,000 ሊትር ብቻ እንደነበርም ተገልጿል፡፡ በሰበታ የተጀመረው የማስፋፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ላይ የድርጅቱ ማምረቻዎች በቀን የሚኖራቸው ጥቅል የማምረት አቅም 30 ሺሕ ሊትር ይደርሳል፡፡ 18 ሺሕ ሊትር በመካኒሳ፣ ቀሪው 12 ሺሕ ሊትር አረቄና አልኮል በሰበታ ይመረታል፡፡

ድርጅቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከዕቅዱ በላይ በመሥራት ውጤታማ መሆን ችሏል ተብሏል፡፡ እንደ ድርጅቱ መረጃ ከ2003 እስከ 2007 በነበሩት ዓመታት ውስጥ በአማካይ 123 በመቶ ውጤት እያስመዘገበ ተጉዟል፡፡ በ2008 ዓ.ም. 9.3 ሚሊዮን ሊትር የአልኮል መጠጥ አምርቷል፡፡ 88 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ አቅዶ 131 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈ ተገልጿል፡፡ የዓምና ጠቅላላ ሽያጩ 460 ሚሊዮን ብር እንደነበር የሚያስረዳው ድርጅቱ፣ የዚህ ዓመት ዕቅዱ 10.5 ሚሊዮን ሊትር የአልኮል መጠጦችና 4.3 ሚሊዮን ሊትር ንፁህ አልኮል ማምረት እንደሆነ ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህ ምርት ሽያጭ 508 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ በአማካይ 38.04 ሚሊዮን ብር በየዓመቱ ትርፍ ለማግኘት ቢያቅድም፣ ክንውኑ ግን 166 በመቶ እያደገ ስለነበር በአማካይ 63.01 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሎ ነበር፡፡

ባለፈው የዕድትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን መጀመሪያ ላይ ማለትም በ2003 ዓ.ም. 22.5 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ አቅዶ በአፈጻጸሙ 36.7 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ እንደቻለ ድርጅቱ አስታውሷል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን በየዓመቱ እያደገ ሄዶ በተለይ በ2007 ዓ.ም. ከዕቅዱ በላይ 104 ሚሊዮን ብር አትርፎ እንደነበር ጠቅሷል፡፡ በዕቅዱ መሠረት የሚታሰበው ትርፍ 64 ሚሊዮን ብር እንደነበር የድርጅቱ መረጃ ያሳያል፡፡

ከታክስ በፊት የተመዘገበው የ104 ሚሊዮን ብር ገቢ፣ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ላስቆጠረው ድርጅትና ከ100 ዓመታት በላይ ለቆየው ታሪኩ መዘከሪያ የሚሆን ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘት መቻሉ ተገጣጥሞሹን አሳምሮለታል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን፣ የትርፍ መጠኑ ይበልጥ እያደገ እንደሚሔድ ተገምቷል፡፡ ድርጅቱ ከ2008 እስክ 2012 ዓ.ም. ላሉት አምስት ዓመታት ያስቀመጠው ዕቅድ እንደሚያሳየው፣ የፋብሪካው የሽያጭ መጠን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስ ነው፡፡ ይህም አሁን ካለው የሽያጭ መጠኑ በእጥፍ የሚጨምር ነው፡፡   

ፋብሪካው የምርት መጠን ከማሳደግ ባለፈ የራሱን G+10 ሕንፃ እና የፍሳሽ ማጣሪያ ማሽን ተከላም እያከናወነ ነው፡፡ አዳዲስ ምርቶችንም ለገበያ እንደሚያበቃ አስታውቋል፡፡ በተለይ ቮድካ ለማምረት የሚያስችለውን ማሽን በመግዛት ተከላውን አጠናቆ የሙከራ ምርት እንደጀመረ አቶ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ብሔራዊ ቮድካ›› የሚል መጠሪያ ያለው የቮድካ ምርት በደንበኞች ቅምሻ ተደርጎበት ተቀባይነት ማግኘቱ የገለጹት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ገበያ ላይ ያልዋለው ለቮድካው ማሸጊያ ጠርሙስ እስኪዘጋጅለት ነው ብለዋል፡፡ አሁን ፋብሪካው በሚጠቀምበት ጠርሙስ አሽጎ ላለማውጣት ሲባል ለገበያ አልቀረበም ብለዋል፡፡ አዲስ የጠርሙስ ዲዛይን ተመርጦና በህንድ ተመርቶ በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ በመሆኑ፣ ብሔራዊ ቮድካ በጥቂት ወራት ውስጥ ለገበያ ይቀርባል ተብሏል፡፡ ፋብሪካው ቮድካውን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ምርቶቹንም በአዲስ ጠርሙስ አሽጎ እንደሚያቀርብ  ያመለከቱት አቶ ኃይለ ማርያም፣ አሁን ገበያ ላይ ያሉ ጠርሙሶች እንደሚቀየሩ ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ አረቄና አልኮል ፋብሪካ ለ110 ዓመታት በዘለቀው ታሪክ በአርመኖችና በተለያዩ የግል ኩባንያዎች ባለቤትነት ሥር ሲተዳደር ቆይቷል፡፡ በ1969 ዓ.ም. በደርግ መንግሥት አራቱ ፋብሪካዎቹ በመወረሳቸው በአንድ ተጨፍልቀው ሲተዳደሩ ነበር፡፡ ከደርግ በኋላም በኢሕአዴግ መንግሥት ባለቤትነት ሥር የቆየው ይህ ፋብሪካ፣ የተከፈለ ካፒታሉ 12.2 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከ450 በላይ ሠራተኞች እያስተዳደረ ሲገኝ፣ ጂንን ጨምሮ ከአሥር በላይ የተለያዩ የአረቄ ምርቶች፣ ንፁህ አልኮልና የእሳት አደጋ አልኮል ያመርታል፡፡ ከድርጅቱ የአረቄ ምርቶችም ግማሽ ያህሉ አዲስ አበባ ከተማ እንደሚሸጡ ታውቋል፡፡

  

Standard (Image)

የባህር ዳር ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንቱን አገደ

$
0
0

 

የባህር ዳር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቦርድ አባላት የንግድ ምክር ቤታቸውን ፕሬዚዳንት አገዱ፡፡ የቦርድ አባላቱ ፕሬዚዳንቱን ለማገድ የበቁት፣ በቅርቡ ከቦርድ ዕውቅና ውጭ ለአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አወዛጋቢ የተባለ ደብዳቤ በመጻፋቸው ነው ተብሏል፡፡

በፕሬዚዳንቱ የተጻፈው ደብዳቤ በአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት፣ የባህር ዳር ንግድ ምክር ቤትን ወክለው ተገኝተዋል የተባሉ ሦስት አባላት ክልከላ ተጥሎባቸው ስለመሆኑ ማረጋገጫ እንዲሰጥ ምክር ቤቱ ለተጠየቀበት ደብዳቤ፣ ያለቦርዱ ዕውቅና በራሳቸው ውሳኔ ማረጋገጫ ሰጥተው በመጻፋቸው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትን ካጋጠመው ችግር ጋር እንደሚያያዝ የሚገመተውን ውሳኔ የያዘው ይህ ደብዳቤ፣ ሁሉም የቦርድ አባላት ሊመክሩበትና ውሳኔ ሊሰጡበት የሚገባ ቢሆንም ይህ እንዲሆን ባለማድረጋቸው በፕሬዚዳንቱ ላይ ዕርምጃ እንዲወስዱ ማስገደዱን አባላቱ ገልጸዋል፡፡ የምክር ቤቱ ዘጠኝ የቦርድ አባላት በወሰኑት መሠረት የታገዱት አቶ ሙላቴ አበበ፣ የክልሉ የንግድ ምክር ቤት ለጠየቀው ማብራሪያ ቦርዱን ሳያሳውቁ በከተማው ንግድ ምክር ቤት ስም የራሳቸውን መግለጫ የያዘ ደብዳቤ መጻፋቸው ትክልል ባለመሆኑ የተወሰደ ዕርምጃ ነው ተብሏል፡፡

የቦርድ አባላቱ በታገዱት ፕሬዚዳንት ላይ ከመወሰናቸው በፊት የሠሩት ሥራ ስህተት በመሆኑ ይቅርታ እንዲጠይቁና ሥራቸውንም እንዲቀጥሉ የቀረበላቸውን ጥያቄ ሳይቀበሉ በመቅረታቸው ዕርምጃው እንደተወሰደባቸው ተነግሯል፡፡

አቶ ሙላቴ ቦርዱ ያቀረበላቸውን ሐሳብ ካለመቀበላቸውም በላይ ቦርዱ በእሳቸው ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ትክልል አለመሆኑን፣ እሳቸውን ማገድ የሚችለው ጠቅላላ ጉባዔ እንጂ ቦርዱ አለመሆኑን በመጥቀስ ተቃውሟቸውን በደብዳቤ ለቦርድ አባላቱ አቅርበዋል፡፡ ሳይመከርበት ወጭ ተደርጓል ስለተባለው ደብዳቤም ቦርዱን ሳያማክሩ ደብዳቤ መጻፍ እንደሚችሉና ይህንን የሚፈቅድ ሥልጣን እንዳላቸው አቶ ሙላቴ አስታውቀው እንደነበር፣ ከባህር ዳር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ንግድ ምክር ቤቱን የተመለከቱ ውሳኔዎችን መወሰን እንደሚችሉ፣ በዚህ ረገድ ቦርዱ እሳቸውን ለማገድ የሚበቃ ምንም ዓይነት ሥልጣን እንደሌለው በመግለጽ ውሳኔውን ተቃውመዋል፡፡ የቦርድ አባላቱ ግን ፕሬዚዳንቱ የሕግ ጥሰት መፈጸማቸውን በመግለጽ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋቸው እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡ ጉዳዩን ከሕግ አንፃር ለመፍታትም ለከተማው ንግድ ቢሮ እንዲቀርብ በማድረግ ፕሬዚዳንቱ የሕግ ስህተት ፈጽመዋል አልፈጸሙም የሚለውን ለማየት እንደተሞከረ ሪፖርተር የደረሰው መረጃ ይገልጻል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱም ሆነ ፕሬዚዳንቱ የተለዋወጧቸው ደብዳቤዎች ከሕግ አንፃር ተተንትነው እንዲታዩ ከተደረገ በኋላ አቶ ሙላቱ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ይቅርታ ጠይቀው፣ የጻፉት ደብዳቤም እንዲሻር ተደርጎ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ እንደተሞከረ ተነግሯል፡፡ ይቅርታ ጠይቀው እንዲመለሱ የተሰጠውን ዕድል  ባለመቀበላቸው ዘጠኙ የቦርድ አባላት በወሰኑት መሠረት ፕሬዚዳንቱ እንዲታገዱ መደረጋቸው ታውቋል፡፡

ፕሬዚዳንቱንና ንግድ ምክር ቤቱን ጨምሮ 11 የቦርድ አባላት ያሉት የባህር ዳር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ፕሬዚዳንቱ ከዕውቅናችን ውጪ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ወቅት፣ ከባህር ዳር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተወክለው ስለተሳተፉት ሦስት የቦርዱ አባላትና ተሳትፏቸውን የተመለከተ ማረጋገጫ የሚሰጥ ደብዳቤ መጻፋቸውን አስታውሷል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ታኅሳስ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ከአማራ ክልል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለተጻፈላቸው ደብዳቤ የቦርድ አባላቱን ሳያማክሩ የሰጡት ምላሽ እንዲህ የሚል አንቀጽ አካቷል፤‹‹...መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. የአማራ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ስድስተኛ መደበኛ ጉባዔ ወቅት ቀደም ብሎ ከተማችንን ወክለው በክልልና በአገር አቀፍ ንግድ ምክር ቤቶች በቦርድ አመራርነት ሲያገለግሉ ነበሩ...›› ይላል፡፡ ተወክለዋል የተባሉት ሦስት አመራሮች ለባህር ዳር ከተማ፣ ለአማራ ክልልና ለአገር አቀፍ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ካበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አንፃር በክልሉ ጉባዔ ላይ ለመወከል የሚያስችል ሁኔታ ነበር በማለት ደብዳቤው አክሏል፡፡

የአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በ2007 ዓ.ም. ባካሄደው ጉባዔ ወቅት ‹‹በሥራ ላይ ያለው ቦርድ ከከተማው ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ልዩ ክልከላ ካልተደረገበት በስተቀር በሥራ ላይ ባለበት ወቅት በሚያካሂደው ጉባዔ አባል ሆኖ መሳተፍ ይችላል፤›› ብሎ በወሰነው መሠረት፣ አባላቱ በጉባዔው እንዳይሳተፉ የሚከለክላቸው ሕጋዊ ነጥብ የሌለ መሆኑን በመግለጽ የተጻፈ ነበር፡፡

ይህ ደብዳቤ ለክልሉ ንግድ ምክር ቤት ሲጻፍ ቦርዱ እንዲያውቀው ማድረግ ይገባ ነበር የሚል መከራከሪያ አስነስቷል፡፡ በተለይ አቶ ሙላቴ ለክልሉ ንግድ ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤም ሆነ የክልሉ ፕሬዚዳንት ለባህር ዳር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የጻፉት ደብዳቤ ውስጥ ተወክለዋል የተባሉት ግለሰቦችም ስምና የሥራ ድርሻ ሳይጠቀስ በደፈናው ‹‹ሦስቱ›› እየተባለ የሚጠቅሳቸው ግለሰቦች ለጉባዔ መወከላቸው ነገሩን አክርሮታል፡፡

ይህ ሆን ተብሎ እንደተደረገ የሚገልጹ አስተያየት ሰጪዎች፣ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደውና አወዛጋቢ በነበረው የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት፣ ተወክለዋል ተብለው ከደፈናው ከሚጠቀሱት ሦስት የባህር ዳር ተወካዮች አንዱ አቶ ሙላቴ ራሳቸው መሆናቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ሆኖም በአማራ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጉባዔ ወቅት ከባህር ዳር ተወክለናል ብለው ለአገር አቀፍ ምክር ቤቱ የታጩ አሉ ከመባሉ ጋር ይያያዛል፡፡

ደብዳቤው በጉባዔው የተወከሉትን ሦስት ሰዎች ትቀበላላችሁ አትቀበሉም ለሚለው የክልሉ ንግድ ምክር ቤት ምላሽ እንዲሰጥ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ፕሬዚዳንቱን ያገደው ቦርድ ግን በታገዱት ፕሬዚዳንት የተጻፈው ደብዳቤ ቦርድና ምክር ቤቱ ያላመኑበት እንደሆነና አቶ ሙላቴ ስለሦስት ግለሰቦች ሕጋዊ ውክልና ማረጋገጫ የጻፉት ደበዳቤ እንዲሻር ማድረጋቸውን ያስረዳል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አቶ ሙላቴ በበኩላቸው፣ ተፈጠረ የተባለው ነገር በአሁኑ ወቅት በክልሉና በከተማው ንግድ ቢሮዎች የተያዘና የመጨረሻ ውሳኔ ያልተሰጠበት በመሆኑ አሁን ባለበት ደረጃ ምላሽ ለመስጠት እንደሚቸገሩ አስታውቀዋል፡፡ የባህር ዳር ንግድ ምክር ቤት ቦርድ ፕሬዚዳንቱ እንዲታገዱና ቀጣይ ጠቅላላ ጉባዔ እስኪጠራ ድረስ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የፕሬዚዳንትነቱን ሥራ ተክተው እንዲሠሩ በመወሰን መደበኛ ሥራውን እንደቀጠለ ይፋ ማድረጉ ታውቋል፡፡

 

Standard (Image)

በበልግ ወራት የዝናብ ሥርጭት መዳከሙ በድርቅ የተመቱ አካባቢዎችን የማገገም ዕድል አጥብቦታል ተባለ

$
0
0

 

  • በድጋሚ በተከሰተው ድርቅ ለ5.6 ሚሊዮን ዜጎች የሚያስፈልገው 948 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ማግኘት አልተቻለም

በባህር ሙቀት መጨመር ሳቢያ በተፈጠረው የአየር ፀባይ ለውጥ ሳቢያ ከ10.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ተዳርገው መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡ ይህ ክስተት መቃለል በጀመረበት ወቅት የበልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች በድጋሚ በተቀሰቀሰው የዝናብ እጥረት ምክንያት ከአምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለዕለት ደራሽ አስቸኳይ ዕርዳታ መዳረጋቸው ሲዘገብ ሰንብቷል፡፡

በበልግ ወቅት የሚጠበቀው የዝናብ ስርጭት መቀነሱም በበልግ ዝናብ አምራች የሆኑ አካባቢዎች የምርት መቀነስ እንደሚጠብቃቸው በመገመቱ፣ በድርቅ የተመቱትን አካባቢዎች ይበልጥ ሥጋት ውስጥ እንደከተታቸው ሪፖርቶች ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም በድርቅ የተመቱ የአርብቶ አደር አካባቢዎች የማገገም ተስፋቸውን ጥያቄ ውስጥ እንደከተተው የብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ትንበያዎች ዋቢ እየተደረጉ ነው፡፡ 

በበልግ ዝናብ በመታገዝ ከሚያመርቱ አካባቢዎች መካከል የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ክፍሎች በአብዛኛውም የደቡብ ሶማሌ ክልል፣ በኦሮሚያ የቦረና ቆላማ አካባቢዎች፣ የጉጂና የባሌ ዞኖች እንዲሁም የደቡብና የአፋር ክልሎች እንደ አዲስ ባገረሸው ድርቅ ተጎጂ መሆናቸው ሲታወቅ፣ ከየካቲት አጋማሽ እስከ ግንቦት ወር በሚኖረው የበልግ ወቅት የሚያገኙት ዝናብ ደካማ እንደሚሆን በመገመቱ የማገገም ዕድላቸውን አሳሳቢ አድርጎታል ተብሏል፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች እንደሚኖር የሚጠበቀው ደካማ የዝናብ ሥርጭት ከሚጠበቀው ከመደበኛውም ዝናብ ያነሰ እንደሚሆን በመገመቱ፣ ለበልግ ሰብሎች ታስቦ የሚደረገውን የመሬት ዝግጅትም ሆነ የሰብል መዝራት ተግባር በእጅጉ እንደሚጎዳው ይጠበቃል፡፡ የውኃ አቅርቦትንና እርጥበትን በመቀነስ በሚሳድረው ተፅዕኖ ሳቢያም ዜጎች ለምግብ እጥረትና ለተመጣጠነ ምግብ እጦት እንዲዳረጉ በር የሚከፍት በመሆኑ፣ ቀድሞውንም በድርቅ የተጎዱትን ይበልጥ ጉዳት ላይ እንደሚጥላቸው ሥጋት  ፈጥሯል፡፡

የበልግ አብቃይ የሆኑት አካባቢዎች ከ30 እስከ 60 ከመቶ የሰብል ምርታቸውን በበልግ ዝናብ አማካይነት የሚያገኙ በመሆኑ፣ የዝናቡ መምጣት በተስፋ ሲጠበቅ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ይፋ ባደረገው ትንበያ መሠረት የበልግ ዝናብ ዝቅተኛ ስለሚሆን፣ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎች በመዝራት በሰዎች ህልውና ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት መከላከል እንደሚገባ አስጠንቅቋል፡፡ ደረቃማነትን የሚቋቋሙ ሰብሎችን መዝራት፣ የዝናብ ውኃን ማቆር፣ ዕጥርበትን ማቆየት የሚቻልባቸው ዘዴዎች እንዲተገበሩም ኤጀንሲው  አሳስቧል፡፡

የአሜሪካ ግብርና መሥሪያ ቤትን መረጃዎች የሚያጣቅሱ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ አዲሱ የኢትዮጵያ ድርቅ 5.6 ሚሊዮኖችን ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያጋልጣቸው ይታመናል፡፡ ብሔራዊ የሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሚያስተባብራቸው 30 ያህል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎችና ሌሎች ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች የሚሳተፉበት ጥምረት፣  በጥር ወር መጀመሪያ አካባቢ ይፋ ባደረጉት ሰነድ መሠረት ለድርቁ መቋቋሚ ከ948 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ የሰብዓዊ ጉዳዮችና አስቸኳይ ዕርዳታዎች አስተባባሪ የተመድ ምክትል ዋና ፀሐፊ ስቴፈን ኦብራየን ይህንኑ በማስመልከት፣ በጥር ወር ኢትዮጵያን ለሦስት ቀናት በጎበኙበት ወቅት አስቸኳይ ዕርዳታ ለኢትዮጵያ መደረግ እንዳለበት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

ዓርብ ጥር 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ነገሬ ሌንጮ፣ ለ5.6 ሚሊዮን ዜጎች ያስፈልጋል የተባለውን የ948 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ በሚፈለገው መጠን ማግኘት እንዳልተቻለ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

ባንኮች ማኅበር ለሦስት የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ዕውቅና ሰጠ

$
0
0

የአገሪቱን ባንኮች በአባልነት ያቀፈው የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር፣ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውንም ሆነ ማኅበሩን በዕውቀታቸውና በጉልበታቸው በማገልገል አስተዋጽኦ ላበረከቱ የባንክ ፕሬዚዳንቶች ከኃላፊነታቸው በሚለቁበት ጊዜ ዕውቅና እንዲሰጣቸው ለማድረግ ወሰነ፡፡

ማኅበሩ ይኼንን ውሳኔ ያሳለፈው የማኀበሩን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም በገመገመበትና በልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመከረበት ስብሰባ ወቅት እንደሆነ የባንኮች ማኅበርና የደቡብ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ ገልጸዋል፡፡

እንደ  አቶ አዲሱ ገለጻ፣ ከዚህ ቀደም ለባንክ ባለሙያዎች ዕውቅና የመስጠት ልማድ ያልነበረ ቢሆንም አስፈላጊነቱ ስለታመነበት በየትኛውም መንገድ ከባንክ ፕሬዚዳንትነታቸው የሚለቁ ሰዎች ስላበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅና እንዲሰጣቸው ተወስኗል፡፡ ይህ የዕውቅና አሰጣጥም በቋሚነት እንደሚካሄድና እ.ኤ.አ. በ2016 ከፕሬዚዳንትነት ከለቀቁ ባለሙያዎች እንዲጀመር ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ውሳኔ መሠረት ይመሩት የነበረውን ባንክ ወክለው በማኅበሩ ውስጥ ሲያገለግሉ ቆይተው በተለያዩ ምክንያቶች ከሥራ ለለቀቁ ሦስት የባንክ ፕሬዚዳንቶች ዕውቅና በመስጠት ቋሚ መርሐ ግብሩን ጀምሯል ተብሏል፡፡

በመሆኑም ሐሙስ፣ የካቲት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በተሰናዳው ፕሮግራም ወቅት የጀመሪያዎቹ ዕውቅና የተሰጣቸው የቀድሞ የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባሕረ፣ የቀድሞ የቡና ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ እሸቱ ፋንታዬና የቀድሞ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለኢየሱስ በቀለ ናቸው፡፡

ሦስቱም ፕሬዚዳንቶች በአዲሱ የማኅበሩ ውሳኔ መሠረት ላበረከቱት አስተዋጽኦ መግለጫ የምስክር ወረቀትና ለእያንዳንዳቸው የወርቅ የጣት ቀለበት ተበርክቶላቸዋል፡፡   

የምስክር ወረቀቱንና የጣት ቀለበቱን በፕሮግራሙ ወቅት በመገኘት ያበረከቱላቸው ታዋቂው የባንክ ባለሙያ አቶ ለይኩን ብርሃኑ እንዲሁም በቅርቡ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሆነው የተሾሙት አቶ ጥሩነህ ሚጣፋ ናቸው፡፡

በዕለቱ በማኅበሩ ዕውቅና ከተሰጣቸው የቀድሞ የባንክ ፕሬዚዳንቶች ውስጥ አቶ ኢሳያስ ባሕረ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡ ያልተገኙበት ምክንያት ባይገለጽም ለክብራቸው የተዘጋጀው የምስክር ወረቀትና የጣት ቀለበት በማኅበሩ ጽሕፈት ቤት በኩል እንዲደርሳቸው ይደረጋል ተብሏል፡፡ አቶ ኃይለ ኢየሱስ፣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡

ማኅበሩ ለባንክ መሪዎች በቋሚነት መስጠት የጀመረውን ዕውቅና በተመለከተ ንግግር ያደረጉት አቶ ለይኩን፣ እንዲህ ያለው ተግባር የባንክ ባለሙያዎችን ያበረታታል ብለዋል፡፡ መለመድና መቀጠል ያለበት በጎ ተግባር መሆኑን በመግለጽ፣ በሌሎች ዘርፎችም እንዲህ ያለው ሥራ መለመድ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

 

Standard (Image)

የቆዳ ነጋዴዎች ማኅበር ዋጋ እያዛቡ ነው በማለት ፋብሪካዎችን ኮነነ

$
0
0

- መንግሥት በቆዳ ፋብሪካዎች ላይ ቁጥጥር እንዲያደርግ ጥሪ አቀረበ

በአገሪቱ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ገበያ ልቅ በመሆኑ ምክንያት ዘርፉን የሚመራ ሕግ ያስፈልጋል ያለው የኢትዮጵያ ጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ማኅበር፣ ቆዳ ፋብሪካዎች ይህንን ክፍተት በመጠቀም ዋጋ በማዛባት ገበያውን እየበጠበጡ እንደሚገኙ አስታወቀ፡፡

የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ አባተ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአገሪቱ ከ30 በላይ ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ቢኖሩም፣ ጥሬ ቆዳ የሚገበያዩበት መንገድ ልቅ በመሆኑ ለዋጋ መውደቅም ሆነ መናር ተጠያቂ ናቸው፡፡

ከአዲስ ዓመት ማግሥት ጀምሮ ባልተመለደ ሁኔታ የበግ ቆዳ ከ15 ብር ጀምሮ እስከ 30 ብር ሲሸጥ ታይቷል፡፡ እንዲህ በወረደ ዋጋ ሊሸጥ ከቻለባቸው ምክንያቶች መካከል የዓለም ዋጋ መውረድ እንደሆነ የቆዳ ፋብሪካዎችም ሆኑ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሲገልጽ መቆየቱን ይታወሳል፡፡ ይሁንና ቆዳ አቅራቢዎቹ ግን ይህ ሆን ተብሎ እየተፈጸመ የሚገኝ፣ ቆዳ ፋብሪካዎች መግዛት ሲፈልጉ አንዱ ከሌላው ዋጋ እየጨመሩና የገበያ ዋጋ እያዛቡ ሲሻሙ እንደሚታዩ የሚናገሩት አቶ ብርሃኑ፣ አልሆን ሲላቸው ደግሞ ጥሬ ቆዳ ነጋዴው በሕጋዊ መንገድ ከሕዝቡ በውድ ዋጋ ያጠራቀመውን ቆዳ ዋጋ አራክሰው አንገዛም እያሉ እንደሚገኙ በመግለጽ መንግሥት ተገቢውን የገበያ ሥርዓት እንዲያበጅለት ጠይቀዋል፡፡

ከ40 በላይ አባላትን በማሰባሰብ በሕጋዊ መንገድ ቆዳ አሳበስበው ለቆዳ ፋብሪካዎች ለማቅረብ የተቋቋመው ማኅበር፣ የበኩሉን እየጣረም ቢሆን ስምምነት የተደረሰባቸውን ነጥቦች ሳይቀር ፋብሪካዎች እየጣሱ ዋጋ በማዛባትና ገበያውን በማመሳቀል ነጋዴዎችን ለኪሳራ እየዳረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

እርስ በርሳቸው በሚሻሙበት ወቅት ሕጋዊ ያልሆኑ ሰብሳቢዎችንና ነጋዴዎችን በማሰማራት መንግሥት ለፋብሪካዎች እንዲቀርብላቸው የሠራውን ዋጋ በማጣረስ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ ፋብሪካዎች ለዋጋው መዘበራረቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በተለይ በአገር ውስጥና በውጭ ባለሀብቶች መካከል የሚታየው የጥሬ ቆዳ ሽሚያ ለዋጋው መውጣትና መውደቅ አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱን የጠቀሱት አቶ ብርሃኑ፣ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በቅርቡ ለሪፖርተር የሰጠው መግለጫ ማኅበሩን ቅር እንዳሰኘውም አልሸሸጉም፡፡

ፋብሪካዎች የሚረከቡበት ዋጋ እስከ 50 ብር እንዲደርስ መወሰኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ለገሠ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይሁንና ከዚህ ዋጋ በታች ገበያው ላይ ከ15 ብር ጀምሮ ሲሸጡ የነበሩ ሰዎች ማኅበሩ የማያውቃቸው፣ ሕገወጦች ከመሆናቸውም ባሻገር ከኅብረተሰቡ እንዲህ ባነሰ ዋጋ ገዝተው ለፋብሪካዎቹ እንዲያቀርቡ የሚያደርጉት ፋብሪካዎቹ እንደሆኑ በመግለጽ መንግሥት በአግባቡ እንዲያጣራው ማኅበሩ ጠይቋል፡፡

በተለይ ከመቶ ብር በላይ ሲሸጥ የሚታወሰው የበግ ቆዳ፣ በአሁኑ ወቅት በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች አምራቾች በብዛት እየታዩ ባሉበት ወቅት እንዲህ ታች የወረደበት ምክንያት ሆን ተብሎ ነው የሚሉት አቶ ብርሃኑ፣ የጥሬ ቆዳ ግብይትን የሚመራ ሕግ መንግሥት እንዲያወጣ አሳስበዋል፡፡ የዓለም ዋጋ ስለወረደ፣ የህንድ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ገበያ ስለተቀዛቀዘ ነው አለያም የቻይና ገበያ ስለተዳከመ ነው የሚሉ ምክንያቶች እንደማያዋጡ የሚገልጹት አቶ ብርሃኑ፣ በአገር ውስጥ ያለው ገበያና ዋጋው በመዛባቱ ምክንያት ከ20 ሺሕ እስከ 30 ሺሕ ጥሬ ቆዳ ገዝተው ለፋብሪካዎች ለማቅረብ ሲጠባበቁ የነበሩ ነጋዴዎች የሚገዛቸው በማጣት ለኪሳራ መዳረጋቸውንና ቆዳውም በመበላሸቱ ምክንያት ለመጣል መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ቆዳ እንዲህ ዋጋ እያጣ እንዲጣል የሚደረግ ከሆነ ወደፊት ከፍተኛ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ሥጋታቸውን በመግለጽም፣ በአሁኑ ወቅትም የበሬ ቆዳ ፈላጊ እያጣ ጥራቱም ችግር እየገጠመው እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ ዋጋው እጅግ በመውረዱ ሳቢያ ገበሬውም ሆነ ሌላው ተጠቃሚ አካል ለቆዳ የሚያደርገውን ጥንቃቄ እየተወ በመሆኑ ችግር እየተፈጠረ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው የበግ ቆዳም ባልተገባ ሁኔታ ዋጋው የሚበላሽ ከሆነ፣ ኅብረተሰቡ ጥቅም ለማያገኝበት ቆዳ ጥንቃቄ ማድረግ ትርጉም የለውም የሚል አዝማሚያ ሊፈጠር እንደሚችልም ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በቆዳ ነጋዴዎች ቅሬታ የቀረበባቸው ፋብሪካዎች ምላሽ እንዲሰጡበት ለማድረግ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበርን ለማነጋገር በተደጋጋሚ የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ይሁንና የጥሬ ቆዳ ዋጋ እየተሻሻለ መምጣቱ ቆዳ ነጋዴዎች የሚደግፉትን ያህል ፋብሪካዎቹ የማይቀበሉት መሆኑ እየታየ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ይመስላል መንግሥት ፋብሪካዎች የሚረከቡበትን ዋጋ በስምምነት እንዲወሰን ሁለቱንም ወገን ለማግባባት ሲጣጣር የከረመው፡፡

በአንፃሩ ነጋዴዎች በአቅርቦትና በፍላጎት ላይ መሠረት ያደረገ የዋጋ ትመና እንዲኖር፣ በተለይም ነጋዴውን ከሕዝቡ የሚገዛበት፣ ለቆዳ ጥራት ማስጠበቂያ በተለይ በጨው ለማልፋት የሚያወጣው ወጪ፣ የትራንስፖርት ወዘተ ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ማኅበሩ ይፈልጋል፡፡ መንግሥትም ነጋዴዎች ከኅብረተሰቡ ጥሬ ቆዳ እስከ 40 ብር ድረስ በመክፈል እንዲገዙ፣ ለፋብሪካዎችም በ50 ብር እንዲያቀርቡ የሚያስማማ ሐሳብ አቅርቦ በዚሁ መሠረት እየተሠራ ቢሆንም፣ የዋጋ መጨመር በመታየቱና የቆዳ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ዋጋ ጨምረዋል በማለት ኢንስቲትዩቱ ነጋዴዎችን መውቀሱ አይዘነጋም፡፡

ይህ አግባብ አይደለም የሚሉት አቶ ብርሃኑ፣ ዋጋው ሲጨምር ብቻም ሳይሆን ሲወድቅም ትኩረት ተሰጥቶት ለምን እንደተፈጠረ መከታተል ይገባል ብለዋል፡፡ መንግሥት ፋብሪካዎችን መቆጣጠር አለበት ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ 60 በመቶ የጥሬ ዕቃ አቅርቦታቸው ቆዳ የሆነው ፋብሪካዎች በዱቤ የሚገዙበት አሠራርም ሊታይ ይገባዋል ብለዋል፡፡ አብዛኞቹ በቂ የሥራ ማስኬጃ የሌላቸው፣ ከአቅማቸው በታች የሚያመርቱ  ሆነው በመገኘታቸው፣ በመንግሥት እንደ አዲስ የተቋቋመው የኢንዱስትሪ ዕቃዎች አቅራቢ ድርጅት ባደረገላቸው ዕገዛ ሳቢያ ጥሬ ቆዳ ለመግዛት መብቃታቸውም ታውቋል።

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ባለው ሁኔታ በያመቱ ለፋብሪካዎች መቅረብ ከሚገባው 40 ሺሕ ቶን ቆዳ ውስጥ ግማሹ ብቻ እየቀረበላቸው እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ ይህም ሆኖ እየቀረበ ያለውም ቆዳ በዋጋና በጥራት ችግር በተገቢው መንገድ በፋብሪካዎች ዘንድ ተቀባይነት እንደማያገኝ ነጋዴዎች ይገልጻሉ፡፡

መንግሥት እሴት ያልተጨመረበት ወይም በከፊል ያለቀለት ቆዳ ወደ ውጭ እንዳይላክ ለመግታት የ150 በመቶ የወጪ ንግድ ታክስ መጣሉ ይታወሳል፡፡ ይህ በመሆኑ ምክንያትም በከፊል ያለቀለት ቆዳ ወደ ውጭ መውጣት ካቆመ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ መንግሥት ያሰበውን ያህል ያለቀለት ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ለውጭ ገበያ ማቅረብ አልቻለም፡፡ በዚህ ዓመት ስድስት ወራት እንኳ ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ለማግኘት ከታቀደው 113 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ከግማሽ ያነሰው ገቢ መገኘቱ ይታወቃል፡፡

 

Standard (Image)

በሐዋሳ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የብረታ ብረት ፋብሪካ ተገነባ

$
0
0

- የአንድ ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው አራት ፋብሪካዎች በመጪው ዓመት ሥራ ይጀምራሉ

አለታ ላንድ ቢዝነስ ግሩፕ የተባለ ኩባንያ፣ በመጪው ዓመት ወደ ሥራ ከሚያስገባቸው አራት ትላልቅ ፋብሪካዎች መካከል የ560 ሚሊዮን ብር ካፒታል የሚጠይቀውን የብረታ ብረት ፋብሪካ ግንባታ በማገባደድ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

 የግሩፕ ኩባንያው ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ሲላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሐዋሳ ከተማ ሲገባ ትልቅና የመጀመሪያ የሆነውን ብረት ማቅለጫ ፋብሪካን ጨምሮ የፓስታና መኮረኒ ማምረቻ፣ በገላን ከተማ የወረቀት ፋብሪካ እንዲሁም በዱከም የውበት መጠበቂያ ኮስሜቲክሶችን የሚያመርት ፋብሪካ ግንባታዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የሁሉም ፋብሪካዎች ግንባታ በመገባደድ የማሽን ተከላ መጀመሩን አቶ ሀብታሙ አብራርተዋል፡፡

በሐዋሳ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው አለታ ላንድ የብረት ማቅለጫ ፋብሪካ ከ13 ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ በሆነ ቦታ ላይ የሰፈረ ሲሆን፣ በዓመት 300 ሺሕ ቶን ብረት የማምረት አቅም እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፋብሪካው ሥራ ሲጀምር ለ200 ሰዎች የሥራ ዕድል ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በክልሉ በዚህ ደረጃ የብረት ማቅለጫ ፋብሪካ ሲገነባ የመጀመሪያው እንደሆነና ይህ ፋብሪካ ለግንባታ የሚሆኑ ብረቶችን በደቡብ ክልል ማምረት መቻሉ ከሌሎች አካባቢዎች የሚጓጓዘውን መጠን እንዲቀንስ በማድረግ የግንባታ ሥራዎችን እንደሚያፋጥን አቶ ሀብታሙ ይናገራሉ፡፡ ይህ ፋብሪካ ከስምንት እስከ 24 ሚሊ ሜትር መጠን ያላቸውን የአርማታ ብረቶች በማምረት የክልሉን የብረታ ብረት ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ለሌሎች ገበያዎችም ሊያቀርብ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በሐዋሳ ከተማ የሚገነባው ሌላው ፕሮጀክት የፓስታና የዱቄት ፋብሪካ ነው፡፡ በ190 ሚሊዮን ብር ካፒታል የሚገነባው ይህ ፋብሪካ በ2010 ዓ.ም. ሥራ ይጀምራሉ ከተባሉት ውስጥ ሲመደብ፣ ከውጭ የሚገባውን የፓስታና የማካሮኒ መጠን ለመተካት እንደሚያግዝና ለ200 ሰዎችም የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

በገላን ከተማ በ10 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ80 ሚሊዮን ብር ካፒታል ግንባታው ተገባዶ እንደሌሎች ፋብሪካዎች ማሽን እየተገጠመለት ያለው የወረቀት ፋብሪካ ነው፡፡ ይህ ፋብሪካ ለማንኛውም ዓይነት የሕትመት አገልግሎት የሚውል ወረቀት የሚያመርት ሲሆን፣ በዓመት ሰባት ሺሕ ቶን ያመርታል ተብሏል፡፡ ለ60 ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚሰጥም ይጠበቃል፡፡

ግሩፕ ኩባንያው እየገነባቸው ከሚገኙት አራተኛው የሆነው ለውበት መጠበቂያ የሚሆኑ ቅባቶች ማምረቻ ፋብሪካ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ለውበት መጠበቂያነት ከሚውሉት ቅባቶች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው፣ የፋብሪካው ግንባታ ሲጠናቀቅ በዚህ መስክ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ ሲበጠቅ፣ 80 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ በ12 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አብዛኛው የፋብሪካው ግንባታ ተጠናቆ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ዝርጋታ የማሽን ተከላ እየተካሄበደት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ከ80 በላይ ሠራተኞች እንደሚቀጥርም ይጠበቃል፡፡ ሁሉም የአለታ ላንድ ግሩፕ ፋብሪካዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሥራ የሚጀምሩ ከሆነ፣ ከ540 በላይ በተለያየ ደረጃ ያሉ የሚሰማሩ ሠራተኞች ያስፈልጓቸዋል፡፡  

አቶ ሀብታሙ እንደሚናገሩት፣ ኩባንያው በአባታቸው የቡና ንግድ መነሻነት ቀስ በቀስ እዚህ የደረሰ ሲሆን፣ ወደፊት የሚከፈቱትን ፋብሪካዎች ጨምሮ ሰባት ድርጅቶች በሥሩ ያሉት ሲሆን በንግድ፣ በእርሻ ሥራ፣ በፋብሪካ፣ በመዝናኛ እንዲሁም በአስመጪና ላኪነት ሥራ ላይ የሚሳተፉ ድርጅቶችን ያስተዳድራል፡፡ በጉዟቸው በጣም ፈታኝ አጋጣሚዎችን በማለፍ አሁን ለሚገኙበት ደረጃ መድረሳቸውን በማስታወስ፣ አሁንም ግን ሊፈቱ ያልቻሉ ችግሮች ድርጅቶቻቸውን እያጋጠሟቸው እንደሚገኙ አቶ ሀብታሙ ይናገራሉ፡፡ የሠራተኛው የባለቤትነት ስሜት መቀዛቀዝ፣ የተማረ የሰው ኃይል እንደልብ አለማግኘት ለድርጅቱ ፈተና እንደሆኑበት ጠቅሰዋል፡፡

በመንግሥት በኩልም መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አውስተው በቅርቡ በሐዋሳና በዱከም በመዝናኛው ዘርፍ አዳዲስ ይዘቶችን በማምጣት ግንባታቸው ተጠናቆ ለሕዝብ ክፍት የሚሆኑ ተቋማት እንዳሉም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አለታ ላንድ ግሩፕ የቤተሰብ ድርጅት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል የሚያንቀሳቅስ፣ በሥሩም ከአራት ሺሕ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች እንደሚያስተዳድር ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዋጭ ቢዝነሶችን በማስጠናት እስከ መጪው 2030 ላለው ጊዜ ዕቅድ በመንደፍ በተለያዩ ዘርፎች እስከ 20 ሺሕ  ሠራተኞችን የሚያስተዳድሩ ድርጅቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየሠሩ ስለመሆናቸውም የኩባንያቸው ሰነዶች ይጠቁማሉ፡፡ 

Standard (Image)

ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ መንገዶች በአዲስ አበባ ሊገነቡ ነው

$
0
0

ከጥቂት ወራት በፊት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣንን እንዲመሩ በቀድሞው ሥራ አስኪያጅ እግር የተተኩት ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ፣ አዲሱን የኃላፊነት ቦታ ሲረከቡ ቀዳሚ ያደረጉት ተግባር በአራቱም የከተማዋ አቅጣጫዎች የሚገኙ የተበላሹ መንገዶችን መጠገን ነው፡፡

ባለሥልጣኑ ከዋና ተግባራቱ መካከል የሚያሰፍረው የአዲስ አበባ መንገዶች ጥገና ሥራ በእስካሁኑ ሒደት 80 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ መንገዶችን ለመጠገን አብቅቶታል፡፡ ይህ ተግባር ቀጥሏል፡፡ ለመንገድ ጥገና ተብሎ ከአስተዳደሩ የተመደበው 270 ሚሊዮን ብርም ለጥገና የተመደበ ከፍተኛው በጀት ሆኗል፡፡ ለከተማዋ የትራፊክ መጨናነቅ መንስዔ ናቸው የተባሉ አደባባዮችን በማፍረስና ለትራፊክ ፍሰቱ አመቺ እንዲሆኑ ለማድረግ በአዲሱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሚመራው ባለሥልጣን እስካሁን ሁለት አደባባዮችን በማፍረስ፣ በምትኩ ተሽከርካሪዎች በትራፊክ መብራት እንዲስተናገዱ አድርጓል፡፡ በተለይ በቀለበት መንገድ ውስጥ የሚገኙ አደባባዮችም ተራቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡ የዕድሳቱ ሥራ ለተጨናነቀው የከተማው የትራፊክ ፍሰት ማስተንፈሻ በመሆን፣ በተወሰነ ደረጃ ማቃለል እንዳስቻለ እየታየ ነው፡፡

እንዲህ ባሉ ተግባራት ከግማሽ ዓመት በላይ ለዘለቁት ኢንጂነር ሀብታሙ፣ የጥገና ሥራዎቹ መበራከት አዲስ የመንገድ ግንባታ ውሎች እንዳይፈርሙ ተፅዕኖ ሳያሳድርባቸው አልቀረም፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ባለሥልጣኑ ከ200 በላይ የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን እያስተዳደረ ቢሆንም፣ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ በአንድ የበጀት ዓመት አዲስ ኮንትራት ሳይፈርም ከግማሽ ዓመት በላይ የቆየበት ጊዜ እስካሁን አልነበረም፡፡

ዓርብ የካቲት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ባለሥልጣኑ በሰፊው ከተያያዘው የመንገድ ጥገናና የትራፊክ ፍሰትን የማቃለል ሥራ ላይ ካነጣጠረው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ከአገር በቀል ኮንትራክተሮች ጋር ውለታ ገብቷል፡፡ ኢንጂነር ሀብታሙም አዲሱን ኃላፊነታቸውን ከተረከቡ ወዲህ የመጀመሪያቸው በሆኑት  የመንገድ ግንባታ ስምምነቶች ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ስምንተኛው ወር ላይ ስምምነት የተፈረሙባቸውና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገነቡት አምስቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች በጥቅሉ ከ887 ሚሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ ናቸው፡፡

ኢንጂነር ሀብታሙ እንደገለጹት፣ ከአምስት ተቋራጮች ጋር ውለታ የተፈጸመባቸው አምስት ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ ከ20 እስከ 30 ሜትር ስፋትና ከ11 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው መንገደች ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተመደበው በጀት የግንባታ ወጪያቸው የሚሸፈኑትን መንገዶች ለመገንባት በጨረታ ያሸነፉት ተቋራጮች፣ ድሪባ ደፈሻ፣ ተክለብርሃን አምባዬ፣ የማነ ግርማይ፣ ስናንና ኢትዮ ጠቅላላ የተባሉት ተቋራጮች ናቸው፡፡

መንገዶቹ ለከተማው ሕዝብ የተቀላጠፈ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲያገኝ ከማድረግ ባሻገር፣ የመንገድ ሽፋኑ እንዲሻሻል የሚያስችሉ ናቸው ተብሏል፡፡ የግንባታ ሒደታቸውም የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላንን ተከትለው ለነባር መንገዶች ደረጃውን የጠበቀ ዲዛይን ሠርቶ የማስፋት ሥራንና ለአዳዲስ ኮንዶሚኒየም ቤቶች አዲስ የመንገድ መሠረተ ልማት የማቅረብን ሥራ እንደሚያጠቃልሉ ኢንጂነር ሀብታሙ ገልጸዋል፡፡

በከተማው ማስተር ፕላን መሠረት ከሚገነቡ ነባር መንገዶች መካከል አራራት ሆቴል፣ ኮተቤ ኮሌጅ ካራ የመንገድ ሥራ ይጠቀሳሉ፡፡ የዲዛይን ሥራው በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ የተሠራው ይህ መንገድ ለሁለት ተቋራጮች ተከፍሎ ተሰጥቷል፡፡

በዕለቱ እንደተገለጸው ከሁለቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ የሆነውና በ5.94 ኪሎ ሜትር ርዝመትና በ30 ሜትር ስፋት የሚገነባው ከአራራት ሆቴል እስከ ኮተቤ ኮሌጅ ያለውን ፕሮጀክት ለመገንባት በጨረታ ያሸነፈው ዲሪባ ደፈርሻ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ነው፡፡ የጨረታ አሸናፊ በመሆን ሥራውን የተረከበበት ዋጋ 272.9 ሚሊዮን ብር መሆኑም ታውቋል፡፡ የግንባታ ሥራው በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ 2.84 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 30 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ ከኮተቤ ኮሌጅ እስከ ካራ ያለውን አካባቢ የሚሸፍን ነው፡፡ ይህንን መንገድ ለመገንባት በጨረታ ያሸነፈው ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ነው፡፡ ለመንገዱ ሥራ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ በ260.7 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡ ተክለብርሃን አምባዬ በአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ግንባታ ሥራ ሲረከብ የመጀመሪያው ነው፡፡ ለዚህ መንገድም የተያዘለት የግንባታ ጊዜ ሁለት ዓመት ተኩል ነው፡፡

በተጨማሪም ከሲቪል ሰርቪስ መገንጠያ ጉርድ ሾላ መንገድ ሥራ ፕሮጀክት በ68.9 ሚሊዮን ብር አሸናፊ የሆነው የማነ ግርማይ ተቋራጭ ነው፡፡ 1.04 ኪሎ ሜትር ርዝመትና የ20 ሜትር ስፋት ያለው ይህንን መንገድ በ240 ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ ውለታ ተገብቶለታል፡፡

ለአዳዲስ የኮንዶሚኒየም ቤቶች አዲስ የመንገድ መሠረተ ልማት ለማቅረብ ከሚከናወኑት ሁለት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው የተባለውን የቦሌ አራብሳ ኮንዶሚኒየም-አያት ኮንዶሚኒየም መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ደግሞ ስናን የተባለው ኮንስትራክሽን ኩባንያ በ194 ሚሊዮን ብር ይገነባዋል፡፡ በ540 ቀናት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል፡፡ የኮሎ ፍቼ ሁለት ኮንዶሚኒየም የመንገድ ሥራ ፕሮጀክትን ደግሞ ኢትዮ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ በ79.6 ሚሊዮን ብር ገንብቶ ለማስረከብ ተዋውሏል፡፡ ለግንባታ የተሰጠውም ጊዜ 365 ቀናት ናቸው፡፡

በዕለቱ ግንባታቸው እንዲፈጸም ከሥራ ተቋራጮች ጋር ውለታ የተፈጸመባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ በከተማዋ የመንገድ መሠረተ ልማት አቅርቦት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያመጡ የታመነባቸው መሆኑን ኢንጂነር ሀብታሙ ገልጸዋል፡፡ የመንገድ ግንባታዎቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንደውም ከዚያ በፊት መጠናቀቅ እንዳለባቸው ያስገነዘቡት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ጥራቱን በጠበቀ ደረጃ እንደገነቡ አሳስበዋል፡፡ ተቋራጮችም ሥራውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ 

Standard (Image)

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በ240 ሚሊዮን ብር የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ሊገነባ ነው

$
0
0

- ሦስትሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ተረክቧል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ለአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ የሚውል ቦታ በመነሻ የሊዝ ዋጋ እንዲሰጠው በመወሰነው መሠረት ንግድ ምክር ቤቱ ቦታውን መረከቡ ተገለጸ፡፡  

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ንግድ ምክር ቤቱ የራሱን ሕንፃ ለመገንባት ባቀረበው የቦታ ጥያቄ መሠረት መገናኛ አካባቢ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ጽሕፈት ቤት አጠገብ በአነስተኛ የሊዝ ዋጋ እንዲሰጠው የተወሰነለት ቦታ ሦስት ሺሕ ካሬ ሜትር ስፋት አለው፡፡

እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፣ አስተዳደሩ ለንግድ ምክር ቤቱ የሕንፃ ግንባታ የፈቀደለት ቦታ እንዲሰጠው የተወሰነው በካሬ ሜትር 4,140 ብር የሊዝ ዋጋ መሠረት ነው፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ በተረከበው ቦታ አካባቢ ካለው የሊዝ ዋጋ እጅግ ዝቅ ባለ ዋጋ እንዲተመንለት አስተዳደሩ ከፍተኛ እገዛ አድርጎለታል ተብሏል፡፡

ለ60 ዓመታት በሚቆይ ሊዝ የተሰጠው ይህ ቦታ ጠቅላላ የሊዝ ዋጋው 12.4 ሚሊዮን ብር መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ በ30 ዓመት ተከፍሎ እንደሚያልቅ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ መሠረት ከጠቅላላው የሊዝ ዋጋ ውስጥ የቅድሚያ ክፍያውን 20 በመቶ ገንዘብ ማለትም የ2.1 ሚሊዮን ብር ሒሳብ ንግድ ምክር ቤቱ መክፈሉን አስታውቋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ የራሱን የሕንፃ ዲዛይን ካሠራ ከአራት ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ የሚታወቅ ሲሆን፣ ለግንባታ የሚሆነውን ቦታ ለማግኘት ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ሲጠባበቅ ቆይቷል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ በማግኘቱ ወደ ግንባታ ለመግባት መዘጋጀቱን አቶ ጌታቸው ገልጸው፣ አርክቴክቶችን በማወዳደር ከዚህ ቀደም መርጦት በነበረው የሕንፃ ዲዛይን ላይ መጠነኛ ማስተካከያዎች ከተደረጉ በኋላ ወደ ግንባታ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

በዲዛይኑ ላይ ይደረጋሉ ተብለው ከሚጠበቁ ለውጦች መካከል ቀደም ብሎ G+10 የነበረውን የሕንፃ ወለል ብዛት አሁን G+11 ማድረግ አንዱ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ግንባታው በሚካሄድበት አካባቢ መገንባት የሚፈቀደው የሕንፃ ወለል ብዛት ከG+10 በላይ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ዲዛይኑን ለማስተካከል የዲዛይን ክለሳ ሥራ መጀመሩን አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል፡፡

ዲዛይን የማስተካከል ሥራውንና የግንባታ ፈቃድ ሒደቱን በሦስት ወራት ውስጥ አጠናቆ ለግንባታ ተቋራጮች ጨረታ እንደሚወጣ ከዋና ጸሐፊው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የግንባታ ሥራውም በመጪው ዓመት ለማስጀመር መታቀዱን፣ ለሕንፃው ግንባታ የሚውለውን ወጪም ንግድ ምክር ቤቱ ከሚያዘጋጃቸው የገቢ ማሰባሰቢያዎችና ከተለያዩ ምንጮች ለመሸፈን ማቀዱን አቶ ጌታቸው ጠቅሰዋል፡፡

ለንግድ ምክር ቤቱ ዋና መሥሪያ ቤትነት የሚውለው ሕንፃ፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎች እንደሚኖሩት ታውቋል፡፡ አነስተኛ የንግድ ዓውደ ርዕይ ማካሄጃ አዳራሽን ጨምሮ፣ የባንክና የኢንሹራንስ ድርጅቶች የሚጠቀሙባቸው ክፍሎችም ይኖሩታል፡፡ ከንግድና ኢንቨስትመንት ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች የሚሰጡበት አዲሱ ሕንፃ፣ ለንግድ ኅብረተሰቡ መሰብሰቢያነት የሚያገለግሉ፣ አዳራሾችም ይኖሩታል ተብሏል፡፡

የዚህ ሕንፃ ግንባታ ዕውን መሆን ንግድ ምክር ቤቱ ከ70 ዓመታት ቆይታው በኋላ የራሱ ሕንፃ ባለቤት እንዲሆን ያስችለዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለሕንፃው ግንባታ ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግ ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት፣ ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሕንፃ የተወሰኑ ክፍሎች በመጋራት እየተገለገለ ይገኛል፡፡ ለአንዳንድ የሥራ ክፍሎቹ የሚጠቀሙባቸውን ቢሮዎች ከሌሎች ሕንፃዎች ተከራይቶ ሲገለገል ቆይቷል፡፡ ‹‹ይህም ሆኖ በቢሮ እጥረትና ምክንያት መሥራት የምንችለውን ያህል ልንሠራ አላስቻልንም፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ለቢሮዎች ኪራይ በዓመት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ምክር ቤቱ እንደሚያወጣ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በከተማና በክልል ደረጃ ከተዋቀሩት ንግድ ምክር ቤቶች ውስጥ የራሳቸው ሕንፃ ባለቤት እንደሆኑ የሚጠቀሱት የአዳማ፣ የድሬዳዋና የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ናቸው፡፡

 

Standard (Image)

ምርጥ ቡናዎች ጉባዔ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ እንዲያንሰራራ ተስፋ ተጥሎበታል

$
0
0

ለአንድ ዓመት ያህል በአገሪቱ የተካሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ የአገሪቱ የቡና ወጪ ንግድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ መቆየቱ ይታመናል፡፡ ምንም እንኳ ቡና እየተላከም ቢሆን የቀድሞውን ያህል እየወጣ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ ወደ ውጭ የሚላከውን ቡና ይበልጥ ለማሻሻል እንደሚረዳ ተስፋ የተደረገበት ‹‹አፍሪካን ፋይን ኮፊስ ኮንፈረንስ ኤንድ ኤግዚቢሽን›› የተባለው ጉባዔ፣ ከወዲሁ አንድ ሺሕ ያህል የውጭ ታዳሚዎች እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል፡፡

በአፍሪካ የምርጥ ቡናዎች ማኅበር (አፍሪካን ፋይን ኮፊስ አሶሲዬሽን አፍሪካ) አማካይነት በየዓመቱ በአባል አገሮች እየተዟዟረ የሚካሄደው ጉባዔ ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በተለያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ ተሰናድቷል፡፡ በይፋ የሚከፈተው ዛሬ፣ የካቲት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ቢሆንም ካለፈው እሑድ ጀምሮ ግን የተለያዩ ዝግጅቶች ሲካሄዱበት ቆይቷል፡፡

ጉባዔው ለኢትዮጵያ የቡና ወጪ ንግድ ተስፋ የተጣለበት፣ በኢትዮጵያ በተፈጠረው ፖለቲካዊ ትኩሳት ምክንያት የውጭ ገዢዎች ከአገሪቱ የሚፈለገውን ያህል ቡና ማግኘት እንደማይቻል ያደረባቸውን ሥጋት ለመቅረፍ እንደሚረዳ ስለታመነበት መሆኑን፣ የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢና የኤስኤ ባገርሽ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብደላ ባገርሽ ጠቅሰዋል፡፡ አብዛኞቹ የውጭ ገዥዎች በአገሪቱ ታድመው ሁኔታውን ተመልክተው ቡና ለመግዛት ሥጋት እንዳይገባቸው ለማድረግ እንደሚረዳ ለሪፖርተር በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል፡፡

ጉባዔው ይካሄዳል በተባለበት ጊዜ ሳይዛነፍ ከየካቲት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ አቶ አብደላ ገልጸዋል፡፡ ከወራት በፊት ጉባዔው በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ ይፋ ቢደረግም በአገሪቱ የተከሰተው ሕዝባዊ ተቃውሞና አለመረጋጋት፣ የውጭ ተዳሚዎች እንዳይገኙ እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ማኅበሩ ግን በኢትዮጵያ ጉባዔው ያለችግር መካሄድ እንደሚችል ማረጋገጫ በመስጠት የውጭ ተሳታፊዎች እንዲገኙ ጥሪ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከውጭ ከሚመጡት ባሻገር በአገር ውስጥ በቡና መስክ የተሰማሩ አካላትም በብዛት እንዲታደሙበት ጥሪ ቀርቧል፡፡

የአገሪቱ ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቦ ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ባሻገር በአገር ውስጥ ያለው የገበያ ድርሻም ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህም በላይ በቡና እርሻና በንግድ ሥራ የተሰማሩ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎችም የህልውናቸው መሠረት በመሆኑ ፋይዳው በእጅጉ የሚታወቅ ቢሆንም፣ በተከታታይ ዓመታት በተለይ ለውጭ ከሚቀርበው የቡና ምርት እየተገኘ ያለው የውጭ ምንዛሪ ገቢ እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡  

የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በግማሽ ዓመቱ 98,561 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ይቀርባል ተብሎ ሲጠበቅ ማቅረብ የተቻለው ግን 85,425 ቶን ሆኗል፡፡ ከገቢ አንፃርም ቡና ያስገኛል ተብሎ የሚጠበቀው መጠን 385 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ የተገኘው ግን 315.7 ሚሊዮን ዶላር በመሆኑ ገቢው ከዕቅዱ በ19 በመቶ ያህል ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በአንፃሩ በ2008 ግማሽ ዓመት ለውጭ ገበያ የቀረበው ቡና መጠን 87,785 ቶን ሲሆን፣  በ2009 በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት ወደ ውጭ ከተላከው ጋር ሲነፃፀር በ2,332 ቶን ወይም በ2.7 በመቶ የቀነሰ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡  ከገቢ አንፃር የተገኘው የውጭ ምንዛሪ በዘንድሮ ግማሽ ዓመት የ2.8 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ባለፉት ጥቂት ወራት የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ መጠነኛ መሻሻል በማሳየቱ እንደሆነ ባለሥልጣኑ ጠቅሷል፡፡

የባለሥልጣኑ መረጃ ይህን ጨምሮ ከዚህ ቀደም ዕርምጃ በወሰደባቸው ላኪዎች አማካይት የውጭ ገበያው በተፈለገው መጠን ሊሳካ እንዳልቻለ ይጠቁማል፡፡ ባለፉት ዓመታት በሕገወጥ መንገድ የኤክስፖርት ቡና ምርት ከገበያ ገዝተው መላክ ባልቻሉ ላኪዎች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ ከመወሰዱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የባለሥልጣኑ የስድስት ወራት ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በምርት ገበያው ያላቸውን ወንበር በመጠቀም ምርት የገዙላቸው አንዳንድ የምርት ገበያው አገናኝ አባላት በሆኑ ላኪዎች ላይ የተወሰደው የዕግድ ዕርምጃ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡

የዓለም የቡና ገበያ ዋጋ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የተሻለ እንደሆነ የሚጠቁመው የባለሥልጣኑ ሪፖርት፣ ቡና ላኪዎች በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት  (ከሐምሌ እስከ መስከረም) ቀደም ብሎ የዓለም ቡና ዋጋ ዝቅተኛ በነበረበት ወቅት ላይ ኮንትራት በመፈጸማቸው ከአገር ውስጥ ዋጋ ጋር መናበብና በግዥ መሟላት አለመቻሉ ለአፈጻጸሙ መቀነስ ምክንያት ሆኖ ቀርቧል፡፡

ባለፈው ዓመት በተከሰተው የአየር ጠባይ ለውጥና ድርቅ ምክንያት በቡና ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፈጠሩ፣ ጥቂት ላኪዎች የገቡትን ውል ለማክበር ተገቢውን ጥረት አለማድረግ፣ ቡና ገዥ ኩባንያዎችም አዲሱን ምርት የመጠበቅ አዝማሚያ ማሳየታቸው ለቡና ደካማ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ምክንያት ሆነው ቀርቧል፡፡ ላኪዎች በበኩላቸው ግን በአገሪቱ የተከሰተው ግርግርም አስተዋጽኦ ማበርከቱን እየተናገሩ ነው፡፡

                                                    

Standard (Image)

ለ20 ኪሎ ሜትር ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ መንገዶች ግንባታ ተጀመረ

$
0
0

በአዲስ አበባ ከተማ ከተገነቡና እየተገነቡ ከሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ የሚጠበቀው ዘመናዊ መንገድ ግንባታ ሥራ ማክሰኞ የካቲት 7 ቀን 2009 ዓ.ም.  በይፋ ተጀመረ፡፡

መነሻውን ቃሊቲ የአሽከርካሪዎች ማሠልጠኛ አደባባይ በማድረግ በሁለት ኮሪደሮች የሚጓዘውና ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቀውን የመንገድ ግንባታ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥበት ሥራውን በይፋ አስጀምረዋል፡፡

አዲስ አበባን መነሻና መድረሻ በማድረግ የአገሪቱን የወጪ ንግድ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የሚያስተናግደው ይህ መንገድ ሲጠናቀቅ፣ ከተማዋን የባለሦስት ተሻጋሪ መንገዶች ባለቤት እንደሚያደርጋት ይጠበቃል፡፡

 የመንገድ ግንባታውን የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጡት ከንቲባ ድሪባ እንደገለጹት፣ አዲስ አበባ ዘመናዊ ከተማ እንድትሆን ለማድረግ አንዱ ማሳያ የዚህ መንገድ ፕሮጀክት ነው፡፡ የመንገዱ ግንባታ የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያነሷቸውን ቁልፍ ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ ከሚከናወኑ የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታና በከታማዋ ውስጥ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ ከተዘረጋው ፕሮግራም ጋር  ተያያዥነት አለው ብለዋል፡፡

 በአሁኑ ወቅት በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚ አካላትና በከተማዋ ነዋሪ ሰፊ ውይይት እየተደረገበት የሚገኘው አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ መሪ ፕላን ለከተማዋ ዘመናዊነት አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

በአስተዳደሩ ዘመናዊ ከተማ ለመገንባት ከተያዙ ፕሮግራሞች አንዱ የሆነው የመንገድ ግንባታ ሥራ በከተማዋ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ጉልህ ድርሻ በመያዝ ላይ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡ ሰኞ፣ የካቲት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ግንባታቸውን ለማስጀመር የመሠረት ድጋይ የተጣለባቸው የቃሊቲ፣ ቱሉ ዲምቱ አደባባይና የቃሊቲ - ቡልቡላ - ቂሊንጦ መንገድ ፕሮጀክቶችም የከተማዋን የመንገድ ሽፋን በማሳደግ ድርሻ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡ የአዲሱ መንገድ ግንባታ የአገሪቱን የወጪና የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ በማስተናገድ፣ የትራፊክ ፍሰቱን በማቀላጠፍ የትራንስፖርት እንቅስቃሴው እንዲሻሻል ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኘ ገልጸዋል፡፡

በተለይ ከቃሊቲ ቀበለት መንገድ አደባባይ - በቡልቡላ በኩል አድርጎ ወደ ቂሊንጦ የሚገነባው መንገድ ቀደም ሲል በአካባቢው ምንም ዓይነት የመንገድ መሠረተ ልማት በሌለበት ሥፍራ እንደሚገነባም አስታውሰዋል፡፡ አዲስ የመንገድ መሠረተ ልማትና የትራንስፖርት አገልግሎት አቅርቦትን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ለአካባቢው ነዋሪዎች ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በይፋ ግንባታቸው የተጀመረው እነዚህ ፕሮጀክቶች በዓይነታቸው እስካሁን ከተገነቡት ይልቅ ዘመናዊ ሲሆኑ፣ ከቻይናው ኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድርና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጀት በአጠቃላይ ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የሚገነቡ ናቸው፡፡

የፕሮጀክቶቹ አጠቃላይ ርዝመት 20.6 ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎች እንደመንገዶቹ ሁኔታ የ40፣ የ50 እና የ60 ሜትር ስፋት ኖሯቸው የሚገነቡ ናቸው፡፡ ግንባታውን የቻይና ኮንስትራክሽን ኮሙዩኒኬሽንስ ኩባንያ (ሲሲሲሲ) ተረክቧል፡፡

ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመት የተሰጠው ሲሆን፣ የሚለከታቸው ባለድርሻዎች ድጋፍ ከተጨመረበት ከዚህ ጊዜ ቀድመው የሚጠናቁቀበት ተስፋ  እንዳለ ኢንጂነር ሀብታሙ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡

በተለይም የአገሪቱ የወጪና ገቢ ንግድ መውጫና መግቢያ በመሆን ለረዥም ዓመታት ሲያገለግል የቆየው ከቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ በመነሳት ቱሉ ዲምቱ አደባባይ የሚደርሰው አንደኛው የመንገድ ፕሮጀክት፣ አጠቃላይ የፕሮጀክት ወጪው 2.45 ቢሊዮን ብር ሆኖ 11 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 50 ሜትር ስፋት የሚኖረው ትልቁ መንገድ ነው፡፡ 11 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው በአንደኛው መንገድ ይካተታሉ ከተባሉት ውስጥ የአቃቂ ድልድይን ጨምሮ አምስት ዋና ዋና የተሻጋሪ ድልድይ ግንባታዎች ተጠቅሰዋል፡፡ የግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ሥራውን ኢንጂነር ዘውዴ እስክንድር አማካሪ ኩባንያ ተረክቦታል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ሁለተኛው ክፍል የቃሊቲ ቡልቡላ ቂሊንጦ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት ሲሆን፣ አጠቃላይ ርዝመቱ 5.4 ኪሎ ሜትር በ50 ሜትር ስፋት፣ 3.5 ኪሎ ሜትር በ40 ሜትር እንዲሁም 16 ሜትር በ60 ሜትር ስፋት የሚገነባ ሆኖ በልዩ ሁኔታ ዲዛይን መደረጉ ተነግሮለታል፡፡ የዚህ መንገድ ግንባታ አጠቃላይ ወጪ 2.33 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በዚህ ግንባታ ክፍል ውስጥ ከላይና ከታች የትራፊክ ፍሰቱን የሚያስተናግድ አንድ አደባባልይ፣ ሁለት ተሻጋሪ ድልድዮችና ሁለት 125 ሜትር ርዝመት ያላቸው ድልድዮች ግንባታን አካትቶ የሚካሄድ ውስብስብ ፕሮጀክት እንደሆነ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ የቂሊንጦ የኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በቃሊቲ ቡልቡላ፣ በቂሊንጦ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለተሸጋገሩ አንቀሳቃሾች ማምረቻዎችና በአካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎች በሙሉ ከፍተኛ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ አዲስ የሚገነባ መንገድ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

የዚህን ፕሮጀክት የዲዛይንና የቁጥጥር ሥራ ሄክ የተባለ ሌላ አገር በቀል አማካሪ ድርጅት የሚያከናውን ሲሆን፣ 11 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን መንገድ ደግሞ ኢንጂነር ዘውዴ እስክንድር የተባለው አማካሪ ድርጅት ተረክቧል፡፡

የዚህ መንገድ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን፣ መንገዱ በሚያልፍበት አካባቢ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ተደራጅተው ለሚንቀሳቀሱ ኢንተርፕራይዞችና ለቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የንግድ እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ኢንጂነር ሀብታሙ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የዚህ መንገድ ግንባታ በኮዬ ፈጩ አካባቢ እየተገነቡ ለሚገኙ 70 ሺሕ ያህል ኮንዶሚኒየም ቤቶችና ወደፊትም የሚገነቡትን ጨምሮ ከ300 ሺሕ ላላነሱ ነዋሪዎች ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገለግሎት ለማቅረብ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ አክለዋል፡፡

በአካባቢው እየተገነቡ የሚገኙትና የአንድን ከተማ ያህል ብዛት ያለው ሕዝብ ሊኖርባቸው የሚችሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታቸው ሲጠናቀቅ፣ በአካባቢው የሚኖረው ሕዝብ ከመሐል ከተማው ጋር የሚኖረውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ጠቀሜታቸው የላቀ እንደሚሆን ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለወጣቶች፣ ለአምራቾችና ለተቋራጮች እንዲሁም በመንገድ ኮንስትራከሽን ዘርፍ ለተሰማሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያም ብዙ ድርሻ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡

ለመንገድ መሠረተ ልማት ዕድገት መንግሥት ትኩረት እንደሰጠ የገለጹት ከንቲባ ድሪባ፣ ለአዲስ አበባ የመንገድ ልማት የሚውል ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በማፅደቅ የተለያዩ የግንባታና የጥገና ሥራዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ መንገዶችን ለተጠቃሚዎች ምቹ ለማድረግ አስተዳደሩ ለጥገና ከ267 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ለጥገና ሥራው ትኩረት መሰጠቱንና በጥቂት ወራት ውስጥም በአዲስ አበባ ከተማ ለውጥ ስለመመዝገቡ የከተማው ነዋሪ ምስክር ይሁነኝ ብለዋል፡፡ ከጥገና ሥራው ጎን ለጎን አዳዲስ የመንገድ ግንባታ ሥራዎች በሌሎችም የከተማዋ አካባቢዎች እንደሚተገበሩ ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

ይሁንና የግንባታ ሥራቸው የተጀመሩት መንገዶች 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ቢሆኑም፣ ለግንባታ የሚጠይቁት ወጪ 4.7 ቢሊዮን ብር መሆኑ ብቻም ሳይሆን በአንድ ኪሎ ሜትር ከ235 ሚሊዮን ብር በላይ የሚጠይቁ መሆናቸው ከሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶች የተለዩ አድርጓቸዋል፡፡ 

Standard (Image)

ኬንያን እየተገዳደረ መምጣቱ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ

$
0
0

ከሰሞኑ ትዊተርን ጨምሮ በሌሎችም ማኅበራዊ ድረ ገጾች መነጋገሪያ ሆነው ከነበሩ ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ ሆኖ የተገኘው ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ልዕለ ኃያልነቱን ከኬንያ እየተረከበች መምጣቷን የሚያትተው ዜና ነው፡፡

በኬንያ ዋና ዋና የዜና አውታሮች ሽፋን የተሰጠው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማትና ዕቅድ ኢንስቲትዩትንም ያሳተፈ ነበር፡፡ ኢንስቲትዩቱ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው ከሆነ ኢትዮጵያ ለዓመታት በኬንያ የበላይነት ተይዞ የቆየውን የምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ የበላይነት ለመውሰድ ተቃርባለች፡፡

ከስምንት ዓመታት በፊት የሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚ ዓመታዊ ዕድገት ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ ሲነፃፀር ኬንያ ኢትዮጵያን ታስከነዳ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2000 የኬንያ ኢኮኖሚ የ14 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ የጠቅላላ ምርት ዕድገት እንደነበረው ይገመት ነበር፡፡ በአንፃሩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በግማሽ ያህል ቀንሶ ማለትም በስምንት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይከተል እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም በ72 በመቶ ገዳማ ከኬንያ ያነሰ መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡

እንዲህ የነበረው የሁለቱ አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት ልዩነት በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ እየጠበበ መጥቶ፣ ጭራሹንም ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ኬንያን መብለጥ እንደምትጀምር የሚያሳዩ መረጃዎች ይፋ ወጥተዋል፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክን ጨምሮ ሌሎች አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የሚሳተፉበት፣ ዓመታዊው የአፍሪካ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ዕድገትን የሚቃኘው ሪፖርትን መሠረት ያደረጉ ትንበያዎች እንደሚያረጋግጡት፣ ዘንድሮ ኢትዮጵያ የሚኖራት የኢኮኖሚ ደረጃ በምሥራቅ አፍሪካ የበላይ እንድትሆን የሚያበቃት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በዚህም የበላይነቱን ከኬንያ ለመረከብ ያስችላታል ተብሏል፡፡

የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ትኩስ አኃዛዊ መረጃዎች ዋቢ ያደረጉት ዘገባዎች እንደሚያትቱት፣ በወቅቱ የገበያ ዋጋና ምንዛሪ ስሌት መሠረት፣ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ወይም የአገር ኢኮኖሚ አጠቃላይ እንቅስቃሴ በሚለካበት መመዘኛ መሠረት፣ በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 70 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚገመት ግዝፈት ይኖረዋል፡፡ ይህ ካቻምና ከነበረበት 62 ቢሊዮን ዶላር ገደማ አኳያ ሲታይ የስምንት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ በአንፃሩ ኬንያ ካቻምና ከነበራት የ64 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ኢኮኖሚ ወደ 69 ቢሊዮን ዶላር የምታሻቅብ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ በስላሽ ተቀድማ አውራነቱን እንደምታስረክብ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግዝፍናው እያየለ፣ ዕድገቱም እየጨመረ መምጣቱ በመላው ዓለም ሲነገር ሰንብቷል፡፡ በያመቱ በአማካይ የአሥር በመቶ ዓመታዊ ኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበ የመጣው የአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ በምሥራቅ አፍሪካ በኬንያ የተያዘውን የበላይነት ጠብቆ እንደሚዘልቅም ተነግሮለታል፡፡ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ከባዱን ሚዛን የያዘው የመንግሥት ድርሻ ነው፡፡ መንግሥት የሚያከናውናቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ዋናውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ በመቀጠል ሊጠቀስ የሚችለው በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ነው፡፡

በመንግሥት የሚካሄደው ኢንቨስትመንት፣ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ የ40 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው ተገምቷል፡፡ ይህ ከስምንት ዓመት በፊት ከነበረው አኳያ በእጥፍ እየጨመረ መምጣቱን እንደሚያሳይ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ በባቡር መስመር ዝርጋታ፣ በኢነርጂ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታና በሌሎችም አውታሮች የመንግሥት ሚና ገዝፎ የሚታይበት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወደፊትም በዚሁ አኳኋን እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡ በአንፃሩ የኬንያ መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ የሚያካሂደው ኢንቨስትመንት በ22 በመቶ እንደሚያድግ ሲጠበቅ፣ ዓመታዊው የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም በስድስት በመቶ እያደገ እንደሚገኝ የኬንያ መገናኛ አውታሮች ዘግበዋል፡፡ ኢትዮጵያም ባለሁለት አኃዝ ዕድገቷ ላለፉት ሁለት ዓመታት ወደ ታች እየወረደ በመምጣት ከስድስት እስከ 8.5 በመቶ ባለው እርከን ውስጥ ሲዋልል ቆይቷል።

ይሁንና በአገሪቱ የተከሰተው ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ድርቅ እንዲሁም በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የአገሪቱ የብድር ዕዳ መጠን የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ሊያቀዛቅዙ የሚችሉ ፈተናዎች ሆነው ይቀርባሉ፡፡ መንግሥት በበኩሉ የእነዚህ ተፅዕኖ ዝቅተኛ መሆኑን ደጋግሞ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር መንግሥት የሚከተለው ፖለቲካዊ ሥርዓትም በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊሳርፍ እንደሚችል ይተችበታል፡፡ በተለይ የፖለቲካ የበላይነቱን በመያዙ ምክንያት የሚያሳድረው ጫናና የመብት ረገጣ በምዕራባውያኑ ዘንድ ሲያስኮንነው ቆይቷል፡፡ የኬንያ ጋዜጦችም መንግሥት በመገናኛ ብዙኃንና በጋዜጠኞች ላይ የሚያደርሰው ወከባና እንግልት በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ከሚችሉ ነጥቦች መካከል ይመድቡታል፡፡ በዚህ መመዘኛ ኬንያ ከኢትዮጵያ የተሻለ ነፃነት የሰፈነባት ሆና እንደምትገኝ ያምናሉ፡፡

በነፍስ ወከፍ ገቢም ቢሆን ኬንያ ከኢትዮጵያ የተሻለች ሆና እንደምትገኝ አኃዞች ያረጋግጣሉ፡፡ የኢትዮጵያ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) 686 ዶላር እንደሆነ ይገመታል፡፡ በዚህ ዓመት ወደ 760 ዶላር ከፍ እንደሚል ይጠበቃል፡፡ በአንፃሩ የኬንያ የነፍስ ወከፍ ገቢ ካቻምና ከነበረበት 1,434 ዶላር በዚህ ዓመት 1,522 ዶላር ገደማ እንደሚደርስ ስለሚጠበቅ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በዚህ መመዘኛ ከኢትዮጵያ የተሻለ ሆኖ ይገኛል፡፡

እርግጥ 100 ሚሊዮን የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ከኬንያ አኳያ ከእጥፍ በላይ ብልጫ አለው፡፡ የኬንያ ሕዝብ ብዛት ለ50 ሚሊዮን ፈሪ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ያህል መሆኑ ትልቅ ገበያ መሆኑን በመጥቀስ በተለይ የውጭ ኩባንያዎችን ለመሳብ ትልቅ ሚና እንዳለው ሲገለጽ ይደመጣል፡፡ መንግሥት በበኩሉ ትልቁን ማበረታቻና የኢንቨስትመንት ድጋፍ የሚሰጠው በአገር ውስጥ ለውጭ ገበያ የሚመረቱ ፕሮጀክቶች እንዲስፋፉለት ነው፡፡

ይህም ቢባል በያመቱ በቢሊዮን ዶላር የሚገመቱ የውጭ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ አገሪቱ እየመጡ እንደሆኑ የዓለም ባንክ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አቶ ፍፁም አረጋ ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ባደረጉት መረጃ መሠረት፣ በግማሽ ዓመቱ ውስጥ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገቡ የውጭ ኢንቨስትመንቶች መጥተዋል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ የበላይነት እንድትይዝ እያስቻሏት ከሚገኙ መገለጫዎች ውስጥ ቢመደብም፣ አገሪቱ መሳብ ከምትችለው የውጭ ኢንቨስትመንት ውስጥ አሁንም አነስተኛውን መጠን እያገኘች እንደምትገኝ ይገልጻል፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ በሌሎች የኢኮኖሚ መለኪያዎች (ሒውማን ዴቨሎፕመንት ኢንዴክስ) ማለትም የትምህርት፣ የጤና፣ አማካይ የዕድሜ ጣሪያ፣ የኑሮ ደረጃና የመሳሰሉት መለኪያዎች ሲታከሉበት የኢኮኖሚው ዕድገት ወደ ታችኛው ሕዝብ ድረስ በመውረድ እያስገኘ ያለው ለውጥ ብዙ ይቀረዋል፡፡ ይህም ሆኖ በአገሪቱ የተንሰራፋውንና ከድህነት ወለል በታች የሚኖረውን የሕዝብ ቁጥር መጠን በግማሽ ለመቀነስ እንዳስቻለ የዓለም ባንክና ሌሎች ተቋማትም እማኝ ይሆኑለታል፡፡ 

 

Standard (Image)

አነጋጋሪው የዳስፖራዎች የአክሲዮን ድርሻ ገበያ

$
0
0

ከ23 ዓመታት በፊት የግል ባንኮችንና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን በማደራጀት ማቋቋም እንደሚቻል ሲፈቀድ፣ በወቅቱ የፋይናንስ ኩባንያ ለማቋቋም ያስፈልጋል ተብሎ የተደነገገው ዝቅተኛው የካፒታል መጠን ከአሥር ሚሊዮን ብር ያነሰ ነበር፡፡

ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው የተከፈለ ካፒታል መጠን አሥር ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያ ለመመሥረት የሚሰባሰቡ ግለሰቦች የሚጠበቅባቸው ሦስት ሚሊዮን ብር ብቻ ማሟላት ነበር፡፡ ይህ ገንዘብ ለዛሬዎቹ የፋይናንስ ተቋማት ምንም ማለት አይደለም፡፡ ምናልባትም በአንዳንድ ባንኮች ውስጥ አንድ ግለሰብ ደንበኛ ወይም ድርጅት በግሉ ሊኖረው የሚችል የአክሲዮን ድርሻ መጠን ሊሆን ይችላል፡፡

ከ23 ዓመት በፊት ግን ባንክም ሆነ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ለማቋቋም የተነሱ ግለሰቦች፣ ሦስትም አሥርም ሚሊዮን ብር አሟልተው ወደ ሥራ ለመግባት ሲቸገሩና ሲፈተኑ እንደነበር የሚያስታውሱ አሉ፡፡ በተለያዩ አክሲዮን ኩባንያዎች ውስጥ በተለይም የሕብረት ኢንሹራንስና የሕብረት ባንክ መሥራቶች ከሆኑት አንዱ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉም ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡

በደርግ ውድቀት ማግሥት የግሉ ዘርፍ በባንክና በኢንሹራንስ ሥራ መሰማርት እንደሚችል ቢፈቀድለትም፣ ለሥራው የሚያስፈልገውን አነስተኛ የካፒታል መጠን ለመሰብሰብ ግን እንዲህ ቀላል አልነበረም፡፡ በወቅቱ የግል የፋይናንስ ተቋማትን ለማቋቋም በአገር ውስጥና በውጭ አገር የኖሩ፣ የካበተ ልምዳቸውንና ዕውቀታቸውን በመጠቀም አክሲዮን ለማሻሻጥ ወዲህ ወዲያ ሲሉ የነበሩ የፋይናንስ ሰዎች የአንድ አክሲዮን የመሸጫ ዋጋቸውም ይህንኑ ያሳይ ነበር፡፡

በወቅቱ የአንድ የአክሲዮን ዋጋ ከ25 ብር እስከ 100 ብር ባለው መጠን ውስጥ እንዲዋልል ካደረጉበት ምክንያቶች አንዱ የአገሬው ሰው የመግዛት አቅም ነበር፡፡ በወቅቱ ግፋ ቢል አንድ ሰው አሥር አክሲዮኖችን ሊገዛ ቢችልም፣ ከዚህ በላይ መሔድ ግን ለብዙዎች ከባድ ነበር፡፡ ይህም ማለት ለአሥር አክሲዮን 1,000 ብር እንደማዋጣት ማለት ነው፡፡ ይህ ለብዙዎች የሚቻል ባለመሆኑ በአንድ ጊዜ አጠቃሎ መክፈልም ግዴታ አልነበረም፡፡ ስለዚህም ቀዳሚዎቹ ባንኮች አሥር ሚሊዮን ብር ለመሙላት ፈተና ይገጥማቸው ነበር፡፡

በዚያን ወቅት ለባንክ መመሥረቻ የሚፈለገውን ካፒታል በቶሎ ለመሙላት እጅግ ከባድ እንደነበር አቶ ኢየሱስ ወርቅ ያስታውሳሉ፡፡ በተለይ የካፒታል ገበያ ያልነበረበት፣ የሰውም አመለካከትም ገና ያልነቃበት ወቅት በመሆኑ፣ ለሽያጭ የቀረበውን አክሲዮን ዋጋ ብቻ እንዲገዙ ለማግባባት ትልቅ ፈተና እንደነበርም ይገልጻሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የመጀመርያዎቹ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ሲቋቋሙ እንደዛሬው በእያንዳንዱ አክሲዮን ዋጋ የሚጠየቀውን ፕሪምየም ክፈሉ እንደማይባሉም አቶ ኢየሱስ ወርቅ አስታውሰዋል፡፡

ይህ ሁሉ ግን ዛሬ ተለውጧል፡፡ ባንኮች አክሲዮናቸውን ሲሸጡ ፕሪሚየም ይጠይቃሉ፡፡ ያወጡትን ካፒታል ታሳቢ በማድረግም የኢንቨስትመንቱ ዋጋ ስለጨመረ ለአክሲዮን ሽያጩ የሚከፈል ተጨማሪ ገንዘብ ወይም ፕሪሚየም ይጠይቃሉ፡፡ የሚጠየቀው ፕሪሚየም ከአንዱ አክሲዮን ዋጋ እስከ 75 በመቶ ሊደርስ እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡ የፕሪሚየሙ ዋጋ እንደ ባንኩ ይለያይ እንጂ ፕሪሚየሙ መኖሩ ኩባንያዎቹ የደረሱበትን ደረጃ እንደሚያመላክት ይታሰባል፡፡

አጋጣሚ ሆኖ ግን ከኢትዮጵያ ውጭ ለዓመታት ቆይተው የተመለሱና ዜግነታቸውን ያልቀየሩ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ከነበሩት ሰዎች የተሻለ ገንዘብ ስለነበራቸው፣ የግል የፋይናንስ ድርጅቶቹ ለመፈጠራቸው አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ እንዲህ ባለው መንገድ የተሰባሰበው ካፒታልም በየጊዜው እያደገ መጥቷል፡፡

ባንክ ለማቋቋም የሚጠየቀው የዱሮው የካፒታል መጠን አሥር ሚሊዮን ብር መሆኑ ቀረና 75 ሚሊዮን ብር ገባ፡፡ ቆይቶም ወደ 100 ሚሊዮን ብር አደገ፡፡ አሁንም ኢንቨስትመንቱ ስላልጠቀመው ወደ ግማሽ ቢሊዮን ብር ያደገ የተከፈለ ካፒታል ማሟላት ግዴታ ተደርጎ ቆየ፡፡ በአሁኑ ወቅት 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ማሰባሰብ ካልተቻለ ባንክ ማቋቋም አይቻልም፡፡ እንደውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የባንኮች የተከፈለ ካፒታል ሁለት ቢሊዮን ብር እንዲደርስ ለማድረግ ተዘጋጁ ተብለዋል፡፡ ይህ የብሔራዊ ባንክ ማሳሰቢያ በአብዛኛዎቹ ባንኮች ላይ ሥራ ማብዛቱ ባይቀርም፣ የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አትራፊ በመሆናቸው በቀላሉ አክሲዮን በመሸጥ ከኢኮኖሚው ገንዘብ ማሰባሰብ ይችላሉ በማለት የገዥውን ባንክ አቋም የሚቀበሉ አሉ፡፡ በኢንሹራንሱም ዘርፍ ቢሆን በሦስት ሚሊዮን ብር የተጀመረው የካፒታል መጠን ዛሬ ላይ ወደ 60 እና 75 ሚሊዮን ብር አሻቅቧል፡፡ 17ቱ የግል የመድን ድርጅቶችም ይህንን የካፒታል ጣራ አልፈው ሄደዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት 34 የግል ባንኮችና የመድን ድርጅቶቸ ያሰባሰቧቸው ባለአክሲዮኖች ቁጥር ከ140 ሺሕ በላይ ደርሷል፡፡ የተመዘገበና የተከፈለ ካፒታላቸውም ከ46 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ከ100 ሺሕ በላይ ሠራተኞችንም ማስተዳደር ችለዋል፡፡

የዜግነት ገደብ

የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንዲቋቋሙ ከተፈቀደበት ጊዜ ጀምሮ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከተው አዋጅ፣ አዋጁንም ተከትለው በወጡ ማስፈጸሚያ ሕጎች ውስጥ በጉልህ ከተቀመጡ አንቀጾች አንዱ በፋይናንስ ኩባንያዎች ውስጥ ባለቤት መሆን የሚችሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ሌሎች የውጭ ዜጎችና የውጭ ኩባንያዎች በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ባለድርሻ መሆን እንደማይችሉ ተቀምጧል፡፡ ይህ ድንጋጌ አግባብ አይደለም የሚሉ በርካታ ሙግቶችን ሲያስነሳና ሲያነታርክ ቆይቷል፡፡ በተለይ የዓለም ገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት እንዲያደርግ ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡ ዘርፉ ለሁሉም ክፍት እንዲደረግና በውድድር ብሎም በነፃ ገበያ የሚመራ መሆን እንደሚገባው የሚያምኑ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችም የውጭ ኩባንያዎች ዕድሉ እንዲሰጣቸው ቢደረግ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ደጋግመው ተንትነዋል፡፡

አሁንም ድረስ ይህንኑ አቋም የሚያራምዱ ምሁራን ጥቂት አይደሉም፡፡ መንግሥት ግን በውሳኔው እንደፀና ይገኛል፡፡ የመንግሥት አቋም በዚሁ ቢቀጥልም ዘርፉ ሌላው ቢቀር ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉበት መፈቀድ አለበት የሚለው ውትወታ ቀጥሏል፡፡ ዳያስፖራው ቢያንስ በሕግ ተገድቦ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ እንዲሳተፍ ይፈቀድለት በማለት የሚከራከሩ አሉ፡፡

ይህንንም ቢሆን መንግሥት አልተቀበለውም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ወቅት እንዳሉት፣ ወደፊት መንግሥት ዘርፉን ለውጭ ክፍት ማድረጉ ባይቀርም አሁን ግን ባለበት እንደሚቆይ አስታውቀው ነበር፡፡ ይህ እንደማይቀር ሲያጣቅሱም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመግባትም ሆነ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ በመሆኑ ዘርፉን መዝጋት እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ዘርፉን መክፈት ጉዳቱ እንደሚያመዝን ማስረጃዎችን አጣቅሰዋል፡፡ በመሆኑም ዳያስፖራው ማኅበረሰብ በቀጥታ ከፋይናንስ ሥራ ጋር በማይገናኙ ነገር ግን እንደ ሊዝ ፋይናንሲንግ ባሉት ኢንቨስትመንቶች ውስጥ በመሳተፍ እንዲንቀሳቀስ ይፈቀድለት ነበር ብለዋል፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ግን በተነወሰ ገደብ ዳያስፖራዎች ባለአክሲዮን ቢሆኑ ችግር እንደሌለው ይሞግታሉ፡፡

ዳያስፖራውና የፋይናንስ ተቋማት

ለውጭ ዜጎች ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ቢሆኑ ኢንቨስት ከማድረግ የተከለከሉበት የፋይናንስ ዘርፍ ይፈቀድላቸው ከሚለው ጥያቄ ጎን ለጎን በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የዳያስፖራውን ስም የሚያስነሳ ጉዳይ ተከስቷል፡፡ ይህም በተለያዩ ባንኮችና ኢንሹራንስ ተቋማት ውስጥ የውጭ ዜግነት ያላቸውን ባለአክሲዮኖች ያቀፉ ባንኮች ተገኝተዋል የሚለው ጉዳይ አጀንዳ እየሆነ መጥቷል፡፡

ብሔራዊ ባንክ በሕግ ክልከላ የተደረገባቸው የውጭ ዜጎች በተለይም የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ባለአክሲዮን ሆነው ከተገኙ ባስቸኳይ እንዲያሳውቁት ባንኮችንና መድን ድርጅቶችን አዘዘ፡፡ ባለአክሲዮን ሆነው ከተገኙ በወንጀል የሚያስጠይቅ ድርጊት ነው እስከማለት ተደረሰ፡፡ የባንክ ኃላፊዎችም የውጭ ዜጋ የሆነ ባለአክሲዮኖችን አስወጡ የሚለውን የሰርኩላር ትዕዛዝ መተግበር ሥራቸውን ሲረብሸው ቆይቷል፡፡ የውጭ ዜግነት እያላቸው አክሲዮን የገዙ ስለመኖራቸው ማስረጃ ባይቀርብም፣ አክሲዮን ከገዙ በኋላ ዜግነታቸውን የቀየሩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ግን ግልጽ ነበርና እነዚህን ለይቶ ሪፖርት ለማድረግ እንዴት እንደሚቻል የብዙዎች ጥያቄ ነበር፡፡

ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌላቸው ባለአክሲዮኖች ድርሻቸው እንዳይጠቀስ ይደረጋል የሚለው ጉዳይም ብዙዎች መንግሥት ገንዘባቸውን ሊወርሱ አስቦ ነው ወደሚለው አመለካከት እንዲያዘነብሉ አስገድዷቸዋል፡፡ ቆይቶ በተደረገ ድርድር የውጭ ዜግነት ያላቸው ባለአክሲዮኖች ጥሪ እንዲደረግላቸው፣ ባንኮችም ይህንኑ አጣርተው እንዲያቀርቡ፣ ለዚህም 60 ቀናት እንዲሰጥ ጊዜ ገደብ እንዲሰጥ ተደረገ፡፡ በጥሪው መሠረት የቀረቡትም ያላቸው አክሲዮን ብዛትና ዋጋ ተሰልቶ የትርፍ ድርሻቸውን ይዘው እንዲወጡ ተደረገ፡፡ ይህ መደረጉም ጊዜያዊ ዕፎይታን ፈጠረ፡፡

ሰሞኑን እንደተገለጸው ግን በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ግን ደግሞ ባለአክሲዮን የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስለመኖራቸው የሚያረጋግጡ መረጃዎች ቀረቡ፡፡ ከ700 በላይ የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በባንክና በኢንሹራንስ ውስጥ እስከ 400 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድርሻ ይዘው መገኘታቸው ይፋ ተደረገ፡፡ እነዚህ ባለአክሲዮኖች እንደ ሕጉ ቅጣት ቢጠብቃቸውም አክሲዮኖቻቸውንና የትርፍ ድርሻቸውን ይዘው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ ኩባንያዎቹም የእነዚህን አክሲዮኖች ድርሻ በጨረታ መሸጥ ጀምረዋል፡፡

ከተለያዩ ባንኮች የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኩባንያዎቹ ውስጥ ባለድርሻ ሆነው የተገኙባቸው የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ነው፡፡

አንዱና ዋናው ምክንያት በኩባንያዎቹ ውስጥ ባለድርሻ የሚያደርጋቸውን አክሲዮኖች በገዙበት ወቅት ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ሲሆን፣ ቆይተው ግን ዜግነታቸውን መለወጣቸው ነው፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ ውርስ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ብዙ አከራክሮ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ ብሔራዊ ባንኩ ገዥ ገለጻ፣ ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተሰጠን መብት ኢትዮጵያዊነቱን ሲቀይር ያገኘው መብት መመለስ አለበት የሚል አቋም መንግሥት እያራመደ ይገኛል፡፡ ትልቁ ችግርም ይህ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ግን ይህም ከተባለ የባለአክሲዮኖች ድርሻ በባንኮች በጨረታ ከሚሸጥ ይልቅ ግለሰቦቹ በራሳቸው መንገድ ለባለአክሲዮኖች ቢሸጡ ይመረጥ ነበር ብለዋል፡፡ ‹‹በእርግጥ ያላቸውን አክሲዮን ይዘው መውጣታቸው መልካም ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ የተሻለ ቢደረግ ጥሩ ነበር፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡ ከአንዳንድ የባንክ ኃላፊዎች ያገኘነው መረጃ ደግሞ ይህ ጉዳይ አክሲዮኖችን በመሸጥ መቋጨቱ መልካም እንደሆነ የሚጠቁም ነው፡፡ ይህ ባይሆንና ጉዳዩ ወደ ሕግ ቢሔድ ኑሮ ገንዘባቸው መወረሱ አይቀሬ ነበር ይላሉ፡፡

የዳያስፖራ አክሲዮን ዋጋ

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት በውጭ ዜጎች ተይዘው የነበሩ አክሲዮኖችና የባለቤትነት ማረጋገጫቸውም እንዲመልሱ ተደርጓል፡፡

ባንኮች የውጭ ዜጋ መሆናቸው ተረጋግጦ በግንባር አለያም በወኪል ለቀረቡ ባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ዋጋቸውንና ትርፋቸውን በመስጠት በምትኩ ሰርተፍኬታቸውን እንዲያስረክቡ አድርግዋል፡፡ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ያልቀረቡትም ድርሻቸው ተቀምጦ በቀሪው ጊዜ እንዲሰጣቸው ተወስኗል፡፡ ነገር ግን ይዘውት የነበረው አክሲዮን ኢትዮጵያዊ ለሆነ ሰው መተላለፍ ስላለበት አክሲዮኑን ለማስተላለፍ የተመረጠው ሒደት ጨረታ ሆኗል፡፡ ሁሉም ኩባንያዎች በውጭ ዜጎች የተያዙትን የአክሲዮን ድርሻዎች ለመሸጥ ጨረታዎችን ሲያወጡና ሲያስተዋውቁ ከርመዋል፡፡

በመመርያው መሠረት በውጭ ዜጎች ነበር የተባሉት አክሲዮኖች ለሁሉም ባለድርሻ ክፍት ይደረጋሉ፡፡ ዘወትር እንደሚደረገውም ቅድሚያ ተቋማቱ ባለአክሲዮኖች ይሰጥ የሚለውን አሠራርም ያስቀረ ሒደት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከሽያጩም የሚገኘው ትርፍ ለመንግሥት፣ ዋናው ገንዘብ ለባንክና ኢንሹራንሶች ገቢ ይደረጋል፡፡ እስካሁን በተከታታይ የአክሲዮን ሽያጭ ለማከናወን ይፋ ማስታወቂያ ካወጡት ውስጥ አዋሽ ባንክ ሰሞኑን ባደረገው ጨረታ የ1,000 ብር መነሻ ዋጋ ያለውን የአንድ አክሲዮን በ14 ሺሕ ብር እስከመሸጥ ደርሷል፡፡

ከምሥረታ ጀምሮ የነበሩ ባለአክሲዮኖች በተለይ በባንክ ውስጥ ያወጡትን ኢንቨስትመንት በስድስት ዓመት መመለስ እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡ ኢንቨስትመንቱም አዋጭ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ቀዳሚ በሆኑ ባንኮች ውስጥ የነበሩ ባለአክሲዮኖች አብዛኛዎቹ በመጀመርያ የነበራቸውን አክሲዮን ከእጥፍ በላይ ማሳደጋቸውን የተናገሩም አሉ፡፡

በሁለት ባንኮች ውስጥ ባለአክሲዮን የሆኑት አንድ ባለአክሲዮን እንደገለጹት፣ ከ14 ዓመት በፊት በአንደኛው ባንክ በአሥር ሺሕ ብር የገዙት አሥር አክሲዮን በየዓመቱ እያደላቸው መጥቶ የገዙት አሁን 110 ሺሕ ብር ደርሶላቸዋል፡፡

ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አሁን ከታወቁት ባለአክሲዮኖች ሌላ እስካሁን ያልታወቁ ባለአክሲዮኖች ሊኖሩ የሚችሉ መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንዳንድ ባለአክሲዮኖች ኢትዮጵያዊ መሆን አለመሆናቸውን ለማወቅ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥት ግን በዚህ ጥሪ ያልቀረቡት እያወቁ ያላመለከቱ ካሉ ቀጣዩ ዕርምጃው ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው በእንጥልጥል ላይ ይገኛል፡፡ 

Standard (Image)

የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት የፕሪሚየም ስዊች ቦርድ ሰብሳቢ ሆኑ

$
0
0

ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትን በጋራ ለማቅረብ ሰባት ባንኮች በአባልነት የመሠረቱት ፕሪሚየም ስዊች ሶሉዊሽን አክሲዮን ማኅበር፣ አዲስ የቦርድ ሰብሳቢ ሰየመ፡፡ በዚሁ መሠረት የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነዋል፡፡

ሕብረት፣ አዋሽ፣ ንብ፣ ብርሃን፣ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ማኅበር፣ ቡና ባንክና አዲስ ኢንተርናሽናል ባንኮችን በአባልነት ያካተተው አክሲዮን ኩባንያ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አዲስ የቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ የሰየማቸው የአዋሽ ባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው አዲሱን ቦታ ተረክበው ለመሥራት ፈቃደኛ ሆነዋል፡፡

አክሲዮን ኩባንያውን ከተመሠረተ ጀምሮ ላለፉት ሦስት ዓመታት አክሲዮን ኩባንያውን በቦርድ ሰብሳቢነት ሲመሩ የቆዩት የቀድሞው የሕብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ጌታነህ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ አቶ ብርሃኑ ከአንድ ወር በፊት ኃላፊነታቸውን ካስረከቡ በኋላ ሰሞኑን ቦርዱ ባደረገው ስብሰባ አቶ ፀሐይን በምታካቸው ሰይሟል፡፡

ሰባቱ ባንኮች በየራሳቸው የኤቲኤም ካርድ የአንደኛው ደንበኛ በሌላኛው ባንክ ያለምንም ችግር መገልገል የሚችልበትን አሠራር የዘረጉ ሲሆን፣ ሌሎች ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶችንም በጋራ ለማቅረብ በማሰብ ያቋቋሙት ኩባንያ ነው፡፡

እነዚህ የግል ባንኮች በአሁኑ ወቅት በጋራ የሚጠቀሙባቸው ከ650 በላይ ኤቲኤም ማሽኖች አሏቸው፡፡ ባንኮቹ በጋራ በማዕከላዊነት በሚጠቀሙበት አንድ ስዊች አማካይነት እስካለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ ማንቀሳቀስ እንደቻሉ መግለጹ ይታወሳል፡፡

 

Standard (Image)
Viewing all 720 articles
Browse latest View live