ከተቋቋመ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠረው ሴፍዌይ ሱፐር ማርኬት 50 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ኢንቨስትመንት አምስተኛ ቅርንጫፉን አገልግሎት መስጠት አስጀመረ፡፡ ገርጂ መብራት ኃይል አካባቢ በ2,175 ካሬ ሜትር ቦታ በሚሸፍነው ሕንፃ ላይ የተከፈተው አዲሱ ቅርንጫፍ የካፌና የባንክ አገልግሎቶች፣ የሕፃናት ልብሶች መሸጫ፣ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ያቀርባል፡፡ ሌሎች እንደ ሕፃናት ማቆያና ደንበኞች ወዳሉበት ቦታ የማድረስ የመሳሰሉትን አገልገሎቶች ማካተቱን ቅዳሜ ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ባዘጋጀው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ወቅት ተገልጿል፡፡
በፌም ኢምፔክስ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤትነት ሴፍዌይ ሱፐርማርኬት፣ በለገ ጣፎና በሰሚት አካባቢ ተጨማሪ አዳዲስ ቅርንጫፎች እንደሚከፍት የድርጅቱ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ ከበደ ተናግረዋል፡፡ በርካታ ሸቀጣ ሸቀጦችና አገልግሎቶችን በአንድ ጥላ ሥር የሚያቀርቡ ሱፐር ማርኬቶች መኖር የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን ፋይዳ አላቸው፡፡ ይሁንና በተመሳሳይ የገበያ ማዕከሎች የሚሸጡ ቁሳቁሶችና ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ የተጋነነ ነው የሚል እምነት በማኅበረሰቡ ውስጥ በመኖሩ በዕለት ተዕለት ኑራቸው የሚያስፈልጋቸውን ለመግዛት ወደ ሱፐር ማርኬቶች ጎራ የሚሉ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ለዚህም ይመስላል በከተማው የሚገኙት የሱፐር ማርኬቶች ቁጥር ውስን ሆኖ የቆየው፡፡
‹‹ሱፐር ማርኬቱ የተቋቋመው በዝቅተኛ ትርፍ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለማዳረስ ነው፤›› የሚሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ አገልግሎታችንን የምናቀርበው እጅግ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ነው ይላሉ፡፡ እንዲሁም አዲሱን የገርጂ ቅርንጫፍ መከፈትን ምክንያት በማድረግ እስከ መስቀል በዓል ድረስ የደንበኝነት ካርድ ለማግኘት ለሚመዘገቡና ከ750 ብር በላይ ለሚገዙ ደንበኞች 25 በመቶ ቅናሽ እንደሚደረግላቸው፣ እንዲሁም ባለፉት አምስት ዓመታት የገበያ ማዕከሉ ሲያደርግ እንደቆየው፣ በተመረጡ ዕቃዎች ላይ የዜሮ ትርፍ ሽያጭ በሁሉም ቅርንጫፎቹ ለማካሄድ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
ከ450 አቅራቢዎች ጋር እየሠራ የሚገኘው ሴፍዌይ ሱፐር ማርኬት፣ ከ600 ለሚበልጡ ዜጐች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በመጪው ዓመት የሚኖረው ዓመታዊ ሽያጭም ግማሽ ቢሊዮን ብር እንደሚገመት አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የቅርንጫፎቹን ቁጥር አሥር ለማድረስ እየሠራ እንደሚገኝ አክለዋል፡፡
አዲስ የተከፈተው ቅርንጫፍ አምስት ፎቆች ሲኖሩት፣ በሦስቱ የካፌ፣ የሸቀጣ ሸቀጥና ልዩ ልዩ የሽያጭ አገልግሎቶች ይከናወኑበታል፡፡ ለደንበኞች ወዳሉበት ቦታ በነፃ የማድረስ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ በቅርቡም እንደ በርገር፣ ፒዛ፣ ኬክ ያሉ የበሰሉ ምግቦችን ለደንበኞች በነፃ የሚያደርስበትን ሥርዓት ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ደንበኞች የሚፈልጉትን ምግብ በቀላሉ ባሉበት ሆነው ሊያዙ የሚችሉበት የስልክ አፕሊኬሽን እየተዘጋጀ መሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአገሪቱ የመጀመሪያው ሱፐር ማርኬት እ.ኤ.አ. በ1931 የተከፈተው በአዲስ አበባ ፍትሕ ሚኒስቴር አካባቢ የተተከለው ሱፐር ማርኬት ነው፡፡ የዚህ ሱፐር ማርኬት መከፈት ለአካባቢው ባምቢስ የሚለውን መጠሪያም አጋብቶበታል፡፡ ባምቢስ የሱፐርማርኬቱ ይዞታም ቻራ ላምቦስ ሲማስ በተባሉ ግሪካዊ ባለሀብት ሥር ነው፡፡ በወቅቱ የሱፐር ማርኬቱ ደንበኞች የነበሩት የውጭ አገር ዜጐች ብቻ ነበሩ፡፡ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ በከተማው የነበሩ የሱፐር ማርኬቶች ቁጥርም ውስን ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ጥቂት የማይባሉ ሱፐር ማርኬቶች ሊከፈቱ ችለዋል፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት በከተማው የሚገኙ ሱፐር ማርኬቶችና በጣት የሚቆጠሩ ሃይፐር ማርኬቶች ቁጥር 323 ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ቁጥራቸው 764 መድረሱን ከአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 201 ሱፐር ማርኬቶች በቦሌ ክፍለ ከተማ፣ 21 ደግሞ በልደታ ክፍለ ከተማ እንደሚገኙ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት ይፋ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙትም በአዲስ አበባ በርካታ ሃፐር ማርኬቶች መከፈት እንደሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ይህም የከተማዋ ዓለም አቀፍነት ብሎም የነዋሪው የፍጆታ ፍላጐት እያደገ መምጣት ለሃፐር ማርኬቶች መስፋፋት በዋና ምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡
