ከተለመደው የንግድ ትርዒት አዘገጃጀትና ክዋኔ በተለየ የተሰናዳው ‹‹ማይስ ኢስት አፍሪካ 2016 ፎረም ኤክስፖ›› እንዲሁም ‹‹ሆቴል ሾው አፍሪካ 2016›› የንግድ ትርዒት ባለፈው ሐሙስ በሚሊኒየም አዳራሽ በይፋ ለጎብኚዎች ክፍት ሆኗል፡፡
በፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ተመርቀው የተከፈቱት ሁለቱ የንግድ ትርዒትና የስብሰባ ፎረምና ኤክስፖ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ አገሮች የተወከሉ የቱሪዝም ባለሙያዎችና ከ250 በላይ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሲሰናዳ አዲስ የሆነው ‹‹ማይስ›› ዘመናዊው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የሚመራበት አዲስ የቱሪዝም ገበያ መሳቢያ መንገድ ነው፡፡ የማይስ ኤክስፖ አዘገጃጀትና ዓላማ ከሌሎች የንግድ ትርዒቶች በተለየ የሚታይ ስለመሆኑም አዘጋጁ ተቋም አስታውቋል፡፡
በዓለም የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው የተባለው ማይስ፣ አራት ዋና ዋና ክንዋኔዎችን ይዞ የሚካሄድ ነው፡፡ ስብሰባ፣ የማነቃቂያ ጉዞ፣ ኮንፈረንስና የንግድ ትርዒትን በጥምረት በመያዝ የሚካሄድ ሲሆን፣ ዝግጅቱም በአንድ አገር ሲካሄድ ለአገሬው ሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ አዲስና ዘመናዊ የገበያ ምንጭ በመሆን የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ያሳድጋል፡፡ ማይስን የተለየ የሚያደርገው ባህሪው በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ኩባንያዎችና የትላልቅ ስብሰባ አዘጋጆችን በመጋበዝ ከየአገሩ ሆቴሎችና ሌሎች ተዋናዎች ጋር በማገናኘት ቀጥተኛ ግብይት እንዲፈጽሙ ማስቻሉ ነው፡፡
ዝግጅቱ የአገሪቱን የሆቴልና ሌሎች በቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ ያሉ ተዋንያኖች ገበያ የሚያገኙበትን ዕድል የሚፈጥር ስለመሆኑ በኢትዮጵያ የማይስ አዘጋጅ የሆነው የኦዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ማኔጅመንት ግሩፕ መሥራችና ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል ገልጸዋል፡፡
ይህንን እንግዳ ዝግጅት ለማሰናዳት ብዙ ልፋት መጠየቁን የገለጹት አቶ ቁምነገር፣ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ወሳኝ የሆነው የማይስ ዝግጅት በኢትዮጵያ ዕውን ማድረግ መቻሉ በዘርፉ የኢትዮጵያን ተወዳዳሪነት ያሳድጋል ይላሉ፡፡
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት ዓለም አቀፍ የስብሰባ አገናኞች በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ውስጥ ከተሳሰሩ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋር በሚያደርጉት የገጽ ለገጽ ድርድር፣ አዳዲስ ገበያዎችን ለማምጣት የሚያስችል ዕድል ይፈጠራል ተብሎም እየተጠበቀ ነው፡፡ ከዚህ በኋላም የአገሪቱ ሆቴሎች ገበያ ለመፍጠር ማይስ ቀዳሚ ድልድያቸው ይሆናል፡፡
በሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄዱትን ሁለቱን የንግድ ትርዒቶች የከፈቱት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በማይስ በኩል በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ አንቀሳቃሾችን ትደግፋለች፡፡ አያይዘውም ዝግጅቶቹ አዳዲስ ገበያ ለመፍጠር የሚያስችሉ ያላቸውን እምነት ጠቅሰዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ እንደገለጹትም፣ እንዲህ ዓይነት ንግድ ትርዒትና ኤክስፖዎች ለአገሪቱ የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለዕድገት ዕገዛ ያደርጋል፡፡
ዝግጅቱ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘመናዊ ገበያ ማስገኛ በመሆን ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ያመለከቱት ኢንጂነር አይሻ፣ ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም ሀብት በዘመናዊ መንገድ ለመጠቀም ያስችላታል ብለዋል፡፡
የማይስ ኢስት አፍሪካ 2016 ፎረምና ኤክስፖ በኢትዮጵያ በጅምር ላይ ያለ ሲሆን፣ ከንግድ ትርዒቱ በኋላ በሚፈጸሙ ስምምነቶች በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ዓለም አቀፍም ሆነ የተለያዩ ተቋማት ስብሰባዎችን ቁጥር ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተለይ አዲስ አበባ ለዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ምቹ የሆኑ ሁኔታዎች ቢኖሯትም፣ እንደ ማይስ ያሉ ኤስፖዎችን በማዘጋጀት ገበያውን ለማግኘት ሳትችል ቆይታለች፡፡ አሁን ግን ዓለም አቀፍ የስብሰባ አዘጋጆች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ስብሰባዎች አዲስ አበባን ታሳቢ እንዲያደርጉ ያስችላል፡፡ ይህ ዕድል መከፈቱም ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች በተሻለ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት ለሆቴሎችና ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው አዲስ ገበያ በመፍጠር ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ እንደሚያስችል አቶ ቁምነገር ገልጸዋል፡፡
በሰሞኑ ዝግጅት ላይ ከ800 በላይ ዓለም አቀፍ የስብሰባ አዘጋጅ ድርጅቶችና ባለሙያዎች እንዲሁም የአገር ውስጥ የዘርፉ ተዋንያኖች በጋራ ከሚደረጉት ድርድሮች አዲስ አበባን በስብሰባ ገበያ ተጋሪ ስለሚያደርጋት ዘርፉን አንድ ዕርምጃ ወደፊት ያሳድገዋልም ተብሏል፡፡
ከማይስ ዝግጅት ጎን ለጎን አራተኛው ሆቴል ሾው አፍሪካ 2016 የሆስፒታሊቲና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት የንግድ ትርዒትም 250 ኩባንያዎች የተሳተፉበት ሲሆን፣ በተለይ በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፍ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን አምራቾችና አቅራቢዎች ምርቶቻቸውን ያስተዋወቁበት መድረክ ሆኗል፡፡
በንግድ ትርዒቱ ላይ ከፈረንሣይ፣ ከጣልያን፣ ከአሜሪካ፣ ከታይላንድ፣ ከቱርክ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከቻይና፣ ከዱባይ፣ ከዴንማርክ፣ ከግብፅና ከሌሎች አገሮች ኩባንያዎች ተሳታፊዎች ሆነውበታል፡፡ ከንግድ ትርዒቱና ከገበያ ድርድር መድረኩ ባሻገር በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ የሚያተኩር አሥር የውይይት መድረክ ፕሮግራሞች ይካሄዳሉ፡፡ ከተሳታፊ ኩባንያዎችና ታዋቂ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች አዘጋጆች ሌላ የዓለም አቀፍ የማይስ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡
