Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

ውዝፍ ሪፖርቶች የሚቀርብበት ጠቅላላ ጉባዔና ቀጣዩ የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫ

$
0
0

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሦስት ዓመታት ክንውኖቹን በአንድ የሚያስደምጥበትን ጠቅላላ ጉባዔ መስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ያካሂዳል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ባልተለመደ ሁኔታ የሦስት ተከታታይ ዓመታት ጠቅላላ ጉባዔዎችን በአንድ ላይ ለማካሄድ የተገደደው፣ ከዚህ ቀደም ንግድ ምክር ቤቱ ሕግ ጥሷል በሚል በተፈጠረ አለመግባባት ነው፡፡ ውዝግቡም ወደ ፍርድ ቤት በማምራቱ ወቅቱን ጠብቆ የየዓመቱን ክንውኖቹ ሪፖርት ለማቅረብ አላስቻለውም፡፡ ወቅቱን ጠብቆ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ባለመቻሉ የሦስት ዓመታት ውዝፍ ሪፖርቱን አንድ ላይ ለማቅረብ ተገዷል፡፡  

የ2006፣ የ2007 እና 2008 በጀት ዓመታት የኦዲት ሪፖርቶችና የንግድ ምክር ቤቱን ክንውን የሚያሳዩ ሪፖርቶች የሚቀርቡበት የመስከረም 29ኙ ጠቅላላ ጉባዔ፣ ንግድ ምክር ቤቱን የሚመሩ አዳዲስ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የቦርድ አባላትን ምርጫ ይካሄዳል፡፡

እንደ ንግድ ምክር ቤቱ መረጃ አዳዲስ የንግድ ምክር ቤቱ መሪዎችን ለመምረጥ የምርጫ አመቻች ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ የቀደሙ የንግድ ምክር ቤቱ የምርጫ ዋዜማ ክንውኖችና የምርጫ ሒደቶች ውዝግብ የበዛባቸው እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡

በዚህ ውዝግብ ውስጥ በተለይ ንግድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ጣልቃ ገብነት ጐልቶ የሚታይ በመሆኑ፣ በቡድን ተከፋፍሎ ወደ አመራር ለመምጣት የሚደረጉ ጥረቶች ንግድ ምክር ቤቱን የሽኩቻ ቦታ እስከማድረግ ደርሰው ነበር የሚሉ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የሚካሄደው ምርጫም ተመሳሳይ እንዳይሆን ሥጋት ያላቸው ወገኖች አሉ፡፡ አሁንም መታሰብ ያለበት ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ነው የሚሉት እኒሁ አስተያየት ሰጪ፣ ከዚህ ቀደም እንደታየው የጽሕፈት ቤቱ ጣልቃ ገብነት መገደብ ይኖርበታል የሚልም አስተያየት ያክላሉ፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም እንደተመለከትነው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጽሕፈት ቤቱ የሚፈልጋቸው ሰዎች ወደ አመራር እንዲመጡ፣ ያልፈለጋቸው ደግሞ ተወዳድረው እንዲያሸንፉ እጁን ያስገባ ነበር፤›› የሚል እምነት ያላቸው እነዚህ ወገኖች፣ የቀድሞ ስህተቶች መደገም እንደሌለበት ይመክራሉ፡፡

የንግድ ኅብረተሰቡም ቢሆን ለንግድ ምክር ቤቱ መጠናከር እንዲህ ያሉ ክፍተቶች እንዲሞሉ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚኖርበትም አስታውሰዋል፡፡ ለዘለቄታው ደግሞ ጽሕፈት ቤቱ የሚመራበት እንዲሁም የሥልጣን ወሰኑን በግልጽ የሚያሳይ የራሱ የሥነ ምግባር መመሪያ ሊኖረው እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ ገለልተኛ ኦዲተርም ቢኖረው ደግሞ እንዲህ ተደጋግሞ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ማስቀረት ይቻል እንደነበር በሚመለከት መጪው ጉባዔም እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ቢያደርግ ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ ገነቲ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ምርጫው ግልጽና ፍትሐዊ እንዲሆን ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ አባላት የሚፈልጉትን ዕጩ እንዲጠቁሙ በምርጫው ዕለትም በነፃነት የሚመርጡበት ይሆናል የሚል እምነት ያላቸው አቶ ኤልያስ፣ እንደ ቀድሞው ግርግር ይፈጠራል የሚል ግምት እንደሌላቸውም አስረድተዋል፡፡

ምርጫው በምንም መንገድ ይከናወን ሌላው መታሰብ ያለበት ጉዳይ ንግድ ምክር ቤቱን ለመምራት የሚታጩና ሊመረጡ የሚችሉ ግለሰቦች በቲፎዞ ሳይሆን ሊያበረክቱ በሚችሉት አስተዋጽኦ መመዘን ይገባቸዋል ያሉም የንግድ ምክር ቤቱ አባላት አሉ፡፡

‹‹ዘወትር ሦስትና አራት ኮንሰልታንቶች በተደጋጋሚ የሚመረጡበት መሆን የለበትም፤›› ያሉት እኒሁ የቀድሞ አመራር፣ በቦርዱ የሚካተቱት ተመራጮች ከተለያዩ ዘርፎች ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡ ከሆቴል፣ ከእርሻ፣ ከአገልግሎት፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከፋይናንስና ከመሳሰሉት ዘርፎች የተውጣጡ ሊሆኑ ካልቻሉ የተሻለ አገልግሎት ሊሰጥ አይችልም፡፡

የምርጫ ሒደቱም ይህንን መንገድ የተከተለ መሆን እንዳለበት እንዲሁም ስመጥር ሰዎችንና የትላልቅ ኩባንያዎች መሪዎችን ማምጣት ካልተቻለ ንግድ ምክር ቤቱ ውጤታማ አይሆንም ይላሉ፡፡  

የተጠያቂነት ጉዳይ አሁንም በንግድ ምክር ቤቱ አመራሮች ዘንድ ይታያል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ ንግድ ምክር ቤቱ የሦስት ዓመታት ሪፖርት በአንዴ ለማቅረብ መዘጋጀቱ ተገቢነት ያልነበረው ነው ይላሉ፡፡ የ2007 በጀት ዓመት ሪፖርቱን መጋቢት ላይ ማካሄድ ሲገባው አለማካሄዱ አሠራሩን መጋፋቱን ያመለክታልም ብለዋል፡፡

በንግድ ምክር ቤቱ የ10ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔዎችና በወቅቱ ተካሂዶ የነበረው ምርጫ በፍርድ ቤት ተሽሮ በባላደራ ቦርድ አዲስ ምርጫ ከተካሄደ ወዲህ አባላቱ የንግድ ምክር ቤቱን የሦስት ዓመታት ክንውን ለማወቅ አላስቻለም፡፡ ቢያንስ በመጋቢት 2008 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄድ ግድ እንደነበር የሚጠቁሙት አባላት፣ ይህ ለምን እንዳልሆነ በቀጣዩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ መጠየቅ አለበት ይላሉ፡፡

ከንግድ ምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ግን በተጠቀሰው ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማከናወን ያልተቻለበት በቂ ምክንያት እንደነበር ነው፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባል ንግድ ምክር ቤቶች የምርጫ ጊዜያቸውን በማሸጋሸጋቸው እንጂ ጠቅላላ ጉባዔውን ላለማከናወን አይደለም ብሏል፡፡ የሦስት ዓመታት ሪፖርቱን በአንድ ላይ ለማቅረብ የተገደድነው ወድደን አይደለም ያሉት አቶ ኤልያስ፣ መቅረብ በነበረበት ወቅት ያልቀረበበትን ምክንያት ለአባላት መገለጹን አስታውቀዋል፡፡

መስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ከጠቅላላ ጉባዔው ጐን ለጐን የሚካሄደው ምርጫ እንደ ቀድሞው ከምርጫው ጥቂት ወራት በፊት ራሳቸውን ለውድድር የሚያቀርቡ ዕጩዎች እስካሁን የቀረቡበት አይደለም፡፡

በፍርድ ቤት ታግዶ በነበረው አስረኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በተለይ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ዕጩ ሆነው የቀረቡት ተወዳዳሪዎች የባላደራ ቦርዱ ባካሄደው ድጋሚ ምርጫ ላይ ከወራት በፊት ራሳቸውን በዕጩነት አቅርበው ነበር፡፡ በዘንድሮ ምርጫ እነዚህ ዕጩዎች ድጋሚ ለመወዳደር ሐሳብ እንደሌላቸው ለማረጋገጥ እንደተሞከረው፣ በቅርቡ በሚካሄደው ምርጫ እንደማይወዳደሩ ሐሳቡም የሌላቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በወቅቱ ለፕሬዚዳንትነት ራሳቸውን ዕጩ አድርገው ቀርበው የነበሩት የቀድሞ የንግድ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊና የኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጄኔራል ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ተሾመ በየነና የአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ እስራኤል ካሣ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡     

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles