Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

ሴንትራል ሆቴል በሐዋሳ ከተማ 20 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ ሪዞርት ሊገነባ መዘጋጀቱን አስታወቀ

$
0
0

 

  • ኤክስኪዩቲቭ አፓርትመንት ሆቴል ለመገንባት ቦታ ተረክቧል

 

 

በሐዋሳ ከተማ የሚገኘው ሴንትራል ሆቴል፣ እስካሁን ሲያካሂዳቸው ከቆዩት የማስፋፊያ ግንባታዎች በተጓዳኝ በአሁኑ ወቅት በሐዋሳ ሐይቅ አቅራቢያ 20 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ ሪዞርት ሆቴል ለመገንባት ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

የሴንትራል ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍትሕ ወልደ ሰንበት ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በሐዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ይገነባል ለተባለው ሪዞርት ሆቴል መንግሥት እስካሁን የ10 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ አመቻችቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ኤክስኪዩቲቭ አፓርትመንት ሆቴልና የገበያ ማዕከል ለመገንባት የሚያስችለው ቦታ መረከቡን አስታውቀው፣ ግንባታ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በሐዋሳ ከተማ ቀደምት ዘመናዊ ሆቴሎች ከሆኑት ተጠቃሽ የሆነውን ሴንትራል ሆቴልን በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ወ/ሮ አማረች ዘለቀ ሸንቁጥ፣ ከታች በመነሳት በአሁኑ ወቅት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማካበት የቻሉበትን ትልቅ ኢንቨስትመንት በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ እስካሁን 250 ሚሊዮን ብር የሚገመት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ማከናወናቸው የሚነገርላቸው ወ/ሮ አማረች፣ መነሻቸው 25 ኪሎ ጤፍ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይናገራሉ፡፡

ይኸውም የወር ቀለባቸው ከነበረችው 25 ኪሎ ጤፍ እየቆነጣጠሩና እያገላበጡ በሐዋሳ ከተማ በተለያዩ የፕሮጀክት ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ ሠራተኞች ምግብ አብስለው በማቅረብ አንድ ብለው የንግዱን ዓለም እንደተቀላቀሉ የሕይወት ታሪካቸው ይዘክራል፡፡ ቀስ በቀስ የደንበኞቻቸው ቁጥር እያደገ፣ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሠራተኞች ለወ/ሮ አማረች መነሻ ምክንያት ለመሆን በቅተዋል፡፡

ከእነዚህ ተቋማት ሠራተኞች ባሻገር ለተለያዩ መንግሥታዊና ለግል የመስክ ሥራ ወደ ሐዋሳ የሚያቀኑ ሁሉ በመኖሪያ ቤታቸው ይስተናገዱ የነበረ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ የመጣው የምግብ ቤታቸው ደንበኛውን ለማስተናገድ ባለመቻሉ፣ በግቢያቸው ተጨማሪ ቤቶችን በመሥራት ለማስተናገድ ሲጥሩ ቆይተዋል፡፡ ቀስ በቀስም በሳጠራ የተከለለ፣ በቀርካና በስጋጃ መጋረጃ የተዋበ፣ ዙሪያውን በእበት የተለቀለቀ የባህል አዳራሽ በመሥራት ቢዝነሳቸውን እያስፋፉ የቀጠሉት ወይዘሮ አማረች፣ በቅጽል ስማቸው ሴንትራል እየተባሉ እንዲጠሩ ያበቃቸውን ትልቅ ሆቴል ለመገንባት የሚያስችላቸውን አቅም ለመገንባት አስችሏቸዋል፡፡

ሴንትራል ሆቴል ሲጀመር ከ40 እስከ አንድ ሺሕ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ስድስት አዳራሾችን፣ ሱፐር ማርኬትና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን ያካተተ ባለሦስት ፎቅ ሕንፃ ለመገንባት የቻሉ ሲሆን፣ ብዙም ሳይቆዩ ምድር ቤቱን ጨምሮ ባለስምንት ፎቅ ባለኮከብ ደረጃ ዘመናዊ ሆቴል አድርገውታል ያሉት አቶ ፍትሕ፣ ሆቴሉ 72 መኝታ ክፍሎችን ጨምሮ መዋኛ ገንዳ፣ ጂምናዚየም፣ ሬስቶራንቶች እንዲሁም ሌሎች የሆቴል አገልግሎት ይዘቶችን አሟልቶ የተገነባ ነበር፡፡

በምዕራፍ ሦስት የሴንትራል ሆቴል ማስፋፊያ ግንባታ ከምድር ቤቱ በተጨማሪ ጂ ፕላስ ሰባት የሆነ ሕንፃ በመገንባት ወደ ሥራ አስገብተዋል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ 112 ክፍሎች ያሉት ሆቴል ለመሆን የበቃው ሴንትራል ሆቴል፣ በአራት ሰዓት ትዕዛዝ ብቻ 2,000 ሰዎች በቀላሉ መስተናገድ የሚችሉበት ተቋም ለመሆን በቅቷል፡፡ የድርጅቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ሴንትራል ሆቴል ለ300 ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል አስገኝቷል፡፡ ተጨማሪ 60 ሰዎችም ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ 11 አዳራሾቹን ልደት፣ ጉዱማሌ፣ ሴንትራል ሚሊኒየም፣ አክሱም፣ አደሬ፣ አይቤክስ፣ ፉራ፣ ታቦር፣ መለስ ዜናዊ፣ ፍሮንት ሚኒ እንዲሁም አፕን ጋርደን የሚሉ ስያሜዎችን በመስጠት ለአገልግሎት አብቅቷቸዋል፡፡

የአምስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ አማረች፣ ባለቤታቸው ለውትድርና ግዳጅ በወጡበት ወቅት ሕይወታቸው በማለፉ ከባድ ፈተና ቢገጥማቸውም በአሁኑ ወቅት በርካታ ሚሊዮን ብሮችን ያለ ችግር ለማንቀሳቀስ የቻሉና በሐዋሳ ከተማ አንቱታን ያተረፉ ከመሆን አልገታቸውም፡፡ አዳዲስ የጀመሯቸው ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ወደ ሥራ እንደሚገቡ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ሴንትራል ሆቴል ፈር በቀደደባት ሐዋሳ በአሁኑ ወቅት በርካታ ባለኮከብ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles