ከመሬት በላይ 107 ሜትር ከፍታ ባለው የሕንፃ አናት ላይ እንገኛለን፡፡ ከሕንፃው አናት ላይ በመሆን አዲስ አበባን በሁሉም አቅጣጫ መቃኘት ይቻላል፡፡ ከአዲስ አበባ ብሔራዊ ስቴዲየም ፊት ለፊት የሚገኘው አዲሱ ሕንፃ በከተማው ከበቀሉ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች አንዱ ሲሆን፣ ሕንፃውን ያስገነባው የወጋገን ባንክ ኃላፊዎችም የከተማውን ረጅም ሕንፃ ዕውን እንዳደረጉ ይናገራሉ፡፡
የፎቶ ጋዜጠኞች በዚህን ያህል ከፍታ አዲስ አበባን በምስል ለማስቃኘት ዕድሉ ገጥሟቸው እንደማያውቅ በሚያሳብቅ አኳኋን፣ በትጋት ከየአቅጣጫው የካሜራዎቻቸውን ሌንስ እያሽከረከሩ ሲያነጣጥሩ የሚፈጥረው ድምፅ አስገራሚ ነበር፡፡ ረዥሙ ሕንፃ እየተባለ የተጠቀሰው አዲሱ የወጋገን ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት፣ ከምድር በታች ሦስት ከምድር በላይ ደግሞ 23 ወለሎች የተገነቡለት መለሎ ሕንፃ ነው፡፡
አራት ዓመታት የፈጀው ይህ ሕንፃ፣ ግንባታው ተጠናቆ ለምርቃት ከመብቃቱ ቀደም ብሎ መስከረም 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በጋዜጠኞች ተጎብኝቷል፡፡ በዚህ ወቅት እንደተገለጸው፣ የሕንፃው አጠቃላይ የግንባታ ሥራ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ፈጅቷል፡፡ ሕንፃው ያረፈበት የመሬት ስፋት 1,800 ካሬ ሜትር ሲሆን፣ ከምድር በታች ሦስት የተሽከርካሪ ማቆሚያ ወለሎችና ከምድር በላይ 23 ወለሎች እንዳሉት የወጋገን ባንክ የገበያና የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፍቅሩ ወልደ ትንሳዔ ገልጸዋል፡፡ ከመሬት በላይ ያለው ከፍታ 107 ሜትር ሲሆን፣ በዚህም እስካሁን ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ ከተገነቡት ሕንፃዎች ቀዳሚው እንደሚያደርገው አቶ ፍቅሩ ይናገራሉ፡፡ ሕንፃው በአንድ ጊዜ 81 ተጠቃሚዎችን የማጓጓዝ አቅም ያላቸው ስምንት የመወጣጫ አሳንሰሮች ተገጥመውለታል፡፡ የደኅንነት፣ የሙቀትና ቅዝቃዜ መቆጣጠሪያዎች፣ ልዩ ልዩ የኤሌክትሪክ ቴክኖሎጂዎች የተገጠመለት ሲሆን፣ በዘመናዊ የሕንፃ አስተዳደር ሥርዓት እንደሚመራም ተጠቅሷል፡፡
ሕንፃው ከቢሮ አገልግሎት በተጨማሪ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የሠራተኞች ካፍቴሪያና ለሱቅ የሚከራዩ ክፍሎችንም አካቷል፡፡ በግንባታው ሒደት ሕንፃው ምቹ አገልግሎት አቀላጥፎ እንዲሰጥ የተለያዩ የዲዛይን ለውጦች ተደርገዋል ያሉት የባንኩ ኢንጂነሪንግ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ገብረ እግዚአብሔር ናቸው፡፡ በጉብኝቱ ወቅት ከተደረገው ገለጻ መረዳት እንደተቻለው፣ በሕንፃው ውስጥ 450 ሰዎችን የሚያስተናግዱ የስብሰባ አዳራሾችን ጨምሮ አሥር አነስተኛ አዳራሾችን አካቷል፡፡ የወጋገን ባንክ አዲሱ ዋና መሥሪያ ቤት 19ኛው ወለል ላይ የሚገኘው የባንኩ ፕሬዚዳንት ቢሮም በተለየ መንገድ የሚደራጅ ነው፡፡ የባንኩ የመጀመርያ ወለል ላይ ልዩ ደንበኞቹን የሚስተናግድበት ፕሪሚየም ቅርንጫፍ ይከፍታል፡፡
ሕንፃው ውስጣዊ የቢሮ ዕቃዎችንና መገልገያዎችን የማሟላት ሥራ ይቀረዋል፡፡ ይህ እንደተጠናቀቀ ወጋገን ባንክ ለ20 ዓመታት በዋና መሥሪያ ቤትነት ሲጠቀምበት ከነበረው ከደንበል ሕንፃ ወጥቶ ወደ ራሱ ሕንፃ ይገባል፡፡ በነባሩ ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ከ500 በላይ ሠራተኞች ወደ አዲሱ ሕንፃ ሲዛወሩ ከዘጠነኛ እስከ 23ኛ ድረስ ያሉትን የአዲሱን ሕንፃ ወለሎች ይጋራሉ፡፡
እንደ አቶ ፍቅሩ ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት በዋና መሥሪያ ቤትነት በሚገለገልባቸው የደንበል ሕንፃ አምስት ወለሎች በዓመት ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከሁለተኛ እስከ ስምንተኛ ድረስ ያሉትን የሕንፃውን ወለሎች አገልግሎቶች ለኪራይ እንደሚያውላቸውም አስታውቋል፡፡
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተፈሪ ዘውዱ ስለሕንፃው እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹ይህ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ የባንካችን የ20 ዓመታት የስኬት ጉዞ መገለጫ ሲሆን፣ ባንኩ ለቢሮ ኪራይ በየዓመቱ ያወጣ የነበረውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በማዳንና ከሕንፃው ኪራይ በሚያገኘው ተጨማሪ ገቢ ትርፋማነቱን የበለጠ በማሳደግ ለባለአክሲዮኖች የተሻለ ጥቅም ያስገኛል፡፡›› አቶ ተፈሪ አክለውም ሕንፃው የባንኩን ተወዳዳሪነት በማሳደግ በተለይም እ.ኤ.አ. በ2025 በአፍሪካ ከሚገኙ አሥር ስመ ጥር ተፎካካሪ ባንኮች አንዱ ለመሆን ያለውን ራዕይ ማሳካት ይቻለው ዘንድ ትልቅ አቅም ይፈጥርለታል ብለዋል፡፡
የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ የባንኩ ደንበኞችና ባለድርሻ አካላት በባንኩ ላይ ያላቸውን እምነት እንደሚያሳድግ፣ የባንኩንም መልካም ገጽታ ከመገንባት አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ሲገለጽ፣ በአዲሱ ሕንፃ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችን መስጠት ይጀምራል ተብሏል፡፡
በአዲሱ ሕንፃ ከሚከፈተው የፕሪሚየም ደንበኞች ቅርንጫፍ በተጨማሪ በሕንፃው ውስጥ በርከት ያሉ የኤቲኤም ማሽኖች ይተከላሉ፡፡ እነዚህም ገንዘብ መክፈል ብቻ ሳይሆን፣ ለመቀበል የሚችሉበት አሠራር እንደሚተገበርም ተገልጿል፡፡ ለ20 ዓመታት ሲገለገልበት የቆየውን ዓርማ በአዲስ ተክቶ ወደ አዲሱ ሕንፃ የሚገባው ወጋገን ባንክ፣ በአሁኑ ወቅት ከ3,500 በላይ ባለአክሲዮኖችን ያፈራ ተቋም ነው፡፡ 20 ዓመታትን ካስቆጠሩና ዓመታዊ የትርፍ መጠናቸውን ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ካደረሱ አምስት ባንኮች መካከል አንዱ ነው፡፡
የዚህ ሕንፃ የግንባታ ሥራ ያከናወነው የቻይና ጂያንግዙ ኮርፖሬሽን ፎር ኢንተርናሽናል ኢኮኖሚክ ኤንድ ቴክኒካል ኮፕሬሽን የተባለ የቻይና ኮንስትራክተር ነው፡፡ የማማከርና አርክቴክቸራል ዲዛይኑን የሠራው ኢቲጂ ዲዛይነርስ ኤንድ ኮንሰልታንትስ የተሰኘው አገር በቀል አማካሪ ድርጅት ሲሆን፣ የሕንፃውን ስትራክቸራል ዲዛይን የሠራው ሌላው አገር በቀል ድርጅት ደግሞ ኤምኤች ኢንጂነሪንግ መሆኑን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
ሽንጠ ረጅሙ የወጋገን ባንክ ሕንፃ፣ ከርዝመቱ ባሻገር መግቢያው ላይ የሚታዩት ፏፏቴዎች ለሕንፃው ውበት ናቸው፡፡ ሕንፃው በርካታ የግዙፍነት መገለጫዎች ቢኖሩትም፣ ይህንን ለሚያክል ሕንፃ የተገነባው የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ 100 ተሽከርካሪዎችን ብቻ የሚያስተናግድ ሆኗል፡፡ ለዚህ ሕንፃ 100 መኪና ብቻ የሚይዝ ቦታ መሰናዳቱ በቂ እንዳልሆነም የባንኩ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ ‹‹የመኪና ማቆሚያው በቂ አይደለም፡፡ ይህንን በመገንዘብ የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ላይ ሲሆኑ፣ ለመኪና ማቆሚያ ተጨማሪ ቦታ ለማግኘት እየተሞከረ ነው፤›› በማለት አቶ ተስፋዬ ስለጉዳዩ ገልጸዋል፡፡
