- ግዥውን የፈጸመው ኩባንያ በኢትዮጵያ ወኪሉ በኩል ድርድር እያደረገ ነው
ከኢትዮጵያ ሞያሌ ድንበር ወደ ኬንያ ማለፍ ያልቻለው የስኳር ኤክስፖርትና ውዝግቡ እስካሁን መፍትሔ አልተገኘለትም፡፡
ይሁን እንጂ ግዥውን የፈጸመው አግሮ ኮሞዲቲስ ኤንድ ፋይናንስ የተባለው ተቀማጭነቱ ዱባይ የሆነው ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ ወኪሉ በኩል ድርድር መጀመሩን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በአቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም የሚመራው የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለሥልጣን በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት፣ ስኳሩን ገዝቶ ካስጫነው ኩባንያና በትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪው ብራይት ድንበር አቋራጭ የትራንስፖርት ማኅበር ጋር ድርድር ማስጀመር መቻሉ ተገልጿል፡፡
የትራንስፖርት ማኅበሩ ያስጫነው ኩባንያ ከገባው ውል በተቃራኒ ላለፉት 50 ቀናት ደብዛውን አጥፍቶ መቆየቱን፣ ጭነቱም ኬንያ እንዲገባ ማሟላት የነበረበትን ቀድሞ ባለመፈጸሙ ሳቢያ ውሉን ማቋረጡን ገልጾ፣ በማኅበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚገኘውን የስኳር ምርት ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ሦስት የመፍትሔ አማራጮችን ለኩባንያው ማቅረቡን፣ የማኅበሩ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ላለፉት 50 ቀናት በሞያሌ ድንበር ለቆሙበት የዲሜሬጅ ክፍያ በመፈጸም በሌላ ትራንስፖርት የስኳር ምርቱን ከሞያሌ ወደ ኬንያ ማጓጓዝ የመጀመርያው አማራጭ ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ አዲስ ውል ከዚሁ ማኅበር ጋር በመፈራረም ጭነቱን ወደ መዳረሻው ኬንያ ማጓጓዝ መሆኑን ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስኪያጁ ለሪፖተር ገልጸዋል፡፡
ሦስተኛው አማራጭ ትራንስፖርት ማኀበሩ የስኳር ምርቱን ወደተጫነበት ፋብሪካ በተሽከርካሪዎቹ እንዲመለስ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በእነዚህ አማራጮች ላይ ስኳሩን የገዛው አግሮ ኮሞዲቲስ ኤንድ ፋይናንስ የተባለው ኩባንያ ውሳኔውን እንዲያሳልፍ እስከ መጪው ረቡዕ መስከረም 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ጊዜ እንደተሰጠውም፣ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስኪያጁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የኩባንያው የኢትዮጵያ ወኪል ሆነው የቀረቡት አቶ ኃይሉ አስፋው የተባሉ ግለሰብ ናቸው፡፡ አቶ ኃይሉ በጉዳዩ ላይ መረጃ እንዲሰጡ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው ቢሆንም፣ መልሰው እንደሚደውሉ ገልጸው ዳግም ሊገኙ አልቻሉም፡፡
የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ለዱባዩ ኩባንያ 4,400 ቶን (44 ሺሕ ኩንታል) ስኳር በመሸጥ ለኬንያ ኤክስፖርት ለማድረግ ቢሞክርም፣ ስኳሩ ከኢትዮጵያ ድንበር ማለፍ አለመቻሉን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ግዥውን የፈጸመው ኩባንያ የሚጠበቅበትን 2.2 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ አለመፈጸሙ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
