የኦሮሚያ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በቦረናና በምዕራብ ጉጂ ዞን ለሚገኙ አርብቶ አደሮች በከብቶቻቸው ላይ ለደረሰ ጉዳት ከ5.23 ሚሊዮን ብር በላይ የካሳ ክፍያ መክፈሉን ተገለጸ፡፡
ከኢንሹራንስ ኩባንያው የተገኘ መረጃ እንደሚያስረዳው የእንስሳት ኢንሹራንስ ኢንዴክስ ተብሎ የሚጠራውን የኢንሹራንስ ሽፋን በሁለቱ ዞኖች ለገዙ አርብቶ አደሮች የተከፈለው የጉዳት ካሳ መጠን በዚህ የመድን ሽፋን የተከፈለ ከፍተኛ መጠን ያለው ካሳ ነው፡፡
ለአንድ አርብቶ አደር እስከ 218,000 ብር እንደተከፈለ የሚገልጸው የኩባንያው መረጃ፣ ይህን ያህል የጉዳት ካሳ የተከፈላቸው አርብቶ አደር ለመድን ሽፋኑ በዓመት 30 ሺሕ ብር ይከፍሉ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ የኢንሹራንስ ሽፋኑ የረዥም ጊዜ ዝናብና የረዥም ጊዜ ድርቅ ለሚያስከትለው ጉዳት የሚሰጥ ሲሆን፣ ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. የዚህ የመድን ሽፋን ተጠቃሚ ሆነው ጉዳት ደርሶባቸው ካሳ የተከፈላቸው አርብቶ አደሮች ቁጥር 2,195 እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኩባንያው በተመሳሳይ ከጥቂት ወራት በፊት በእነዚሁ ዞኖች 1,474 ለሚሆኑ አርሶ አደር አባወራዎች 1.6 ሚሊዮን ብር ካሳ ክፍያ መፈጸሙን አስታውሷል፡፡
Standard (Image)
