Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

​በኪሳራ ምክንያት የአዳዲስ መርከቦች ግዥ ዕቅድ ተሰረዘ

$
0
0

የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ዕቃዎች የሚጓጓዙባቸው 11 መርከቦች አክሳሪ ሆነው በመገኘታቸው፣ ሌሎች 15 መርከቦችን ለማስገንባት ተይዞ የነበረው ግዙፍ ዕቅድ ተሰረዘ፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ በአንድ ጊዜ 250,753 ሜትሪክ ቶን ደረቅ ጭነት የመጫን አቅም የነበራቸው ዘጠኝ መርከቦች፣ 87,300 ሜትሪክ ቶን የመጫን አቅም የነበራቸው ሁለት ነዳጅ ጫኝ በድምሩ አሥራ አንድ መርከቦች ባለቤት ነው፡፡

ኢንተርፕራይዙ በእነዚህ መርከቦች ብቻ የአገሪቱን ገቢና ወጪ ዕቃዎች ማስተናገድ ስለማይቻል፣ በኪራይ በሚገኙና በቻርተርድ የውጭ መርከቦች አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የአገሪቱን የመርከቦች ቁጥር በመጨመር አገልግሎቱን ለማስፋት በያዘው ዕቅድ 15 መርከቦችን ለመግዛት፣ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ ተሽከርካሪዎችን የሚያጓጉዙ መርከቦች እንዲሆኑ ታስቦ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ቅዳሜ መስከረም 13 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የኢንተርፕራይዙ መርከቦች በተለያዩ ምክንያቶች አክሳሪ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

መርከቦቹ አክሳሪ የሆኑባቸውን ጉዳዮች ሲያስረዱ በማኔጅመንት አቅም ማነስ፣ በመጫን አቅም አነስተኛ መሆን፣ በቴክኒክ ችግር፣ በሥምሪት መስመሮች አዋጭ አለመሆን፣ የዓለም ገበያ ተለዋዋጭ መሆኑ፣ ከዓለም አቀፍ የሎጂስቲክ ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ መሆን አለመቻልና የመርከቦቹ ቁጥር አነስተኛ መሆን ተጠቃሽ ችግሮች መሆናቸውን አቶ ሮባ አስረድተዋል፡፡

‹‹ባለፉት አምስት ዓመታት በተለይም በ2009 በጀት ዓመት የኢንተርፕራይዙ መርከቦች አክሳሪነት እየጨመረ መጥቷል፤›› ሲሉ አቶ ሮባ ገልጸው፣ ‹‹በሌላ በኩል ደግሞ በኪራይ በሚገኙ በቻርተር የውጭ አገር መርከቦች የሚሠራው ሥራ አትራፊ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

የአገር ውስጥ መርከቦች በብልሽት ምክንያት ያለ ሥራ እንደሚቆሙና ሌሎች ችግሮችም እንዳሉባቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ችግሮች ሳይፈቱ ሌሎች መርከቦችን መግዛት ለተጨማሪ ኪሳራ የሚዳርግ በመሆኑ የግዥ ዕቅዱ መሰረዙን አረጋግጠዋል፡፡

በአገር ውስጥ መርከቦች ላይ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት የመርከቦቹን ኦፕሬሽን የሚያስተዳድረውን ማኔጅመንት ማስተካከል፣ የጉዞ መስመሮችን አዋጭነት በድጋሚ መፈተሽ፣ የቴክኒክ ችግራቸውን እየተከታተሉ መፍታትና የታሪፍ ሥርዓቱን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ አቶ ሮባ ጠቁመዋል፡፡

ኢንተርፕራይዙ የራሱ መርከቦች ለኪሳራ ቢዳርጉትም በኪራይ በሚያገኛቸው መርከቦች በመጠቀም፣ እንዲሁም ከሚሰጣቸው አጠቃላይ አገልግሎቶች በ2009 በጀት ዓመት 15.8 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ ታውቋል፡፡

ኢንተርፕራይዙ በ2010 በጀት ዓመትም 23.6 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላት፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት፣ ኢኮኖሚዋም እያደገና የቀጣናው ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር እንደ መሆኗ ከጂቡቲ ወደብ በተጨማሪ የበርበራንና የሱዳን ወደቦችን በሰፊው ለመጠቀም እየሠራች መሆኑን አቶ ሮባ ተናግረዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ በአቅራቢያዋ ያሉ ወደቦችን መጠቀሟ አማራጭ ሳይሆን ተጨማሪ አቅም መፍጠር ነው፤›› ሲሉ ቀጣዩን የመንግሥት አቅጣጫ ጠቁመዋል፡፡ 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles