Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

የቻይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ በግሉ የገነባው ኢንዱስትሪ ፓርክ እየተጠናቀቀ ነው

$
0
0

በኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ትልልቅ የሚባሉ የግንባታ ሥራዎችን በማከናወን የሚታወቀው በቻይና መንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደረው ቻይና ኮንስትራክሽን ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን (ሲሲሲሲ)፣ በግሉ እየገነባ ያለውን የኢንዱስትሪ ፓርክ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከተገነቡትና እየተገነቡ ካሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተጨማሪ፣ በግል የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ፈቃድ በመውሰድ ሲሲሲሲ የራሱን ኢንዱስትሪ ፓርክ በመገንባት ላይ የሚገኘው በአረርቲ ምንጃር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር በላቸው መኩሪያ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኩባንያ በአረርቲ ምንጃር እየገነባ ያለው ኢንዱስትሪ ፓርክ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች የሚመረቱበት ነው፡፡

እስካሁን በዚህ ኢንዱስትሪ ፓርክ የፈርኒቸርና የሴራሚክ ምርቶችን የሚያመርቱ ሁለት ኩባንያዎች ከወዲሁ መግባታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የፓርኩ ግንባታ ከ80 በመቶ በላይ መጠናቀቁም ታውቋል፡፡

ይህ የኢንዱስትሪ ፓርክ ከ120 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን፣ በባለቤትነት የሚያስተዳድረውም የቻይና ኮንስትራክሽን ድርጅት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአገሪቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኮንስትራክሽን ግንባታ ውስጥ ተሳታፊ የሆነው ይህ የቻይና ኩባንያ፣ እስካሁን የመቐለና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብቶ ለመንግሥት አስረክቧል፡፡ የራሱን የኢንዱስትሪ ፓርክ ግን በራሱ ወጪ ገንብቶ ያስተዳድረዋል፡፡ ይህ የቻይና ኩባንያ ከመንግሥት ጋር ተዋውሎ ከገነባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና አሁን በግሉ የራሱን ኢንዱስትሪ ፓርክ ከመገንባት በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልልቅ የግንባታ ሥራዎችን በማከናወን በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

ከሚያካሂዳቸው ትልልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተርሚናል ግንባታ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከ126 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ከሚጠይቀው የኤርፖርት ፕሮጀክት ሌላ፣ የአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድን መገንባቱ ይታወሳል፡፡ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ የተጀመረው የአቃቂ-ቂሊንጦ መንታ መንገድ ፕሮጀክትን በ4.7 ቢሊዮን ብር ለመገንባት ተፈራርሟል፡፡  

የቦሌ-መስቀል አደባባይን መንገድ በመገንባት የሚታወቅ ሲሆን፣ ግምታቸው ወደ አራት ቢሊዮን ብር የሚደርስ ሦስት የመንገድ ፕሮጀክቶችን ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ተረክቦ እየሠራ ነው፡፡

እንደ ቻይናው የኮንስትራክሽን ድርጅት ሁሉ በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ይዞታ ውስጥ አንድ የጣሊያን ኩባንያ በኢትዮጵያ የመጀመርያ ነው የተባለውን ሴንቴቲክ ለማምረት የራሱን ኢንዱስትሪ ፓርክ በመገንባት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከ100 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለውን ይህንን የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በስምንት ወራት ውስጥ ያጠናቅቃል ተብሎ እንደሚጠጠበቅ ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

እንደ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታን በተለያዩ መንገዶች ማካሄድ ይቻላል፡፡ በመንግሥት ደረጃ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማልማት እንደ አንድ የንግድ ተቋም ተደራጅቶ የተቋቋመው የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ምክትል ኮሚሽነሩ እንደገለጹት፣ የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን የአልሚነት ፈቃድ ከኮሚሽኑ ወስዶ እያለማ ነው፡፡ ‹‹ይህንን መሬት ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት እንድታውል እፈልጋለሁ ብሎ ክልሉ ሲያቀርብለት ተቀብሎ ያለማል፡፡ ወይም ቆርሶ ለግል አልሚ ይሰጣል፡፡ በዚህ መንገድ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማልማት ላይ ነው፤›› ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የግል አልሚ እንዲመጣ የሚሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርክ ማልማት ራሱን የቻለ  የኢንቨስትመንት መስክ በመሆኑና በኢንቨስትመንት አዋጁ ላይ እንደተቀመጠውም የኢንዱስትሪ ፓርክ ለማልማት፣ ኢንተርፕራይዝ ሆኖ (ወይም የግል የመንግሥትም ሊሆን ይችላል) አልሚ ወይም ኦፕሬተርም ሆኖ መምጣት ይቻላል ተብሏል፡፡

በግል የሚቋቋሙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ሆኑ መንግሥታዊው የኢንዱስትሪ ፓርክ ኮርፖሬሽንን፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሚከታተላቸው እንደሆነም ተገልጿል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles