Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

የኦጋዴን የጋዝ ልማት ፕሮጀክት ዘግይቷል

$
0
0

 

በሶማሌ ክልል በኦጋዴን ቤዚን ውስጥ የሚካሄደው የጋዝ ልማት ፕሮጀክት ከተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መዘግየቱ ተጠቆመ፡፡

ፖሊጂሲአል የተሰኘው የቻይና ኩባንያ በኦጋዴን ካሉብ፣ ሒላላና ገናሌ በተባሉ ቦታዎች የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ለማልማትና ተጨማሪ የነዳጅ ክምችቶች አግኝቶ ለማልማት፣ እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 2013 ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ስምምነት መፈጸሙ ይታወሳል፡፡

ኩባንያው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቱ ከሚገኝበት አካባቢ የጋዝ ማስተላለፊያና ቧንቧ ጂቡቲ ወደብ ድረስ ለመዘርጋትና ወደቡ አቅራቢያ የጋዝ ማጣሪያ ጣቢያ ለመገንባት የተስማማ ሲሆን፣ ለዚህም አራት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ማቀዱ ይታወሳል፡፡

ፖሊጂሲኤል የተፈጥሮ ጋዝ ከኦጋዴን በማውጣት በቧንቧ ወደ ጂቡቲ በመላክ ጂቡቲ በሚገነባው የጋዝ ማጣሪያ ጋዙን አቀዝቅዞ ወደ ፈሳሽ በመቀየር፣ በልዩ የፈሳሽ ጋዝ (LNG) ተሸካሚ መርከቦች ወደ ቻይና ለመላክ ዕቅድ ነድፏል፡፡ ኩባንያው የተፈጥሮ ጋዝ ምርቱን እ.ኤ.አ. በ2018 እንደሚጀምር ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ዝርጋታና የጋዝ ማጣሪያ ጣቢያው ግንባታ እንዳልተጀመረ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የጋዝ ልማት ፕሮጀክቱ ግዙፍና የተወሳሰበ በመሆኑ ጊዜ የሚጠይቅ ነው፡፡ ‹‹የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቱ መኖሩ የተረጋገጠ ነው፡፡ አሁን ጥረት እያደረግን ያለነው ጋዙን አውጥተን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ እስከ ጂቡቲ ወደብ ድረስ የማስተላለፊያ ቧንቧ መዘርጋት አለበት፡፡ በጂቡቲ ወደብ የሚገነባ የተፈጥሮ ጋዙን ወደ ፈሳሽ የሚቀይር (LNG Plant) አለ፡፡ ይህ የሚገነባው ጂቡቲ ውስጥ በመሆኑ ከጂቡቲ መንግሥት ጋር እየተደራደርን ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ሞቱማ በጋዝ ልማት ፕሮጀክቱ ላይ መጓተት እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አንዳንድ ችግሮች አሉ፡፡ ፕሮጀክቱ ትንሽ ዘግይቷል፡፡ የጋዝ ማስተላለፊያ ዝርጋታና ወደብ አጠቃቀም ዙሪያ ከጂቡቲ መንግሥት ጋር ድርድር እየተካሄደ ነው፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ የተጠቀሱትን ግንባታዎች ለመጀመር ድርድሩ መጠናቀቅ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ድርድሩን የሚያካሂደው ፖሊጂሲኤል እንደሆነ ገልጸው ድርድሩ ረዥም ጊዜ ወስዷል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ድርድሩ በፍጥነት ተቋጭቶ ወደ ሥራ እንዲገባ ግፊት እያደረገ እንደሆነ አቶ ሞቱማ ገልጸዋል፡፡ ስምምነቱ በ2010 ዓ.ም. ተፈርሞ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ዝርጋታ እንደሚጀምር ያላቸውን እምነት አክለዋል፡፡

በካሉብና በሒላላ የሚገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት 118 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚገመት ሲሆን፣ ፖሊጂሲኤል በዓመት ሦስት ሚሊዮን ቶን ጋዝ ለማምረት አቅዷል፡፡

ፖሊጂሲኤል የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ዝርጋታውንና የጋዝ ማጣሪያ ግንባታ ሥራውን ያልጀመረ ቢሆንም፣ ሰፊ የሆነ ነዳጅ ፍለጋ ሲካሂድ እንደቆየ ተገልጿል፡፡  ኩባንያው በካሉብና በሒላላ የነዳጅ ጉድጓዶች በመቆፈር የጋዝ ክምችቱን መጠን ጥናት እንዳካሄደ የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ባለሙያዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው ቢጂፒ ጂኦ ሰርቪስስ የተሰኘ ሌላ የቻይና ኩባንያ በኮንትራት በመቅጠር ሰፊ የሴስሚክ ጥናት ማካሄዱን፣ በዚህም በርካታ የከርሰ ምድር መረጃዎች መሰብሰቡን ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው አዲስ የነዳጅ ክምችት ለማግኘት ጥረት ላይ መሆኑንና አበረታች ውጤት ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡

ፖሊጂሲኤል የጋዝ ማጣሪያ በሲንጋፖር ኩባንያ ለማሠራት ድርድር ላይ እንደሆነና የፈሳሽ ጋዝ ማጓጓዣ መርከብ በቅርቡ እንደገዛ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተከለሰው የጋዝ ልማት ፕሮጀክት ዕቅድ ኩባንያው እ.ኤ.አ. በ2020 የጋዝ ምርቱን ለመጀመር አቅዷል፡፡

የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የጋዝ ምርቱ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ማብቂያ እንደሚጀመር ዕቅድ አለው፡፡   

 

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles