Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

ኢትዮጵያ ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚያነሳሱ ማበረታቻዎችን እንድታጤን የኢኮኖሚ ባለሙያው መከሩ

$
0
0
  • የተመድ ሪፖርት በዓለም አሳሳቢ የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ ተንሰፋርቷል ይላል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ በየጊዜው ይፋ ከሚያደርጋቸው ጥናታዊ ሪፖርቶች መካከል የንድና የልማት ጉባዔ የተሰኘው ይጠቀሳል፡፡ የዚህ ዓመት ሪፖርትም ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት ይፋ ተደርጓል፡፡

ሪፖርቱ ‹‹Trade and Development Report 2017: Beyond Austerity towards a global new deal›› በሚል ርዕስ የወጣ ሲሆን፣ በሪፖርቱ ሽፋን ካገኙ ጉዳዮች መካከል ኪራይ ሰብሳቢነትና የአውቶሜሽን ወይም የሮቦቶች ተፅዕኖና ሥጋትን በተመለከተ የቀረቡት ርዕሰ ጉዳዮች ሚዛን ይደፋሉ፡፡

በዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ አካታች ወይም ‹‹ኢንክሉሲቭ ግሮውዝ›› እንዳይታይ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ጥቂት አሸናፊዎች የዓለም ሀብት መቆጣጠራቸው፣ ትርፍ የሚያጋብሱ እንጂ ብልጽግናን የማያመጡ ጥቂት ባለፀጎች ግለሰቦች፣ ኩባንያዎችና ትልልቅ ኮርፖሬሽኖች መበራከታቸው መንስዔ እንደሆነ ሪፖርቱን ካቀረቡት መካከል ዶ/ር ተስፋቸው ታፈረ አንዱ ናቸው፡፡

ዶ/ር ተስፋቸው በተመድ የንግድና ልማት ጉባዔ በዝቅተኛ ደረጃ ያደጉ አገሮች፣ የአፍሪካና የልዩ ፕሮግራም ዳይሬክተር በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተው ጡረታ ቢወጡም፣ በአሁኑ ወቅት የንግድና የልማት ጉባዔው ዋና ፀሐፊና አማካሪ በመሆን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ እንደ ዶ/ር ተስፋቸው ምልከታ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ለአገር ውስጥና ለውጭ ኩባንያዎች የሚሰጧቸው የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ለኪራይ ሰብሳቢነት ሲዳርጉ እንደሚታዩ በሪፖርቱ አመላክተዋል፡፡ ከሪፖርቱ በመነሳት በተደረገ ውይይት ወቅትም በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ከመጣው የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን አኳያ መታየትና መፈተሽ የሚገባቸው የማበረታቻዎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነት በአብዛኛው በሞኖፖል የበላይነትን በመያዝ ያልተገባ ትርፍና ጥቅም ለማግኘት የሚደረግ መራወጥ እንደሆነ ሲተረጎም፣ በተጨማሪም ለአገርና ለማኅበረሰቡ ይህ ነው የሚባል ጥቅም ሳያስገኙ፣ ለራስ ትርፍና ጥቅም ሲባል መንግሥታዊ መዋቅሮችን ጭምር በተፅዕኖ ሥር የማድረግ አካሔድ እንዳለው ዶ/ር ተስፋቸው ይተነትናሉ፡፡ 

እንደ ዶ/ር ተስፋቸው ማብራሪያ፣ አብዛኞቹ ለኢንቨስትመንት የሚሰጡ ማበረታቻዎች ለአሥር ዓመታትና ከዚያም በላይ የሚሰጡ እንደመሆናቸው፣ ኩባንያዎችም ሆኑ ግለሰቦች በዚህ ጊዜ ውስጥ ትርፋቸውን ካጋበሱ በኋላ ጥለው የሚሔዱበት፣ ያገኙትን ትርፍና ጥቅም በሙሉ ወደየመጡባቸው አገሮች አለያም ወደ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እየላኩ በማጠራቀም፣ የኢንቨስትምንት ማበረታቻ በሰጣቸው አገርና መንግሥት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ በሚጀምሩበት ወቅት ግን ደብዛቸው ሲጠፋ ይታያል፡፡ ዶ/ር ተስፋቸው እንዲህ ያለው አድራጎት በበርካታ ታዳጊ አገሮች ውስጥ በተለይም በአፍሪካ ሲታይ መቆየቱን ይናገራሉ፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ ለአገር ውስጥና ለውጭ ኢንቨስተሮች የምትሰጣቸው ማበረታቻዎች የሕዝብ ጥቅምና የአገር ሀብት ጉዳት ላይ የማይጥሉ መሆናቸው ማረጋገጥ፣ በየጊዜውም መከታተልና መቆጣጠር እንደሚገባት አሳስበዋል፡፡

የታዳጊ አገሮች መንግሥታት በሁለት መስቀለኛ መንገድ ላይ እንደሚገኙ ሲያብራሩም በአንድ በኩል የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ለማስተናገድ ደግሞ የኢንቨስትመንት ዕድሎችንና ማበረታቻዎች ማቅረብ ግድ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሚሰጡ ማበረታዎች ሳቢያ የሕዝብና የአገር ሀብት እንዳይበደል፣ ጥቂቶች እንዲጠቀሙና ብዙዎች እንዲጎዱ የማያደርግ ሥርዓት ማስፈን የአገሮቹ ፈተና መሆናቸውን ዶ/ር ተስፋቸው ያብራራሉ፡፡ በመሆኑም ሁለቱን አመጣጥኖ መጓዝ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

ይህ በመሆኑም የዓለም ኢኮኖሚ ባለፉት አሥርታት ውስጥ ከገባበት የቁልቁሊት ጉዞ ለመውጣት እየዳኸ እንደሚገኝ የተመድ ሪፖርት አመላክቷል፡፡ በአፍሪካ፣ በእስያ ከታየው አመርቂ የኢኮኖሚ ዕድገት በቀር በተቀረው ዓለም የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ቀጥሏል፡፡ በተለይም በዓለም የፋይናንስ ቀውስ ሳቢያ የተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ በበርካታ አገሮች ውስጥ የበጀትና የወጪ ቅነሳ ማስከተሉ ይታወሳል፡፡

የምዕራቡ ዓለም በርካታ አገሮች በተለይም እንደ እንግሊዝ ያሉት፣ ለኮሌጅ ተማሪዎች ይሰጡ የነበረውን ጥቅማጥቅም ከመቀነስ ጀምሮ የጡረታ ዕድሜን ማራዘም፣ ሌሎችም ለማኅበራዊ ድጋፍ ይውሉ የነበሩ ወጪዎችን መቀነስን ጨምሮ በርካታ ዕርምጃዎችን ወስደዋል፡፡ ሆኖም ለአሥር ዓመት ገደማ በቀጠለው በዚህ ዓይነቱ ቀውስ ውስጥ እንደ ግሪክ ያሉ አገሮች ከተዘፈቁበት ማጥ መውጣት ተስኗቸው እየተንኮታኮቱ ይገኛሉ፡፡ 

ከእንዲህ ያለው ውጥንቅጥ ዓለም ለመውጣት በምትዳክርበት ወቅት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ፣ ነዳጅ አልባ አገሮች የሚያስመዘግቡት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሳይገታ መቀጠሉ ተስፋን አጭሯል፡፡ ይህም ሆኖ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገሮች ከቀደሙት ዓመታት ይልቅ እየተዛቀዘ የመጣ የኢኮኖሚ ዕድገት አሳይተዋል፡፡ ‹‹ቴክኒካል ሪሴሽን›› እየተባለ በሚጠራው የኢኮኖሚ ዕድገት መገለጫ ሥርዓት ውስጥ እያለፉ ይገኛሉ፡፡

ሪፖርቱ ከሚገባቸው በላይ ስንጥቅ ሲያተርፉ እንደታዩ በጥናት ካመላከታቸው ኩባንያዎች መካከል እ.ኤ.አ. ከ1995 እስከ 2000 በነበሩት ዓመታት ውስጥ ሲያገኙ የቆዩት ስንጥቅ ትርፍ አራት በመቶ እንደነበር ይጠቅሳል፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ. ከ2009 እስከ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ በተደረገ ጥናት ግን ይህ ትርፍ ወደ 23 በመቶ አሻቅቧል፡፡ በተለይ ደግሞ ትልልቅ የሚባሉ 100 ኩባንያዎች ወደ 40 በመቶ ያሻቀበ፣ ተገቢነት የጎደለው ትርፍ ሲያጋብሱ ቆይተዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በዓለም ገበያ በታየው መዋዠቅ የተፈጠረውን ክፈተት ተንተርሰው ባገኙት አጋጣሚ፣ አቋራጭ የትርፍ ማጋበሻ መንገድ በማግኘታቸው እንደሆነ ሪፖርቱ አስፍሯል፡፡

በሌላ በኩል ሪፖርቱ ለየት ያለ ምልከታ ይዞ ብቅ ካለባቸው ጉዳዮች መካከል በአፍሪካና በሌሎች አኅጉራት ውስጥ የሚገኙ ታዳጊ አገሮች እያስፋፏቸው የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሮቦቶች ሥጋት እንደሌለባቸው ያቀረበበት ክፍል ይጠቀሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዓለምን 43 በመቶ ገዳማ የሮቦቶች ምርትና ሥርጭት የተቆጣጠሩት አሜሪካ፣ ጀርመንና ጃፓን እንደሆኑ ሪፖርቱ ጠቅሶ፣ እ.ኤ.አ. በ2015 በዓለም ላይ የተሰራጩት ሮቦቶች ብዛት ከ1.6 ሚሊዮን እንደሆኑ፣ እ.ኤ.አ. እስከ 2019 የሚሰራጩት ሮቦቶች ብዛትም ከ2.5 ሚሊዮን በላይ እንደማይሆን ዶ/ር ተስፋቸው ይገልጻሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ሮቦቶች የታዳጊ አገሮችን የሥራ ዘርፎችና አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚቆጣጠሩበት ጊዜ ሩቅ መሆኑን ነው የሚሉት ዶ/ር ተስፋቸውና አጋሮቻቸው፣ በተለያዩ የሚዲያ ሪፖርቶች የሚነገረው ከእውነታው ይቃረናል ይላሉ፡፡

ሮቦቶች በርካቶች ከሥራ ዓለም እያገለሉ፣ የህልውና ፈተና ሆነዋል ቢባልም፣ እውነታው ግን ተደጋጋሚና አሰልቺ የሆኑ እንደ ኤሌክትሮኒክስና የመኪና መገጣጠም ሥራዎችን ብቻ መረከባቸውን በዋቢነት ያቀርባሉ፡፡ ይህም ቢባል ግን በረጅም ጊዜ ውስጥ ሮቦቶች ወደ አፍሪካም ሆነ ታዳጊ አገሮች በብዛት ወደ ሌሎች አይስፋፉም ብሎ መገመት ስህተት እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ሮቦት አምራቾች የገበያ ድርሻቸውን ለማስፋት የሚያስችሏቸውን ዕድሎች እስካገኙ ድረስ የሮቦቶች መዛመት ወደፊት ለአፍሪካ ትልቅ ሥጋት መሆኑ እንደማይቀርም ያሳስባሉ፡፡    

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles